Sunday, 25 February 2018 00:00

የወጣቱ ህልም - “ኢትዮ ኸርባል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(13 votes)

  • ፋብሪካው ዕፀ መዓዛ የሚባለውን ዘይት ከባህር ዛፍ ያመርታል
     • በአሁኑ ወቅት ሽያጫችን በቀን 30 እና 40 ሺህ ደርሷል
     • ትልቁ እቅዳችን የእሬት ጁስ ለገበያ ማቅረብ ነው

   ማቲዎስ መባ ይባላል፡፡ የ28 ዓመት ባለራዕይ ወጣት ነው፡፡ ከ7 ዓመት በላይ ከእሬት የሚዘጋጁ ምርቶችን ለሚያስመጣ የአሜሪካ ድርጅት የሽያጭ ሰራተኛ በመሆን እንደሰራ ይናገራል፡፡ በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ያልመው የነበረውን እፅዋት ተፈጥሮአቸውን ሳይለቁ ከሳይንስ ጋር በማዋሃድ የፀጉርና የቆዳ ውበትን የሚጠብቁ የፀጉር ቅባቶች፣ሻምፖዎችና ሳሙናዎች የሚያመርት ፋብሪካ አቋቁሟል፡፡ ተሳካለት
ይሆን? ምን አዳዲስ ምርቶችን እያቀረበ ነው? በገበያው ላይ ያለው ተቀባይነትስ እንዴት ነው? የፋብሪካው አቅምና ራዕይስ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከፋብሪካው መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ማቲዎስ መባ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

    እስቲ እንዴት ወደዚህ ዘርፍ እንደገባህ አጫውተኝ …?
ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ በMIS የተመረቅሁት፣ በ2002 ዓ.ም ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ እንደወጣሁ ግን ከእሬት የሚዘጋጁ ምርቶችን ለሚያመርት አንድ የአሜሪካ ኩባንያ፣ እዚሁ አገር የሽያጭ ሰራተኛ ሆኜ መስራት ጀመርኩና ለአንድ ዓመት ሰራሁ። ከዚያ ወጥቼ ደግሞ አንድ የማሌዢያ ኩባንያ ውስጥ ተቀጠርኩ፡፡ ይሄኛውም ኩባንያ የውበትና የጤና መጠበቂያ ምርቶችን የሚያከፋፍል ነው። ለዚህ ኩባንያ በሽያጭ ሰራተኛነት ከመስራት አልፌ፣ ፍራንቻይዝ ነኝ፡፡ ምርቶቹን እኔ አከፋፍላለሁ፡፡ በአጠቃላይ ግን በነዚህ ሰባትና ስምንት የሽያጭ ሰራተኝነቴ ዓመታት በርካታ ስልጠናዎችን በውጭም በአገር ውስጥም የመውሰድ እድሉን አግኝቻለሁ፡፡
ምን ዓይነት ስልጠናዎችን ነው የወሰድከው…?
እንግዲህ ለእነዚህ ኩባንያዎች ስትሰሪ፣ የሽያጭ ሰራተኛ ብቻ ሳትሆኚ ፕሮሞተርም ሆነሽ ነው የምትሰሪው፡፡ በዚህ ሂደትም ስልጠናዎችን  ታገኚያለሽ፡፡ ምርቶቹ እንዴት እንደሚመረቱ፣ ከምን ከምን እንደሚመረቱ፣ ምን ጥቅም እንደሚሰጡ፣ እንዴት ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸውና በአጠቃላይ በምርቶቹ ዙሪያ በርካታ ስልጠናዎች ለሰራተኞች ይሰጣል፡፡ ይህንን ምርት ልትሸጪ ስትሄጂ፣ ሰው ስለ ምርቱ ምንነትና ጥቅም ይጠይቃል፡፡ ሰፊ መረጃ ይፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ በደንብ ማስረዳት መቻል አለብሽ፡፡ እኔም በነገርኩሽ ዓመታት የወሰድኳቸው ስልጠናዎች በዚህ ዘርፍ እንድሰማራ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል፡፡ እኛ አገር ደግሞ ቁጥራቸው ከ1500 በላይ የሆኑ፣ ለውበትና ለጤና መጠበቂያ ምርት መሥሪያነት የሚያገለግሉ እፅዋቶች አሉ፡፡ ስለዚህ እኔም ወደ ዘርፉ ተሰማራሁ፡፡
እስኪ አንተ ስላቋቋምከው ፋብሪካ ንገረኝ--?
