Sunday, 28 January 2018 00:00

ከስሜት ይልቅ ብስለት አያሳጣን!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ቀበሮ መሞቻዋ ደርሶ በዱር አራዊት ፊት ትናዘዛለች፤ አሉ፡፡
“ወዳጆቼ ሆይ! እንግዲህ እኔ ከዚህ ዓለም መሰናበቴ ነው፡፡ ስለዚህ ጥቂት ቃላት ልናገር፤ አያ አንበሶ ጉልበት ባታበዛ ጥሩ ነው፡፡ እሜት ጦጢትም ብልጣ ብልጥነቱን አታብዢው! ዝንጀሮ ወሬ እያቀባበልክ፣ የዱር አራዊቱን እርስ በርስ አታባላቸው፡፡
ከርከሮ ቀን አመቸኝ ብለህ፣ አቅመ ደካሞችን አታጥቃ፡፡
ነብር አንዴ ሰሶችን፣ አንዴ የሜዳ አህዮችን፣ አንዴ ፍየሎችን እንዳፈተተህ እያሳደድክ መብላትህን ጋብ አድርገው፡፡
ድብ ማድባትህን ተው!
ዱኩላ አመሻሹ ላይ የቤት እንስሳት ለማጥቃት መውጣትህን አቁም፡፡
ጅብ ለአህዮች ብታዝን ጥሩ ነው፡፡ ታቀብ!
ዝሆን ሳታንቀላፋ ወዳጆችህን ተግተህ ጠብቅ፡፡
ጎሽ ልጄን ለማዳን በሚል ሰበብ፣ ሌሎችን መውጋት፣ ዘዴው የተበላ ዕቁብ ስለሆነ ማንንም እንደማታታልል ዕወቅና ተቆጠብ….
በዚህ ዓይነት ስለ ሁሉም ማስረዳቷን ስትቀጥል፣ ድንገት አውሬዎቹ ሁሉ አጉረመረሙባት!
አንበሳ ከሁሉ በላይ ተቆጣ፡፡
ነብር ሊያንቃት ተቁነጠነጠ፡፡
ዝሆን መሬቱን ይጭር ገባ፡፡
ጎሽ በንዴት ዛፍ እየታከከ፣ ቀበሮን ዘሎ ሊወጋ አሰፍስፏል!
ሁሉም ሊወነጨፉባት እንደሆነ እመት ቀበሮ ስለተገነዘበች፡-
“ጎበዛዝ አውሬዎች ሆይ! እንደው ለጊዜው ተንፍሰን እንሙት ብለን ነው እንጂ የተባላችሁትን እንደማትፈፅሙት‘ኮ እናውቃለን!” አለችና፣ ክልትው ብላ ወድቃ ቀረች!!
* * *
የሚፈልገውን ለማለት የሚችል፣ የታደለ ህዝብ ነው! የሚፈልገውን መመገብ የሚችል የታደለ ህዝብ ነው! የትም ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችል የታደለ ህዝብ ነው፡፡
“ደብዳቤ ቢፅፉት እንደቃል አይሆንም
እንገናኝና ልንገርሽ ሁሉንም”
ለማለት የሚችል የታደለ ህዝብ ነው!
የጠየቀው የሚፈፀምለት የታደለ ህዝብ በመሆኑ ያስቀናል፡፡ ያለ ደጅ-ጥናት፣ ያለ መጉላላት፣ ያለ ድህነት ህይወቱን የሚመራ ህዝብ እጅግ ያስቀናል!
በአገሩ የመጣ ማናቸውም ነገር የሚቆጨው፣ የሚያንገበግበው ምሁር ያለው ህዝብ፣ የተቀደሰ ነው! ለዕድገቱ የሚበጅ ዓይነት ትምህርት የሚማርና ሁሌ ከአትሮንሱ ግርጌ የሚገኝ ህዝብ የታደለ ነው! ይጭነው አጋሠሥ፣ ይለጉመው ፈረስ ያለው ህዝብ ማንንም ያስቀናል!
“ከአገር እኖር ብዬ
ልጅ አሳድግ ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ!”
ሳይል፣ ሳይሳቀቅ፣ ሳይገፋ የሚኖር ህዝብ፣ አምላክ የመረቀው ህዝብ ነው!
“ለመቶ ሃምሣ ጌታ
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ፤ አለቀ በላዬ!”
የማትል ምስኪን እናት ያለችው አገር፣ ዕድለኛ አገር ነው! ፍትሑ የተስተካከለ፣ ዲሞክራሲው ያልተበረዘ፣ አስተዳደሩ ያልተዛባ፣ ጤናው የተጠበቀ፣ ልማቱ የሚያኮራ፣ የማይዋሽና የማይዋሽበት ህዝብ፤ ተስፋው የሚለመልም፣ የተመኘው የሚፈፀምለት ህዝብ ነው! አገራችንና ህዝቧ እንዲህ ያለ ፀጋና ባለፀጋነት ትጎናፀፍ ዘንድ፤ የሁላችን ትጋትና ርብርብ፣ የሁላችን የመንፈስ ፅናት፣ የሁላችን የባህል ትሥሥር ሊኖር ይገባል!
አገርና ህዝብ የማሳደግ ጉዞ መቼም ቢሆን አጭር ሆኖ አያውቅም፡፡ አልጋ በአልጋም አይደለም! የምንከፍለው ግብር ተመጣጣኝ ጥቅምና ዕድገት እናገኝ ዘንድ ነው! የምንሄድበት መንገድ እንዲገነባልን፣ የምንገለገልበት መብራትና ውሃ እንዲኖረን፣ ልጆቻችንን የምናስተምርበት ት/ቤትና የምናሳክምበት ሆስፒታል እንዲኖረን ነው ከደሞዛችን፣ ከንግዳችን፣ ከምርታችን ቆጥበን ግብር የምንከፍለው! “እኔ ግብር ከፋይ ነኝ!” ብለን እንድንኮራ ነው ልፋታችን! በእርግጥም “አገሬ ምን ትሠራልኛለች” ማለት ብቻ ሳይሆን፣ “እኔ ለአገሬ ምን እሠራለሁ?” ማለት የሚቻለው ያኔ ነው! ለዚህ አርቆ ማስተዋል፣ አስቦ መራመድ ወሳኝ ነው! ከስሜት ይልቅ ብስለት አያሳጣን የሚባለውም ለዚህ ነው! ለስሜታዊነት፣ ለምሬት፣ ለትኩሳት፣ ለእዚህም እዚያም መነሳሳት የሚገፋፋ መመሪያዎችን፣ አዋጆችንና እርምጃዎችን በላይ በላዩ ከማከል በፊት ቆም ብሎ ማሰብን ብንለምድ መልካም ነው፡፡ በየትኛውም ወገን ያለን የሀገራችን ሰዎች ከስሜት ይልቅ ብስለት አያሳጣን ብለን የምናይበት መንገድ እንሻ!!

Read 7466 times