Monday, 05 February 2018 00:00

ከአባት የተወረሰ የሥራ ፈጠራና የቢዝነስ ግንባታ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  • የሰራተኞቻችንን ቁጥር ወደ 20 ሺህ ለማሳደግ ዕቅድ አለን
     • ህልማችን ከዚህ በኋላ 20 ድርጅቶችን ማቋቋም ነው
     • ከ1 ቢ. ብር በላይ ኢንቨስትመንት እያንቀሳቀስን ነው
     • ራዕይ አንዳንድ ጊዜ ብዙ መስዋዕትነት ያስከፍላል

   አለታ ወንዶ ላይ የአንድ ትልቅ ሰው ስም በስፋት ይታወቃል፡፡ ሲላ ዳኤ ጉራሮ ይባላሉ። እኒህ ሰው ፈር ቀዳጅ ሥራ ፈጣሪ ናቸው። ያልሰሩት ሥራ፣ ያልገቡበት ንግድ የለም። ለብዙዎች አርአያ ሆነዋል፡፡ ልጆቻቸውን ጨምሮ፡፡ ዛሬ የ90 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ሲላ፤ የሳቸውን የሥራ ፈጠራና የቢዝነስ ግንባታ የወረሱ ልጆች አሏቸው፡፡ የአቶ ሲላ ቤተሰብ የዛሬ ሳምንት በሃዋሳ ሁለት ትላልቅ ሥራዎችን አስመርቋል፡፡ አንደኛው ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ያለው ሮሪ ሆቴል ሲሆን ሌላው የእኒህን ጀግና ነጋዴ ታሪክ የሚዘክር መጽሐፍ ነው - “ሲላ ዳኤ ጉራሮ፣ አርአያነት ያለው ድንቅ ትጋት፣ የስራ ፈጠራና ስኬት” ይሰኛል፡፡  
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከአቶ ሲላ ልጆች አንዱ የሆኑትንና በተለያዩ ዘርፎች የሚንቀሳቀሱ 14 ኩባንያዎችን ከሚያስተዳድሩት አቶ ሀብታሙ ሲላ ጋር “አለታ ላንድ ግሩፕ” በሚል ባቋቋሙት ቢዝነስ ዙሪያ እንዲሁም ስለ አባታቸው የስኬት ታሪክ አነቃቂና አስደማሚ ቃለ ምልልስ አድርጋለች። በዚህ ቃለ ምልልስ፤ ሥራ ፈጣሪነት፣የቢዝነስ ግንባታ፣ ፈር ቀዳጅነት፣ የስኬት ምስጢርና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡ እነሆ፡-

    እስቲ ራስዎን ያስተዋውቁ …
ሀብታሙ ሲላ እባላለሁ፣ ተወልጄ ያደግሁት አለታ ወንዶ ነው፡፡ ለቤተሰቤ ስንተኛ ልጅ እንደሆንኩ ከመናገር ይልቅ ከመጨረሻ አራተኛ ልጅ መሆኔን መግልፁ ይቀለኛል፡፡ የመጀመሪያና መለስተኛ ትምህርቴን በዚያው  በትውልድ መንደሬ ነው የተማርኩት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አሜሪካን አገር በሚገኝ “ዊን ፎርድ” በተሰኘ ት/ቤት ከተከታተልኩ በኋላ፣ ከካምቤል ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ፡፡
ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ በአሜሪካ ነው የተማሩት እንዴት ዕድሉን አገኙ?
አባቴ ከአራተኛ ክፍል የዘለለ ትምህርት ባይኖረውም ለትምህርት የሚሰጠው ቦታ ከፍተኛ ነው፡፡ እሱ የተለያዩ ነገሮችን ለማሳካት ሲሮጥ ባለመማሩ ይቆጨዋል፡፡ አንድ ሰው በራሱ ያላደረገውን ነገር፣ ቁጭቱን በልጆቹ መወጣት ይፈልጋል፡፡ በዚህ ምክንያት እኔም ውጭ ሄጄ እንድማር ነው የተደረግኩት፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ካባቴ ስር ስር እያልኩ፤ እሱን በስራ አግዝ ነበር። ገና ህፃን ሆኜ ነው ስራ የለመድኩት፡፡ በስራው ምክንያት በትምህርቴም ደከም ብዬ ስለነበር ነው አሜሪካ የተላኩት፡፡ ጓደኞቼ በጣም የተማሩ ናቸው። ሀኪም፣ ረዳት ፕሮፌሰር እስከመሆን የደረሱ አሉ፡፡
እናንተ የአባታችሁን ፈለግ ተከትላችሁ ውጤታማ ሆናችሁ ብዙ እየሰራችሁ ነው፡፡ አንዳንድ አባትና ብዙ ደከመው ለልጆቻችው ጥሪት ቢያፍም ልጆች የወላጆቻቸውን ራዕይ አያስቀጥልም የእናንተ ጥንካሬ ምስጢር ምንድ ነው?
