Print this page
Saturday, 14 April 2012 11:12

የፋሲካ ገበያ ተቀዛቅዟል

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(1 Vote)

የሸቀጦች ዋጋ መናር የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል ገበያ በእጅጉ አቀዝቅዞታል፡፡ የገበያው ዋጋ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ያሰቡትን ሳይሸምቱ ከገበያ የሚመለሱ ሸማቾች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ የበዓል ገበያውን ለመቃኘትና ሻጭና ሸማቹን ለማነጋገር ሰሞኑን በተለያዩ የገበያ ስፍራዎች ተዘዋውረናል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ሸማቾች የሚያነሱት ጉዳይ የዋጋውን መናርና ፈፅሞ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ነው፡፡ወ/ሮ የሺ በላቸው ለዘንድሮው የትንሣኤ በዓል ገበያ የመረጡት ቀን ረቡዕን ነበር፡፡ በአንድ የመንግሥት የልማት ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ሠራተኝነት ተቀጥረው 870 ብር ወርሃዊ ደመወዝ የሚከፈላቸው ባለቤታቸው ደመወዛቸውን ዘግይተው በማግኘታቸው ለበዓል ገበያው ቀደም ብለው መውጣት አልቻሉም፡፡ ከወር አስቤዛ ተርፎ ለበዓል ገበያ የሚውል በቂ ገንዘብ ስለሌላቸው ተጨንቀዋል፡፡

ምኑን ከምኑ አብቃቅተው ባለቤታቸውንና ሁለት ልጆቻቸውን አስደስተውና ቤታቸውን በዓል በዓል አሽትተው እንደሚያሳልፉት ግራ ገብቷቸዋል፡፡ የዶሮው ዋጋ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቦት በግ ሊገዛ የሚችል ገንዘብ ላይ ደርሶ፣ የቅቤው ዋጋ አልቀመስ ብሎ አስጨንቋቸዋል፡፡ ከመርካቶው ገበያ የደረሱት 4 ሰዓት ላይ ቢሆንም ምሳ ሰዓትም አልፎ እንኳ ከገበያው አልወጡም፡፡

ከቅቤ ተራ ሽንኩርት ተራ፣ ከቅመም ተራ ዘይት ተራ ሲሉ ቆይተው ዶሮ ተራ ደርሰዋል፡፡ ከዶሮ ነጋዴው ጋር በዋጋ ቀንስ አልቀንስም ሲነታረኩ ተጠጋሁና ጠየኳቸው፡- “ገበያ እንዴት ነው እማማ?” በእጃቸው ይዘው ክብደቱን ለማወቅ የሚመዝኑትን ዶሮ እንደያዙ ቀና ብለው አዩኝና “እንደምታይው ነዋ! የእናንተ ዘመን የተረገመ ዘመን ነው፡፡ በአስራ አምስትና ሃያ ብር እንገዛው የነበረውን ዶሮ ይኸው 180 ብር አደርሳችሁት ምኑ ከምኑ ይደረጋል? ቅቤው 160 እና 180 ይባላል፤ የጤፉ ዋጋ ሰማይ ደርሷል፤ እንኳንስ ከወር አስቤዛ ተርፎ ዶሮና ቅቤ የሚገዛበት የእለት ሆድ የሚሸፈንበት ገንዘብ ጠፍቷል፡፡ ምን ሁኑ እንደሚሉን አልገባኝም፡፡ እግዜሩም ጨከነ ምነው አሁንስ አመት በዓሉም ባይመጣ” ብሶታቸው ከምር ነው፡፡ ከባለቤታቸው የወር ደመወዝ ገበያ ይዘው የወጡት 300 ብሩን ቢሆንም ያሰቡትን መግዛት ተስኖአቸው ግራ ተጋብተዋል፡፡ በስቅለት በዓል እለት የተለመደውን የጉልባን እህል ለመግዛት ገበያ ገብተው፣ አንዱን ኪሎ የባቄላ ክክና ስንዴ 26 ብር ተብለው ደንግጠው መውጣታቸውን ነግረውኛል፡፡ ለሽንኩርት ገበያ የሄዱበት የፒያሳው አትክልት ተራም እንዲሁ ኪሎውን የፈረንጅ ቀይ ሽንኩርት 10 ብር፣ የአበሻውን 15 ብር ብሎ አስበርግጐ አባሯቸዋል፡፡ ከመደብ ላይ የገዙትን የ30 ብር ሽንኩርት እንዳያት ከዘንቢላቸው ውስጥ ከነፌስታሏ ብቅ አደረጓት፡፡ የወጥ ቅመምና የቅቤ ማንጠሪያ ነጭ ሽንኩርት የቅንጦት እቃ እንደሆኖባቸው ነገሩኝ፡፡ ግማሿን ኪሎ መሀከለኛ ቅቤ በ75 ብር ገዝተው ይዘዋል፡፡ ከቤታቸው ሲወጡ አንጠልጥለው የወጡት ትልቅ ዘንቢል ግን ውስጡ ምንም የለም፡፡ የዛሬን አያድርገውና በመቶ ብር ይሞላ ነበር የሚሉትን ዘንቢላቸውን እንዳንጠለጠሉ በመርካቶ ገበያ ግራ ተጋብተው ይንከወከዋሉ፡፡ የዶሮ ነጋዴው ግን ብሶታቸውን ከእኔ እኩል የሚሰማበት ጊዜውም ጆሮውም ያለው አይመስልም፡፡ ከግራ ከቀኝ “ባለ ዶሮ” እያሉ የሚጠሩትን ሸማቾች ያስተናግዳል፡፡ የዶሮ ዋጋውን ሲሰሙ ደንገጠው የሚሄዱትን ያህል ባይሆኑም ጥቂት ተከራክረውና ትንሽ አስቀንሰው ብዙ ባውንዶችን ከፍለው የገዙትን ዶሮ እያንጠለጠሉ ከገበያው ውልቅ የሚሉም ሸማቾች አሉ፡፡ ከሚጋፋው ጋር እየተጋፋሁ ዶሮ ተራን ለቅቄ ሽቅብ ወደ ቅቤ ተራ አመራሁ፡፡ መርካቶ የድሮ ቅርጿና ድባብዋ ጠፍቷል፡፡ እነቅቤ ተራ፣ እነሳጥን ተራ፣ እነዱባይ ተራ፣ እነሚሊቴሪ ተራ ሁሉ ትዝታ ሆነው ቀርተዋል፡፡

