Saturday, 21 April 2012 15:53

“ሁሉንም ህዝብ ማስደሰት የሚችል መንግስት የለም” (የመላዕክት ስብስብ ከሆነስ?)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

ኢቫኖቭ የተባለ አንድ ሩሲያዊ፤ የኮሙኒስት ፓርቲ አባል ለመሆን ፓርቲው ቢሮ ማመልከቻ ያስገባል፡፡ (በድሮዋ USSR ማለት ነው) የፓርቲው ኮሚቴ ማመልከቻውን ከመረመረ በኋላ አመልካቹን ለኢንተርቪው ይጠራዋል፡፡

“ጓድ ኢቫኖቭ፤ ሲጋራ ታጨሳለህ እንዴ?”

“አዎ፤ በጥቂቱ አጨሳለሁ”

“ጓድ ሌኒን እንደማያጨስና ሌሎችም ኮሙኒስቶች እንዳያጨሱ እንደሚመክር ታውቃለህ?”

“ጓድ ሌኒን የማይወዱ ከሆነማ ማጨስ አቆማለሁ”

“እሺ መጠጥስ ትጠጣለህ?”

“ትንሽ ትንሽ”

“ጓድ ሌኒን እኮ ጠጪነትን ክፉኛ ነው የሚቃወመው”

“እንዲያ ከሆነማ እኔም መጠጥ አቆማለሁ”

“ጓድ ኢቫኖቭ፤ ሴቶች ላይስ እንዴት ነህ?”

“ያው ትንሽ ትንሽማ አይቀርም”

“ጓድ ሌኒን እንዲህ ያለ ስነ ምግባር የጐደለው ነገር እኮ ያወግዛል!”

“እሳቸው ካወገዙትማ ሴቶችን ማፍቀር አቆማለሁ”

“ጓድ ኢቫኖቭ፤ ህይወትህን ለፓርቲው ለመሰዋት ዝግጁ ነህ?”

“እንዴታ! እንዲህ ያለውን ህይወት ማን ይፈልገዋል!”

ኢህአዴግ “ነፍሴ” ራሱን ከእንዲህ ያሉ እጩ አባላት መጠበቅ እንዳለበት በቅንነት ብናስታውሰው ከፌዘኝነት እንደማይቆጠርብን እምነታችን ነው፡፡ ይኸውላችሁ … የሚጠሉትን ህይወት መስዋዕት ማድረግማ መስዋዕትነት አይባልም! የፍቅርም መግለጫ አይደለም! እንደው ለነገሩ ግን… መስዋዕትነት የግድ ነው እንዴ? (በኮሙኒዝም አዎ!)  አያችሁ ከልብ የሆነ መስዋዕትነት ያስታውቃል፡፡ አሁን ለምሳሌ የተንደላቀቀ ህይወት የሚመራ ሰው “ህይወቴን ለፓርቲዬ!” ቢል ያሳምናል፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? የተንደላቀቀ ህይወት የሚመራ ሰው ቀድሞውኑ ለምን የፓርቲ አባል ይሆናል? (ምን አጥቶ!)

በያኔዋ ሶቭየት ህብረት ኮሙኒስት ፓርቲው የራሱ ልሳኖች የሆኑ ሁለት ትላልቅ ጋዜጦችን ያሳትም ነበር አሉ፡፡ አንደኛው ፕራቭዳ (እውነት) የሚባል ሲሆን ሌላው ኡዝቬስትያ (ዜና) ይባል ነበር፡፡ አንድ ከፖለቲካው የሌለበት የሩሲያ ዜጋ እንዲህ ሲል ጠየቀ፡-

“አንድ ፓርቲ ለምን ሁለት የተለያዩ ጋዜጦችን ያሳትማል?”

የተሰጠው ምላሽም፤ “ፕራቭዳ ውስጥ ዜና የለም፤ ኢዝቬስቲያ ውስጥ ደግሞ እውነት አይገኝም!”

