Saturday, 17 February 2018 14:57

ከ3 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ሲጋራ ያጨሳሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 • 44% ትምባሆ ወደ አገራችን የሚገባው በኮንትሮባንድ ነው
   • ትምባሆ በችርቻሮ መሸጥ ህገወጥ ሊሆን ነው
   • የትምባሆ ፍላጐትን ለመቀነስ በትምባሆ ላይ የሚጣለው ታክስ ከፍ ማለት አለበት
   • ትምባሆ በዝቅተኛ ዋጋ ከሚሸጥባቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት

    ኢትዮጵያ ትምባሆን ለመቆጣጠር ከዓለም የጤና ድርጅት ቀድማ የራሷን ሕግ ያፀደቀች ሲሆን፤ ይህ ሕግ በኋላ ይፋ ከሆነው የዓለም የጤና ድርጅት ሕግ አንፃር ሲታይ ብዙ የሕግ ክፍተቶች እንደነበሩበት በመታወቁ ሕጉን ከጤና ድርጅቱ ጋር ለማጣጣም በድጋሚ ማስተካከያ ተደርጐበት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይገኛል፡፡ ሕጉ የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ እንዲፀድቅ፣ የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ከኢትዮጵያ ምግብ መድሐኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥርና አስተዳደር ባለስልጣን ጋር በመሆን እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማህበር ምክትል ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ጌትነት ጋር በማኅበሩ እንቅስቃሴዎች፣ በተጀመረው የትምባሆ ቁጥጥር ዘመቻና ማኅበሩ እየከወናቸው ባለው ተግባራትና ግብ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

   ማኅበሩ እንዴት እንደተቋቋመና እስካሁን ምን ተግባራት እንዳከናወነ ይግለፁልኝ?
ማኅበሩ የተቋቋመው በ1990 ዓ.ም ሲሆን አመለካከቱም በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በአስጊ ደረጃ ተከስቶ ከነበረው የወባ ወረርሺኝ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይህ ወረርሺኝ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከመንግስት አቅም በላይ ሆኖ የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በወቅቱ የነበረውን አደጋ “እልቂት” የሚለው ቃል የሚገልፀው ይመስለኛል። በዛን ወቅት እጃችንን አጣጥፈን ከምንቀመጥ፣ የአቅማችንን እገዛ እናበርክት ብለው በተነሱ በጐ ፈቃደኞች የተቋቋመ ማኅበር ነው፡፡ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት አከናውኗል፡፡ በወቅቱ የተከሰተውን ወረርሺኝ ለመግታት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ፣ ከኅብረተሰቡ ሀብት አሰባሰቦ፤ መድሐኒት በመግዛትና ለኅብረተሰቡ በማቅረብ የወቅቱን አስጨናቂ የወባ ወረርሺኝ መግታት ችሏል፡፡
ይህ ችግር የወለደው ማኅበር፣ የተቋቋመበትን ዓላማ ውጤታማ ካደረገ በኋላ አልቆመም፡፡ በአሁኑ ወቅት ጤንነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብ ማየት ራዕዩ አድርጐ እየሰራ ይገኛል፡፡ አንደኛ ወባን በመከላከል፣ በመቆጣጠርና በማጥፋት ሥራ ላይ ትኩረቱን አድርጐ ይሰራል፡፡ በዚህ በኩል ኅብረተሰቡ የወባ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገብርና ራሱን እንዲጠብቅ የሚያደርግ ፕሮጀከት በ5 ወረዳዎችና በሦስት ዞኖች የሚከወን ነው፡፡ የዛሬ 20 ዓመት አብዛኛው ኅብረተሰብ በወባ ወረርሺኝ ያለቀው ወረርሺኙ እንደሚከሰት ቀድሞ መተንበይ ባለመቻሉ ነበር፡፡ የኛ ማኅበር ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የወባን ወረርሺኝ ቀድሞ መተንበይ የሚያስችል የምርምር ማዕከል፣ አሜሪካ ከሚገኘው ሳውዝ ዳኮታ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አቋቁመን፣ የምርምር ስራ እንሰራለን፡፡
ምርምሩ የሚካሄደው የት የት አካባቢዎች ነው?