አባቴ ጠንካራ ሰው ነው፡፡ በመፅሐፉ ምረቃ ላይ ተገኝተሽ እንደሰማሽው፤ እኔም፣ መፅሀፉን የፃፈው ሰውም ሆነ፣ የአባታችን የቅርብ ጓደኞች፡- ስለ ጥንካሬው፣ ስለ ራዕዩ … ብዙ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ በሲዳማ ማህበረሰብ በንግድ ዘርፉ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ብዙዎችን ንግድ ያስተማረ ሰው ነው፡፡ በአጠቃላይ ስራ ፈጣሪ (ኢንተርፕረነር) ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከአባቱ ወይም ከእናቱ የወረሰው ነገር ሳይኖር ሀሳብ ብቻ ይዞ ነው ለዚህ የበቃው፡፡
የአባትዎን የሥራ (ቢዝነስ) አጀማመር ታሪክ ይንገሩኝ …
አባቴ በንጉሱ ጊዜ የቀን ስራ ይሰራ ነበር፡፡ በቀን 25 ሳንቲም እየተከፈለው፣ በመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ላይ ድንጋይ ይሸከም ነበር፡፡
አገርም አቅንተዋል ማለት ነዋ?
እውነት ለመናገር … ትክክለኛ አማርኛ ነው የተጠቀምሽው፡፡ አባቴ አገር ከማቅናት ነው ታሪኩ የሚጀምረው፡፡ በዚህ ስራ ላይ ለትንሽ ጊዜ ከሰራ በኋላ ወደ ቡና ንግድ ገባ፡፡ እንዴት እንደገባ ሲነግርሽ ደግሞ ይገርምሻል፡፡ አለታ ወንዶ አካባቢ፣ ቡና ገዥ የሆኑ ታዋቂ ሰው ነበሩ፡፡ ያኔ የእጅ ሚዛን በሚባለው እየመዘኑ ሲገዙ ይመለከታል፡፡ ከዚያ ያ ሚዛን ምን ያህል ቡና እንደሚይዝ ለማወቅ፣ ከቅርጮ የተሰራ መስፈሪያ ነበር፡፡
ቅርጮ ምንድን ነው?
ከቀርከሃ የተሰራ መስፈሪያ ነው፡፡ አባቴ ሰውዬውን፤ “ይሄ አንድ ኪሎ ምን ያህል ቅርጮ እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም ቡና የመግዛት ሀሳብ አለኝ” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ከዚያ ያንን አንድ ኪሎ፤ ወደ ቅርጮው ገለበጠና ምልክት አደረገባት፡፡ ሰውዬው፤ “አሁን ቡናውን ገዝተህ የት ልትወስደው ነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ “ገዢ አፈላልጋለሁ፤ በስራውም እቀጥላለሁ” አላቸው፡፡
ሰውየው መልሰው፤ “ለመሆኑ ገንዘብስ አለህ?” ብለው ጠየቁት፡፡ “እርግጥ ገንዘብ የለኝም ግን ሀሳብ አለኝ” አለ አባቴ፡፡ እውነትም በወቅቱ ገንዘብ አልነበረውም፡፡ የጉልበት ስራ ነበር የሚሰራው፡፡ ሰውየው የአባቴን ሀሳቡንና ጥረቱን ተመልክተው፤ “ቡናውን ለእኔ ገዝተህ አምጣልኝ” ብለው የተወሰነ ገንዘብ ሰጥተው ላኩት፡፡ ከዚያ በዚያች ምልክት ባደረገባት ቅርጮ እየሰፈረ፣ ከገበሬው ቡና እየገዛ ለእሳቸው እያስረከበ፣ ትንሽ በስራው ላይ ከቆየ በኋላ የከብት ንግድ ጀመረ፡፡ የአባቴ አባት (አያቴ) በዓል ሲሆን በሲዳማ ባህል አባታቸውን የሚዘክሩበት ስርዓት አለ፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅቤ ይፈልግ ነበር፡፡ ይህን ቅቤ ለማግኘት ወደ ኦሮሚያ፣ ብድሬሆፎርሶ የሚባል ቦታ ቅቤ በስፋትና በርካሽ እንደሚገኝ ይሰሙና፣ አባቴ ያንን ገዝቶ እንዲመጣ ይልኩታል። ያኔ ገና በጣም ህፃን ነበር፡፡ እናቱ፤ “ለምን ይህን ህፃን ትልካለህ?” ብላ ተቆጣችው፡፡፣ አባቱ ግን “ከዚህ ያልወጣ፣ ሌላ አገር ያለ አይመስለውም፤ ይሂድ ይልመድ” ብለው ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር ላኩት፡፡ እሱ ያኔ ያጠራቀማት ገንዘብ ነበረችው፡፡ ያንን ገንዘብ ይዞ ሄደ፡፡ እዚያ ከብት እርካሽ ነው፡፡ እናም ለአባቱ ቅቤ፣ ለራሱ አንድ ከብት ይዞ ተመልሶ ነው የከብት ንግድ የጀመረው፡፡ ከዚያ እያተረፈ እያተረፈ፣ ለትልቅ ደረጃ ደርሷል፡፡
እዚያ ከብት የሚገዛበት ቦታ ደርሶ መልስ 12 ቀን ነው የሚፈጀው በሌላ በኩል አለታ ወንዶ ዝርዝር ሳንቲም ይፈለጋል፡፡ ከብት የሚገዛበት ደግሞ ብር ይፈለጋል፡፡ ከዚህ ሳንቲም ይዞ ይሄዳል፤ ከዚያ ብር ይዞ ይመለሳል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአንድ ጊዜ 30 እና 40 ከብት ነድቶ መምጣት ጀመረ፡፡ እድገቱ እንዲህ … እንዲህ እያለ ነው የቀጠለው፡፡
ከዚያም ወደ ቡና ንግድ ገቡ አይደል?
እውነት ነው፤ የከብቱ ንግድ ባመጣው አቅም፣ ወደ ትልቁ የቡና ንግድ ነው የገባው፡፡ “አለታ ምንጭ” የሚባል ቡና ኤክስፖርት የሚያደርግበት ድርጅት ሁሉ ነበረው፡፡ መጀመሪያ ቡና ከገበሬ እየገዛ፣ ለአዲስ አበባ አቅራቢ ሆነ፡፡ ቀስ በቀስ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ፣ የቡና ማጠቢያ ማሽን ገዝቶ ሲሰራ፣ ደርግ መጥቶ ወረሰው፡፡ ማሽኑ ሲወረስ፣ ወደ ደረቅ ቡና ንግድ ገባ፡፡ ከዚያ የደረቅ ቡና መፈልፈያና መቀሸሪያ አቋቋመ፡፡ እንደዚህ እየሰራ ወደ ትራንስፖርት ዘርፍ ገባ፡፡ የህዝብ ትራንስፖርት ወደ አካባቢያችን ያስገባ የመጀመሪያው ሰው ነው። የራሱን የቤት መኪና የገዛው በንጉሱ ጊዜ ነው። በጣም ጠንካራ ሰው ነው፡፡ እንግዲህ የተማረው ከሶስተኛና ከአራተኛ ክፍል በላይ አይደለም። በዚያች መኪና ቡና ይጭናል፡፡ በዚያ ላይ ነፍሰ ጡሮች ምጥ ሲያዙ እንዳሁኑ በቅርብ ጤና ጣቢያ አልነበረም አባቴ በላንድክሩዘሩ ራቅ ያለ ስፍራ ወደሚገኘው ሆስፒታል በመውሰድ ማህበረሰቡን ያገለግል ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ 42 ሰው የሚጭን የህዝብ ማመላለሻ ሎንችና ገዛና፣ ወደ ትራንስፖርቱ ዘርፍ በደንብ ገባበት፡፡ መንጃ ፍቃዱን አሻሽሎ ትንሽ ከሰራ በኋላ ለልጆቹ አስተላለፈ፡፡ ብቻ የአባታችን ታሪክ ትልቅ ነው፡፡ ዝርዘሩ ስለሱ ታሪክ በተፃፈው መፅሐፍ ላይ በስፋት ተቀምጧል፡፡
ከአባትዎ የሚደነቁበት፣ የሚገረሙበትና ወርሼዋለሁ የሚሉት ባህሪ ይኖር ይሆን?