አያችሁልኝ አለመታደል! “ፕራቭዳ” እውነት ያቀርባል ተብሎ የሚታሰብ ጋዜጣ  ቢሆንም ዜና ግን የለውም (ዜና የሌለው እውነት!) “ኢዝቬስቲያ” ደግሞ የዜና ጋዜጣ ቢባልም እውነት አይገኝበትም (እውነት አልባ ዜና!)

አንዳንድ ወገኖች ይህቺን አንብበው እነ “ኢቴቪ” እና “አዲስ ዘመንስ?” የሚል ጥያቄ ሊያነሱ እንደሚችሉ ጠረጠርኩና ከወዲሁ ምላሽ ልሰጣቸው ወደድኩ፡፡ ምን መሰላችሁ? ሁለቱም ከራሺያዎቹ ጋዜጦች ጋር የሚያመሳስላቸው ባህርይ መኖሩ ባይካድም ቅሉ እነ ኢቴቪ የፓርቲ ሚዲያ አይደሉም፡፡ የመንግሥት ልሳኖች ናቸው፡፡ የተመሰረቱትም በኢህአዴግ ዘመን ሳይሆን በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ነበር፡፡ በእርግጥ የህዝብ ሃብት ናቸው የሚሉ አሉ! (በመርህ ደረጃ!) በተግባር ግን የመንግሥት መሆናቸውን ሳንነጋገር የተስማማንበት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ መቼ የህዝብ ይሆናሉ? አይታወቅም! የፖለቲካ ፓርቲዎችን መቼ እኩል ያስተናግዳሉ? ይሄም አይታወቅም፡፡ መቼ የጭፍን ትችትና ዘለፋ ይተዋሉ? ይሄ ደግሞ የበለጠ አይታወቅም፡፡

በነገራችሁ ላይ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰሞኑን ፓርላማ ቀርበው ለተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች “የተለመደ” ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ የሰጡት ማብራሪያ አንዳንዶችን ሊያንጨረጭር እንደሚችል ይገመታል፤ ይጠበቃል፡፡

“የም/ቤት አባላት ልብ አላላችሁት ይሆናል እንጂ በጥምቀት በአል ላይ “አንድ አገር አንድ ሃይማኖት” የሚል መፈክር ይዘው የወጡ ጥቂት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ፤ ይሄ ፀረ ህገመንግስት ነው” ሲሉ የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የእስልምና መንግሥት እንዲመሰረት የሚያቀነቅኑ ጥቂት አክራሪዎች እንዳሉም አስረግጠው በመናገር፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ በስፋት አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዓለማዊ መንግሥት እንጂ ሃይማኖታዊ መንግሥት አይደለም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “የሙስሊም መንግሥት የለም፤ የዋቄ መንግሥት የለም፤ የክርስትያን መንግሥት የለም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ መንግሥት ብቻ ነው ያለው!” በማለት የማያዳግም ማብራሪያ ሰጥተዋል (በተለይ ለአክራሪዎች!)

እኔን በተለይ ያረካኝ ግን ምን መሰላችሁ? “የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ነው ያለው!” የሚለው ቁርጥ ያለ አነጋገራቸው ነው፡፡ ይሄን ሲናገሩ አጠገቤ ተቀምጠው የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር ሲኮመኩሙ የነበሩ ሽማግሌ ወዳጄ “ንግግሩ እኮ ቦንብ ነው!” (ተናጋሪውን ማለታቸው ነው!) ብለው ተነስተው ውልቅ አሉ - ከቤቴ (ተቀየሙዋቸው እንዴ?)

እኔ ግን ለምን አነጋገራቸው እንዳረካኝ ላስረዳችሁ፡፡ ባለፉት ዓመታት አንዳንድ የኢህአዴግ አክራሪ ካድሬዎች “የኢህአዴግ መንግሥት ነው ያለው” በሚል ደረታቸውን ሊነፉብን ሲሞክሩ ደጋግመን ታዝበናቸዋል፡፡ (No more! ብለናል)

አንዳንዶች ተቃዋሚዎች ደግሞ “ኢህአዴግና መንግሥት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው” በሚል “የኢህአዴግ መንግሥት” ተባለም “የኢትዮጵያ መንግሥት” ለውጥ የለውም ሲሉ ሊከራከሩኝ እንደሚችሉ ይገባኛል፡፡ ግን ማን እጅ ሊሰጣቸው?

