Tuesday, 13 March 2018 13:00

ፓርኪንሰን ህመም መሆኑ ከታወቀ 200 ዓመት ሞላው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(12 votes)
· ማኅበሩ ለመገንባት ላሰበው የህሙማን ማዕከል የድርጅቶችን ድጋፍ ጠይቋል · ሚያዚያ 6 ቀን 2010 የእግር ጉዞ ይደረጋል አቶ አሰፋ ዘገየ የ76 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ የፓርኪንሰን ታማሚና የማህበሩ የቦርድ አባል ናቸው። የሰውነት ሚዛናቸውን መጠበቅ ስለማይችሉ የሚሄዱት በከዘራ ተደግፈው ነው፡፡ እጃቸው በጣም ስለሚንቀጠቀጥ፣ ስክሪብቶ ጨብጦ መጻፍ፣ ውሃ መጠጣት፣ በአጠቃላይ ዕቃ መያዝ ከፍተኛ ችግር አለባቸው፡፡ የታሸገ ውሃ መክፈት አይችሉም፤ ተከፍቶ ቢሰጣቸውም እንኳ ውሃው ወደአፋቸው እስኪያደርሱት ግማሹ ይፈስሳል፡፡ በሽታው እየባሰባቸው ስለሄደ መጻፍ አቃታቸው። ስለዚህ፣ ከሚያስተምሩበት የፈለገ ዮርዳኖስ ት/ቤት በፈቃዳቸው ለቅቀው እቤት ተቀመጡ፡፡ አንድ ጎረቤታቸው የሆነ ሰው “ይህ ፓርኪንሰን የሚባል በሽታ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚህ በሽታ የምትሰቃይ አንዲት ሴት አለች፡፡ ከእሷ ጋራ ላስተዋውቆት” ይልና አሁን የ20 ዓመት የፓርኪንሰን በሽተኛ ከሆነችውና የፓርኪንሰን ሕሙማን ማኅበር መስራች ከሆነችው ከወ/ሮ ክብራን ከበደ ጋር ያገናኛቸዋል፡፡ የያዛቸው በሽታ ፓርኪንሰን መሆኑን ከተረዱ በኋላ ምን ማድረግ አለብን በማለት ከወ/ሮ ክብራን ጋር ተወያተው፣ በበሽታው የተጠቁ ሌሎች ሰዎችም የሚረዱበት ማኅበር ለማቋቋም ወስነው፣ ወ/ሮ ክብራን የማኅበሩ መስራች፣ አቶ አሰፋ ዘገየ ደግሞ የቦርድ አባል በመሆን ከጥቂት የበሽታው ተጠቂዎች ጋር በመሆን ከ7 ዓመት በፊት የፓርኪንሰን ሕሙማን ማኅበር መሰረቱ፡፡ ከጥቂት ሰዎች በስተቀር፣ ኅብረተሰቡ፣ ስለበሽታው ምንም ግንዛቤ የለውም ለማለት ይቻላል፡፡ ፓርኪንሰን በሽታ መሆኑን ስማያውቁ፣ እጁ የሚንቀጠቀጥና ሲሄድ ሚዛኑን የማይጠብቅ ሰው ሲያዩ፣ “ድመት ገድሎ ነው፣ ሰይጣን ለክፎት ነው፣ ተረግሞ ነው …” የሚሉ ከእውነት የራቁ ሐሳቦች ይሰነዘራሉ፡፡ ፓርኪንሰን ግን የአዕምሮ ሕመም ነው፡፡ በዓለም ህመም መሆኑ ከታወቀ ዘንድሮ 200 ዓመት ሲሆነው በኢትዮጵያ ግን ምን ያህል ህመምተኞች እንዳሉ እንኳ አይታወቅም፡፡ የ2010 ዓ.ም የፓርኪንሰን ሕሙማን ማህበር የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የሆነው አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ፣ በዓለም ላይ 10 ሚሊዮን የፓርኪንሰን ሕሙማን እንዳሉ ጠቅሶ፣ በኢትዮጵያ ግን ስለበሽታው ስለማይታወቅና ጥናትም ስላልተደረገ ምን ያህል የበሽታው ተጠቂዎች እንዳሉ አይታወቅም ብሏል፡፡ በዓለም ላይ ፓርኪንሰን ህመም መሆኑ ከታወቀ 200 ዓመት እንደሆነውና ሚያዚያ 6 ቀን 2010 የእግር ጉዞ እንደሚደረግ ለመግለጽ ከትናንት በስቲያ በኔክሰስ ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫጫ፣ አምባሳደሩ ደሳለኝ ኃይሉ፣ “አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ይህ በሽታ የሚያጠቃው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸውን አረጋውያን ነው ቢልም ወጣቶችም በበሽታው ሲያዙ እያየን