አንድ ሰው ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ማለትም ባለፀጋም ይሁን ትልቅ ባለስልጣን ለመሆን ዋናው ነገር ራስን ማሸነፍና መግዛት ነው፡፡ የሰው ልጅ የሚያቅተው ትልቁ ነገር ደግሞ ራስን መግዛት ነው። ራስን መግዛት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሰው ገንዘብና ስልጣን ሲያገኝ… ራሱን ካላሸነፈና ስርዓት ካላስያዘ፣ ገንዘቡንም ስልጣኑንም ይዞ መቀጠል አይችልም፡፡ ያለውን ክብርም ሆነ ተሰሚነት ለማስቀጠል ራስን መግዛት ወሳኝ ነው፡፡
ከአባታችን የሚያስደንቀኝ የሚገርመኝ አንዱና ዋነኛው ይሄ ነው፡፡ አንድ ሰው ብርና ስልጣን ሲኖረው፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ፍላጎቶች አሉ፡፡ ያንን በአግባቡ መምራትና ራስን ከዚያ ፍላጎት ተገዢነት ማውጣት፣ የሚያስገኘውን ውጤት ከአባታችን ተምረናል፡፡ አባታችን ስራችንን እንድንወድ፣ ቁሳቁስ እንዳያስደንቀን አድርጎናል። ሁለተኛው ነገር፣ ከህብረተሰቡ ጋር የነበረው ቁርኝት ነው፡፡ ሲላ በሰላምተኝነቱ ይታወቃል፡፡ ሲላ የትም ቦታ በሀዘንም ሆነ በደስታ ጊዜ ከህዝቡ ጎን ነው፡፡ ለራሱ ድንበር አላበጀም፡፡ ለእኛም ይመክረን የነበረውም ይሄንኑ ነው፡፡ ለሲላ ሰው ሰው ነው፤ ሁሉንም እኩል ነው የሚያየው፡፡ ሰው ለእሱ የሚሰጠው ደረጃ ይኖራል፤ እሱ ግን እኔ እንዲህ ነኝ፣ እንዲህ እለያለሁ ብሎ አያውቅም፡፡ ማህበራዊ ህይወቱ የተሳካና ያማረ ነው፡፡ ሶስተኛው ነገር፣ ከቤተሰቡ ጋር ያለው ቁርኝትና ቅርበት በጣም የሚገርመኝ ነው፡፡ ቤቱን ሚስቱን ልጆቹን በእጅጉ ያከብራል፤ ይወዳል፡፡
እሱ ለእራሱ የተለየ ነገር አላደረገም፤ አልተዝናናም፤ ከቤተሰቡ በላይ ደስታ የለውም። ሩቅ መንገድ ካልሄደ በስተቀር ሆቴል ውስጥ አይመገብም፡፡ ስጋ ካማረው ገዝቶ ወደ ቤቱ ወስዶ ነው ከቤተሰቡ ጋር የሚመገበው፡፡ ጥሩ የሚለውን ነገር ሁሉ፣ ከቤተሰቡ ጋር ይጋራል። ቤተሰብ ማክበር፤ በረከትን፣ ክብርን፣ ፍቅርን … እንደሚያጎናፅፍ ከአባታችን ተምረናል፡፡ አባታችን አስተዋይ፣ ታማኝና ጠንካራ ሰው ነው፡፡
እንግዲህ አንድ ዛፍ በፍሬው ነው ውጤቱ የሚለካውና፣ እናንተም በሥራችሁ ስኬታማ መሆናችሁ የአባታችሁ ልፋት ውጤት አፍርቷል ማለት ነው ያስብላል?
