Print this page
Saturday, 28 October 2017 09:57

የራሱን ልጅ አስከሬን አዝሎ፣ የታመመውን የሹም ልጅ ለመጠየቅ ይሄዳል

Written by 
Rate this item
(22 votes)

(በር ነኣ አሃ በእድ በጎዳ ነኣ ሀርግያጋ ቤአነ ቤስ)
- የወላይትኛ ምሳሌያዊ ንግግር

  በጥንት ጊዜ በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን፣ በአሜሪካው ፕሬዚዳንትና በራሺያው ፕሬዚዳንት ላይ የተቀለደ አንድ ተረት ቢጤ ዕውነት ነበር፡፡ እነሆ፡-
የሁለቱ አገሮች ፕሬዚዳንቶች፤ ወታደራዊ ኃይላቸውን ያወዳድራሉ፡፡ የእኔ ይበልጥ፣ የእኔ ይበልጥ፣ ይፎካከራሉ። በመጀመሪያ የሩሲያው ፕሬዚዳንት፣ አሜሪካንንና የአሜሪካን ወታደራዊ ኃይል ሊጎበኙ ይሄዳሉ! ከዚያም አንድ ጉዳይ ያነሳሉ፡፡
“የአንድ አገር ወታደራዊ ኃይል የሚለካው፤ ወታደሩ ለፕሬዚዳንቱ ባለው ታዛዥነት መጠን ነው!”
“እርግጥ ነው!” አሉ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት፡፡
“በል እንግዲያው ወታደሮችህ ምን ያህል ለአንተ ታማኝ እንደሆኑ አሳየኝ?”
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ይዘው፣ ወደ ወታደሮቻቸው ይሄዱና አንዱን ወታደር ጠርተው፤ ወደ አንድ ገደል አፋፍ ይወስዱትና፤
“በል ወደዚህ አዘቅት ገደል ተወርወር” ይሉታል፡፡
ወታደሩም፤
“አይ አላደርገውም” ይላል፡፡
“ለምን?” ይሉታል፡፡
“ጌታዬ፤ በእኔ ደሞዝ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች” አሉኝ፤ (I have a family to support!) ይላል፡፡ የሩሲያው ፕሬዚዳንት በአሜሪካኑ ወታደር ታዛዥ አለመሆን እየሳቁ፤
“ቆይ የእኔን ወታደር ታማኝነት አሳይሃለሁ!” ይሉና የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ወደ ሩሲያ ይዘውት ይሄዳሉ፡፡ ከዚያም አንዱን ወታደር ጠርተው፤
“ወደዚህ አዘቅት ገደል ተወርወር!” ይሉታል፡፡
ወታደሩም፤
“ታዛዥ ነኝ ጌታዬ!” ብሎ ወደ ገደሉ ይወረወራል፡፡
እንዳጋጣሚ ግን አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ያርፍና ከሞት ይተርፋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወደሳቸው እንዲመጣና ጥያቄ እንዲያቀርቡለት ይጠይቃሉ፡፡
ወታደሩ ተጠርቶ መጣ!
የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም፤
“የእኔ ወታደር ወደ ገደል ተወርወር” ብለው፣ ‹የማስተዳድረው ቤተሰብ አለኝ› አለ፡፡ አንተስ እንዴት ልትወረወር ቻልክ?” አሉና ጠየቁት፡፡
ወታደሩም፤
“I too, have a family to support (እኔም የማስተዳድረው ቤተሰብ ስላለኝ ነው)” አለ፡፡
“እንዴት?” ቢሉት፤
“እኔ አልወረወርም ብል፤ እኔንም ቤተሰቤንም ነው የሚፈጁን!” ሲል መለሰ!
*       *      *
