Saturday, 14 April 2012 12:04

የኑሮ ውድነት የሚፈታበት ቀን ናፍቆኛል (እንደፆሙ!)

Written by  -ኤልያስ-
Rate this item
(2 votes)

“ጐበዝ! ቁርጥ እየበላን ፎቶ እንነሳ!”

ባለፈው ሳምንት ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን/መንግስትን በተመለከተ ለሁለት አስርት ዓመታት ወጥረው ይዘውት የነበረውን አቋም የቀየሩ የሚያስመስል ስሜት የተንፀባረቀበት ድንገተኛ መግለጫቸውን አንብቤአለሁ - እዚሁ ጋዜጣ ላይ፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ክስተቱን “ስልታዊ ማፈግፈግ” ሲሉት፤ ሌሎች ደግሞ ተቃዋሚዎች እኮ “ተከረበቱ” ብለዋል (ወዴት ነው የሚከረበቱት?) ከ97 ምርጫ በኋላ ፖለቲካን እርም ያለው ወዳጄ ደግሞ ነገርዬውን የኢህአዴግ ሴራ ነው ብሎታል፡፡ ወዳጄ እንደሚለው ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በ1ለ5 የአደረጃጀት ስልት አጥምቆዋቸዋል! (ቆመው ነው ሞተው?) የሆነስ ሆነና የአቋም ለውጡን ከደጋፊዎቻቸው ጋር መክረውበት ነው ወይስ በግብታዊነት የደረሱበት ውሳኔ ነው? አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በሰጡት አስተያየት፤ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ነው ማለታቸውን ስሰማ ጠላታችሁ ክው ይበል ክው አልኩላችሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ?

ተቃዋሚዎቹ በቅርቡ ካወጡት መግለጫ ጋር ይጋጫል እኮ! እኔ የምለው… ማነው በአንድ ጀንበር የባህርይ ለውጥ ያመጣው? ኢህአዴግ ወይስ ተቃዋሚዎች? ኢህአዴግ ከተባለ መቼም ግርም ነው የሚለኝ… ለምን ቢባል? በአንድ ጀንበር “የመላዕክት ስብስብ” ሆነ ማለት እኮ ነው፡፡ ይሄን አሜን ብለን እንዳንቀበል ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ “መንግስት የመላዕክት ስብስብ አይደለም” ሲሉ አስረግጠው ነግረውናል (መላዕክታዊ ምግባር እንዳንጠብቅ!)

 

ወዳጆቼ… በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የግንዛቤ ስህተት ፈፅሞ እንዲፈጠር አልሻም፡፡ ተቃዋሚዎች ለገዢው ፓርቲ ሥራዎች እውቅና በመስጠታቸው ቅር ያለኝ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል (ይሄማ ጨለምተኝነት ነው!) ነገር ግን “ብዥታው” መጀመርያ መጥራት አለበት ባይ ነኝ፡፡በነገራችሁ ላይ… አንዳንድ የፖለቲካ በፈገግታ አንባብያን ባለፈው ሳምንት ያስኮመኮምኳቸው የሩሲያ ቀልዶች በሃይለኛው እንደተመቻቸው ነግረውኛል፡፡ በስልክ፤ በዩቲዩብ፤ በፌስቡክ ወዘተ… (ደሞ አብዮት እንዳታስመስሉብኝ!) እኔ ደሞ አንባቢዎቼ ሁሌም እንዲመቻቸው ስለምፈልግ ዛሬም ከዚያች ምቾት ቆንጥሬ ላቀምሳቸው ወስኛለሁ፡፡ አያችሁ ቀልድ በአገራችን እንደ meat ሳይወደድ አልቀረም፡፡ ለዚህ ነው ሩሲያ እየከነፍን የምንሄደው፡፡እኔ የምለው ግን… ለምንድነው “የቀልድ ባለሙያዎች” ማህበር የማይቋቋመው (እንደመምህራን አድማ መምታት አይፈቀድም!)