በአሁኑ ሠዓት በአማራ ክልል፣ በ47 ወረዳዎች እንሰራለን፡፡ በየሳምንቱ የወባ ሁኔታን መተንበይ እንችላለን፡፡ ይሄም ማለት በክልሉ መቼ ወባ እንደሚከሰት፣ እንዲሁም ወረርሺኝ ነው አይደለም የሚለውን በማወቅ፣ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ለውሳኔ ሰጪዎች መረጃ እንሰጣለን። ይህንን በአገር አቀፍ ደረጃ የማስፋፋት እቅድ አለ፡፡ ከዚህ በፊትም “አክማድ” ከተባለ ድርጅት ጋር በስድስት ክልሎች፣ ስድስት ጣቢያዎች ላይ ወባን ለመተንበይ የሚያስችል ስራ ተሰርቶ ነበር። ቦታዎቹም ጅማ፣ ዝዋይ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳርና ፓዌ መተከል ሳይቶች ናቸው፡፡ ሥራውም ከሜትርዎሎጂና ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆንና የእውቀት ሽግግር በማድረግ፣ ምን አይነት የአየር ፀባይ ሲኖር ነው፣ የወባ ወረርሺኝ የሚከሰተው የሚለውን “አርክ” የተባለ ሶፍትዌር በመጠቀም ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል፡፡
ኤችአይቪ ኤድስ ላይም ትሰራላችሁ አይደል?
አዎ! እንሰራለን፡፡ ማኅበራችን የኤችአይቪ መቆጣጠርና መከላከል ሥራ የጀመረው ከወባው ጋር በተያያዘ ነው፣ የወባ መድሐኒት ሲሰጣቸው፣ ለመድሐኒቱ ምላሽ የማይሰጡ ማለትም መድሐኒቱ የማያድናቸው ሰዎች ይገጥሙን ነበር፡፡ ጉዳዩ ሲታይ የወባ ታማሚዎቹ በተጨማሪም ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ናቸው፡፡ እናም ወባን በማከም ብቻ የተሟላ ጤና ማኅበረሰቡ ስለማያገኝ፣ ይህንንም አጣምረን መስራት ጀመርን፡፡ በዚህም ረገድ ተማሪዎችና ሴተኛ አዳሪዎች ላይ በማተኮር ከግንዛቤ ጀምሮ ሴተኛ አዳሪዎች ህይወታቸው የሚቀየርበትን መንገድ እስከ መፈለግ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል፡፡ አጫጭር የንግድ ስልጠና፣ ተዘዋዋሪ ብድር፣ የቁጠባ ባህል ማዳበርና በቡድን ሆነው ንግድ እንዲጀምሩ በማድረግ ትልቅ ለውጥ መጥቷል፡፡
ማኅበሩ በህፃናት ድጋፍ ላይም ይሰራል፡፡ ወባና ኤችአይቪ ኤድስ ብዙ ህፃናትን ያለ አሳዳጊ ያስቀረበት ችግር የቅርብ ትዝታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወባና ኤችአይቪ ላይ ስንሰራ ያገኘነው ሌላው ክፍተት በመሆኑ፣ በሁለት መንገድ መሥራት ጀመርን፡፡ አንደኛው ልጆቹ ከቅርብ አሳዳጊዎቻቸው ጋር ሆነው እንዲማሩ፣ ለትምህርትና ለምግብ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ - Fostered Program እንለዋለን፡፡ ሁለተኛው በወረርሺኙ ጊዜ ማኅበሩ በየወረዳው ያቋቋማቸው ኮሚቴዎች ነበሩ፤ እነዚህ ኮሚቴዎች በየአካባቢያቸው ሐብት በማሰባሰብ፣ የአካባቢውን ችግረኛ ህፃናት ይደግፋሉ፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ 166 ህፃናትን የወረዳ ኮሚቴዎች መደገፍ ችለዋል፡፡ በተጨማሪም የወጣት ልጃገረዶች ድጋፍም አለን፡፡ ከከተማ በጣም በራቅሽ ቁጥር የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በቅርብ አይገኙም። እናም እስከ 8ኛ ክፍል በአካባቢያቸው ከተማሩ በኋላ ቀጣይ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ከቤተሰብ ወጥተው፣ ራቅ ወዳለ ከተማ ሲሄዱ ቤት ይከራያሉ፣ ምግብ አለ፣ የትራንስፖርት ወጪ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ለቤተሰባቸው ተጨማሪ ጫና ነው፡፡