ፋብሪካው በ2009 ዓ.ም ነው የተቋቋመው። የሚገኘውም ጉርድ ሾላ ጀርባ፣ በተለምዶ ፊጋ በሚባል ቦታ ነው፡፡ ፋብሪካው እንግዲህ “ኢሴንሻል ኦይል” (ዕፀ መዓዛ) የሚባለውን ዘይት ከባህር ዛፍ እያመረተ ይገኛል፡፡ የባህር ዛፍ ዘይት በተለይ የአተነፋፈስ ችግር ላባቸው ሰዎች በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ ቁርጥማትና የሰውነት መተሳሰር ሲያጋጥም፣ የሚያምሽ ቦታ ላይ ዘይቱን ብትቀቢው ሰውነት ያፍታታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጉንፋን ይዞን ስንታፈን፣ እናቶቻችን ባህር ዛፍ ያጥኑን የለም እንዴ? ይሄ ደግሞ በሳይንሳዊ መንገድ ስለሚመረት በጣም ጠቃሚ ዘይት ነው፡፡ ለምሳሌ ተረከዝሽ ላይ ብታደርጊው፣ እስከ ራስ ፀጉርሽ ድረስ በሚሊዮን ወደ ሚቆጠር ሴልሽ ደቂቃ ሳይሞላ ይሰራጫል። እንደዚሁም ሮዝሜሪ (መጥበሻ ቅጠል) ከሚባለውም ዕፀ መዓዛ እናወጣለን፡፡
የሮዝሜሪ ኢሴንሻል ኦይል (ዕፀ መዓዛ) ጥቅምስ ምንድን ነው?
ከቅጠሉ የሚወጣው ዘይት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ፣ በጥናት የተረጋገጠ ጥቅም አለው፡፡ የተጎዳ ፀጉርን ለመጠገን፣ ለፀጉር መፋፋትና ለራስ በራነት ፍቱን መድሀኒቶች ናች፡፡ እነዚህን ዕፀ መዓዛዎችና እሬትን በሳይንሳዊ መንገድ በመቀመር፣ የእሬት ሳሙና እናመርታለን፡፡ የእሬት ሳሙና በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዳ ፊትን ይጠግናል፡፡ በተለይ ምገባ ላይ በጣም ውጤታማ ነው፡፡ እሬት በተፈጥሮው “አዳብቶጂን” ነው፡፡ አዳብቶጂን ማለት ደረቅ ቆዳን ወደ ማውዛት ሲያመጣ፣ በጣም ወዝ ያለውን ፊት፣ ወዙን የማመጣጠንና ትክክለኛ መጠን የማስያዝ ከፍተኛ ስራ ይሰራል፡፡ እኛም ቤዝ ኦይሎቹን ከእሬቱ ጋር ቀምረን፣ ለፊት ቆዳ እንዲስማማ አድርገን ነው የሰራነው፡፡ በዚህ በኩል ውጤታማ ሆነናል፡፡
ቤዝ ኦይል የሚባሉት ምንድን ናቸው?
ሳሙናው ሲሰራ በርካታ ዘይቶችን እንጠቀማለን፡፡ ለምሳሌ የወይራ፣ የኮኮናት ካስተር፣ አኩሪ አተርና ሰንፍላወር ዘይቶችን ከፋቲ አሲድ ጋር እንቀምርና ከዚያ እሬት ይጨመራል፡፡ እነዚህ ዘይቶች መጠናቸው ተቀምሮ ካልገቡ፣ እሬቱ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡
ታዲያ የእሬቱ ሚና ምንድን ነው?