ከቀልዱ በፊት ማሳሰቢያ:- ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የሚያጠነጥን ፊልም ለመስራት ስላሰብኩ ማንም የፊልም ባለሙያ ካሜራ እንዳያነሳ በሃይማኖት አባቶች በቅርቡ ላስገዝት አስቤአለሁ፡፡ ተስገብግቤ ግን እንዳይመስላችሁ… ቃል የተገባልኝን ስፖንሰር (የገንዘብ ድጋፍ) በአልባሌ ነገር እንዳላባክነው ፈርቼ ነው፡፡ እስቲ ለማንኛውም ወደ ሩስያ ቀልዳችን እንለፍና ዘና እንበል!!

አንድ የውጭ ልኡክ ድንገት ሳይታሰብ የገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበርን ለመጐብኘት ከች ይልላችኋል (ሩሲያ አንዲት ወረዳ ውስጥ) የህብረት ስራ ማህበሩ መረጃው ስላልደረሰው ተደነባበረ፡፡ ልኡኩም እውነትን እርቃኗን አይቷት ተመለሰ - በፕሮፖጋንዳ ያልተሸፋፈነ የሩሲያን ገበሬ እውነት (ህይወት) ማለት ነው፡፡

ልኡኩ እንደሄደ የህብረት ስራ ማህበሩ ሊ/መንበር በንዴት ቱግ ብሎ የወረዳዋን ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ያስጠራና “ምን ማድረጋችሁ ነው? መች በቅድምያ አስጠነቀቃችሁኝ? ገበናችንን እኮ ነው ያዩት፤ የፈራረሰውን የከብቶች በረት፣ ቆሻሻውን… ኮተቱን፣ እበቱን… መከራችንንና ድህነታችን ሁሉ እኮ ነው የተመለከቱት!” ይላል በቁጣ ቅላፄ፡፡

“አትጨነቅ ባክህ… ምን ያመጣሉ?” አለ የፓርቲው ፀሐፊ - በግዴለሽነት፡፡

“እንዴ… ለዓለም ያወሩብናላ!”

“ተዋቸው! ..ሥም ማጥፋት እንደሆነ ሥራቸው ነው!” ሲል መለሰ የፓርቲው ፀሐፊ፡፡

አያችሁልኝ… የኮሙኒስትን ዓይናውጣነት! ያዩትንም ቢናገሩ ስም ማጥፋት ነው… ወይም ጥላሸት መቀባት… አሊያም ገጽታ ማበላሸት… ወይም የፈጠራ ወሬ… ካልሆነም መሠረተ ቢስ ውንጀላ ወዘተ…ወዘተ…

(ውድ አንባብያን፤ ቀልዱ ከአገራችን አንዳንድ እውነታዎች ጋር የመመሳሰል ሁኔታ ከታየበት እንደው በአጋጣሚ የተፈጠረ እንጂ ድብቅ አጀንዳ ያላነገበ እንደሆነ ተረዱልኝ!)

ጉርሻ እንኳን አንድ ያጣላል ይባል የለ… አንድ ሌላ ቀልድ ልድገማችኋ! አሁንም እዚያው ሩሲያ ነን፡፡ አንድ አያትና የልጅ ልጅ በመንገድ ሲያልፉ፣ ልጅ በየቦታው ሰዎች ወረፋ ይዘው ይመለከትና አያቱን ይጠይቃል:-

“ባባ ይሄ ምንድነው?”

“ወረፋ ይባላል ልጄ”

“ምንድነው ወረፋ?”

“አንዴ የስጋ እጥረት ተከስቶ በነበረ ጊዜ ነው የተፈጠረው”

“ባባ..ስጋ ምንድነው?”