በሚገባ አፍርቷል፡፡ እኛም በሱ መርህ፣ በሱ መንገድ፣ ራሳችንን በመግዛት፤ ቤተሰባችንን በማክበርና በሥርዓት በመታነፅ ለዚህ ደርሰናል፡፡ አባታችን ለብዙ ነገር ምሳሌ መሆን የሚችል ሰው ነው፡፡
አሁን ደግሞ ወደ እርስዎ የቢዝነስ አጀማመር እንግባ …  
በመግቢያችን እንደገለፅኩልሽ፤ ከህፃንነቴ ጀምሮ ስራ ላይ ነበርኩ፤ አባቴን በጣም እያገዝኩና እየረዳሁ ነው ያደግሁት፡፡ የአባቴን ድርጅትም መምራት ጀምሬ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የራሴ ራዕይም ነበረኝ፡፡ ቤተሰባችን በጣም ሰፊ በመሆኑ፣ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ሊመነጩ ይችላሉ፡፡ እናም በራስ ሃሳብ ብቻ መመራት አስቸጋሪ ነበር። የእኔ ሀሳብ በሌሎች የቤተሰቡ አባላት ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል፡፡ ያንን አጣጥሞ መቀጠል አዳጋች ሲሆንብኝ ወደ ራሴ ራዕይ ማተኮር ጀመርኩኝ፡፡ በወቅቱ የኔ እህትና ወንድሞች ትዳር መስርተው፣ ራሳቸውን ችለው ወጥተው ነበር፡፡ እኔና ሁለት ልጆች ብቻ ነበርን የቀረነው፡፡ ሁሌም ልጆች የወላጆቻቸውን ሌጋሲ የማስቀጠል ስጋት ይኖራል፡፡ እኔ ደግሞ የአባታችን ራዕይ እንዲቀጥል የማነሳቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ቀጣይነት የሌለው ቢዝነስ እንዳይሆን፣ ለትውልድ እንዲተላለፍና ለአገር ያለው አስተዋፅኦ እንዳይመክን፣ መሰረቱ በደንብ መገንባት አለበት በሚለው ሀሳቤ ፀናሁ። ከእኔ አስተሳሰብ ጋር የሚጣጣም ቤተሰብ ስላላገኘሁ፣ ስራውን አልፈልግም ብዬ፣ ከአባቴ ትንሽ ተቀያይሜ፣ ስራዬን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ ስወጣ ግን ብዙ ሀሳብ ከአባቴ ከመውሰዴ ውጭ ምንም ሳንቲም አልወሰድኩም፡፡
ከዚያስ ምን ሆኑ?  
ከአባቴ የስራ ልምድ ሀሳብ አግኝቻለሁ። እኔ ባለራዕይ ስራ ፈጣሪ ነኝ ብዬ አፌን ሞልቼ የምናገረውም ለዚህ ነው፡፡ አንድ ሰው ባለራዕይ ከሆነ፣ ዛሬ ላይ ሆኖ፣ ከ10 ዓመት በኋላ ሊሆን የሚችለውን ነገር ማሰብና ማቀድ አለበት፡፡ እህትና ወንድሞቼ ወደፊት ሊመጣ ይችላል ያልኩትን ሃሳብ፣ ውድቅ በማድረጋቸው ባዶ እጄን ወጣሁ። አለታ ወንዶ ላይ የሰራኋት ትንሽ ቤት ነበረችኝ። የወንድሞቼ ቤቶችም ነበሩ፡፡ እነዚህን ቤቶች አስይዤ፣ ከባንክ ብድር ወሰድኩ፡፡
ምን ያህል ተበደሩ?  
