Print this page
Saturday, 06 January 2018 12:37

የኢህአዴግ መግለጫና ተግባር!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(11 votes)

    አራቱ ገዥ ፓርቲዎች በሃያ ሰባት አመታት የአገዛዝ ዘመናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ለመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። እስከ ዛሬ በነበረው ታሪካቸው የኦሮሞ ድርጅት የሆነው ኦሕዴድ፡- ለኦሮሞ ሕዝብ፣ ሕወሓት፡- ለትግራይ፣ ደኢሕዴግ፡- ለደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ብአዴን፡- ለአማራ ሕዝብ ሲነግሩና ሲናገሩ ኖሩ እንጂ አንድ የጋራ አገር አለን እንደሚሉት አምነውበት፣ የኦሮሞ ድርጅት የሆነው ኦሕዴድ፣ የእኔና የኦሮሞ ሕዝብ  ጉዳይ የአማራውም፣ የትግሬውም፣ የደቡብም ነው ብሎ አጀንዳውን ለሕዝብ የዘረጋበት ጊዜ መኖሩን አላስታውስም። እንዲያውም የከፋፍለህ ግዛ መሳሪያ ሆነው፣ አንደኛው አካባቢ ሲያነባ ከንፈር መምጠጥ እንኳ ይከብዳቸው እንደነበር የምንዘነጋው አይደለም። ስለዚህም ይህ የመጀመሪያ መግለጫቸው፣ እንደ እኔ፣ እያንዳንዳቸው በግልና በጋራ ወደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለመድረስ የመፈለጋቸው ማሳያ ሆኖ የሚወሰድ ነው፡፡
የአራቱ የገዥ ፓርቲ መሪዎች በጋራና በየራሳቸው መግለጫውን ለመስጠት መነሳታቸው እስከ አሁን እንደ ነበር የሚታመነውን የአንደኛው ፓርቲ  የበላይነት፣ የሌላኛው የበታችነት ያለቀለት ጉዳይ መሆኑን  ለማሳየት ታስቦ የተሠራ ፕሮግራም እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ እንደቀደመው ጊዜ  የግንባሩ ሊቀ መንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደስአለኝ (ጠቅላይ ሚኒስትር) መግለጫውን ሰጥተው ቢሆን ኖሮ፣ የእኔም ሆነ የሌላው ሰው ጆሮ አዲስ ነገር አገኛለሁ ብሎ ለመጠበቅ አይነሳም ነበር፡፡ ስለዚህም እንኳንም እንዲያ ሆነ ብያለሁ፡፡
የአራቱ ድርጅቶች መሪዎች አቶ ለማ መገርሳ ከኦሕዴድ፣ አቶ ኃይለ ማርያም ደስአለኝ ከደኢሕዴግ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ከብአዴን እና ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ከሕወሓት፤ ጎን ለጎን ተቀምጠው ማየት፣ ለእኔ “ነገር በዓይን ይገባል” የሚለውን ምሳሌ እንዳስታውስ አድርጎኛል። በተጨማሪም ዶ/ር ደብረ ጽዮን በአንድ ስብሰባ ላይ፤ ‹‹ከአስፈለገ  ተጨማሪ መሰዋዕትነት በመክፈል የተጀመረውን ለውጥ እንታደጋለን›› በማለት የገለፁትን ቃል በተግባር እንዳሳዩም ጠርጥሬአለሁ። ካልተሳሳትሁ እሳቸው ትምክህት (በደርግ አማርኛ፡- የድርጅት እብጠት)  የሚሰማቸውን የሕወሓት አባላት ባይገሩ ኖሮ፣ ይህ ቀን ይመጣል ብሎ ለማሰብ የሚከብድ ነበር፡፡
የግል የመገናኛ ብዙኃን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንዲገኙ አልተጋበዙም፡፡ አራቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚመሯቸው የክልል መንግሥታት ሥር የሚተዳደሩ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ቢኖሩም እነሱም አልተጠሩም፡፡ በመግለጫው ላይ ዞሮ ዞሮ የሕወሓት ናቸው የሚባሉት ፋናና ዋልታም ብቅ እንዲሉ አልተፈቀደም፡፡ ባለሥልጣናቱ መግለጫቸውን የሰጡት ቀደም ሲል እንደገለፅሁት፤  በፌደራል መንግሥቱ ሥር ለሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ነው፡፡ ይህን ያደረጉት አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ወገንተኝነት ስለሚታይባቸው፣ የመግለጫቸው ይዘት በልዩ ልዩ መንገድ እንዳይበረዝ አስበው ሊሆን ይችላል፡፡