ከተሰሩት ፎቆች ሌላ ሌሎች አዳዲሶቹም ጅምር ላይ ናቸው፡፡ ከጅምር ፎቆቹ ስር ስር ገበያው ደርቷል፡፡ ቅቤ ተራ ገባሁ፡፡ እነሠኒ ቅቤ ቤት፣ ቀቡል ቅቤ መሸጫ፣ ውባለም ቅቤ ቤት ወዘተ ክምር ቅቤአቸውን ለሸማቹ እያሳዩ መደዳውን ተደርድረዋል፡፡ የቅቤ ቤቶቹ የቅቤ ዋጋ በአስገራሚ ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም አንዱን ኪሎ የሸኖ ቅቤ በ180 ብር፣ መሀከለኛውን በ160 ብር ለሽያጭ አቅርበዋል፡፡ ሸማቹ አቅሙ ስላልቻለ በአብዛኛው ግማሽ ኪሎ ቅቤ ሲገዛ ይታያል፡፡ አይብ ኪሎው ከ45 ብር እስከ 50 ብር፣ አንድ ፍሬ እንቁላል ከ2.10 እስከ 2.25 ሣንቲም ሲሸጡም ነበር፡፡

በሾላ ገበያም የፋሲካ ሸመታ ቀዝቀዝ ብሏል - እንደሌላው ጊዜ ግርግር የለም፡፡ የዶሮ፣ የቅቤ … ዋጋ ተሰቅሏል፡፡ ቅቤ ሸኖ ለጋ 180 ብር መካከኛ የጐጃም 160፣ የበሰለ የወለጋ 150 ብር ይሸጣል፡፡ የሁሉም ነጋዴ ዋጋ ተመሳሳይ ነው፡፡

ሁለት ቀን ሾላ ገበያ ቅቤ ተራ ሄጄ ነበር፡፡ ታዲያ አንድም ሰው ቅቤ ሲገዛ አላየሁም፡፡ ወ/ሮ ዘነበችና ወ/ሮ አስካለ የቅቤ፣ ቆጮና መሰል ዕቃዎች ነጋዴ ናቸው፡፡ የዓመት በዓል ገበያ እንዴት ነው? አልኳቸው፡፡ “ይኼው እንደምታየው ነው፤ ቀዝቅዟል፤ ሥራ የለም፡፡ የዕቃው መወደድ ይመስለናል” አሉ፡፡