እሬት ከ200 በላይ አክቲቭ ኮምፓዎንዶች እንዳሉት በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ብዙ ቫይታሚኖች፣ ሚኒራሎች፣ አሚኖ አሲዶችና ሌሎችንም ይዟል፡፡ ቫይታሚን A B C K የተባሉት አሉት፡፡ ካልሲየምና ዚንክም እሬት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በውስጡ ይዞ፣ ፊትንና ፀጉርን ይመግባል። ሁለት አይነት ችግር በፊትና በፀጉራችን ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ አንደኛው፡- ከላይ የገለፅናቸው ቫይታሚኖችና ሚኒራሎች እጥረት ነው፤ ሁለተኛው፡- ከውጭ ወደ ቆዳችን የሚገቡ መርዛም (ቶክሲክ) ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እጥረቱን በተመለከተ እሬቱ ፊታችንን (ቆዳችንን) ይመግባል፡፡ ከውጭ ወደ ቆዳ የሚገቡ መርዛማ ነገሮችን ያስወግዳል። ስለዚህ እሬት በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ እሬት በተፈጥሮው ፀረ ኦክሲድ ነው፤ ፀረ ፈንጋይ፣ ፀረ ባክቴሪያም ስለሆነ ከውጭ የሚገቡ ጎጂ ነገሮችን ያስወግድልሻል፡፡ በምድራችን እስከ ሶስተኛው የቆዳ ክፍል (ሌየር) የሚገባና የሚያክም ዕፅዋት እሬት ስለመሆኑ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ይሄ የምነግርሽ የእሬት ጉዳይ እንደ ብሪቲሽና አሜሪካን ጆርናል ላይ የተፃፉ የምርምር ውጤቶችን ነው፡፡ በዓለም ላይ ከፍተኛ ጥናት የተደረገበት ዕጽዋት፣ አሎውቬራ (እሬት) ነው፡፡ በዚህ እና በቤዝ ኦይል የሚሰራ የፀጉር ቅባት እናመርታለን፣ የፀጉር ሻምፖም እንዲሁ እያመረትን በደንበኞቻችን ተወዳጅ ሆነናል፡፡
ተወዳጅነታችሁንና ውጤታማነታችሁን እንዴት ነው የምትለኩት?
ደንበኞቻችን በተደጋጋሚ ይጠቀሙታል። ተጠቅመው ያገኙበትን ውጤት ይነግሩናል። ተፈላጊነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ ገና ሁለተኛ ዓመቱን በያዘበት በዚህ ሰዓት የቀን ሽያጫችን በቀን 30 እና 40 ሺህ ደርሷል፡፡ ይሄ ተወዳጅነታችንን ይጠቁመናል፡፡ እኛ በዘርፉ በጣም ትልቅ ቦታ የመድረስ ራዕይ ነው ያለን፡፡
ኢትኸርባል (ኢትዮ ኸርባል) በምን ያህል ካፒታል ነው የተቋቋመው?
የሚገርምሽ መነሻ ካፒታሉ ብዙ አይደለም፤ በመቶ ሺህ ብር ነው ስራ የጀመርኩት፡፡ አሁን ግን ብዙ ውጤት እያየን ነው፡፡ ይህን መቶ ሺህ ብር በብድርም ከራሴም ያለችኝን ጨማምሬ፣ ህልሜን አክዬበት ነው ለዚህ የበቃው፡፡ የመጀመሪያ ምርታችንን ኤግዚቢሽን ላይ ይዘን የገባን ሲሆን በፍጥነት ነው ተቀባይነት ያገኘነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ15 በላይ ቋሚ ሰራተኞችንና ከ20 በላይ የሽያጭ ሰራተኞችን ይዘን ለሌሎችም ስራ ፈጥረናል፡፡
እንዴት ነው ምርቶቻችሁን ለህዝቡ ተደራሽ የምታደርጉት?