በእርግጥ ኢህአዴግ በ2002 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ በ99 ነጥብ ምናምን ድምፅ (99.9 በመቶ መምህራን በአድማው አልተሳተፉም ነው የተባለው?) በ”ዝረራ” አሸንፎ ሥልጣን መያዙን አውቃለሁ (አውቃለሁ ሳይሆን ሰምቻለሁ ለማለት ፈልጌ ነው) አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍም ፓርቲው ከ20-40 ዓመት የመንግሥት ሥልጣን እንደሚፈልግም አውቃለሁ፡፡ (የግል ሥልጣን አለ እንዴ?) ይሄ ማለት ግን አሁን ያለው የኢህአዴግ መንግስት ነው ማለት አይደለም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ አስረግጠው እንደተናገሩት፤ የማንም የምንም መንግሥት የለም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ መንግሥት ብቻ ነው፡፡

ሌላውን ተውትና በንጉሱ ዘመን የሃይለስላሴ መንግሥት ነው ወይስ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው የነበረው? የኢትዮጵያ መንግሥት ነው!! በደርግ ዘመንም ቢሆን የደርግ መንግሥት የሚባል አልነበረም - የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ እንጂ! አሁን ለምሳሌ ኢዴፓ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝ (ኢህአዴግ እንዳይሰማኝ!) የኢዴፓ መንግስት ልንል ነው? (ያለ ደንቡ!) የኢትዮጵያ መንግስት ነው ሊባል የሚችለው፡፡

አያችሁ… “የኢትዮጵያ ህዝብ መንግሥት ነው ያለው” ሲባል.. ክርስትያኑንም፣ ሙስሊሙንም፤ ኢህአዴጉንም ተቃዋሚውንም …ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚያይ መንግስት ነው ማለት ነው፡፡ ያኔ ደህንነት ይሰማናል፡፡ “የኢህአዴግ መንግሥት ነው” ሲባልስ? … ያኔማ የሥራ እድል ቅድምያ የሚሰጣቸው ለኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ነው የሚል ሃሜትና ስሜት ይፈጠራል፤ ይናፈሳል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት እድልም እንዲሁ ለኢህዴጋውያን ብቻ ነው የሚሰጠው እየተባለ ወሬ ይነዛል! “የኢትዮጵያ መንግሥት ነው” ሲባል ግን ይሄን ማድረግ አይችልም (ስያሜው አይፈቅድለትማ!) እንግዲህ ተወደደም ተጠላም አሁን ያለው የኢህአዴግ አፍቃሪዎች መንግሥት ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን መንግሥት መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ በማያሻማ መልኩ ተናግረዋል፡፡ (ካድሬዎች ቢያቅራችሁም እቺን እውነት ዋጧት!)

ትንሽ ቅር ያለኝ ግን ምን መሰላችሁ? … ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን ለመናገር እስከዛሬ መዘግየታቸው ነው! (20 ዓመት እኮ ብዙ ነው!)

ጠ/ሚኒስትሩ ለመምህራን ከተደረገ የደሞዝ ጭማሪ ጋር በተገናኘ የተነሳውን ተቃውሞ አስመልክቶ ከመድረክ ተወካይ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ማብራሪያ ደግሞ ለብዙዎች “ሰርፕራይዝ” (ድንገቴ!) ነበር ማለት ይቻላል፡፡ “የደመወዝ ጭማሪ አልተጠየቀምም፤ አልተደረገምም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የተደረገው የእርከን ማሻሻያ ነው ሲሉ ከቤቱ የቀረበው ጥያቄ ላይ ማሻሻያ አድርገዋል፡፡ ለብዙዎች ሰርፕራይዝ የሆነባቸው ግን ምን መሰላችሁ? ተቃውሞ ያስነሱት 1 በመቶ ያህል መምህራን ብቻ እንደነበሩ መናገራቸው ነው፡፡ 99.9 በመቶ የሚሆኑት ግን በእርከን ማሻሻያው የረኩ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ (አንዳንድ ነገሮች በስታቲስቲክስ ሲገለፁ ግርም ያሰኛሉ!)