አቅም የሌላቸው ወላጆች ደግሞ ይህን ማድረግ አይችሉም፤ ችግሩ ደግሞ ልጃገረዶች ላይ ይበረታል፡፡ ልጃገረዶቹ ያላቸው እድል ሁለት ነው፤ አንደኛው ከ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ማቋረጥ ሲሆን ሁለተኛው ለትምህርት ርቀው ሲሄዱ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት ወዳልተፈለገና አደገኛ ህይወት ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት ማኅበሩ በጣም ችግረኛ ለሆኑና አማራጭ የሌላቸውን ልጃገረዶች በቡድን ቤት በመከራየት፤ ምግባቸውን እያበሰሉ፣ ከ9-12ኛ ክፍል እንዲማሩ በማድረግ፣ እና እስከ ዩኒቨርስቲ በመላክ ውጤታማ የሆኑ ሐኪሞችን፣ የሂሳብ ባለሙያዎችን፣ መሐንዲሶችንና የሌላ ሙያ ባለቤት የሆኑ ልጃገረዶችን አስመርቋል፡፡ ከት/ቤቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠርም የተለየ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ማኅበሩ በትጋት ይሰራል፡፡
በአሁኑ ሠዓት 14 ልጃገረዶች በጋራ ቤት ውስጥ እየኖሩ የሚማሩ ሲሆን 20 ተማሪዎች ደግሞ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያየ ሙያ በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የትራንስፖርትና የኪስ ገንዘብ ከመስጠት አልፎ ተመርቀው ሥራ እስኪይዙ መቋቋሚያ ገንዘብም ይሰጣል፡፡ ይህን ሥራ በማድነቅ የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከሊዝ ነፃ የሆነ 10 ሺህ ካ.ሜ. ቦታ ሰጥቶን፣ በአሁኑ ሰዓት ስድስት እያንዳንዳቸው 20 ተማሪዎች የሚይዙ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት፣ በአንድ ባች የሚማሩ ተማሪዎችን 120 ለማድረስ ጥረት ላይ እንገኛለን፡፡ አንድ ብሎክ የቡድን መኖሪያ ተሠርቶ 14 ልጃገረዶች እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ ሌላው የቤተሰብ ምጣኔን፣ ኤችአይቪንና ቲቢን ያቀናጀ ፕሮጀክት ነድፈን፣ በስድስት የጤና ጉዳዮች ላይ አተኩረን በ12 ወረዳዎችና በ60 ቀበሌዎች “GSI” ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር እየተገበርን ነው፡፡ በአጠቃላይ ማኅበሩ ጤና ላይ ትኩረት አድርጐ፤ ድህነትን በቤተሰብ ደረጃም ቢሆን ለመቀነስና ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የሚችለውን እያደረገ ነው፡፡
እስኪ ወደ ትንባሆ ጉዳይ እንምጣና በዚህ በኩል የማኅበሩ ሚና ምን እንደሆነ ይንገሩን?
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተባበሩት መንግስታት ስነ-ሕዝብ ፈንድ ጋር በመተባበር በ25 ት/ቤቶች ወጣቶችን ትኩረት ያደረገ ፕሮጀክት ቀርፀን ፈጽመን ነበር፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ ደግሞ ወጣቶቹ ባለ ራዕይ እንዲሆኑ፣ ራሳቸውን ከስነ-ተዋልዶ ጤና ችግር እንዲጠብቁና ጤናማ ዜጋ እንዲሆኑ ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት የተረዳነው ነገር ምንድን ነው? ወጣቶች ለተለያዩ ሱሶች እየተጋለጡ መሆኑንና ከሱሶቹ መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የትምባሆ ሱስ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ አገር ተረካቢ ወጣቶች በሱስ ምክንያት መድረስ የሚችሉበት ሳይደርሱ እንዳይመክኑ ልንጠብቃቸው እንደሚገባ ተገነዘብንና ወደ ትምባሆ ፕሮጀክት ገባን ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የነደፍነው ፕሮጀክትና የምንተገብረው ሥራ የትምባሆ ቁጥጥር ፕሮጀክት ነው፡፡ የትምባሆ ቁጥጥርን ተግባራዊ ያደረጉ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው፤ ጠንካራ ሕግ ከእነማስፈፀሚያው ያወጡ አገራት በቁጥጥሩ ረገድ ውጤታማ ሆነዋል፡፡
በዚህ በኩል እንደምሳሌ የሚጠቀሱ አገሮችን ቢነግሩኝ?