ለጊዜው በሱቅም በሱፐር ማርኬትም አንሸጥም። በየቦታው ሱቆችን እየከፈትን ራሳችን ነው የምንሸጣቸው፡፡ ይህን ያደረግንበት ምክንያት እኛ ተፈጥሮንና ሳይንስን ቀምረን በጥራት ያመረትነው ምርት ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ ያለ ጥራት ከተሰሩት ጋር እንዲሸጥ ስለማንፈልግ ነው። በሌላ በኩል ለደንበኞቻችን ሀላፊነት መውሰድም እንፈልጋለን፡፡ ከእኛ ሱቅ ገዝተውና ተጠቅመው “ፊታችን ላይ ችግር ደረሰብን፣ አልተስማማንም” ቢሉ ኃላፊነት እንወስዳለን፡፡ እስካሁን በዚህ መልኩ የመጣ ደንበኛ የለንም፡፡ ሌሎችም ከእሬት የተሰራ በሚል ከሚሸጧቸው የውሸት ምርቶች ብራንዳችንን መጠበቅ ስለምንፈልግ፣ በቦሌ በስታዲየምና በተለያዩ ቦታዎች በከፈትናቸው ሱቆች ነው እየሸጥን የምንገኘው፡፡
አንድ አዲስ ምርት ሲሰራ ወይም ሲፈጠር የባለቤትነት መብት የማስከበር ስራ ይሰራል፡፡ እናንተስ የባለቤትነት መብታችሁን አስከብራችኋል?
አሁን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ወጥቷል። የባለቤትነት መብት ጠይቀን በሂደት ላይ ነው። የሚገርምሽ እኔ የዚህ መብት አስፈላጊነት ትዝ ያለኝና የገባኝ ዘግይቶ በመሆኑ ነው እስከ ዛሬ ያልጠየቅነው፡፡ የባለቤትነት መብቱ በቅርቡ በእጃችን ይገባል፡፡
የተስማሚነት ምዘና እንዲሁም የኢትዮጵያ የምግብ የመድሀኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የብቃት ማረጋገጫ ሰጥተዋችኋል ?
እንግዲህ የኮስሞቲክስ የመድኃኒትና የምግብ ነክ ጉዳዮችን ለመስራት ስትነሺ መጀመሪያ የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ማለፍ ግድ ነው፡፡ ይሄን በሙሉ አልፈናል፡፡ ምርቶቻችን ጠቅላላ ፓስተር ገብተው ተመርምረው፣ “ቶክሲሲቲ ቴስት” የሚባለውን ምርመራ አልፈው፣ ለቆዳ ተስማሚና ጤነኛ መሆናቸው ተረጋግጦልናል፡፡ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና የምትመለከቺውን ማረጋገጫ ሰጥቶናል፡፡ “ቢዩቲ ሶፕ” በሚባለው ዘርፍ ነው የጥራት ማረጋገጫውን ያገኘነው፡፡ በቀለም፣ በሽታ፣ በያዛቸው ንጥረ ነገሮች፣ መርዛማ ነው አይደለም፣ የሚለው ታይቶ ጠቅላላ ምርቶቻችን አልፈዋል። ይሄ ሁሉ በራስ መተማመን እንድንጨምር አድርጎናል። ሳሙናችን፣ ቅባታችን፣ ሻምፖና ኮንዲሽነራችን ሁሉም አስተማማኝ ናቸው፡፡
በፋብሪካችሁ ላብራቶሪ እና ይህን የሚሰራ ባለሙያ አላችሁ?
ፋብሪካችን ውስጥ ላብራቶሪ አለን፡፡ መጠነኛ ላብራቶሪ ሳይኖር፣ ባለሙያ ሳትቀጥሪ  የፋብሪካውን ስራ ማስጀመር አትችይም፡፡ ኬሚካል ኢንጂነር ባለሙያም አለን፤ በተቻለ መጠን ሁሉንም አሟልተን ነው የምንሰራው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ምርቶች ከተፈላጊነታቸው አንፃር ዋጋቸው ውድ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ እናንተ የምትሸጡበት ዋጋ የአገራችንን የኑሮ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው?
እኛ እንደነገርኩሽ፣ ምርቶቹን በጥንቃቄና በጥራት ብናመርታቸውም፣ ዋጋችን ከጥቅማቸው አንፃር ውድ የሚባል አይደለም፡፡
ለምሳሌ ኢትኸርባል አሎው ሶፕ የሚባለውን ሳሙናና ኢትኸርባል አውሎ ሄር ግሮውዝ ኦይል የሚባለውን ቅባት በስንት ብር ትሸጡታላችሁ?
