Sunday, 11 February 2018 00:00

ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ በመሲና የቃጤ ግጥሚያ ተከፍቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 • ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው
       • ‹‹ከጥቃት ነፃ ህይወት መብቴ ነው›› በሚል መርህ ይካሄዳል፡፡
       • 12ሺ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ 300 የክለብ አትሌቶች ናቸው፡፡

   በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ለ15ኛ ጊዜ ሊካሄድ ነው፡፡ የካቲት 27 በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫው 12 ሺ ሴት ስፖርተኞች እንደሚሮጡበት ይጠበቃል። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ በ5 ኪሎ ሜትር ሩጫው 300 ሴት አትሌቶች የተለያዩ ክለቦችን በመወከል እንደሚወዳደሩ፤ ለአሸናፊ የተዘጋጀው 20 ሺ ብር ሽልማት እንደሆነ፤ በተለያዩ ደረጃዎች ለሚያሸንፉት ከ100ሺ ብር በላይ ለሽልማት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ በየዓመቱ የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ሴቶችን ስኬት ለማክበር መሆኑን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ይገልፃል፡፡ ስለሆነም ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ ሲዘጋጅ፤ የውድድሩም መክፈቻ ስነ ስርዓት አትሌት መሰረት ደፋር በታዳጊነቷ የተማረችበትና አስኮ አካባቢ የሚገኘው የፊታውራሪ አውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ 1ኛና መለስተኛ ደረጃ ት/ቤት ሆኗል፡፡ በቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ አምባሳደርነት ለረጅም ጊዜ ማገልገሏን ለማመስገንና አስተዋፅኦዋን ለማድነቅ ነው፡፡ እንደውም አትሌቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫውን “የመሲ ሩጫ” ይሉታል ስትል የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስትራቴጂና አቪየሽን ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ለስፖርት አድማስ ተናግራለች፡፡
የመክፈቻው ስነ ስርዓት በት/ቤቱ ቅጥር ጊቢ ሲካሄድ የቃጤ ስፖርት የተለመደ ባይሆንም ብዙዎቹ ተማሪዎች በየሰፈራቸው ስለሚጫወቱት ይህንን የልጆች ጨዋታ ለማስተዋወቅ ጥረት አድርገን ተሳክቶልናል ያለችው ዳግማዊት፤ ቃጤ የቡድን ስራ ቅልጥፍናና ፍጥነት እንዲሁም ቴክኒክ የሚያስተምር ስፖርታዊ ጨዋታ መሆኑን በተግባር ተማሪዎች አይተውታል፡፡ ስለሆነም በየትምህርት ቤታቸው ሊያዘወትሩት ይገባል። በማለትም መልክቷን አስተላልፋለች፡፡
ከአትሌት መሰረት ደፋር ባሻገር 15ኛው የቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የመክፈቻ ዝግጅት ታላለቆቹ አትሌቶች ጌጤ ዋሚና ብርሃኔ አደሬ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ ታላቁ ሩጫ ለኢትዮጵያ አድልቷል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኃላፊ የማራቶን አትሌቷ ጌጤ ዋሚ በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ በመገኘት “ከጥቃት ነፃ ህይወት መብቴ ነው” የሚለውን መርህ ከተማሪዎች ጋር ማስተጋባቷ ትልቅ ውጤት እንደሆነም አመልክታለች፡፡ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ 1ኛና መለስተኛ ት/ቤት ውስጥ የተዘጋጀውን የቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ መክፈቻ ከ2 ሺ በላይ ተማሪዎች ታድመውታል፡፡
ለ15ኛው የተባበሩት መንግስታት ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ምዝገባው የፊታችን ረቡዕ የሚጀመር ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት የእናት ባንክ 4 ቅርንጫፎች፤ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮና በካፒታል ሆቴል እንደሚገኝ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡   የቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫው መክፈቻ የማራቶን አትሌቶቸ መሰረት ደፋርና ጌጤ ዋሚ ከት/ቤቱ በእያንዳንዱ ቡድን 5 ተማሪዎች በአምበልነት በመምራት 4 ግጥሚያዎችን አድርገዋል፡፡ የእነ መሰረት ደፋር ቡድን 3 ለ 1 ያሸነፈበት ነበር፡፡
ለ35 ዓመታት በት/ቤቱ አስተማሪነት የሰሩት ሁለገብ አስተማሪ ለስፖርት አድማስ ሲናገሩ፤ የታላላቆቹ አትሌቶች ኃይሌ ገ/ስላሴ. ጌጤ ዋሚና መሰረት ደፋር በት/ቤቱ መገኘት ትልቅ መነቃቃት የሚፈትር መልካም ተግባር ብለውታል፡፡ ታላላቆቹ አትሌቶችና የት/ቤቱ ተማሪዎችና አስተማሪዎች በአንድ ጊቢ ለአንድ ዓላማ መሰብሰባቸው፣ አብረው የልጆች ጨዋታ መጫወታቸውና፣ መደነሳቸው ፍፁም አስደስቶናል ብለዋል - የመሰረት አስተማሪ፤ ትምህርት ቤቶች፣ የታላላቅ ስፖርተኞችና ሌሎች ምሁራንና ባለሙያዎች መገኛ ነው ያሉት መምህሯ፤ ይህን ያንፀባረቀ የመክፈቻ ስነስርዓት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስለተዘጋጀ አድናቆታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ስፖርትን ወይም ማንኛውም ሙያ በትምህርት ቤት ከልጅነት መጀመር ያለበት መሆኑን፣ የተሳካላቸው ጀግኖች ተምሳሌትነታቸውን ማሳየታቸውም ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ በቀድሞ ት/ቤቷ ተገኝታ ከተማሪዎች ፊት በመቆም መልእክት ማስተላለፏ ከፍተኛ ኩራት እንደሆነላት የተናገረችው አትሌት መሰረት ደፋር የፈረመችበትን የራሷን ማስታወሻ ፎቶ ያከፋፈለች ሲሆን ለንግግሯ በመድረክ ላይ ቆማ ተማሪዎች ስፖርት መስራት ብንፈልግም ውድድር አይዘጋጅልንም ይላሉ ብላ ጠይቃ ነበር፡፡ የት/ቤቱ ስፖርት አስተማሪ ደግሞ በሰጡት ምላሽ ተማሪዎቹን የምናወዳድርበት ስለሌለን ነው አሉ። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስፖርት ሜዳውን አስጠርጎ ለውድድር ያዘጋጃል ብሎ ቃል ገብቷል፡፡

Read 3689 times