አያችሁ…በአያትየው ዘመን የስጋ እጥረት ነበር የተፈጠረው፡፡ በልጅ ልጅ እድሜ ግን ከነአካቴው ጠፋ (እድሜ ለኮሙኒስቶች!) የሆኖ ሆኖ ግን ለአያትየው የበለጠ ችግር የሆነባቸው የስጋው አለመኖር ሳይሆን የስጋን ምንነት ለልጅ ማስረዳቱ ነበር፡፡ (የስጋ ፎቶ የላቸውማ!)

በነገራችሁ ላይ የሩሲያ የስጋ ተመክሮ ወደኛም አገር እንዳይመጣ ስጋት አድሮብኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቄራ ድርጅት በቅርቡ “ያበሰረውን” ዜና ሠምታችሁልኛል አይደል? ከነገ ጀምሮ 1 ኪሎ የበግ ስጋ በ71 ብር እሸጥላችኋለሁ ብሏል አሉ፡፡ እንግዲህ የበሬውን ስጋ በስንት ብር ሊቸበችብልን እንዳሰበ ቄራ ብቻ ነው የሚያውቀው!

እኔ የምለው ግን.. ይሄው የሁዳዴ ፆም እንኳን ቀኑን ቆጥሮ ነገ ሊፈታ ነው አይደል! እኔን የናፈቀኝ ግን ምን መሰላችሁ? እንደ ፆሙ የኑሮው ውድነት የሚፈታበት ቀን! እንዴ… ችኮ ፊልም ሆነብን እኮ!

አንዱ የጥሬ ስጋ አድናቂ ያለውን ሰምታችሁልኛል? ኪሎ ስጋ 100 ብር የነበረ ጊዜ ነው አሉ፡፡ እናም… ከወዳጆቹ ጋር አንዱ ልኳንዳ ቤት ጮማውን እያወራረደ ሳለ የሂሳብ መክፈያዋን ትኬት (ቢል) ቃኘት ያደርግና በዋጋው ማሻቀብ ክው ብሎ “ጐበዝ ቁርጥ እየበላን ፎቶ እንነሳ እንጂ!” አለ፡፡ የሥጋ ዋጋ መናር ከቀጠለ ቁርጥ መብላት ተረት መሆኑ አይቀርማ! ለዚህ መድሃኒቱ ደግሞ የማስታወሻ ፎቶ መነሳት ነው - ከቁርጥ ስጋ ጋር፡፡ (ለታሪክ ማስረጃ ብናጣስ?)

ይሄውላችሁ የሸቀጦች ዋጋ ያለቅጥ ሲንር ቶሎ ብላችሁ ከዚያ ሸቀጥ ጋር ፎቶ ተነሱ፡፡ እንዴ… በኋላ ተረት ቢሆንስ? አሁን ለምሳሌ ኪሎው 25 ብር የገባው ብርቱካን በአንዳንድ ችግሮች ከምድረ ገፅ ሊጠፋ እንደሚችል ምንጮች እየጠቆሙ ነው (በሰው ሰራሽ ሳይሆን በተፈጥሮአዊ ችግር!) ምን ተሻለ ታዲያ? የሚሻለውማ… ብርቱካን እየላጣችሁና እየተጐራረሳችሁ ምርጥ የማስታወሻ ፎቶዎችን በብዛት መነሳት ነው! ለምን አትሉኝም? አዲሱ ትውልድ ወደፊት “ምንድነው ብርቱካን?” የሚል ድንገተኛ ጥያቄ ሲሰነዝርባችሁ፣ በፎቶግራፍ የተደገፈ ሙሉ ማብራሪያ መስጠት ትችላላችሁ!

አንዱ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ? የትራንስፎርሜሽን ቀስቱ “ሙስና” ላይ አነጣጥሮ ኢላማው ግን ሙስናን ስቶ “ሙዝ”ን እየመታ ነው! ሌላም ብሎኛል - ወዳጄ! የትራንስፎርሜሽን …ቀስቱ “ድህነት” ላይ አነጣጥሮ የሚመታው ግን “ድንች”ን ሆኗል! (በፊደል መመሳሰል) ጉደኛ ምልከታ ነው!