300 ሺህ ብር ተበደርኩ፡፡ ከዳሽን ባንክ፡፡ ከዚህ ብር ውጭ በኪሴ 10 ብር እንኳን አልኝበረም፡፡ የኔ ታሪክ የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ጊዜው 1993 ዓ.ም ነበር፡፡ በተበደርኩት ብር ቡና ማጠቢያ ተከራየሁ፡፡ ያኔ 300 ሺህ ብር በጣም ብዙ ብር ነበር፡፡ ወዲያው 172 ሺህ ብር አተረፍኩ፡፡ ከዚያም አንድ የቡና ማጠቢያ ገዛሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ወንድሞቼም አብረውኝ ይሰሩ ነበር፡፡ በሁለተኛው ዓመት ብዙ አተረፍኩ። እውቀቱም ልምዱም ነበረኝ፤ ሰውም ተዋውቄ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም የኤክስፖርት ፈቃድ ወጣና “አለታ ላንድ” ተቋቋመ፡፡
“አለታ ላንድ” ከተቋቋመ በኋላ አሁንም ከወንድሞቼ ጋር በሀሳብ ባለመስማማት ተለያየን። በራሴ ብቻ ቀጠልኩ፡፡ የራሴን ሀሳብ እየወሰንኩ፣ ስጋቱንም ተቋቁሜ ቀጠልኩ፡፡ ይኸው አሁን ላለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ እግዚአብሔር ረዳኝ፤ ማለት አችላለሁ፡፡
“በአለታ ላንድ ግሩፕ” ስር በርካታ ኩባንያዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ …  
እግዚአብሄር ይመስገን … አሁን ብዙ ናቸው። በትንሹ 14 ያህል ኩባንያዎች አሉ፡፡ “አለታ ላንድ ኮፊ”፤ ቡና ኤክስፖርት የምናደርግበት ድርጅት ነው። “ታኦ ኢንዱስትሪያል አለ ዲተርጀንት”፤ የፅዳት ሳሙናና ተያያዥ ምርቶችን ያመርታል፡፡ በአምስት ኮከብ ደረጃ የተሰራውና ባለፈው ቅዳሜ የተመረቀው “ሮሪ ኢንተርናሽናል ሆቴል” አንዱ ነው፡፡ “አላዱ” ደግሞ የቡና ማጠቢያ ሲሆን ቡና እያጠበ ለኢትዮጵያ ኮሞዲቲ ኤክስቼንጅ (ECX) ያቀርባል፡፡ “ሀብታሙ ሲላ ፕላስቲክ ፋብሪካ” ሀዋሳ የሚገኝ ሲሆን ፒቢሲ፣ ፒፒአር፣ ፓይፖች፣ ኤችዲፒ ፖይፕሮ የሚያመርት ነው፡፡ አሁን ደግሞ አስፋፍተነው ፊቲንግ ለማምረት በዝግጅት ላይ ነን፡፡ ሌላው “ሀብታሙ ሲላ ኮፊ ዴቨሎፕመንት” ሲሆን ይኼ ደግሞ የቡና እርሻ ነው፡፡ ከፋ ላይ በ500 ሄክታር ቦታ ላይ የሚገኝ የቡና እርሻ ነው። ዱከም ላይ የሚገኘው “ወሊማ ሪዞርት”  እንዲሁ በአለታ ላንድ ግሩፕ ሥር ከሚተዳደሩት የቢዝነስ ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡
ይህን ሪዞርት ለማስፋፋትና ትልቅ ለማድረግ አስበናል፤ የውሃ ፊቸር ያለው ትልቅ አሚዩዝመንት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ሪዞርቱ ሰው ቤተሰቦቹን ይዞ የሚዝናናበት፣ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ያካተተ፣ 11 የመሰብሰቢያ አዳራሽ ኖሮት ኮንፈረንስ ዞን ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በመሆኑ ከመዲናዋ ወጣ ተብሎ ተንፈስ የምትልባት ማራኪ ቦታ ለማድረግ ፕሮጀክቱ ተቀርፆ አልቋል፡፡ 10 ሄክታር መሬት ጠይቀን፣ ኦሮሚያ ክልል አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተውናል። እስከዚያው ባለበት እየሰራ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዳሜና እሁድ እስከ 12 እና ከዚያ በላይ ሰርጎች ይሰራል፡፡ በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
ማስፋፊያው መቼ ይጀመራል?
