Sunday, 19 November 2017 00:00

የማይተማመን ባልንጀራ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል

Written by 
Rate this item
(19 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች በአንድ ጫካ ውስጥ አቋርጠው በጣም ረዥም መንገድ እየሄዱ ነበር፡፡ መንገዱን ከመጀመራቸው በፊት፤
አንደኛው - እንግዲህ አደራ መንገድ ነውና የሚያጋጥመን አይታወቅም፡፡ ስለዚህ እንማማል፡፡
ሁለተኛው - ገና ለገና ችግር ያጋጥመናል ብለን ነው የምንማማለው? ማናቸውንም መከራ ልንችል፣ ካስፈለገም በምድር ላይ ለሚያጋጥመን ሞትም እንኳ ቢሆን፤ መስዋዕትነት ልንከፍል ከልባችን የተነሳን ጓደኛሞች፤ እንዴት እንዲህ በአንድ ጊዜ አለመተማመን ደረጃ እንደርሳለን? የማይተማመኑ ጓደኛሞች ነን ወይም ነበርን ማለት ነው?
አንደኛው - አይደለም ወዳጄ፤ ጠዋቱን ወዳጅነታችንን ስንጀምር አገር አማን ነበር፡፡ ያለ ህግ፣ ያለ መመሪያ፣ ያለ ፊርማ ነበር ሁሉንም የጠነሰስነው! አሁን ግን ጊዜው ከፋ፡፡ ከጓደኞቻችን መካከል እነማን ትተውን እንደጠፉ፣ እነማን በቃን ብለው ነገር - ዓለሙን እንደተዉት፣ እነማንስ ወኔያቸው እንደከዳቸው አስታውስ! አሁን የእኛም መጨረሻ ምን እንደሆነ በማይታወቅበት ሁኔታ መማማል መምጣቱ አያስገርምም!
ሁለተኛው - እንግዲህ ካልክ ይሁን! እኔ ግን አላመንኩበትም
ምርጫ የሌላቸው ጓደኞች ተማማሉ፡፡
“የከዳ ክህደቱ በልጅ ልጆቹ ይድረስ ተባባሉ!”
ከዚህ በኋላ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ጫካው ውስጥ እንደገቡ በድንገት አንድ አውሬ መጣባቸው።
“በል ወዳጄ መሳሪያህን አቀባብል” አለው፡፡
ጓደኛው ግን ምን ጊዜ አመለጠ ሳይባል ሮጦ ዛፍ ላይ ወጥቷል፡፡
ያለ አጋዥ የቀረው ጓደኛ፤ ከዚህ ቀደም በሚያውቀው ዘዴ በመጠቀም፣ መሬት ላይ ትንፋሹን አጥፍቶ እንደሞተ ሰው ሆኖ ለጥ አለ፡፡
አውሬው የሞተ ሬሳ አይበላ ኖሮ፤ መጥቶ አሽትቶት አሽትቶት ቀስ እያለ ርቆ ሄደ፡፡
አውሬው ሙሉ በሙሉ ከአካባቢው ርቆ፣ ከዐይን ከተሰወረ በኋላ፤ ዛፍ ላይ ወጥቶ የነበረው ጓደኛው ወደ መሬት ወርዶ የተኛው ጓደኛው ጋ መጥቶ፤
“ለመሆኑ አውሬው ወደ ጆሮህ ቀርቦ ምን ነገረህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
የተኛው ጓደኛም፤
“እጅግ አስገራሚ ነገር ነው የነገረኝ!”
“ምን አለህ በሞቴ?” ሲል ሰፍ ብሎ ጠየቀው፡፡
“እሱማ ያለኝ ከእንግዲህ በህይወትህ አደጋ ሲያጋጥምህ የሚከዳ ወዳጅ ጋር መንገድ እንዳትጀምር! መንገድ ከመጀመርህ በፊት ጓደኛ የምትመርጥበትን ቅድመ - ሁኔታ አጥርተህ ዕወቅ!” አለኝ፡፡ አንተ ባንዳ መሆንህ የገባኝ አውሬውን ካገኘሁ በኋላ ነው! በል ደህና ሰንብት ወዳጄ። ጊዜው ደግ ሲሆን አገኝሃለሁ!” ብሎት ሄደ፡፡
*      *     *
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“ዕምነት ሲታመም
ሺ ወረቀት መፈራረም” ይለናል፡፡
