Saturday, 23 December 2017 09:56

“አንጋጠው ቢተፉ፣ ተመልሶ ባፉ!”

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጨካኝ የናዚ ጄኔራል ነበር፡፡ አንዲት ባሏ የታሰረባት ሚስት ወደ ጄኔራሉ ቀርባ “ባለቤቴ የደረሰበት አልታወቀም፤ እባክዎ ይርዱኝ” አለችው። ጄነራሉም፤
“ተገድሎ ሊሆን ስለሚችል ካሣ ይሰጣት” ብሎ ሃያ ሺህ ዶች ማርክ እንዲከፈላት አስደረገ፡፡ በሳምንቱ ባሏ ሌላ እሥር ቤት እንዳለ ታወቀ፡፡
“ባለቤቴ እንዲህ ያለ እሥር ቤት እንዳለ ተረገግጧልና ገንዘቡን መልሼ ይፈታልኝ” ስትል አመለከተች፡፡
ጄነራሉም፤
“እቺ ሴት እኛን ውሸታም ልታደርገን ፈልጋለች እንዴ? ግደሉትና ገንዘቧን ይዛ ትቀመጥ!” አለ፡፡
ገዳዮቹ ባሏን እንደግሉ ጄኔራሉ የሰጠው ትዕዛዝ፤
“ራቅ አድርጋችሁ ውሰዱና ተኩሱ፤ ለከተማው የማይሰማበት ቦታ ግደሉት!” የሚል ነበር፡፡
ገዳዮቹ ሰውዬውን ራቅ አድርገው ሲወስዱት፣ መንገዱ እጅግ ረዥም ስለሆነበት፤
“ጎበዝ! መገደሌ እርግጥ ከሆነ፣ ለምን ይሄን ያህል ታደክሙኛላችሁ? ሰውነቴ በጣም ዛለ‘ኮ?! ለምን እዚሁ አትገድሉኝም?” አላቸው፡፡
ገዳዮቹም፤
“ኧረ ዝም ብለህ ሂድ! አንተስ ሞተህ እዚያው ትቀራለህ፡፡ እኛ አለን አደለም እንዴ ገና የምንመለሰው!” አሉት፡፡
*      *      *
ጨካኝ ሥርዓት ለማንም አይበጅም፡፡ መፍትሄ የሚመስሉንን ምላሾች ደግመን ደጋግመን እንመርምራቸው፡፡ ለህዝብ የሰጠናቸው መፍትሄዎች ምን ውጤት አመጡ? ምን ፍሬ አፈሩ? ብለን እንጠይቅ፡፡ የፈየዱት ፋይዳ ከሌለ፣ ሌላ አማራጭ እንፈልግ፡፡ የሰጠነው መፍትሔ መሬት ጠብ አይልም፤ ከእኛ ሌላ ለአሳር ነው፤ ብትቀበሉ ተቀበሉ፤ ብለን ተአብዮ አይሰማን፡፡ ከህዝብ ጋር ልብ ለልብ ተግባብቶ፣ ተማምኖ መጓዝ ነው - አገር ከችግር የሚያወጣው፡፡ “ብቆጣም እመታሻለሁ፤ ብትቆጪም እመታሻለሁ” የሚል አካሄድ፣ ከቶ ሁነኛ አካሄድ አይሆንም፡፡
እኛ ወደ መንገዱ እንሄዳለን እንጂ መንገዱ ወደ እኛ አይመጣም፡፡ ባልባለቀ ዲሞክራሲ፣ አጥጋቢ ባሆነ ፍትሕ፣ በሙስና ባህር ውስጥ በተዘፈቀ ሂደት “አገር እድገት እያሳየች ነው” ብለን አንገበዝ፡፡ እርቅና ድርድር መልካም ገፅታ የሚኖረው፣ ልባችን ንፁህ ሆኖ ሁላችንም በአንድ ቅኝት ስለ አገር መዘመር ስንችል እንጂ ተነጣጥለን በመጓዝ አይደለም፡፡ በሁሉም ወገን የጥሞና ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ የአርምሞ ገዳም ያሻናል፡፡ እስከ ዛሬ የተጓዝንበት መንገድ ምን ያህል ሰላምን ያቀፈ ነበር? የህዝባችንን ድምፅ ምን ያህል አዳምጠናል? መሰረታዊ ለውጥ አድርገናል ወይስ የለመድነውን መዝሙር ደግመን እየዘመርን ነው? ልዩነት ያስፈልገናል፡፡ vive la difference! የሚሉት ፈላስፎቹ; ልዩነት ለዘለዓለም እንዲኖር xeneji ሌጣ እንድንሆን አይደለም!
እንስከን!! እንዘጋጅ!! “ሲሮጡ የታጠቁት፣ ሲሮጡ ይፈታልን” አንርሳ! አለበለዚያ “አንጋጠው ቢተፉ ተመልሶ ባፉ” እንደሚሆን እንገንዘብ፡፡ ለህዝብና ለአገር የሚበጀው ይሄ ነው!!  

Read 5942 times