Sunday, 05 November 2017 00:00

አካባቢን በክለዋል የተባሉ ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች ታሸጉ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

  ፋብሪካዎቹ በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ኪሳራ ደርሶብናል አሉ
                
    የከተማዋን አየር ንብረት በክላችኋል፣ የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዳ የአየር ብክለት አድርሳችኋል የተባሉ ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች ታሸጉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከትናንት በስቲያ በወሰደው እርምጃ አዲስ አበባ ቆዳ ፋብሪካ፣ ባቱ ቆዳ፣ ድሬ ቆዳ፣ ዋልያ ቆዳና ፒውኒንግ እና አዋሽ ቆዳ ፋብሪካዎች ታሽገዋል፡፡
የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ በፋብሪካዎቹ በራፍ ላይ የለጠፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፤ ፋብሪካዎቹ ለአካባቢ ጥበቃ አደጋ እየሆኑ በመምጣታቸው፣ የአመራረት ስርዓታቸውን በማስተካከል ለአካባቢና ለህብረተሰቡ ጤና አደጋ ከመሆን እንዲታቀቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንደነበር ተገልጿል፡፡ ፋብሪካዎቹ በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያና የጊዜ ገደብ ተጠቅመው የምርት አመራረት ሂደታቸውን አካባቢን የማይበክልና ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ እንዳይሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ባለስልጣን መ/ቤቱ በሰጣቸው የጊዜ ገደብ ወደ ተባለው የአመራረት ሂደት ለመግባት አለመቻላቸውም ታውቋል፡፡ ሁኔታው ከባድ ችግር ከማስከተሉና ለአካባቢና ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ ከመሆኑ በፊት ፋብሪካውን ማሸግ ተገቢ ተግባር በመሆኑ እርምጃው ሊወሰድ እንደቻለም ተገልጿል፡፡
የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች እንደሚናገሩት፤ ባለስልጣን መ/ቤቱ ቀደም ሲል ፋብሪካዎቹ ለአካባቢ ብክለትና ለህብረተሰብ ጤና ችግር ሊያስከትል የሚችል የአመራረት ሂደት የሚከተሉ በመሆኑ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የአመራረት ሂደታቸውን እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን ፋብሪካዎቹ ይህንኑ ተከትለው በርካታ ማሻሻያዎችን አድርገዋል ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ በአሁኑ ወቅት የፈፀመው ድንገተኛ ፋብሪካዎቹን የማሸግ ተግባር ተገቢ ያልሆነና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዳ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ የእሽግ እርምጃውን በወሰደበት ወቅት ሁሉም ፋብሪካዎች በስራ ላይ እንደነበሩ የገለፁት ኃላፊዎቹ በኬሚካል ተዘፍዝፈው የነበሩና በሰዓታት ልዩነት ከኬሚካል ውስጥ መውጣት የነበረባቸው ምርቶች እዛው ባሉበት በመታሸጋቸው በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ኪሳራ መድረሱንና ይህም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቆዳ ሀብት ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት አቶ ብርሃኑ ሲርጊተን ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ ፋብሪካዎቹ ከአራት አመታት በፊት ከባለስልጣን መ/ቤቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው እንደነበር አስታውሰው፤ በዚሁ መሰረትም ከፍተኛ የማሻሻያ እርምጃዎችን ሲወስዱ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢንስቲቲዩቱም የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ፋብሪካዎች ጉዳት እንዳያደርሱ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልና የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትል የአመራረት ሂደት የሚከተሉ ፋብሪካዎች ወደ ትክክለኛ የአመራረት ስርዓት እንዲገቡ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ፋብሪካዎቹን ያሸገው የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለአመታት ታግሶ የመቆየቱን ያህል አሁን የእሸጋ እርምጃውን በሚወስድበት ጊዜ ትንሽ በምርት ሂደት ላይ ያሉ ቆዳዎች እንዲወጡ ወይም እንዳይነከሩ ትንሽ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥ ኖሮ የሚባክነውን የሀገር ሀብት ለማስቀረት ይቻል ነበር ብለዋል፡፡
የእሽግ እርምጃ በተወሰደባቸው ፋብሪካዎች ውስጥ ከ2 ሺ በላይ ጊዜያዊና ቋሚ ሰራተኞች ይሰሩ እንደነበር ለማወቅ ተችላል፡፡

Read 2645 times Last modified on Saturday, 04 November 2017 13:33