Sunday, 05 November 2017 00:00

የጅማው ሥራ ፈጣሪ - “ጨክኖ ከተሰራ ሀብት ይገኛል” “ትልቁ ምኞቴ በሕይወቴ እያለሁ ጅማ ተለውጣ ማየት ነው”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

በጅማ በቅርቡ አገልግሎት የጀመረው “ዶሎሎ ሆቴል” በከተማዋ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ካሟሉ ጥቂት ሆቴሎች አንዱ ነው፡፡ ዶሎሎ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም አነስተኛ ጅረት ማለት ነው፡፡ ሰዎች እየሄዱ የሚዝናኑበትና ልጆች የሚዋኙበት፣ ለጅማ ከተማ ቅርብ የሆነች ወንዝ ናት - ዶሎሎ፡፡  
ዶሎሎ ሆቴል፤ 71 የተለያየ ደረጃ ያላቸው የመኝታ ክፍሎች አሉት፣ ክፍሎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ ሲሆን የየራሳቸው ካዝና፣ ቴሌቪዥን፣ ፍሪጅ፣ ስልክ፣ አላርም ሲስተም፣ አየር ማቀዝቀዣ፣ ሙቅና ቀዝቃዛ ሻወር፣…የተሟላላቸው ናቸው፡፡  
ምንም ሳይኖራቸው ለፍተው ሀብት ላፈሩባት ከተማ ቋሚና ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነገር ሠርቼ ማለፍ አለብኝ በማለት፣ ሆቴሉን የገነቡት፣ አቶ ፀሀይ አበበ የተባሉ ሥራ ፈጣሪ ባለሀብት ናቸው። ባለሀብቱ ግሩም ሆቴል ገንብተዋል፡፡ ሆቴሉ በአሁኑ ወቅት ለ150 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ የሠራተኞቹም ቁጥር እንደሚጨምር፣ የአቶ ፀሐይ አበበ ድርጅትና የዶሎሎ ሆቴል ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው የባለሀብቱ ልጅ የንጋት ፀሐይ ገልጿል፡፡
የንጋት ፀሐይ እንዲህ ያለ ሆቴል ለመሥራት ምን እንዳነሳሳቸው ሲናገር፤ “በጅማ ከተማ እምብዛም ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል አይገኝም፤ ከተማዋ፣ ወደ አጋሮ፣ ቦንጋ፣ ሚዛን፣ መቱ፣ ቴፒ… የሚንቀሳቀሱ ኢንቨስተሮችና ነጋዴዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን…. ማረፊያ ብትሆንም እንግዶቹ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴል እጦት ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ሌላውና ዋናው ነጥብ፣ አባቴ ሠርቶ ገንዘብ ላፈራባት ጅማ ከተማ ቋሚ ነገር ሠርቶ የማለፍ ፍላጎቱ ነው፤ ብሏል፡፡
