Sunday, 18 March 2018 00:00

ባሉ ሳይገኝ ሚዜ መረጠች

Written by 
Rate this item
(25 votes)

አንድ የታወቀ የዐረቦች ተረት አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ዐረብ በአንድ ገደል አፋፍ እየሄደ ሳለ አንሸራተተው። ሆኖም ወደ ገደሉ ግርጌ ከመውደቁ በፊት አንዲት ሐረግ ይዞ ተንጠለጠለ፡፡ ግቢ - ነብስ ውጪ-ነብስ ሆነ! በመውደቅና ባለመውደቅ ማህል እየታገለ ሳለ፣ አንድ ሼህ በገደሉ አፋፍ ጥግ - ጥጉን ሲሄዱ ዐረቡ ተንጠልጥሎ አዩት፡፡
ሼኹ - “ወዳጄ፤ እንዴት እዚያ ታች ልትንጠለጠል ቻልክ?”
ዐረቡ - “እንዴት ተንሸራትቼ እዚህ እንደወደቅኩ አላወቅሁም፡፡ እንደምንም ተሟሙቼ ጨርሶ ከመውደቄ በፊት ይቺን ሐረግ ያዝኩና ተንጠለጠልኩ፡፡”
ሼኹ - “በጣም ርቀሃል፡፡ እንዳላመጣህ እኔም እዚያ ታች ድረስ ልወርድ አይቻለኝም፡፡ እንዴት አድርጌ ልርዳህ?”
ዐረቡም - “ሼኪ፣ አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅዎትና መልሱልኝ፡፡”
ሼኹ - “መልካም፤ ጠይቀኝ”
ዐረቡ - “ሼኪ፤ ዝም ብዬ አላህን አምኜ ወደታች ልውደቅ? ወይስ ሐረጓን ይዤ ልቀጥል?”
ሼኹም - “ምስኪን ሰው ሆይ! አላህንም እመን፣ ሐረጓንም አትልቀቅ” አሉት፡፡
*   *   *
ድንገተኛ አጋጣሚዎች አደጋ አፋፍ ላይ ሊጥዱን ይችላሉ፡፡ ሲሆን በጥንቃቄ መጓዝ ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ከገቡበት አጣብቂኝ ለመውጣት ሁነኛ መላ መምታት ያስፈልጋል፡፡ ዓይነተኛ መፍትሔ ለማግኘት አስቀድመን አንደኛው ዕቅዴ ባይሳካ ሁለተኛው ዕቅድ ይኖረኛል፡፡ ሁለተኛው ባይሳካ ሶስተኛው ዕቅድ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ አበው፤
“ሁለት ባላ ትከል
አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
አንድ ዕቅድ ብቻ ይዞ እሱው ላይ ሙጭጭ ብሎ መጓዝ ያለመለመጥ ዕዳ (Cost of non-flexibility) ያስከፍላል፡፡ አንዳንዴም ጨከን ብሎ ሁኔታዎችን መቆጣጠር፣ ማፈግፈግ፣ ትክክለኛው ጊዜ ላይ ካልሆንን ጊዜ ለመግዛት መታገስ፤ ያሻል፡፡ ገሞራው እንዳለው፤
“ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር”
መሆኑ ነው፡፡
በሀገራችን ዕቅድን እስከ መጨረሻው ጥግ ድረስ አጥንቶ መጓዝ አልተለመደም። በዚያም ምክንያት ብዙ እንቅስቃሴዎች ወይ በቅጡ አይሰሩም ወይም ዳር አይደርሱም፡፡ አደባባይ ተሰርቶ ይፈርስና የትራፊክ መብራት ይሰራበታል፡፡ ኪሳራውን ማን ይከፍለው ይሆን? ከማለት በስተቀር፤ አሊያም ማነው ተጠያቂው? ከማለት በስተቀር መክሰስም፣ መውቀስም አለመቻሉ አሳዛኝ ነው፡፡ ዕቅድን በጥድፊያ ለመተግበር መሞከር “የቸኮለች አፍስሳ ለቀመች”ን ከማስተረት ሌላ ውጤት አያመጣም፡፡ በዘመቻ መስራትም የአንድ ሰሞን ግርግር ሆኖ እንደሚቀር አያሌ ክስተቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዳልገመገም በሚል ፈሊጥ፣ በታቀደው ጊዜ ጨርሻለሁ ለማለት ብቻ ቢጥደፈደፉና ነካ - ነካ አድርገው ቢተዉት፤ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ነው መጨረሻው፡፡ ሁሉን አጥብቀን ካልከወንን ጉዳያችን ሽባ ሆኖ ይቀራል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለው፤
“ከመታህ ድርግም
ከዋሸህ ሽምጥጥ፤ ነው!”
በጥንቃቄ ካየነው ታምኖ መከበርና ተፈርቶ መከበር ለየቅል ናቸው፡፡ ተወዶ መከበርና ተፈርቶ መከበርም ለየቅል ናቸው፡፡ አዩ ሌላ፣ ወዮ ሌላ እንደማለት! ዕምነት እንዲጣልብን ለማድረግ በቀናነት ሕዝብን ማመንና ማክበር ይገባል፡፡ እንደው በአቦ-ሰጡኝ የምንመራበት ጊዜ አልፏል፡፡ ያለ ጥናትና ያለ ፅናት የረገጥነው መሬት እንኳ አይሸከመንም፡፡ ስንወድቅ እንኳ በመላ ካልሆነ እንከሰከሳለን፡፡ እንደ አውሮፕላን በእርጋታ - መውረድ (soft-landing) የሚቻለው አስተውለን ወደ ላይ በመውጣት፤ ከዚያም መውረጃችንን አስተውለን በመውረድ ነው፡፡ “ሰተት ብሎ መግባት፣ ሰተት ብሎ መውጣትን አይናገርም” የሚባለው ለዚህ ነው! ስንጀምር መጨረሻውንም እናስላ! ረዥም ጊዜ መኖርን (longevity) ከዘለዓለማዊነት (eternity) ጋር አናምታታው! የአገር መሪ ታላቅ ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡ ራዕይ ያለው፣ ለውጥ የማያስፈራው፣ ታጋሽ፣ ሆደ - ሰፊ፣ የህዝብን ድምፅ ማዳመጥ የሚችል፣ ያሰበውን ለመፈፀም በቁርጠኝነት የሚጓዝ፣ ታታሪና የነገሩትን የማይረሳ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ያለውን ሰው ህዝብ በሚፈቅደው መንገድ ማግኘት ለአንድ አገር ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ከቀረ “ባሉ ሳይገኝ ሚዜ መረጠች” ይሆናል፡፡  

Read 9927 times