አራቱ የፓርቲ መሪዎች፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መግለጫ እንደሚሰጡ በይፋ ተነግሮ በቀጥታ ስርጭት ቀርቦ  ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር። ከየቴሌቪዥናችን ወይም ከራዲዮናችን አጠገብ ተቀምጠን  ለማዳመጥ እራሳችንን ባዘጋጀን ነበር። እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ከባለሥልጣናቱ አንደበት ስለምንሰማ፣ ለማመንና ለመቀበል የተመቸ ይሆንልን እንደነበርም ይገባኛል፤ይሁንና ይህ አልተደረገም፡፡ መግለጫው ከተሰጠ ቢያንስ ከ36 ሰዓታት በኋላ ለሕዝብ የሚቀርብ መሆኑ ሲታይ  እየቆረጡ በሚቀጥሉ የኢቢሲ ሰዎች እጅ መውደቁ ሳይታለም የተፈታ ይሆናል፡፡ እንደ ወረደ ባለማግኘታችን መግለጫው ጥርሱ ተነቅሎ፣ በድዱ እየሳቀ እንደመጣ መጠርጠራችን አይቀርም፡፡ ኢቢሲን እናውቀዋለን፤ እነሱም ያውቁታል፡፡
ስለ መገናኛ ብዙኃን መጠናከር የሚነግሩን መሪዎች፤ በዚህ ፈተና መውደቃቸውን ሊረዱት ይገባል፡፡ እነሱ ለገለፁት ሃሳብ፣ ነጻነት ያጡ፣ ለእኛስ  ምኑን  ይተርፈናል ብለን እንጠይቃለን?
መንግሥት የፖለቲካ እሥረኞች መኖራቸውን አምኖ መቀበሉና ይቅርታ ለማድረግ መነሳቱ ‹‹አበጀህ ግፋበት›› መባል ያለበት እርምጃ ነው። የፖለቲካ እስረኞች አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልልም መኖራቸው እንዳይዘነጋ ማሳሰብ ግድ ነው፡፡
ጉዳያቸው በክስ ሒደት ላይ ያሉ ወገኖች ክሳቸው እንደሚቋረጥ ተገልጿል፡፡ ተፈርዶባቸው የእሥር ቅጣታቸውን እየፈጸሙ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች በይቅርታ ሕጉ ማለፍ ሳይኖርባቸው የሚወጡበት መንገድ ካለ መፈለግ፣ የግድ ማለፍ ካለባቸውም ማፋጠን ከድርጅቶችና ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡
በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በመላ አገሪቱ በተቀሰቀሰው የሕዝብ አመጽ ከተሳተፉት ውስጥ ከ1500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በክስ ላይ እንደሚገኙ መንግሥት መግለጹ ይታወሳል፡፡ የእነሱ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ተቃውሞ እንጂ የዘረፋ ተግባር ነው ብዬ አላምንም፡፡ ይቅርታው እነሱንም ሊያቅፋቸው  ይገባል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፤ የድሮው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የአሁኑ ማዕከላዊ ወደ ሙዚየም እንደሚለወጥ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ያለው ከሕንጻው ወይም ከገቢው ጋር ሳይሆን እዚያ ከሚሠሩ ሰዎች ላይ ነው፡፡ መንግሥት ከሕንጻው በፊት በምርመራ ሥራ ያሰማራቸው  ሰዎች፤ ለሰው ልጅ ክብር ያላቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማስተማር አለበት፣ የምርመራ ሥራቸውን ሕግ አክብረው እንዲፈጽሙ ማድረግን ማስቀደም ይኖርበታል፡፡ ህግ ሲጥሱ የአቤት ባዮች ድምጽ መሰማት አለበት፡፡  ከዚህ ጎን ለጎን፣ መሪዎቹ ሊያስቡበትና መግለጫም ሊሰጡበት የሚገባው ጉዳይ በየማረሚያ ቤቱ የሚታየው የእስረኞች አያያዝ ነው። ማረሚያ ቤት በደል እንደሚፈጸምባቸው በየችሎቱ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡ በደረሰበት ድብደባ  አንድ ሰው ነፍስ ካወቀ በኋላ ከእናት አባቱ፣ ከእህት ወንድሙ የሚደብቀውን አካሉን በዳኛ ፊት ገልጦ ለማሳየት መጠየቅ ድረስ መሔዱ ሲታይ፣ በደሉ ምን ያህል እንደሚከፋ ለመገንዘብ አይከብድም፡፡ መንግሥት አፋጣኝ የእርምት እርምጃ ሊወስድበት ከሚያሻቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እባካችሁ ድረሱላቸው ጩኸቴ ነው!!