ለምሳሌ አውስትራሊያን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደነዚህ ያሉ አገሮች ትምባሆን በመቆጣጠር ረገድ ጠንካራ ሕግ ስላወጡ፣ የቁጥጥሩን ሥራ ውጤታማ አድርጐላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በትምባሆ ዙሪያ የራሷን ሕግ አላፀደቀችም እንዴ?
አጽድቃ ነበረ፡፡ ነገር ግን የእኛ አገር ሕግ የወጣው የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ካወጣው ዓለም አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት ሕግ በፊት ነበር፡፡ ይህንን ስምምነት በርካታ የዓለም አገራት ፈርመዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከፈራሚዎቹ አንዷ ናት፡፡ በፓርላማም ፀድቋል፡፡ እንደነገርኩሽ ኢትዮጵያ ከWHO ቀድማ የራሷን የትምባሆ ቁጥጥር አዋጅ አውጃ የነበረ ቢሆንም፤ የዓለም የጤና ድርጅት ካወጣው የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት አንፃር ሲታይ፣ የእኛ ቀድሞ በመውጣቱ፣ አንድ አገር ትምባሆን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ዝርዝር ጉዳይ የያዘ አልነበረም፡፡ በርካታ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ እንደነገርኩሽ አንድ አገር የትምባሆ ቁጥጥርን ለመተግባር የተሟላ ሕግ ማውጣት አንዱና ዋናው ነው፡፡
ሁለተኛ ኢትዮጵያም በWHO የወጣውን ስምምነት ስለፈረመች ያንን ሕጓን ከዓለም አቀፉ ስምምነት ጋር ማጣጣም ስለሚኖርባት፣ የተሟላ ሕግ ለማፅደቅ በእንቅስቃሴ ላይ ናት፡፡ የእኛም ማኅበር በትምባሆ ቁጥጥር ላይ ሲሰራ የመጀመሪያ ተግባሩ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማዳበር ሕጉ የሕዝብ ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግና ሕዝቡም አዋጁን በደንብ ተረድቶ ተግባራዊ በማድረግ ትምባሆ በሕዝብ፣ በአካባቢና በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ መታደግ ነው። ይህንን የምንሰራውም ከሚዲያ ተቋማት ጋር በመተባበር ነው፡፡
የእናንተ ማኅበር ከመንግስት የጤና ተቋማት ጋር የሚሰራው ሥራ አለ እንዴ?
በጣም ጥሩ! ይሄ ሃላፊነት የተሰጠው ለኢትዮጵያ የምግብ መድሐኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ በዋናነት ሥራው የተሰጠው ለጠቀስኩት የመንግሥት ተቋም ቢሆንም፤ የእኛ ሥራ ተቋሙን መደገፍ ነው። የእኛም ማኅበር መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደ መሆኑ፤ ከመንግሥታዊ ተቋም ጋር ስምምነት ተፈራርመን ነው ሥራውን የጀመርነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ትምባሆ በኢትዮጵያ አምራች ኃይል በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት የሚጠቁሙ በቅርብ የወጡ ጥናቶች ይኖራሉ?
