Sunday, 11 February 2018 00:00

በመስከረም የሚቆስል በሰኔ ያሳክከዋል

Written by 
Rate this item
(19 votes)

ሁለት አንበሶች እኔ እገዛ፣ እኔ እገዛ ተጣሉ! አሉ፡፡ አንዱ፤ ዕድሜዬ ረዥም ነውና ለመግዛት የኔ ነው የሚፈቅደው ባይ ነው፡፡
ሌላው፤ “ባያት በቅድመ - አያቴ ስለተመረቅሁ - ገዥው እኔ ነኝ” አለ፡፡
“እንግዲያው ይለይልን” ሆነ፤ የመጨረሺያው መፍትሄ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ጥንቸል ባቅራቢያው ሆና ትታዘባለች፡፡
ክፉ ትግል ገጠሙ፡፡ ብዙ ፍልሚያ ካካሄዱ በኋላ ሁለቱም ደክመው መሬት ላይ ተዘረሩ፡፡ Ending infatigue እንደሚባለው ነው፡፡ ጥንቸል ውጤቱን ስትጠባበቅ ቆይታ ሁለቱም አቅም አጥተው መውደቃቸውን አየች፡፡ ይሄኔ በኩራትና በእብሪት፣ በዙሪያቸው ተቀምጣ ሰው፣ ባለፈ ባገደመ ቁጥር፤
“ትልቅና ጉልበተኛ መሆን ሳይሆን ብልሃተኛ መሆን ነው የድል ሚስጥሩ” እያለች ማስረዳቷን ቀጠለች፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አንደኛው አንበሳ ከተኛበት ነቃ፡፡ ይሄኔ ጥንቸል፤
“እርስዎ እንደሚነሱ አውቄ አካባቢውን ስጠብቅ እስካሁን ቆይቻለሁ፡፡ እንግዲህ በሰላም ከነቁ ብሄድ ይሻላል፡፡” አለች፡፡
አንበሳም፤ ቀጨም አድርጎ ያዛትና፤ “ለሰዎች ሁሉ፤ ብልሃት የሌላቸው አንበሶች ይወድቃሉ ስትይ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ለዚያም ዋጋ ትከፍይበታለሽ፡፡ በኛ ደክሞ መውደቅ አንቺ ዝና ልትገዢ መጣርሽ ምን እንደሚያስከፍል ማወቅ አለብሽ!” አላት
ጥንቸልም፤
“በእንቅልፍ ልብዎ መሆን አለበት የሚያወሩኝ” አለች፡፡
አንበሳም፤
“አይ ጥንቸል! በእንቅልፍ ልቤም’ኮ ልቤ የራሴ ነው!” ብሎ አድቅቆ ደቁሶ በላት!
*        *      *
ጊዜ አመቸኝ ብሎ መፎከር ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ ጊዜ ሰጠኝ ብሎ ዝና ለማፍራት መሞከር በመጨረሻ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ዝና መቼ መጠቂያ እንደሚሆን ስለማይታወቅ ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ አንዲት ያልታወቀች ገጣሚ፤
“ዝናኮ እንደንብ ነው
ዜማ አለው
እሾክ አለው
እግዚኦ ለሰማያቱ ያለህ፣
ለካ ክንፍም አለው!” ብላለች፡፡
የዝና ክንፍ የት እንደሚያደርሰን አይታወቅም፡፡ ለጊዜው የሚያደንቀን ህዝብም መቼ ጀርባውን እንደሚያዞርብን አይታወቅም፡፡ ዝና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው! ዛሬ የገነንን ይመስለናል፡፡ ነገ ግን ስንወድቅ ምሳሩን እኛው ላይ እንደሚሰነዝር አንርሳ፡፡ ቂሙን የማይረሳ ህዝብ፣ መቼም ይሁን መቼ፣ ለሰራነው ዋጋ ሳያስከፍለን አይቀርም፡፡ ለጊዜው ቢያቀረቅርም ቀኑ ሲመሽብን፣ ታሪክን ጠቅሶ ቁጭቱን ይወጣል፡፡ ሁሉም የጊዜ ጉዳይ ነው፤ ይለናል፡፡ ስለዚህ ዛሬውኑ መናዘዝ፣ ዛሬውኑ ህዝብን ይቅር በለኝ ማለት የመዳኛችን አንዱ መንገድ ነው! ውጊያውን እንጂ ጦርነቱን እንዳላሸነፍን እንወቅ! (Won the battle but not the war) ጦርነቱ ያለው ህዝብ ልቦና ውስጥ ነውና! “የጀርመን ግንብ ቢፈርስም፤ ህዝቡ ጭንቅላት ውስጥ አልፈረሰም” የሚባለው ለዚህ ነው! አሁንም ደግመን ደጋግመን፣ ለህዝቡ ምን ደግ ነገር ሰርተናል? ብለን እንጠይቅ፡፡ የወደፊት ዕድሜያችን የሚለካው በዚያ ነው፡፡
የነገ ህይወታችንን የሚወስኑት ዛሬ የምናያቸው ምልክቶች ናቸው፡፡ የሰው ምሬት የት ደርሷል? ኢኮኖሚያችን የህዝብን በልቶ ማደር ያገናዘበነውን? ተጠይቀው ያልተመለሱት የፖለቲካ ጥያቄዎች፣ ዛሬም እንደተንጠለጠሉ ናቸው? ወይስ ተመልሰውልናል? ዲሞክራሲው እየተዳከመ ነው እየጠነከረ የመጣው? ፍትሐችን ሚዛኑን በመጠበቅ ረገድ ወገናዊ ነው አይደለም? “እናቱ የሞተችበትም ገበያ የሄደችበትም እኩል ያለቅሳሉ”፤ የሚባልበት አገር አሁንም አለን? ወይስ ሁኔታው ተለውጧል? እስረኞችን መፍታት አንድ ይበል የሚሰኝ እርምጃ ነው፡፡ በቀጣይ የተሻለ ሁኔታ እንጠብቃለን፡፡ ሌሎች የማይታሰሩበትን ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ ሂደት ነው፡፡ ያማረ ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ሁላችንም መረባረብ ይኖርብናል፡፡ ያም ሆኖ መጪውን ችግር የሚጠቁሙ ሂደቶችን እናስተውል፡፡ Coming events cast their shadows ይላሉ ፀሐፍት፡፡ መጪው ጊዜ ዛሬ ላይ ጥላውን ይጥላል፤ እንደማለት ነው፡፡ ነገን ዛሬ እንጠንቀቅ፡፡ አለበለዚያ “በመስከረም የሚቆስል በሰኔ ያሳክከዋል” የተባለው ተረት ዕውን ይሆናል፡፡ እናስብ! እናስብ! ደጋግመን እናስብ!

Read 5400 times