የላይኛው ተረት መንፈስ በቅጡ ገብቶታል ማለት ነው!
አለመተማመንና ጥርጣሬ አብዮት የሚባለው መሰረታዊ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ፤ ውስጣችን በቅሎ ያደገ ክፉ አባዜ ነው! ከዚህ ይሰውረን! የኢኮኖሚ ጥርጣሬ፣ የፖለቲካ ጥርጣሬ፣ የባህል ጥርጣሬ ወዘተ… ለዘመናት ሲፈታተኑን የኖሩ ሳንካዎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ጥርጣሬዎች አንድም ከመንግስት የተወለዱ፣ ሁለትም ከአብዮተኞቻችን የተቀፈቀፉ፣ ሦስትም በህዝብ የረዥም ጊዜ ትግል የፈለቁ ናቸው! ምንም ያህል ዘመን ስንጠራጠር ብንኖር፤ አንዳንድ ዕውነቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው፣ ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ሲሟሉ፣ ከመከሰት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ቀናቸውን ቆጥረውና ጊዜያቸውን ቀምረው ከተፍ ይላሉ፡፡
ደራሲ ከበደ ሚካኤል፤
“… እንዲሁም በዓለም ላይ፣
አለ አንዳንድ ነገር፤
በዚህ ቢሉት በዚያ
ከመሆን የማይቀር!”
የሚሉን አይቀሬ ነገሮች በምንም መንገድ ከመፈፀም እንደማይቀሩ ሲያስገነዝቡን ነው!
መንገዶች ወደ ግባቸው የሚያደርሱን ነባርና ተዓማኒ በመሆናቸው ነው! ሁሉንም ቀና ያድርግልን!
ሰው መምረጥና የአገር አጋዥ መፈለግ ዛሬ ግዴታችን ነው! የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ እንጂ አማራጭ የሌለው ነው!
በውስጣችን በአስተሳሰብ የበሰሉ፣ ሆደ-ሰፊ፣ በልምድ የበለፀጉ ብርቱ ብርቱ ሰዎች አሉ፡፡ የሽማግሌነት ድልድዮቻችን ናቸው፡፡ አደባባይን ያዩ ዘንድ ዕድል እንሰጣቸው፡፡
የሮበርት ብራውንን ግጥም የተረጎመው ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታም፤
“…አለ በውስጣችን
ዕውነት ፍፁም ሆና የምታበራበት፤
ደግሞም ማወቅ ማለት
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ”
የሚለን ይሄንኑ ሲያፀኸይ ነው!!
ከበረታን መተማመን አያቅተንም፡፡ በቂ የጥርጣሬ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ በቂ የሌሎች መሣሪያ የመሆን የመበለጫ ዕድሜ ቆጥረናል፡፡ ዛሬ ግን እንደ ሁሉም ነገር የማብቂያ ሁኔታ ደርሷል፤ ብንል፤ ላለመዘናጋት በር ለመክፈት የበሰልን የሆንበትና ዐይናችንን የከፈትንበት ወቅት መጥቷል ብንል የማጋነን አይሆንም! ደጋግመን፤ “የማይተማመን ባልንጀራ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል” የሚለውን ተረት፤ ከአንጀታችን ማሰብ ነው፡፡ ያኔ ለውጥ በእጃችን ላይ መሆኑን እንገነዘባለን!! “የበላን አብላላው፣ የለበሰን በረደው” መባሉንም አንርሳ!! እነሆ ለውጥ የተዘጋጁትን ከግትሮቹ፣ በጎቹን ከተኩላዎቹ መለየት ታላቅ አገራዊ ግዴታ ነው!!

Read 5954 times