ቅባቱ 150 ብር ሲሆን ሳሙናው 75 ብር ነው። ለማሳጅና ለመሰል አገልግሎት የሚውለውና ከባህር ዛፍ የምንሰራው ዘይት፣ በትንሿ ብልቃጥ በ30 ብር ትሸጣለች፡፡ ከአሜሪካ ከጃማይካ መጡ ተብለው፣ ምንም ሌላ ኢንግሪዲየንት ሳይጨመርባቸው፣ 600 ብር እና 1200 ብር የሚሸጡ ቅባቶች አሉ፡፡ እኛ ስንት ጠቃሚ ነገሮችን ቀምመን፣ በሳይንስ ቀምረን ነው፣ ከላይ በገለፅኩት ዋጋ የምንሸጠው፤ ከዚህ አንጻር ውድ ነው ብዬ አላስብም፡፡
እሬቱን ከየት ነው የምታመጡት?
እሬቱ ከጫንጮ ወጣ ብሎ ከሚገኝ አካባቢ ነው የምናመጣው፡፡ ሬቱ የሚበቅለው የትኛውም ሜዳ ላይ ስለሆነ ባለቤት የለውም፤ በነፃ ነው የምናመጣው ማለት ነው፡፡ ሆኖም የአካባቢው ሰው ቦታውን እንዲንከባከበው፣ መጥተን ስንወስድ ቅር እንዳይላቸው የተወሰኑ ክፍያዎችን እንፈፅማለን፡፡
የወደፊት ዕቅድህ ምንድን ነው?
በጣም ትልቅ ራዕይ አለኝ፡፡ ወደፊት የእሬት እርሻ እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ እሬት በቅባትና በሳሙና ተወስኖ እንዲቀር አልፈልግም፡፡ የእሬት ጁስ እስከ ማምረት ነው የማቅደው፡፡
የሚጠጣ ጁስ ማለትህ ነው? ምሬቱስ?
አዎ፤ የሚጠጣ ጁስ ከእሬት የመስራት ፍላጎት አለን፡፡ ምሬቱ በተወሰነ መልኩ ይኖራል ግን እየመረረ ይጠጣል፤ ለጤና እጅግ ተስማሚ ነው። የአሜሪካው ኩባንያ ውስጥ ስስራ፣ አንድ ሊትር እሬት ጭማቂ (አውሎ ቬራ ጁስ) በ750 ብር ነበር የምንሸጠው። እዚህ አገር እሬት ዝም ብሎ የትም ቦታ በስፋት ይበቅላል፤ ጥቅሙ አልታወቀም። አሜሪካኖች ጥቅሙን ስላወቁ ስቴብላይዝ አድርገውታል፡፡
ስቴብላይዝ ምን ማለት ነው?
ስቴብላይዝ ማለት ሲቆረጥ ቶሎ እንዳይቀላና እንዳይበላሽ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ሁለት ሶስት ቀን ሲቆይ ይቀላል፣ ይቀየራል፡፡ እኛ ለቅባቱም ለሻምፖና ኮንዲሽነሩም ሆነ ለሳሙናው ወዲያው ቆርጠን በትኩሱ ነው የምንጠቀመው፡፡ እኛ ትልቁ እቅዳችን ስቴብላይዝ የሚደረግበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን፣ የራሳችን የእሬት እርሻ ኖሮን፣ የእሬት ጁስ ለገበያ ማቅረብ ነው። ብዙ የጤና ችግሮችን እንደሚፈታ በርካታ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ እኔም በስራው ላይ በጣም ፍቅር አድሮብኛል፡፡ ሌት ተቀን ይህን ስራ ለማሳካት እየሮጥኩ እገኛለሁ። አሁን በውበትና በጤና መጠበቂያ ምርቶቻችን ላይ የተቀዳጀነውን እምነትና ተቀባይነት በማሳደግ፣ ፋብሪካውን ለማስፋፋት እቅድ አለን፡፡
ፋብሪካው የማምረት አቅሙ ምን ያህል ነው?
 ከእያንዳንዱ ምርት በቀን አንድ ሺህ ያመርታል። ከፍላጎቱ መጨመር አንፃር በፍጥነት ማሳደግና ማስፋፋት ግዴታችን ነው፡፡ በመጨረሻም ማህበረሰቡ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምርቶቻችንን እንዲጠቀም እንጋብዛለን፡፡

Read 5948 times