ነው፡፡ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ሁን ሲሉኝ በደስታ የተቀበልኩት ለራሴ ስል ነው፡፡ ምክንያቱም ማናችንም ብንሆን በበሽታው ላለመያዝ ዋስትና የለንምና ነው፡፡ …” ሲል ገልጿል፡፡ ፓርኪንሰን የጤና ችግር ብቻ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ችግርም ነው ያሉት የማኅበሩ መስራች ወ/ሮ ክብራን፣ በሽታው አካል ጉዳተኛ እንደሚያደርግ፣ አካል ጉዳተኛ ከሆነ ደግሞ እንደቀድሞው መስራት ስለማይችል ገቢው እንደሚቆምና ቤተሰብ እንደሚቸገር፣ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ በራሱ መንቀሳቀስ ስለማይችል ምንጊዜም ድጋፍ የሚያደርግለት ሰው የግድ ያስፈልገዋል። ሚስት/ባል፣ እህት/ወንድም ወይም ሌላ ዘመድ ዕለታዊ ስራቸውን ትተው በሽተኛውን ሲንከባከቡ ገቢ ይቀንሳል፣ ቤተሰብ ለችግር ይዳረጋል፡፡ ማኅበራዊ የሚሆነው ደግሞ ህብረተሰቡ ስለበሽታው ስለማያውቅ፣ ከአጋንንት፣ ከሰይጣን፣ ከድመት መግደል … ጋር ስለሚያያይዘው ተገቢውን እንክብካቤ አይሰጣቸውም፣ ያገላቸዋል፡፡ … በማለት አስረድተዋል፡፡ ማኅበሩ ሲመሰረት ምንም አልነበረውም፤ ዛሬም አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከሚያደርጉለት ጥቂት ድጎማ በስተቀር የሚተዳደርበት በጀት የለውም፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ የመድኃነት አቅርቦትና የዋጋ ውድነት ችግር አለበት፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም፣ በሽታውን እንደአዕምሮ ሕመም ከመቀበል በስተቀር ህሙማኑን የሚጠቅም ይህ ነው የሚባል ነገር እየሰራ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡ በእርግጥ ህብረተሰቡ ስለበሽታው ግንዛቤ እንዲኖረው በዓመታዊው የእግር ጉዞ እንደሚሳተፍና ነርሶች ማሰልጠኑን የመ/ቤቱ ተወካይ ገልጸዋል፡፡ በክልሎች ምን ያህል የበሽታው ተጠቂዎች እንዳሉ ጥናት ስላልተደረገ አይታወቅም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የማኅበሩን መመስረት የሰሙ ሄደው የተመዘገቡ 500 በሽተኞች አሉ፡፡ ማኅበሩም ከእነዚህ ውስጥ ለባሰባቸው 350 ውሱን ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ኅብረተሰቡ ፓርኪንሰን በሽታ መሆኑን ካለመገንዘብ ከኋላቀር ባዕድ አምልኮ ጋር ስለሚያያይዛቸው ወጥተው ያልተመዘገቡ በርካቶች እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡ ማኅበሩ የፓርኪንሰን ህሙማን የሚጠለሉበት፣ የሚታከሙበት፣ የአካል እንቅስቀሴ (ፊዚዮ ቴራፒ) የሚሰሩበት … ማዕከል ለማቋቋም አቅዷል፡፡ ለዚህ ማዕከል ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ስለሌለው በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮን ብር የሚያተርፉ ድርጅቶች (ባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ የቢራ ፋብሪካዎች …) ለቤተክርስቲያን እንደሚሰጠው አስራት እነዚህ ድርጅቶችም 10 በመቶ ለማኅበሩ እንዲሰጡ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሩ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ተማፅኗል፡፡
Read 6034 times