አቶ ፀሐይ አበበ የተወለዱት በወለጋ ክፍለ ሀገር በቀድሞው አጠራር፣ በነቀምት አውራጃ ጉዳያ ጅሬ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ወደ ጅማ ከተማ የመጡት በ1964 ዓ.ም ነበር፡፡ በአጋሮ መስመር ማና በተባለ ወረዳ ሀሮ የምትባል ቀበሌ ትገኛለች፡፡ በዚያች ቀበሌ ገበሬ ማኅበር መኖር ጀመሩ፡፡ አቶ ፀሐይ፣ በዚያን ጊዜ ቤሳቤስቲን አልነበራቸውም፡፡
ያኔ የጅማ ሕዝብ፣ ለቡና ቁርስ ዳቦ ካልሆነ በስተቀር ጥራጥሬ አያቀርብም ነበር፡፡ ይህን የሕዝቡን ፍላጎት የተረዱት አቶ ፀሐይ፤ ከወንዝ ዳር በእፍኝ የለቀሙትን ቡና አድርቀው አንድም ሆነ ሁለት ኪሎ ሲሆን ከተማ ወስደው በመሸጥ በምትኩ ዳቦ ገዝተው ይመለሳሉ፡፡ ዳቦውን ደግሞ በቡና ይለውጣሉ እንጂ በገንዘብ አይሸጡም። እንዲህ እያደረጉ ሲሰሩ ጥሪት ቋጠሩ፤ ካፒታል አፈሩ፡፡
በ1968 ገበሬ ማኅበሩን ለቀው ሀሮ ከተማ ገቡ። እዚያ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት ሺህ ብር ካፒታል የቡና ንግድ ፈቃድ ያወጡት፡፡ የሚገዙትን ቡና የሚያደርቁት፣ በጆንያ (ኬሻ) የሚሞሉት፣ ተሸክመው መኪና ላይ የሚጭኑት፣ ጅማ ከተማ ወስደው የሚሸጡት፣… በአጠቃላይ ሁሉንም ሥራ የሚሰሩት ራሳቸው ነበሩ፡፡ በዚህ ሂደት መጠነኛም ቢሆን ትርፍ እያገኙ መጡ፡፡ በዚያን ጊዜ ነጋዴ ቢሆኑም ወጣት ስለነበሩ፣ በወቅቱ በመላ አገሪቱ ወጣቱን ምርኮኛ አድርጎ ከነበረው ኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ) ሰለባ ከመሆን አላመለጡም፡፡ በየጊዜው መታሰር፣ መገረፍ፣ መለቀቅ እንደገና መታሰር፣ መገረፍ፣… ሆነ ሥራቸው፡፡ ሦስትና አራት ጊዜ ሲታሰሩ፣ ኑሮአቸው ተናጋና ተበላሸ፡፡ በዚህ የተነሳ የቡና ንግዱንም ተውት፡፡ ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ መታሰሩ ቀርቶ ሁኔታዎች ተሻሻሉና ወደ ቀድሞ ሥራቸው የቡና ንግድ ተመለሱ፡፡ 7 ሺህ ብር እንዳፈሩ ሀሮን ለቅቀው፣ ከጅማ ከተማ 20 ኪ.ሜ ወደምትርቀው የቡ ከተማ ገቡ፡፡
ሥራቸውን ማስፋፋት ፈለጉና የቡ ከተማ ውስጥ 7 መኝታ ክፍሎች ያሉት ከጭቃ የተሠራ ሆቴል ገዙ። ሆቴሉን ከረዳቶቻቸው ጋር እየሠሩ፣ በተጓዳኝ የቡናና እህል ንግድ ማካሄድ ቀጠሉ፡፡ መቼም አቶ ፀሐይ እስር አያጣቸውም ማለት ይቻላል፡፡ በ1975 ዓ.ም ለ8 ወር ታሰሩ፡፡ መስመር ይዞ የነበረው ንግድ እንደገና ተበላሸ፡፡ የቡ አልተመቻቸውም፡፡ ያንን ቤት በ20 ሺህ ብር ሸጠው፣ በ1977 ዓ.ም ጅማ ከተማ ገቡ፡፡
