Saturday, 06 January 2018 13:14

በገና ዋዜማና በበዓሉ የት እንሂድ---?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ሞርኒንግ ስታር ሞል - የገና ልዩ ቅናሽ

    ቦሌ ኤድናሞል ጎን የሚገኘውና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ3 ዓመት በላይ የሆነው ሞርኒንግ ስታር ሞል፤ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ የጌታን ልደት ለማስታወስ በአይነቱ ልዩ የሆነና 20 ሜትር ርዝመት ያለው የገና ዛፍ ሰርቶ በሩ ላይ አቁሟል። ይህ ግዙፍ የገበያ ማዕከል ከዛፉ በተጨማሪ ጌታ የተወለደበትን ቦታ ለማስታወስም በረት የሰራ ሲሆን ከማዕከሉ ፊት ለፊት የኢትዮጵያ ቡና አፈላል ሥነ - ስርዓት የሚካሄድበት ዳስ ጥሎ፣ ሰዎች ቡና እየጠጡ የሚፈልጉትን እቃ ለገና በዓል በተደረገ ልዩ ቅናሽ እየሸመቱ፣ የሚዝናኑበትን  ሁኔታ አመቻችቷል፡፡
ይህ ግዙፍና 20 ሜትር ርዝመት ያለው ዛፍ፣ የፈረንጆቹንም የሀበሻንም የገና ዛፍ አሰራር ያጣመረና አካባቢን በማያቆሽሽ መልኩ የተሰራ ሲሆን በአጠቃላይ 60 ሺህ ብር መፍጀቱን የሞርኒንግ ስታር ሞል የማርኬቲንግ ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ሙሉጌታ ጠቁመው፣ እስከ ዛሬ ምሽት በሚቆየው ልዩ ዝግጅት፤ ሰዎች እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

----------------------


           ኢሊሌ ኢንተርናሽናል - ቪአይፒ ሬስቶራንት

   ባለ አምስት ኮከቡ ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴልም እንደዚሁ ልዩ የገና የእራት ምሽት፣ 10ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው እጅግ ምቹና ዘመናዊ በሆነው ቪአይፒ ሬስቶራንቱ አዘጋጅቷል፡፡
“ዴሉክስ ሜኑ” የተባለው ልዩ እራት በምቹው ሬስቶራንት ውስጥ በለስላሳ ሙዚቃ ታጅበው፣ ከወይን መጠጥና ቢራ ጋር የሚያጣጥሙበት ልዩ ምሽት መሆኑን የሆቴሉ የህዝብ ግንኙነት አቶ ታሪኩ ዋስይሁን ተናግረዋል፡፡ ከምሽት 12፡00 እስከ እኩለ ሌሊት በሚዘልቀው በዚህ የእራት ምሽት ላይ ለመታደም ለአንድ ሰው 700 ብር፣ ለጥንዶች 1400 ብር ክፍያ እንዳለውም አቶ ታሪኩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡


---------------


                ኢንተርኮንትኔንታል - እራትና ሙዚቃ በባንድ

   ባለ አራት ኮከቡ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል፣ 11ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘውና አዲስ ባሰራው ተሽከርካሪ ሬስቶራንቱ ልዩ የገና እራትና በባንድ ቀጥታ የሚተላለፍ የሙዚቃ ዝግጅት አሰናድቷል። ዛሬ በበዓሉ ዋዜማ ከምሽቱ 12፡00 እስከ እኩለ ሌሊት በሚዘልቀው በዚህ የመዝናኛ መሰናዶ፤ በተለይ በገና ወቅት በብዛት የሚበሉት ተርኪ፣ ቺክንና መሰል ምግቦች በልዩ ሁኔታ ተከሽነው የሚቀርቡ ሲሆን እንግዶች ያሻቸውን መጠጥ መጠቀም እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡ በዚህ ምሽት  እራት ለመመገብ 760 ብር የሚያስከፍል ሲሆን አስርና ከዚያ በላይ በቡድን ለሚመጡ የ10 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው የሆቴሉ የሽያጭና ገበያ ዳይሬክተር አቶ ወገኔ ታደሰ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በሆቴሉ  የሚገኘው ቮልቴጅ ክለብ፣ ከምሽቱ 3፡00 ጀምሮ ልዩ የገና የዲጄ ሙዚቃ መዘጋጀቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ መግቢያው ነፃ እንደሆነና እስከ ሌሊቱ 9፡00 እንደሚዘልቅ ተናግረዋል፡፡


