Saturday, 14 April 2018 14:59

ቶፕ የታሸገ ውሃ ገበያውን ተቀላቅሏል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

 “ምርታችንን ወደ ጅቡቲ ለመላክ አቅደናል”
              
   ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ 18 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ገፈርሳ ኖኖ (ቡራዩ) በሚባል ስፍራ ከ272 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተመሰረተው “አበበ ድንቁ የታሸገ ውሃና ከአልኮል ነፃ መጠጦች” ፋብሪካ፣ ቶፕ በማለት የሰየመውን የታሸገ ውሃ ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ፣ የምርቱን ወደ ገበያ መግባት አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የፋብሪካው መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ድንቁ፣ የጥራት መቆጣጠሪያ ላቦራቶሪውና የጥራት መመርመሪያ መሳሪያዎቹ እጅግ ዘመናዊና የተራቀቁ መሆናቸው፣ ፋብሪካውን በዘርፉ ግንባር ቀደም ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በቻይናው ኒዎማስተር የማሽን አቅርቦትና ተከላ የተደረገላት ቶፕ የታሸገ ውሃ፣ ከኖኖ ተራራ ስር የሚመነጨውን ውሃ በማጣራት ባለ 20፣ ባለ 5፣ ባለ 2 እና ባለ 1 ሊትር እንዲሁም ባለ 600 እና ባለ 350 ሚ.ሊ ውሃ እንደሚያመርቱ የጠቀሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የፕላስቲክ ጠርሙሶችንና ክዳናቸውን እኛው ስለምናመርት፣ በገበያው ውስጥ በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን ይረዳናል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ሮቦት ስለተገጠመለት፣ እጅ ሳይነካው በሰዓት 18 ሺህ ጠርሙስ የታሸገ ውሃ እናመርታለን ያሉት የቶፕ ውሃ ሴልስና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አጀማ፤ ከአራት ወራት በኋላ በሰዓት 24 ሺህ ጠርሙስ የታሸገ ውሃ ስለምናመርት፣ አጠቃላይ ምርታችን 42 ሺህ ሊትር ይሆናል፡፡ በጅቡቲ ያሉ ሦስት ድርጅቶች፣ ውሃ የሚያቀርቡት ከሐይቅ እያጣሩ ስለሆነ ምርታችንን ወደ ጂቡቲ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አቅደናል በማለት አስረድተዋል፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለ147 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ሽመልስ፤ “ሁለተኛውን መሳሪያ ለመትከል 75 ባለሙያዎች ያስፈልጉናል። መሳሪያው ሥራ ሲጀምር በአጠቃላይ 350 ሰራተኞች ይኖሩናል፡፡ ፋብሪካው የመብራት መቆራረጥ አያስጋውም፡፡ የመብራት ኃይልን የሚመጥን መሳሪያ (ስታብላይዘር) የተገጠመለት ከመሆኑም በላይ በነዳጅ የሚሰሩ ጀነሬተሮችም ተተክለዋል” ብለዋል፡፡
የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት እየሰሩ መሆኑን አቶ ሽመልስ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የውሃ መያዣዎች የትም እየተጣሉ ስለሆነ መዲናዋ በውሃ መያዣዎች እየተበከለች ነው። የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ፣ በአዲስ አበባ ከተማ መንግሥት ያደራጃቸው 74 ማኅበራት አሉ፡፡ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች ከተደራጁ 10 ማኅበራት አንድ፣ አንድ ማኅበር ወስደን ቱታና የእጅ ጓንት በመስጠት የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ አቅደናል ብለዋል፡፡
የገጠሩ ማኅበረሰብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማግኘት ችግር እንዳለበት የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ በዓመት ለመሸጥ ካቀዱት 66 ሚሊዮን ጠርሙስ የታሸገ ውሃ ውስጥ፣ ከአንድ ጠርሙስ 2 ሳንቲም ሂሳብ በመቀነስ፣ በዓመት በሚገኘው 1.3 ሚሊዮን ብር 4 የውሃ ጉድጓዶችን ለማስቆፈር አስበናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡  

Read 4160 times