ያኔ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረው ድርቅ ተፅዕኖው ያልደረሰበት ሥፍራ አልነበረም። ሥራ ስላልነበራቸው ጅማ ለኑሮ ምቹ አልሆን አለች፡፡ በዚህ ላይ ቤተሰብ ስለመሠረቱ ማስተዳደር ነበረባቸው፡፡ ገንዘብ ሲጨምሩበት እንጂ ሲያነሱለት ስር የለውም፡፡ እሳቸውም ሰርተው ሳይጨምሩበት ከላይ ላዩ ሲቀንሱ ተመናምና 10 ሺህ ብር ገደማ ቀራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ባነኑ፡፡ “ቤተሰቦቼን ምን ላበላ ነው?” በማለት በ10 ሺህ ብር አራት ሰው የምታሳፍር ድሮ ሚኒቸንኬ፤ አሁን ላዳ የምትባል ታክሲ ገዙ፡፡
በላዳዋ ታክሲ እየሠሩ፣ የሆቴል ሥራ ከአእምሮአቸው አልጠፋም ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ደግሞ ከፍተኛ 3 ቀበሌ 5 የአንድ ንግድ ቤት ጨረታ ወጣ፡፡ በጨረታው ተሳትፈው አሸነፉና ቤቱን ተከራይተው ምግብ ቤት ከፈቱ፡፡ ራሳቸው ጥሩ ወጥ ቤት፣ ጥሩ አስተናጋጅ… ሆነው ይሰሩ ስለነበር ምግብ ቤቷ ጥሩ ገበያ ያላትና ታዋቂ  ሆነች፡፡ ምግብ ቤቷ “መንደራ” ትባል ነበር፡፡  የአራዳ ልጆች “መንደራ”ን “የገጠሪቱ መናፈሻ” ይሏት ነበር፡፡
ምግብ ቤቷ ታዋቂ ሆና ጥሩ እየሠሩ ሳለ፣ ቀበሌው በራሱ ምክንያት ከቤቱ አስወጣቸው። አሁን ሥራቸውን ከቡና ንግድ ወደ ሆቴል አገልግሎት እየለወጡት ይመስላል፡፡ ቀበሌው ከቤቱ እንዳስወጣቸው መንዲና የተባለ አካባቢ “ሄርማታ” የተባለ ሆቴል ተኮናትረው መሥራት ጀመሩ፡፡ አካባቢው ለገበያ ስለማያመች የዚህ ሆቴል ሥራ አላመቻቸውም፡፡ ስለዚህ ከዚያ ለቀው ሌላ ቤት ተከራይተው “አራዳ ሆቴል”ን ከፈቱ፡፡ ይኼኔ ኢሕአዴግ ገባ፡፡ በዚህ ዓይነት እየሠሩ ቆይተውና ገንዘብ አጠረቃቅመው፣ በ1989 ዓ.ም በጅማ ከተማ ታዋቂ የሆነ “ሙሉ ሱፐር ማርኬት” ከፈቱ። የገበያ ማዕከሉ ብዙ ዕቃዎች የሚያቀርብ በመሆኑ ዘመናዊ በሆኑ ሰዎችና በውጭ አገር ዜጎች ተፈላጊና ተመራጭ ነበር፡፡  
በሱፐር ማርኬቱ እየሰሩ ቆይተው ዕድገት መጣ፡፡ የሆቴል ሥራ በውስጣቸው ሰርፆ የለ! በዚህ ጊዜ አሁን ዶሎሎን በሰሩበት ቦታ ላይ 25 የመኝታ ክፍሎች ያሉት “ተፍኪ” ፔንሲዮንን ሰሩ። ሱፐር ማርኬቱና ፔንሲዮኑ እየሰሩና ገቢ እያስገኙ ቢሆንም፣ ቤቱን በመስራታቸው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እየደከመ መጣ፡፡ ሱፐርማርኬቱ የሚጠይቀው ካፒታል ብዙ በመሆኑ መቀጠል አልቻሉም፣ ተዉት፡፡ ባለሀብቱ አንድ ሥራ ላይ ችክ ብለው መቆየት አይወዱም፡፡ አንዱ ደከም ሲል ሌላ ይጀምራሉ፡፡ ሱፐር ማርኬቱን ትተው ፔንሲዮኑን አጠናክረው እየሰሩ ሳለ፣ ፊታቸውን ወደ ሌላ የንግድ ዘርፍ አዞሩ - ወደ መጠጥ ማከፋፈል። ቀደም ሲል በጅማ ከተማ መጠጥ አከፋፋይ ድርጅት አልነበረም፡፡