መምህሩ በደሞዙ የረካ ነው ወይ በማለት የጠየቁት አቶ መለስ፤ “ባለው ደሞዝ እዚህ አገር የረካ አስተማሪም ሆነ ሌላ ሠራተኛ የለም” ሲሉ ደምድመዋል፡፡ እንዴ… የደመወዝን ነገር ያቁዋታላ! (ደሞዛቸው 6500 ብር አይደለም እንዴ?!)

ይልቅስ እኔን ቅር ያሰኘኝ ምን መሰላችሁ? ማንም በደሞዙ የረካ እንደሌለ ተናግረው፤ መፍትሄውን ወይም ተስፋውን ሳይጠቁሙን ማለፋቸው ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የደመወዝ ጭማሪ ቢደረግ በዚህ ጣራ በነካ የዋጋ ግሽበት ላይ የባሰ ችግር ይፈጠራል ማለታቸውን…እሺ እንቀበላቸው፡፡ ግን መቼ ነው ባንደርስበት እንኳን ትንሽ ወደ እርካታው ጠጋ የምንለው? ከ10 ዓመት? ከ20 ዓመት ወይስ ከ40 ዓመት በኋላ? እንዴ… ሰው እኮ የሚኖረው በተስፋ ነው - በተለይ ደግሞ የታዳጊ አገር ህዝብ! (ድሃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ኖሮ ንጣት ይገለው ነበር… የሚለውን ተረት አስታወሳችሁት?)

ከመምህራን የደሞዝ ጭማሪው (ይቅርታ የእርከን ማሻሻያው!) ጋር በተገናኘ በተነሳው ተቃውሞና የሥራ ማቆም አድማ ላይ የተሳተፉት አንድ በመቶ የሚሆኑት መምህራን ናቸው በሚል ተቃውሞው ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሱበት ጠ/ሚኒስትሩ፤ እነሱም ቢሆኑ አስተማሪነት ያልተዋጣላቸው መምህራን እንደሆኑ ነግረውናል (ማንም ያልነገረን አዲስ መረጃ!)፡፡ “በአድማው ላይ የተሳተፉት የማስተማር ብቃቱና ፍላጐቱ የሌላቸው ነበሩ” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ እናም ቀጣዩ እርምጃ የመምህራን የብቃት ማረጋገጫ (certification) መጀመር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እኔ መንግሥትን ብሆን ኖሮ ግን (ኢህአዴግን ብሆን አልወጣኝም!) 1 በመቶ የሚሆነው መምህር ተቃውሞ ማስነሳቱን ሰበብ አድርጌ ይሄን የብቃት ማረጋገጫ አልጀምርም ነበር፡፡

ይሄንኑ ጉዳይ በተመለከተ አንድ ወዳጄ ምን አለ መሰላችሁ? “ኢህአዴግ እኮ ሁሌም እሳት የማጥፋት ሥራ ነው የሚወደው!” (እሳት አደጋ ነው ማለቱ ይሆን?) ሌላ የኒዮ ሊበራል አቀንቃኝ ወዳጄ ደግሞ ተቃውሞ ያስነሱት መምህራን ችሎታና ብቃት የጐደላቸው ናቸው መባሉን ተከትሎ “ቅዱስ ስጋቱን” ነገረኝ፡፡ “አሁን እንግዲህ ተቃውሞና የመብት ጥያቄ ያነሳ ሁሉ ችሎታና ብቃት የለውም ሊባል ነው!” በማለት፡፡ እንደ ወዳጄ ስጋት ከሆነ እኮ… ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቃውሞ ድምጽና አድማ መሳይ ነገር ከፈጠሩ “1 ከመቶ የሚሆኑ ችሎታና ብቃት የሌላቸው ተቃዋሚዎች ናቸው” ሊባል ይችላል፡፡

(መቃወም ችሎታ ይጠይቃል?)