በ2016 እ.ኤ.አ. የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጤና ማኅበር ከኢትዮጵያ የምግብ መድሐኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባስልጣን ጋር በመሆን፤ “ግሎባል አደልት ሰርቬይ” የተባለ ጥናት አስጠንቶ ነበር፡፡ ጥናቱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን ስልቶች ተጠቅሞ፣ ከ15 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የተሰራ ነው፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው፤ 5 በመቶ ኢትዮጵያዊያን (3.2 ሚሊዮን ሰዎች) ሲጋራ ያጨሳሉ፡፡ ከነዚህም መካከል 8.1 ያህሉ ወንዶች ሲሆኑ፤ 1.8 ያህሉ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ሌሎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ሲጋራ ከሚያጨሱት 50 በመቶዎቹ ይሞታሉ፡፡ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ፤ በሲጋራ ምክንያት ያለ ዕድሜያቸው የሚታመሙና የሚሞቱ ሰዎች በዓመት ሰባት ሚሊዮን ደርሷል። የሚገርመው ከነዚህ መካከል 890 ሺህ (ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉት) ቀጥታ አጫሽ ሳይሆኑ ሁለተኛ አጫሾች (Passive Smokers) የሚባሉት ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር በኤችአይቪ፣ በቲቢ እና በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ከሚያጡት ሰዎች ቁጥር ድምር ይበልጣል፡፡
ዓለማችን በሲጋራ ምክንያት በየዓመቱ ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር ገደማ እንደምታጣ ይነገራል፡፡ ይሄ እውነት ነው?
እኔ ኢትዮጵያ በሲጋራ ምክንያት በዓመት ይህን ያህል ብር ታጣለች፤ በዓለም ደረጃም ይህን ያህል ብር ይወጣል ተብሎ በቁጥር የተጠና ትክክለኛ አሐዝ ባልናገርም፤ በህዝብ፤ በአካባቢና በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ግን በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይሄ በማያሻማ መልኩ በተለያዩ ዶክመንቶች ላይ የሚታይ ነው፡፡
ቀድሞ የወጣው የእኛ አገር የትምባሆ ቁጥጥር አዋጅ በኋላ ከወጣው የዓለም የጤና ድርጅት ስምምነት አንፃር ሲታይ ያሉት ክፍተቶች ምን ምን ነበሩ?
ጥሩ ጥያቄ ነው! ብዙ ክፍተቶችን መጥቀስ ይቻላል ግን ዋና ዋና የምላቸውን ልጥቀስ፡፡ ለምሳሌ ሲጋራ ሕዝብ በተሰበሰበባቸውና በሃይማኖት ስፍራዎች ማጨስ የተከለከለ እንደሆነ የበፊቱ የአገራችን ሕግ ይጠቅሳል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ይህንን ሕግ ተላልፎ ሲያጨስ ቢገኝ፣ የሚደርስበት ቅጣት ምንድን ነው የሚለው ማስፈፀሚያ ስልት የለውም፤ ማስፈፀሚያ ከሌለው ያንን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም፡፡ አንዱ ይሄ ነው፡፡ ሁለተኛው በሲጋራ ፓኮዎች ለይ “ግራፊክ ዋርኒንግ” የሚባል አለ፡፡ የትምባሆ አምራች ኩባንያዎች በዚያ ባኮ ላይ “ግራፊክ ዋርኒንግ” የሚያስቀምጡበት ስታንዳርድ አለ፡፡ የእኛ አገር ሕግ ከዚህ አንፃር ያስቀመጠው ነገር ግልፅ አይደለም፡፡ 30 ፐርሰንት እንዲቀመጥ ይጠይቃል፡፡ ግን የእኛ አገር ሕግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡
ስለዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት፤ ሲጋራ ምን ያህል ጤናን እንደሚጐዳ በግልጽና በሰፊው የሚያሳይ ግራፊክስ መቀመጥ አለበት፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት በጣም ዝቅተኛ ብሎ ያስቀመጠው 30 ፐርሰንት  ነው፡፡ እኛ አገር ትልቅ ሆኖ የተቀመጠው በተቃራኒው 30 ፐርሰንት ነው፡፡ እስከ 70 በመቶ የሚሄዱ አገሮች አሉ፡፡ ሌላው ትኩረት የሚያስፈልገውና የትምባሆ ተጠቃሚውን ለመቀነስ፣ ፍላጐት መቀነስ አስፈላጊ ነው፡፡ ፍላጐትን ለመቀነስ በትምባሆ ላይ የሚጣለው ታክስ ከፍ ማለት አለበት፡፡ በዓለም ላይ ትምባሆ በዝቅተኛ ዋጋ ከሚሸጥባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡
የዳቦ ዋጋ ከሲጋራ ዋጋ ይበልጣል ይባላል?