ከቢጂአይ ኢትዮጵያ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ) ከአምቦ ውሃ፣ ከለስላሳ መጠጥ ፋብሪካዎች ውክልና ወስደው ምርቶቻቸው እየተቀበሉ በአንድ ቮልስዋገን መኪና ማከፋፈል ጀመሩ፡፡ በዚያች መኪና እየሰሩ አንድ አይሱዙ፣ ሁለት፣ ሦስት … እያሉ አሁን የብዙ መኪኖች ባለቤት ሆነዋል፡፡ የመጠጥ ማከፋፈሉን ሥራ ከባንክ ጋር በመገናኘት በስፋት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡  
ሥራ ፈጣሪውን አቶ ፀሐይ አበበን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሆቴል ለመስራት ምን አነሳሳቸው? በአካባቢው ትልልቅ ሆቴሎች ሲሰሩ፣ ‹ተፍኪ ፔንሲዮን› እያነሰች መጣች፡፡ ስለዚህ ትልቅ ሆቴል ለመገንባት ተነሳሱ፡፡ “ትልቅ ሆቴል ከሰራን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ መሆን አለበት በማለት አቅደን፣ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ደሎሎ ሆቴልን ሰራን፡፡ ይህንኑ ያህል ገንዘብ የሚፈጅ ማስፋፊያም ይሰራል፡፡ በ2010 አጋማሽ ማስፋፊያውን ለመጀመር አቅደናል፡፡” ብለዋል - አቶ ፀሐይ፡፡
የወደፊት እቅዳቸውን ሲናገሩ፣ “አሁን ልጆቼም አድገውልኛል፡፡ ሆቴሉን በሥራ አስኪያጅነት የሚመራው የንጋት ፀሐይ የተባለው ልጄ ነው። ከቤተሰቦቼ ጋር አንድ ፒኤልሲ (ድርጅት) አቋቁመናል፡፡ እሱም በራሱ መንገድ እየሰራ ነው። አሁን ቤተሰቦቼም ስለሚረዱኝ፣ አቅማችንም ጥሩ ስለሆነ ወደ ኢንዱስትሪውም ለመግባት ሐሳብ አለን” ይላሉ፡፡
አቶ ፀሐይ አበበ ሥራ መፍጠርና መስራት ብቻም ሳይሆን ቁጠባም ይችሉበታል፡፡ “ሥራ ስጀምር አንድ ዳቦ 3 ቦታ ከፍዬ ነበር የምበላው፤ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት፡፡ ለሻይ 5 ሳንቲም ላለማውጣት ዳቦውን በውሃ ነበር የምበላው፡፡ 44 ዓመት ስሰራ በጣም ብዙ ችግሮች አሳልፌአለሁ፡፡ ጨክኖ ከተሰራ ደግሞ ሀብት ይገኛል፡፡ አሁን የነገርኩህ ጥቂቱንና ዋና ዋናውን ነው” በማለት ብዙ ያልተነገረ ታሪክ እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ “ጅማ አልሰራንባትም እንጂ ጥሩ ከተማ ናት፤ለሰራባት በእጥፍ ነው የድካሙን ዋጋ የምትከፍለው፡፡ እኛ ነጋዴዎችም የግል ጥቅማችንን ስናሳድድ ለከተማዋ ማደግና መለወጥ አልሰራንም። ከተማዋን የመለወጥ ኃላፊነት የሁሉም ነው፡፡ መንግሥት አስተዳደሩ፣ ማዘጋጃ ቤቱ፣ ነጋዴው፣ … ሁሉም ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ እኔ 44 ዓመት ብደክምም ምንም የሰራሁ አልመሰለኝም፡፡ አሁንም እሰራለሁ፡፡ ትልቁ ምኞቴ በሕይወቴ እያለሁ ጅማ ተለውጣ ማየት ነው” ብለዋል፡፡  

Read 3055 times