Print this page
Saturday, 14 April 2012 11:04

ታላቁ የኢትዮጵያ የሥነጥበብ ዋርካ ወደቀ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ የምንሰራው ሥራ የዛሬውን ህይወት ለነገው ትውልድ ማንፀባረቅና ለመጪው ዘመን መንገዱን መጥረግ አለበት የሚሉት ግንባር ቀደሙ የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ሊቅ   የነበሩት እጅግ የተከበሩት የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፤ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ባደረባቸው ህመም ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የቀብር ሥነስርዓት በዛሬው እለት ከቀኑ በ9 ሰዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እንደሚፈፀም የሥነስርዓቱ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡የኢትዮጵያ ዋርካ የነበረው አርቲስት በማለፉ አገር ልታዝን ይገባል ብሏል - ሰዓሊና የሥነቅርፅ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን፡፡ በዓለም ላይ በህይወት ዘመናቸው እውቅና የተሰጣቸው አርቲስቶች ጥቂት እንደሆኑ የጠቆመው ሰዓሊ በቀለ፤ አፈወርቅ ተክሌ ከእነዚያ ጥቂቶች አንዱ እንደነበሩ ይገልፃል፡፡ “ለሞያው ክብር ሲታገል የነበረ በመሆኑ ሊከበር ይገባል” ብሏል - በቀለ መኮንን፡፡

የቀድሞ የሰዓሊያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አብድርሃሚን ሸሪፍ በበኩላቸው፤ አፈወርቅ ለሥነጥበብ ሙያ ሙሉ ጊዜያቸውን የሰጡ ባለሙያ እንደነበሩ ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ የሥነጥበብ እድገት የእሳቸው ሚና የማይሻር ጉልህ ስፍራ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ “በዓለም ደረጃ ዘመናዊና ድንቅ ናቸው፤ የሥነጥበብ ሥራቸው ዘመን አይሽሬ ነው” ብለዋል - አቶ አብድርሃሚን፡፡

ጥበብ ሰዎችን ለማነቃቃትና አገራዊ ስሜትን ለማነሳሳት እንዲሁም ስለህይወት ብሩህ ተስፋ ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጥልቅ እምነት የነበራቸው የሥነ ጥበብ ሊቁ አፈወርቅ ተክሌ፤ በእያንዳንዱ የህይወት ድርና ማግ ውስጥ ጥበብ እንዳለ በአሜሪካ ለሚታተመው “ታዲያስ” መፅሄት ከአራት አመት በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ ጠቁመዋል፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 1925 ዓ.ም በሸዋ ክ/አገር ጥንታዊት በሆነችው የአንኮበር ከተማ ከወ/ሮ ፈለቀች ከተማወርቅና ከአቶ ተክሌ ማሞ የተወለዱት አፈወርቅ ተክሌ፤ የልጅነት ዘመናቸውን ያሳለፉት አገራቸው ከፋሺስት የጣልያን ሃይል ጋር ፍልሚያ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ነው፡፡ የጦርነትን አውዳሚነት አሳምረው የሚያውቁት አፈወርቅ ተክሌ፤ የትውልድ አገራቸውን መልሶ መገንባት እንደሚያስፈልግ የሚጠፋቸው ታዳጊ አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ያለሙት አፈወርቅ፤ ለዚህም ይጠቅመኛል ያሉትን የማዕድን መሃንዲስነት ትምህርት ለመከታተል በ15 ዓመት ዕድሜያቸው ወደ እንግሊዝ አገር ተላኩ፡፡

ከልጅነታቸው ጀምሮ የጋለ የሰዓሊነት ስሜት ያደረባቸው አፈወርቅ፤ በትምህርት ቤት ይሰጡ በነበሩት እንደ ኬምስትሪ፣ ሂሳብና ታሪክ በመሳሰሉ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት እንኳን ዘወትር በእርሳስም ሆነ በብዕር፣ ንድፎችንና ሥዕሎችን በመተለምና በመሳል ሥራ ተጠምደው ይታዩ እንደነበር ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለ ሰዓሊው ሥራዎች በፃፉት መጣጥፍ ላይ ጠቁመዋል፡፡

ወደ እንግሊዝ በመሄጃቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቤተመንግስት ተጠርተው የቀረቡት አፈወርቅ፤ ንጉሱ የለገሷቸውን ምክር ፈፅሞ አይረሱትም፡፡ “ጠንክራችሁ መስራት አለባችሁ፤ ስትመለሱ በአውሮፓ ስላያችኋቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ወይም ሰፋፊ መንገዶች እንድትነግሩን አንፈልግም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያን ዳግም ለመገንባት በሚያስፈልገው ክህሎትና አስተሳሰብ ራሳችሁን አስታጥቃችሁ መመለሳችሁን እርግጠኛ ሁኑ” ሲሉ እንዳሳሰቧቸው ለ”ታዲያስ” መፅሄት አውስተው ነበር፡፡

ይሄ ምክር አገራቸውን ከመገንባትና ህዝባቸውን ከማነሳሳት የሃላፊነት ተግባር ነፃ የሆነ ቀላል ህይወት በተፈታተናቸው ቁጥር፣ በአዕምሮአቸው ውስጥ ያንቃጭልባቸው እንደነበር አፈወርቅ ያስታውሳሉ፡፡