የአንድ ሰው ጥፋት ለቤተሰብና ለዘመድ አዝማድ ከሚተርፍበት ስርዓት ይሰውረን፡፡ ባለፈው ዘመን የመናገር ነፃነት ባልነበረበት ሁኔታ ውስጥ “አፍ-እላፊ” የሚባል ወንጀል ነበር - የአፍ ወለምታ! “ክብረ ነክ ንግግር” ነበር የሚባለው- ከወታደሩ ዘመን በቀደመው የንጉሱ ዘመን! አፍ - እላፊ ባለስልጣንን፣ መሪን፣ ሥርዓትን፣ አስተዳደርን ከመተቸት እስከ አገርን ማንቋሸሽ ድረስ የሚሰፋ ወንጀልን ያካትት ነበር፡፡ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው አነጋገርም ያስቀጣ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- “ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ሀቀኛ ኮሚኒስት ናቸው!” እያለ ቀኑን ሙሉ ይለፈልፍ የነበረ ንክ ሰው፣ ታስሮ ነበር! ወንጀሉ፤ “ማንም የሚያውቀውን ሀቅ እየደጋገምክ የምታናገረው ነገር ቢኖርህ ነው!” ተብሎ ነው! “አለፈልሽ ባሮ!” እያለም የባሮን ወንዝ አስመልክቶ መፈክር ያሰማ ሰው፤ ሽሙጥ ነው ተብሎ የታሰረበት አጋጣሚም ነበር!
ዋናው ጉዳይ ሰው ሲታፈን፤ መናገሪያ፣ መተንፈሻ…፣ ዘዴ መሻቱ አይቀሬ ነው የሚለው ዕውነታ ነው! ያሰበ ጭምር ይቀጣል በሚባልበት ሥርዓት የተናገረ፤ መወንጀሉና መቀጣቱ አይገርምም! ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲያዊ መብት በማይከበሩበት አገር ምሬቶች ይጠራቀማሉ፡፡ መውጫ ቀዳዳ ይፈልጋሉና ሥርዓት ወዳለው አመፅ አሊያም ወደ ሥርዓተ - አልበኝነት ሊያድጉ ይችላሉ፡፡ የገዢዎችን የመግዛት አቅም ይፈታተናሉ፡፡ ምላሽ የሌላቸው ጥያቄዎች ይበዛሉ!! ዓለም የጋዝ ታንክ ለመሙላት ሲሯሯጥ፣ ደሀ አገሮች ሆዳቸውን ለመሙላት ይፍረመረማሉ፡፡ “የምግብ ፍላጎት አለመሟላት ከነፃነት ረሀብ ጋር ከተዳመረ፤ የህዝቦች ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል” ይባላል፡፡ የኢኮኖሚ ህመምና የፖለቲካ ህመም ከተደራረቡ፣ ከማስታገሻ ያለፈ በሽታን ይፈጠራሉ! ፍትሕ-አልባ ሁኔታን ይቀፈቅፋሉ፡፡ ሌብነት እንደ ሥራ ይቆጠራል፡፡ አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር ግን፤ ሰላም -አልባ ሁኔታ ውስጥ ከገባን የሰረቅነውን የምንበላበት ጊዜም ይጠፋል! ያደለብነው ኪስ ያፈሳል! የገነባነው ቪላ ይፈርሳል! ለሌሎች የቆፈርነው ጉድጓድ፣ የእኛው መቀበሪያ ይሆናል! በድሮ ጊዜ አንድ ባለስልጣን እሥር ቤት ሲጎበኙ፣ እስር ቤቱን የማስፋፋት ሰፊ እቅድ መያዙን አስተዳዳሪው ያስረዷቸዋል፡፡ ባለስልጣኑም፤ “ጥሩ ሀሳብ ነው፡፡ በደምብ ገንቡና አስፋፉት፡፡ ዞሮ ዞሮ የእኛም የወደፊት ቤታችን ነው!” አሉ ይባላል፡፡ ያሉት አልቀረም - ገቡበት! ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፤ በአንድ ተውኔቱ ውስጥ ንጉሡ እሥር ቤት መርቀው ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፤ “የአባታችን እርስተ - ጉልት የሆነውን ይህንን የሀገር ወህኒ ቤት መርቀን ስንከፍትላችሁ፤ በተለመደው ባህላችሁ እንድትተሳሰሩበት ነው” ይለናል፡፡    