መሬቱ እንደተሰጠን ይጀመራል፡፡ ሌላው የግሩፑ አካል “ሀብታሙ ሲላ ምስማር ፋብሪካ” ይባላል፡፡ ዱከም ላይ የሚገኝ ሲሆን ተገንብቶ አልቋል፡፡ ከውጭ ማሽነሪዎች እየገቡለት ነው። ቆርቆሮና ምስማር በጥራት ያመርታል። በዴሳ” ቡና አቅራቢ ድርጅት የሚባለው ደግሞ የቡና መፈልፈያዎች አሉት፣ መጋዘኖች ሰርቶ ለኢሲኤክስ ያከራያል፣ “ፎረስት” የሚባለውን ቡና ያቀርባል፤ ራሱም ኢንዱስትሪ አለው፡፡ “አመዘ” የተባለውም ቡና አቅራቢ ነው፡፡ ፕላስቲክ ፋብሪካም አለው። ወንበሮችን፣ የቢራና የለስላሳ ሳጥኖችንና ሌሎች የቤት እቃዎችንም ያመርታል፡፡ “ወንጌል ወረቀት ፋብሪካ” ከአራት ወር በኋላ ሥራ ይጀምራል፤ማሽነሪ እያስመጣን ነው፡፡ ሀዋሳ ላይ ደግሞ የዘይት ፋብሪካ አቋቁመናል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ፣ ማሽነሪ እየገባለት ነው፡፡ ጥሬ እቃ ለማምረትና ከግብርናው ጋር ለማስተሳሰርም አቅደናል፡፡ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ተልባና ሌሎች የቅባት እህሎችን ለማምረት፣ 3 ሺህ ሄክታር መሬት ተፈቅዶልናል፡፡ መሬቱ ቤንች ማጂ ላይ ይገኛል፡፡ በነገራችን ላይ ሰንፍላወር (የሱፍ ዘይት) ሁሉ የማምረት እቅድ አለን፡፡ ይቻላልም፡፡ በሌላ በኩል የወይራ ዘይት (ኦሊቭ ኦይል) ለማምረት ዘሩን ከውጭ አምጥተን፣ ከአየርና ከአፈሩ ጋር ይጣጣም አይጣጣም እየተመረመረ ነው፤፡፡ ደብረ ብርሃን ተሞክሮ ተሳክቷል፡፡ በሞቃት ቦታ እንዴት ነው የሚለው እየተጠና ነው፡፡ ይሄ ውጭ ምንዛሪውንም  ይቀንሳል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ኩባንያዎች  ምን ያህል ሰራተኞች ታስተዳድራላችሁ?
እስካሁን ሶስት ሺህ ሰራተኞችን እናስተዳድራለን። የዛሬ አስር ዓመት፣ የሰራተኞቹን ቁጥር 20 ሺህ ለማድረስ እቅድ ይዘን እየሰራን ሲሆን የስራ ዘርፋችንና ውጤታችንም፣ በዚያው ልክ እንዲያድግ አቅደናል። ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ራዕይ የሚሰጥሽ ከላይ ነው። ራዕይ አንዳንድ ጊዜ መስዋዕትነት ሁሉ አለው፡፡ እኔን ብታይኝ  የአለታ ላንድ ግሩፕ ማናጀር ብቻ ነኝ፣ ሌላ ምንም አይደለሁም፡፡ ከሰራተኛ በፊት ጠዋት 2፡00 እገባለሁ፣ ከሰራተኛ በኋላ ነው የምወጣው፡፡ አዲስ አበባ ካለሁ በሰዓቱ ቢሮዬ እገኛለሁ፡፡ የስራ ክብርን፣ ራስን ለስርዓት ማስገዛትን፣ በስሬ ላሉ ሰራተኞች አርአያ መሆንን አባቴ አስተምሮኛል፡፡ እንዳልኩሽ አባቴ ሲኒየር ነው፤ ደግሞም አልተማረም፤ነገር ግን ለዚህች አገር ከፕሮፌሰሮች በላይ አስተዋፅኦ አድርጓል ባይ ነኝ። እኛ አገር ውስጥ የሚዘፈንለትም የሚዘመርለትም፣ የተማረ የተባለውና ወረቀት ያለው ብቻ ነው፡፡ አሜሪካ ብትሄጂ ያለፍሽበት የስራ ልምድ፣ ያየሽው ውጣ ውረድ ዋጋ አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይሄ የስራ ልምድ ጉዳይ ዋጋ ቢሰጠው በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ የተማረ ሰው አያስፈልግም እያልኩ አይደለም፤ ግን በልምድ የዳበረ ተፈጥሯዊ እውቀት ትልቅ ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ልጆቼ የአባቴን ታሪክ እንዲያነቡ አደረግሁ፤አንብበው ታሪካቸውን መነሻቸውን አወቁ፡፡ “አያታችን ባይሆን እንቀና ነበር” ነው ያሉት፡፡
3ሺ ሰራተኞች  ማስተዳደር ከባድ ይመስለኛል። የሰራተኛ አመራር ሥልታችሁ ምን ይመስላል?
ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ እምብዛም የስራ መዋቅርና ሲስተም በሌለበትና ባላደገበት፣ የስራ ስነ ምግባር ብዙ በማይከበርበት አገር፣ የ14 ኩባንያዎችን ሰራተኛ ማስተዳደር ቀላል አይደለም፡፡ እኛ ግን ጊዜም ገንዘብም ወስደን መዋቅር በደንብ ቀርፀን ነው እየሰራን ያለነው። ደጋግሜ እንደነገርኩሽ፣ ኢትዮጵያ ትልቅና ብዙ ሀብት ያላት አገር ናት። ይህንን ለመጠቀም ያደገና የለማ ጭንቅላት፣ አስተሳሰብ የግድ ነው፡፡ ትልቁ አገራችን ላይ ያለው ችግር፣ እኛንም ተስፋ ያስቆረጠን ይሄው ጉዳይ ነው። በተለይ ችግሩ ያለው ተማርን የሚሉት ሃላፊዎች (ማናጀሮች) ላይ ነው፡፡ ምሳሌ መሆን ያለበት ማን ነው? ኃላፊው ስነ ስርዓት ከሌለው፣ ሰዓት የሚሰርቅ ከሆነ፣ ከስር ያለው ሰራተኛ ይሄንኑ የማያደርግበት ምክንያት የለም፤ ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በግላችን እየጣርን ነው፡፡ ምሳሌ ለመሆን እየሰራን ነው፡፡ የተደራጀና የተዋቀረ የአሰራር ሂደት እንከተላለን፡፡
በቡና ኤክስፖርት በዓመት ምን ያህል ዶላር ታስገባላችሁ?
አሁን አሁን በተለያዩ ምክንያቶች የቡና ገበያና ዋጋ ጥሩ አይደለም፤ የዛሬ 3 እና 4 ዓመት እናስገባ ከነበረው እየቀነስን እየቀነስን ነው የሄድነው፡፡
እስኪ ያነፃፅሩልኝ …
በፊት በዓመት ከ36 ሚ. ዶላር በላይ እናስገባ ነበር፤ ካቻምና 26 ሚ. ዶላር አስገብተናል፡፡ አምና በግማሽ ቀንሰናል፡፡ የገበያው ሁኔታ አክሳሪ ስለነበር ብዙ አልገፋንም፡፡ ዞሮ ዞሮ በቡና ስለሆነ ያደግነው 500 ሄክታር መሬት ላይ የቡና እርሻ አለን፤ ሌላ ተጨማሪ 500 ሄክታር የቡና መሬት እየለማ ነው፡፡ የቡና ኢንቨስትመንታችን ትልቅ ነው፡፡
አረንጓዴ ሻይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያስመዘገባችሁት እናንተ መሆናችሁን ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለሱ  ይንገሩኝ…
እውነት ነው፡፡ ከጃፓኖች ጋር በአጋርነት ለመስራትና ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ብዙ ሂደቶችን አልፈናል። በመጨረሻም መንግስት ፈቅዶልን፣ አምጥተን አስመዝግበናል፡፡ ከተመዘገበ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ አሁን ከጅማ የእርሻ ምርምር ኮሌጅ ጋር አብረን እየሰራን ነው። ዘሩ እዚህ ተሞክሮ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ዘሩን ለማስገባትና ለማስመዝገብ፣ ጉዳት ያደርሳል አያደርስም የሚለውን ለማስመርመር  ብዙ ዶላር ከፍለናል፡፡ አሁን ዘሩን እያባዛን ነው፡፡ የአረንጓዴ ሻይ ባለቤት አለታ ላንድ ነው ማለት ነው፡፡ መሬቱ ቤንች ማጂ ዞን፣ ቤሮ ወረደ ላይ ይገኛል፡፡ 300 ሄክታር መሬት ወስደናል፤ ተጨማሪ 300 ሄክታር ጠይቀን እያመቻቹልን ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ---- የተሰጠንን ራዕይ ለማሳካት ሩጫ ላይ ነን፡፡
በአጠቃላይ የኩባንያዎቹ ኢንቨስትመንት ምን ያህል ይደርሳል?
እንግዲህ ለእኔ (እንደ ባለራዕይ)፣ ካፒታልና ኢንቨስትመንት፣ ሰራተኞቼ ናቸው፡፡ ከፋይናንስና ማርኬቲንግ ዲፓርትመንት ትክክለኛውን ማረጋገጥ ይቻላል፤ ግን የ1.7 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ይመስለኛል፡፡ እንደነገርኩሽ፣ የዛሬ 10 ዓመት፣ የሰራተኞቻችንን ቁጥር 20ሺ የማድረስ ዕቅድ አለን። ኢንቨስትመንቱም የዚያኑ ያህል ያድጋል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ 20 ድርጅቶችን የማቋቋም ህልም ነው ያለን።

Read 3230 times