ለማንኛውም ግን አንዳንድ ዜጐች እንዲህ እንደ አስተማሪዎቹ አድማ ሲመቱ እውነተኛ ዓላማ ያነገቡ ይሁኑ አሊያም ደግሞ ብቃት የሌላቸው … በትክክል እንድንለይ አሁኑኑ የብቃት ማረጋገጫ (certification) ለሁሉም ዜጐች ይሰጥልን - እንደ 1 በመቶዎቹ መምህራን እንዳያሳስቱን ነዋ! (አስተማሪዎቹ ቀላል ሸወዱን እንዴ?!)

በመጨረሻ ስለ ም/ቤት አባላት አንድ የከነከነኝን ጥያቄ ላንሳ፡፡ አብዛኞቹ አባላት ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄና አስተያየታቸውን ሲያቀርቡ ከወረቀት ላይ እያነበቡ ነው፡፡ ማንበባቸው ባልከፋ ነበር፤ በቅጡ ማንበብ አለመቻላቸው እንጂ!…. (እኔ የምለው ጥያቄው የራሳቸው አይደለም እንዴ?) ግዴለም በኮሚቴ ተውጣጥቶ የተሰናዳ ጥያቄም ቢሆን ችግር የለውም… በቅጡ ተረድተውትና ተለማምደው ሊቀርቡ ግን ይገባል (የአገር ገፅ ግንባታ ያበላሻሉ ብዬ እኮ ነው!) በነገራችን ላይ የም/ቤት አባላት ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎችም የንባብ ብቃት ማረጋገጫ እውቅና ቢሰጣቸው አይከፋም፡፡ ምናልባት የብቃት ማረጋገጫውን ከወደቁ መፍትሄው ቀላል ነው፡፡ የንባብ ስልጠና መስጠት ብቻ ነው፡፡

አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ “ልማታዊ መንግስታችን!” ያላለ ካድሬ ደሞዙ ይቆረጣል እንዴ? (እንዲህ ባዮቹ ስለበዙብኝ እኮ ነው!)

የም/ቤት አባላት የሚያቀርቡት ጥያቄ የራሳቸው ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ፣ አንድ የ60ዎቹ ፖለቲካ አቀንቃኝ የነበረ ወዳጄ የነገረኝን ጨዋታ አስታወሰኝ፡፡ በደርግ ዘመን ነው አለ፡፡ አዲስ (ጀማሪ) የጦሩ ጋዜጠኛ አንድ ጄነራል ኢንተርቪው ለማድረግ ይፈልግና ፈቃድ ይጠይቃቸዋል፡፡ “ምንም ችግር የለም!” ይሉታል፡፡ ጋዜጠኛውም ለቀጣዩ ቀን ይቀጥራቸዋል፡፡ በተባለው ሰአት ጄኔራሉ ቢሮ ከች ይላል - የጦሩ ጋዜጠኛ፡፡

ገና እንዳዩት “ጥያቄውን ወዲህ በል!” አሉት ጄነራሉ፡፡ ነገሩ እንግዳ ቢሆንበትም ያዘጋጃቸውን ጥያቄዎች ለጄነራሉ ከመስጠት ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ሰውየው ፊታቸውን ኮምተር ፈታ እያደረጉ ጥያቄዎቹን በጥሞና ካነበቡ በኋላ ወረቀቱን እያገላበጡ ተመለከቱና፤ “መልሱስ የታለ?!” ሲሉ አፈጠጡበት - ጋዜጠኛው ላይ፡፡ ጠላታችሁ ክው ይበል ክው ብሎ ቀረላችሁ!!

በነገራችሁ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ ከሰጡት ማብራሪያ “ለሳምንቱ ጥቅስ” (“Quote’s of the week” እንደማለት) የመረጥኩላቸው አንድ አባባል አለ፡፡ “ሁሉንም ህዝብ ሁልጊዜ ማስደሰት አይቻልም፤ ሁሉንም ህዝብ ማስደሰት የሚችል መንግሥት የለም” የሚለው ነው፡፡ (የመላዕክት ስብስብ ከሆነ ግን ይቻላል!)

መልካም የዳግማይ ትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ!!

 

 

Read 3873 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 15:56