የወ/ሮ ግርሙት አስተያየትም ተመሳሳይ ነው፡፡ “አይ! ይኼው እንደምታየው ነው - ገበያ የለም፡፡ እግዜር የተሻለ ነገር እንዲያመጣ እንፀልያለን፡፡ ሰዉም ከየት ያምጣ? ኑሮ በጣም ተወደደ” አሉ፡፡ የተለየ አስተያየት የሰጠችው መሠረት አህመድ ብቻ ናት፡፡ “ገበያው በጣም ጥሩ ነው፡፡ ነጋዴውም ገበያተኛውም መአት ነው የሚያወሩት፤ ያማርራሉ፡፡ ዕቃ እንደሆነ ሞልቷል፤ ከዚህ በላይ መንግሥት ምን ያድርግ? አየሩም ጥሩ ነው - ዘንቧል፡፡ ኑሮ ውድ ቢሆንም ሰው ተረጋግቶ እየገዛ ነው፡፡ ግርግር የሌለው ሰው ተምሮና ሠልጥኖ ከበዓሉ ቀን በፊት አስቀድሞ ስለገዛ ነው” ስትል ገልጻለች፡፡ አንድ ወፍጮ ቤት አንደኛ ደረጃ ማኛ ጤፍ 1,450 ብር፣ ነጭ ሠርገኛ 1,350፤ ሠርገኛ 1,150፣ መለስተኛ ሠርገኛ 1,100 ብር እየሸጠ ነው፡፡ በቆሎ 650፣ ገብስ፣ ስንዴ ማሽላ እያንዳንዳቸውን 1000 ብር፣ ዳጉሳ ደግሞ 900 ብር እየሸጠ ነው፡፡ አንድ እህል ቤት ደግሞ ማኛ ጤፍ 1,600 ብር ሲሸጥ ታዝበናል፡፡ ነጭ ሽንኩርት በኪሎ እንደየዓይነቱ 40፣ 45፣ 50 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ እንቁላል ከ2 እስከ 2.10፣ ኮረሪማ በኪሎ 80 ብር፣ ጥቁርና ነጭ አዝሙድ 60 ብር፣ ዝንጅብል ከ12 እስከ 14 ብር፤ ቲማቲም 15 ብር፣ ድንች 7.50፣ ካሮት 8 ብር፣ ቃሪያ 30 ብር፣ ሎሚ 20 ብር፣ ጥቅል ጐመን በኪሎ 4.50 ብር፣ ዘይት የሚቀዳ በሊትር 40 ብር፣ የታሸገ ሀቱን 57 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ አውራ ዶሮ ትንሽ ከ110 እስከ 120ብር፤ መካከለኛ ዶሮ ከ120 እስከ 140 ብር፣ ትልቅ ዶሮ ከ150 እስከ 180 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ሴት ዶሮ ከ90 ብር እስከ 110 ብር ትሸጣለች፡፡  ሙክብ በግ ከ3000 እስከ 3500፣ መካከለኛ 1800 እስከ 2000 ብር፣ ትንሽ ከ800 እስከ 1000 ብር ይሸጣል፡፡ የፍየል ዋጋም ተመሳሳይ መሆኑን በግ ተራ ያገኘነው ደላላ ተናግሯል፡፡ አንድ እህል ቤት በር ላይ ታስሮ የነበረ ሙክት ፍየል 4000 ብር ሲባል ሰምተናል፡፡ አንድ ሰው ፍየል እየጐተቱ ሲሄዱ ስንት ብር እንደገዙት ጠይቄያቸው፤ 1700 ብር ብለውኛል፡፡ በክልል ከተሞች ደግሞ በምሥራቅ ሸዋ ኤጄሬ ከተማ አንድ መካከለኛ ዶሮ 130 ብር፣ የአምስት ወር ጠቦት ደግሞ 800 ብር መሸጡን ሰምተናል፡፡ በይርጋጨፌ ከተማ አንድ ዶሮ 200 ብርና ከዚያም በላይ እንደሚጠራ፤ ቅቤ 170 ብር እንደሚሸጥ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

 

 

Read 18366 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:17