ሌላው ደግሞ  መንግሥት ሊያስብበት የሚያስፈልገው፣ በፍትህ  ሥርዓቱ ላይ ሕዝብ ያጣውን እምነት መልሶ እንዲገነባ ማድረግን ነው፡፡
‹‹የአገር ጉዳይ ከማናችንም ሥልጣን  ከማንኛውም ግለሰብ ክብር በላይ ነው›› ብለዋል አቶ ለማ መገርሳ። አገርን ከጥፋት መታደግ ድርጅቶቹ አሁን በቁርጥ የቆሙለት አጀንዳ መሆኑን በመግለጫቸው አመልክተዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ የችግሩ አንድ አካል እራሳቸው መሆናቸው ይጠፋቸዋል ብዬ አልጠብቅም። መፍትሔውን የምናመጣው እኛ ብቻ ነን ብለው የሚያስቡ ከሆነም አሁንም ችግሩን ያባብሱት እንደሆን እንጂ አያቃልሉትም፡፡ ለዚህ የዳረገን ይኸው እኔ ብቻ አውቃለሁ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡
አራቱ ድርጅቶች በተናጠል፣ በጥምረት እንደ ኢሕዴግ  የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መፈለጋቸው መልካም እርምጃ መሆኑን እየጠቆምሁ፣ ዋጋ የሚኖረው ግን ወደ ተግባር ሲሻገር መሆኑን ላሰምረበት እወዳለሁ። ለጀመሩት ለውጥ ሕዝብ እንዲያብራቸው እንደፈለጉት ሁሉ፣ ሀገራዊ መፍትሔ ለማምጣት የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመለከታችው ወገኖች በሙሉ እነሱ ከሚጠሉት ኢሕአፓ ጀምሮ ወደ አገር እንዲገቡ ማድረግ የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡  በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የመደራጀትና የማደራጀት መብታቸው ሊጠበቁላቸው ይገባል። በአሸባሪነት የሰየሟቸውን ኦነግንና ግንቦት ሰባትን ከዚህ ስያሜ ማላቀቅ፣ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ እስከ አሁን ባለው ጊዜያቸው በምንም አይነት ጉዳይ የፖለቲካ ተሳትፎ ይኑራቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ይገቡ ዘንድ መንግሥት ጥሪ ሊያቀርብላቸው  ይገባል፡፡
አራቱ ድርጅቶች  በድምር ኢሕአዴግ ባመጣው የኢኮኖሚ ለውጥ እንደሚመኩ ሁሉ የፖለቲካ ለውጥም አምጥቶ፣ የሚያኮራ ታሪክ ለመጻፍ፣ ኢህእግ እራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ እነ አቶ ኃይለ ማርያም፣ የደቡብ አፍሪካውን ደ ክለርክን ለመሆን ምን ያንሳቸዋል?
የንጉሡ መንግሥት ዘመኑ እያዘቀዘቀ መሔዱን መረዳት አቅቶት ሲንገታገት፣ አገርና ሕዝብ በወታደራዊ አገዛዝ እጅ እንዲወድቅ አደረገ፡፡ ደርግ ለኤርትራ ጉዳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ተስኖት፣ ለኤርትራ መገንጠል የተመቸ ሁኔታ ፈጠረ፡፡ ኢትዮጵያም የባሕር በር አልባ አገር ሆነች፡፡
ኢሕአዴግ ዝቅ ስንልም አራቱ ድርጅቶች፣ እስከ አሁን በቆዩበት ትምክህት ተውጠው፣ ያለኛ ማን አለ ብለው ከቀጠሉ፣ የኢትዮጵያ እጣ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ ለነሱም ይጠፋቸዋል ብዬ አላስብም፡፡ በየቦታው መሳሪያ እየወለወሉ ያሉ ነገ ቀንድ አያወጡም ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሳተፉበት የድርድር ጉባኤ ኢሕአዴግ ያዘጋጅ ዘንድ ሁኔታው    ይጠይቃል፡፡ አገርን ከመፍረስ፣ ሕዝብን ከመበተን የማዳኛው ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ ቃልና ተግባር ይጣጣሙ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ይጠብቅ !!             

Read 4130 times