በነገራችን ላይ አንዳንድ ነገሮች ህልውናቸው ማክተሙ ካልቀረ ታሪክን ብንቀድመው ምን ይመስላችኋል? (ቀድመን ታሪክ በመስራት ማለቴ ነው!) ለምሳሌ የቀድሞ የኢህአዴግ ባለስልጣናት “በመተካካት ስትራቴጂ” ከስልጣን መንበሩ ሸርተት እያሉ አይደል? (ሥልጣንን ታሪክ እያደረጉት ማለት ነው!) እናም እንደስልጣናቸው ታሪክ ከመሆናቸው በፊት አብረናቸው ፎቶ ብንነሳስ? (እንደ ቁርጥ ሥጋው!) ከኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋር ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚ አመራሮች ጋርም ፎቶ መነሳት ብልህነት ነው፡፡ እውነቴን ነው… አብዛኞቹ እኮ ዕድሜያቸው እየገፋ ነው! ምናልባት አንዳንድ ፓርቲዎች ከአመራሮቹ ጋር ታሪክ የመሆን አደጋ ሊጋረጥባቸው ስለሚችል በፓርቲዎቹ ጽ/ቤት ፎቶ መነሳት ታሪክን መቅደም ይመስለኛል፡፡ (ፖለቲካ መስራት ባይሆንልን ታሪክ እንስራ ብዬ እኮ ነው!)

አሁን ለምሳሌ ተቃዋሚዎች ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ የአቋም ለውጥ አድርገው የለ! (አንዳንዶች “መከርበት” ብለውታል) ይሄ “መከርበት” ፀንቶ ሳይቀጥል ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ፎቶ መነሳት ተገቢ ይመስለኛል (እንዲህ ነበሩ ተቃዋሚዎች ለማለት!) አይታወቅም እኮ… ተቃዋሚ የሚባለው ነገር እንደ ሰሜን ዋልያና ቀይ ቀበሮ ሁሉ የህልውና አደጋ ሊገጥመውም እኮ ይችላል (ጨለምተኛነት እንዳይመስላችሁ - ቅዱስ ስጋት ነው!)

መቼም በፋሲካ ዋዜማ ታሪክ ሊሆኑ ስለተቃረቡ ነገሮች ማውጋት ተገቢ አልነበረም፡፡ ግን ወደን አይደለም፡፡ (ብቻ ፋሲካም ታሪክ እንዳይሆን!) እውነታው ስላስገደደን ብቻ ነው፡፡ እስቲ ደግሞ አንዴ ሩሲያ ደርሰን እንመለስ፡፡

አንዱ ሩሲያዊ የአገሩን ፖለቲከኛ፤ “ምነው ቅቤ ከገበያው ላይ ጠፋ?” ሲል ይጠይቀዋል “የሩሲያ የህገ-መንግስት ፀሃይ አቅልጦት ነው!” በማለት መለሰ ፖለቲከኛው፡፡ (ፀረ-ኮሙኒስት መሆን አለበት) የእኛስ ቅቤ… ምነው 200 ብር ገባ?

አንድ ማለዳ ከአንድ ባልደረባዬ ጋር በመኪና ተሳፍረን እንሄዳለን… የኢትዮጵያ ሬዲዮ ደግሞ ስለ ህዳሴው ግድብ ”የሸመደደውን” ያዘንበዋል፡፡ ባልደረባዬ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ለምን የምርጫው ወጪ ለህዳሴው ግድብ አይውልም?” (የቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ማለቱ ነው፡፡) ለምን… አልኩት፡፡ መጀመርያ ዳቦ ከዚያ ምርጫ አለኝ… (የሚያዋጣ አልመሰለኝም)

እኔ የምለው ግን..... የእስልምና ም/ቤት ጉባኤ ምርጫ ለማካሄድ 40ሚ. ብር ያስፈልጋል ያሉት ከምራቸው ነው? አገራዊ ምርጫ ታዲያ ስንት ሊፈጅ ነው? (400 ሚሊዮን?)