ትክክል ነው፡፡ ስለዚህ የአጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ ትምባሆን መቀነስ የግድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ታክስ መጨመር ግድ ይላል፡፡ በሌላ በኩል ቅድም ያነሳሽው ሲጋራን በተናጠል መሸጥ ጉዳይ ነው፤ እሱም በሕጉ ውስጥ በደንብ ትኩረት አግኝቶ መቀመጥ አለበት፡፡
ትምባሆን በተናጠል መሸጥ መከልከል የሲጋራ አዟሪዎችን ያበራክታልና በዚህ መልኩ ሕጉን መተግበር አይቻልም የሚሉ አሉ፤ እርስዎ ምን ይላሉ?
በነገራችን ላይ ሕግ ሲወጣ ለተለያየ ሰው የተለያየ ሕግ አይወጣም፤ ሁሉም ዜጐች የሚያውቁት፣ የሚያከብሩትና የሚያስከብሩት መሆን አለበት፡፡ በፊት በአገራችን የወጣው ሕግ ማስፈፀሚያ ስላልነበረው ያስቸግር ነበር፤ አሁን በሂደት ላይ ያለው ሕግ እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ይሆናል፡፡ ሲጀመር በችርቻሮ መሸጥ ሕገ-ወጥ ነው፣ አሁንም ሕጉ ሲፀድቅ፤ በሱቅም ውስጥ ሆነ ከሱቅ ውጭ ሲሸጥ የተገኘ፣ በሕግ አስከባሪዎች ይቀጣል። ህዝቡም እራሱ ግንዛቤው አድጐ፣ ሕገ-ወጦችን ያጋልጣል፡፡
ሱቅ ያለው ሰው አድራሻ ስላለው በዚያ ሊቀጣ ይችላል፤ አዟሪው እንዴት ይቀጣል?
ይሄ በሲጋራ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሕገ-ወጥ ንግድ ላይ ብናወራ ይሻላል፤ በዚህ ረገድ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በሲጋራ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሕገ-ወጥ ንግዶች ላይ እልባት ማበጀት ያሻል፡፡
በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የሲጋራ መጠን ጤናንም የአገር ምጣኔ ሀብትንም የሚጐዳ ነው፡፡ ይሄስ በሚወጣው ሕግ ታሳቢ ተደርጐ ይሆን?
እንግዲህ አዲሱ አዋጅ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለን ከምንጠብቃቸው ጉዳዮች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የሲጋራ ጉዳይ ነው፡፡ 44 በመቶው የሲጋራ መጠን ወደ አገራችን የሚገባው በሕገ-ወጥ መንገድ ነው፡፡ እንዳልሺው ሕገ-ወጥ ተግባር ነው፡፡ ሁለተኛ የአገር ኢኮኖሚም ይጐዳል፡፡ ይሄ ኮንትሮባንድ ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡
ማኅበራችሁ ባለፈው ሳምንት ሁለት ወርክሾፖችን፣ ለሚዲያ ተቋማትና ለባለድርሻ አካላት አዘጋጅቶ ጥናቶች ቀርበው፣ ውይይቶችና ጥቆማዎች ተደርገዋል፡፡ ማኅበራችሁ የትምባሆ ቁጥጥር አዋጁ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ እንዲፀድቅ በቀጣይ የሚከውናቸው ተግባራት ምንድን ናቸው?
በጣም ጥሩ! ማኅበራችን አዋጁ የህዘብ ድጋፍ እንዲያገኝ መጀመሪያ የሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ሲሆን፤ ይህ የሚከወነው በመገናኛ ብዙሀን ተቋማትና ባለሙያዎች አማካኝነት በመሆኑ የመጀመሪያዎቹ ወርክሾፖች በስኬት ተጠናቀዋል፡፡ ብዙ የሚዲያ ሽፋንም አግኝተዋል፡፡ ማኅበራችን ከወርክሾፖቹ የተገኙ ግብአቶች በመጠቀምና በመቀመር፣ ከሚዲያ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ፣ ሕዝቡ ሲጋራ ምን ያህል ጐጂ እንደሆነ ተገንዝቦ፣ የጉዳዩ ባለቤት እንዲሆንና አዋጁ በማኅበረሰቡ ድጋፍ አግኝቶ እንዲፀድቅ ማድረግ የመጨረሻ ግባችን ይሆናል ማለት ነው፡፡

Read 2935 times