ዛሬ፤ ከፊውዶ-ቡርዥዋው ስርዓት ወደ ሶሻሊዝም፤ ከዚያም ወደ ካፒታሊዝም አድገናል እያልን፤ የግሎባላይዜሽን ቅርቃር ውስጥ የገባን ይመስላል፡፡ በጥናት ያልተደገፈ ሥርዓት፣ መላ-አጥ መንገድ ላይ በትኖናል ቢባል ማጋነን አይሆንም!
ከነስማቸው እማማ ጦቢያ፤ የሚባሉ የዱሮ ሴት ወይዘሮ ነበሩ አሉ- ደርባባና ጨዋ!
“ከዚህ ከባሪያ የገላገልከኝ ለታ፣ ወዲያውኑ ብትገድለኝ ግዴለኝም” ይሉ ነበረ ሲፀልዩ፡፡
ባሪያ ያሉት ሄደና ሌላ መንግሥት መጣ!
ይሄኛውንም ማማረር ቀጠሉ፡፡
“ምነው እማማ፤ ከዚህ ከባሪያ ገላግለኝ ሲሉ ነበረ፡፡ ገላገለዎት፡፡ አሁን ደግሞ ምን ሆኑና ያማርራሉ?” ቢባሉ፤
“አሃ! ያኛውኮ ከፋም ለማም የጨዋ ባሪያ ነው! ይሄኛውኮ የረባ ጌታ እንኳ የለውም! ጌታውን ቢያውቅ የማንም መጫወቻ አያደርገንም ነበር!” አሉ ይባላል፡፡
አይ እማማ ጦቢያ፡፡ አሜሪካንን አላወቁ! እንግሊዝን አላወቁ! የረባ ጌታ ማን እንደሆነ አላወቁም! ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም መሸጋገር፣ የጌታ አማራጭ የማግኘት ጉዳይ ብቻ ቢሆን እንዴት በታደልን ነበር! ጌቶቻችንን በቅጡ አለማወቅ፣ የነገ ዕቅዳችንን በግልፅ እንዳናይ እንዳደረገን ይኖራል! ከዚህ ያውጣን!!
ለችግሮቻችን ምላሽ ፍለጋ ወደ ሹሞቻችን ማንጋጠጥ፣ ዘላቂና ሁነኛ መፍትሔ አያመጣም! ችግሮቹ የራሳችን የመሆናቸውን ያህል መፍትሔም ከእኛ መፍለቅ ይኖርበታል፡፡ በዲሞክራሲያዊና በፍትሐዊ መንገድ ያላፈራናቸው አለቆች፤ መልካም አስተዳደርን ያጎናፅፉናል ብለን ማሰብ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ነው፡፡ ለዕለት ኑሯችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንኳ ሸምተን ማደር እያቃተን፤ ነው፡፡ ያም ሆኖ ስለ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አሀዞች ማውራት አልገደደንም፡፡ አለቆቻችን መፍትሔ-ሰጪ አካላት መሆን ካቃታቸው መሰንበታቸውን እያወቅን፣ ሁነኛ ምላሽ ካልሰጣችሁን እያልን እነሱን ደጅ እንጠናለን፡፡ እንደ ሲቪልም፣ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲም ዕሳቤያችን ያው ነው! አሌ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የቤት-ጣጣ እያለብን፤ ነቅተን፣ በቅተን፣ ተደራጅተን፣ በአንድነት ፈጥረን የበሰለ መፍትሔ ከውስጣችን ማግኘትን ትተን፣ የሌላ ደጃፍ እናንኳኳለን! የወላይታው ምሳሌያዊ አነጋገር ግንዛቤ የሚሰጠን እዚህ ላይ ነው፡- “የራሱን ልጅ አስከሬን አዝሎ፣ የታመመውን የሹም ልጅ ለመጠየቅ ይሄዳል!” ይለናል፡፡ ሹሞቹ ጤና መስለውት ነው!

Read 12423 times
Administrator

Latest from Administrator