---------------


                   ራማዳ አዲስ- ልዩ እራት

   ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በመሃል ቦሌ ከአገልግሎት መስጠት የጀመረው ባለ 4 ኮከቡ ራማዳ አዲስ ሆቴል ለገና ዋዜማ “ሼፍስ ክለብ” እና “ፎጎ ኖቾ” በተባሉት ሁለት ታዋቂ ሬስቶራንቶች ውስጥ ልዩ የእራት ምሽት አዘጋጅቷል፡፡
በዚህ ልዩ የእራት ምሽት “ኢትዮ ኳርቴት” የተባለ የሙዚቃ ባንድ ልዩ የሙዚቃ ትርኢት በቀጥታ ለታዳሚው እንደሚያቀርቡም የሆቴሉ ፀሀፊ አቶ የኔአለም ክፍሉ አስታውቀዋል፡፡


-----------------

           በብሔራዊ ቴአትር - ልዩ ሙዚቃ

    ታላቁ ብሔራዊ ቴአትር በገና በዓል ዕለት እሁድ ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርባል፡፡
ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች በልዩ ሁኔታ በሚቀርቡበት በዚህ የበዓል የሙዚቃ ዝግጅት የቴአትር ቤቱ አንጋፋና ወጣት ድምፃዊያን “ቫራይቲ” በተሰኘው የቴአትር ቤቱ ኦርኬስትራ ታጅበው፣ ታዳሚውን እንደሚያዝናኑ የታወቀ ሲሆን የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራውም ከባህላዊ ሙዚቃ ድምፃውያን ጋር ሆኖ በዓሉን በዓል እንደሚያስመስሉት የቴአትር ቤቱ የሙዚቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወሰን የለህ መብረቁ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
እስከ ቀኑ 11፡00 በሚዘልቀው የበዓል ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ለመታደም  መግቢያው 40 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡

----------------------


              “ሃፒ ኢቨንትስ” ልዩ የገና ዋዜማ ጨዋታዎችን አዘጋጅቷል

              “ለልጆች የደስታ ቀን ለመፍጠር የታሰበ ነው”
                 ግሩም ሠይፉ

    “ሃፒ ኢቨንትስ” አዳዲስና የተለያዩ የገና ዋዜማ ጨዋታዎችን ለልጆች ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ የዋዜማ ዝግጅቱ  ቦሌ ድልድይ አካባቢ ከቦራ መዝናኛ ማዕከል አቅራቢያ በሚገኘው በቦሌ ህብረተሰብ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ 8 ሰዓት የሚካሄድ ሲሆን መግቢያው ለህፃናት 100 ብር፣ ለወላጆች በነፃ መሆኑ ታውቋል፡፡
 አዘጋጆቹ ልዩ የገና ዋዜማ ጨዋታዎችና መዝናኛዎችን ያሰናዱበትን ምክንያት ለአዲስ አድማስ ሲገልፁ፤ከፈተና መልስ ለልጆች የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ  የደስታ ቀን ለመፍጠር በማሰብ ነው ብለዋል፡፡
የ”ሃፒ ኢቨንትስ” ሁለት አርቲስቶች የሻማ ቀራፂና ሰዓሊ አስናቀ ክፍሌ እና ሳሮን ከፍአለ ሲሆኑ አብሯቸው የሚሰራው ደግሞ የህፃናት አጫዋችና የሰርከስ ባለሙያ የሆነው ተመስገን ግርማ ነው፡፡ አርቲስት አስናቀና  ሳሮን ለህፃናት በአዲስ መልክ የፈጠሯቸውንና ከሌሎች አገራት በመመልከት በሰሯቸው ልዩ ልዩ ጨዋታዎችና ውድድሮች ህፃናትን የሚያዝናኑ ሲሆን መዝለያዎች ፤ የቅርጫት ኳስ፤ ቀለም መቀባት፤ የህፃናት ፎቶ፤የፊት ላይ ስዕሎች፤ የህፃናት አዝናኝ ትረካና ሌሎች የተለያዩ መዝናኛዎችን እንደሚያቀርቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በበርካታ ህጻናት ዘንድ “ጥሩንቤ” በሚለው ስሙ የሚታወቀው ተመስገን ግርማ፤ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሳሙና አረፋዎች በሚሰራቸው  አስደናቂ ትርኢቶች አድናቆትን ያተረፈ ሲሆን በዛሬው ዕለት ህጻናትን ለማዝናናት ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃል ተብሏል፡፡  

Read 2868 times