ባለፉት ሦስት ዓመታት በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት፤ በቤተሰብ ችግርና በሌሎች የገንዘብ ኪሳራ እክሎች ስትባክን የቆየችው የ25 ዓመቷ ሊንድሴይ ሎሃን፤ በፊልሙ ላይ ለመስራት ጉጉት እንዳደረባት ሮይተርስ አውስቷል፡፡ “ሊዝ ኤንድ ዲክ” በሰኔ ወር የፊልሙ ቀረፃ እንደሚጀመር ሲታወቅ ሊንድሴይ ሎሃን በተሳካ ትወና የተዳከመ ዝና እና ገቢዋን በማስመለስ ልታገግምበት እንደምትችል ተገምቷል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ ፊልም ከሰራች ሶስት ዓመት ያለፋት ሎሃን፤ ለትወናው በመመረጧ ታላቅ ክብር እንደተሰማት ብትገልፅም አንዳንድ ታዋቂ ሰዎች ለኤልዛቤት ቴይለር ስብእና የማትመጥን ናት በሚል ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡ በሙያው በቆየችባቸው አስር ዓመታት ከ20 በላይ ፊልሞች የተወነችው ሊንድሴይ ሎሃን፤ በዓለም ዙርያ 708 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘች ስትሆን በአንድ ፊልም 39 ሚሊዮን ዶላር አማካይ ገቢ እንዳላት የቦክስኦፊስ ባይ መረጃ ያመለክታል፡፡