በነገራችሁ ላይ… የነገውን የትንሳኤ በዓል ስታከብሩ ካሜራ ከአጠገባችሁ እንዳታርቁ እመክራችኋለሁ (የፎቶ ካሜራ ማለቴ ነው!) በሚቀጥለው ዓመት ፋሲካ ይኑር አይኑር አይታወቅማ! (በኑሮ ውድነት!)

የፋሲካ ወጋችንን ከመቋጨታችን በፊት አንድ የሩሲያ ቀልድ እነሆ በረከት ብላችሁስ… እንደ አውዳመት ስጦታ፡፡

የውጭ አገር ኮሙኒስት የልኡክ ቡድን አንድ የሞስኮ ህፃናት መዋያን ለመጐብኘት ሩሲያ ተገኝቷል፡፡ ልኡኩ ከመምጣቱ በፊት ግን ህፃናቱ ለሚቀርብላቸው ጥያቄዎች ባለ አንድ ዓ. ነገር መልስ ብቻ እንዲሰጡ ቀደም ብለው ተመክረዋል (ታዝዘዋል ማለቴ ነው) A one sentence answer የተባለው ምን መሰላችሁ? “በሶቭየት ህብረት ሁሉም ነገር ምርጥ ነው!” እያሉ እንዲመልሱ ነው፡፡

ጐብኝዎቹ ህፃናት መዋያውን ተዟዙረው ከጐበኙ በኋላ ጥያቄያቸውን ለእምቦቀቅላ ህፃናቱ መሰንዘር ጀመሩ፡-

“ህፃናት፤ ይሄን ህፃናት መዋያ ትወዱታላችሁ?”

“በሶቭየት ህብረት ሁሉም ነገር ምርጥ ነው!” ህፃናቱ በአንድ ላይ በጩኸት መለሱ፡፡

“የሚቀርብላችሁ ምግብስ እንዴት ነው?”

“በሶቭየት ህብረት ሁሉም ነገር ምርጥ ነው!” አሁንም በተመሳሳይ ቃና መለሱ፡፡

“አሻንጉሊቶቻችሁን ትወዷቸዋላችሁ?”

“በሶቭየት ህብረት ሁሉም ነገር ምርጥ ነው!”

ይሄን ጊዜ ከህፃናቱ ሁሉ በጣም ትንሹና ሚሻ የተባለው ህፃን እሪ ብሎ ማልቀስ ጀመረ፡፡

“ሚሻ፤ ለምንድነው የምታለቅሰው? ምን ተፈጠረ?”

“ሶቭየት ህብረት ውሰዱኝ!”

ምስኪኑ ሚሻ … ይህቺ ህፃናቱ ሲጮሁላት የነበረችውን “ከዓለም ምርጧን” ሶቭየት ህብረት አይቷት አያውቅማ! ለነገሩ ይሄ ነገር አንዳንዴ እኛም አገር ያጋጥመናል እኮ … ኢቴቪ በል ሲለው የሚፈጥራት ጦቢያ እስካሁን በተሰናዱ የዓለምም የአህጉርም ካርታዎች ላይ የለችም እኮ ነው የሚባለው (ምናልባት ካርታ ውስጥ አልተካተተች ይሆን?) ለነገሩ “አስማተኛው” ኢቴቪ ቢጠየቅም ያለችበትን አያውቅም (አድነን ከውሸቱ … ብለን እንለፈው!) በሉ የራሳችሁንም የኢቴቪንም አውዳመት በደንብ አክብሩ… መልካም የትንሳኤ በዓል!!

 

 

Read 4472 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 12:11