በእንግሊዝ ት/ቤት ከመጀመርያዎቹ አፍሪካውያን ተማሪዎች አንዱ የነበሩት አፈወርቅ፤ ቀድሞውኑም ስሜታቸውና ፍላጐታቸው ወደ ነበረው ሥነጥበብ እያዘነበሉ ሄዱ፤ ተሰጥኦዋቸውም እየጐላ መታየት ጀመረ፡፡ ከዚያም ለንደን ውስጥ የሚገኘው የሥነጥበብና የኪነጥበብ ማዕከላዊ ት/ቤት ተቀበላቸው፡፡ በተቋሙ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በዝነኛው የለንደኑ “ስሌድ” የስነጥበብ አካዳሚ የመጀመርያው አፍሪካዊ ተማሪ በመሆን ትምህርታቸውን ተከታትለው አጠናቀቁ፡፡ አፈወርቅ በ”ስሌድ” ኮሌጅ ሳሉ ትኩረታቸውን ያደረጉት ስዕል፣ ቅርፃ ቅርፅና ሥነ ህንፃ ላይ ነበር፡፡

አፈወርቅ በእንግሊዝ እየተማሩ ሳሉ በሌሎች የአውሮፓ አገራት እየተዟዟሩ አያሌ የሥነጥበባት መዲናዎችን በመጐብኘት ጠቃሚ ልምዶችን ቀስመዋል፡፡

ወደ አገራቸው ሲመለሱ የሚኒስትርነት ከፍተኛ ሃላፊነት ቢጠብቃቸውም እሱን ችላ በማለት በየክፍለ አገሩ እየዞሩ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ባህላዊ ብዝሃነት ላይ አትኩረው ጥናትና ምርምራቸውን ማካሄድ ጀመሩ፡፡ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ ለመሆን ህልም የነበራቸው አፈወርቅ፤ ይሄን ህልማቸውን እውን ለማድረግ የመረጡት መንገድ ግን የምዕራባውያን ጠበብቶችን የአሳሳል ዘይቤ በመቅዳት ሳይሆን የራሳቸውን ዘይቤ በመፍጠር ነበር፡፡ “የኢትዮጵያን ባህል ማጥናት ነበረብኝ” የሚሉት አፈወርቅ፤ “ምክንያቱም የዓለም አቀፍ ሰዓሊ ዋናው ጉዳይ የሥነጥበብ ሥራው የተወለደበትን ስፍራ ቃና እንዲይዝ ማድረግ ነው” ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ በሥነጥበብ አካዳሚ መማራቸውን ያወሳው ሰዓሊ በቀለ መኮንን፤ ሆኖም አፈወርቅ የሚሰራው ያገኘውን እውቀትና ጥበብ በቀጥታ በመገልበጥ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ትውፊትና ባህል የተዋሳቸውን ነው ብሏል፡፡

አፈወርቅ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩ፣ የሚመኩና የሚያምኑ እንደነበሩ የገለፁት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አብድርሃሚን ሸሪፍ ደግሞ አፈወርቅ ከሁሉም የጥበብ ሰዎች የሚለዩት በዚህ የኢትዮጵያዊነት ገፅታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “በአንድ በኩል ዓለማቀፍ፤ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊ ናቸው” ብለዋል - አቶ አብድርሃሚን፡፡

አፈወርቅ ተክሌ በ22 ዓመታቸው የመጀመርያውንና ለብቻቸው ያዘጋጁትን የሥነጥበብ ትርኢት በ1945 ዓ.ም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ያቀረቡ ሲሆን ከፋሺስቱ ጦርነት ወዲህ የመጀመርያው አይነተኛ የሥዕል ትርኢት ነበር፡፡ ከትርኢቱ በኋላ በጣልያን፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል እና በግሪክ አገሮች በመዘዋወር ጥናታዊ ጉብኝቶችን አድርገዋል፡፡

በፓሪስ ብሄራዊ ቤተመፃህፍትና በሮም የቫቲካን ቤተመዘክር በሚገኙ የኢትዮጵያ የብራና ሥዕላዊ ፅሁፎች ላይ ጥናት በማካሄድና ሲወራረድ የመጣውን ኢትዮጵያዊ የሥዕል ቅርፅ በመገምገም የራሳቸው ስለሆነው የሥነጥበብ ምንጭ ጥልቅ እውቀትንም እንደገበዩ ፕ/ር ፓንክረስት ገልፀዋል፡፡

ወደ አገራቸው እንደተመለሱም የሥዕል ስቱዲዮዋቸውን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመፃህፍት የከፈቱ ሲሆን ከዚህ በኋላ ነበር ለችሎታቸው ፈታኝ የሆኑ ሥራዎች ከመንግሥት የቀረበላቸው - ይላሉ፤ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት በፅሁፋቸው፡፡ በወቅቱ በመዲናዋ ከተሰጣቸው በከፍተኛ ግምት ከሚታዩ ስራዎች አንዱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያንን የውስጥ ግድግዳዎች ማስዋብ ሲሆን ይህንንም በሦስት ዓመት ተኩል ውስጥ በቀለም ቅብ ሥዕሎችና ባለቀለም ከሆኑ ጠጠሮች ከርክመው፤ መስተዋቶችና ከመሳሰሉት በማዋሃድ በሞዛይክ በሸገን ኪነት አሳምረው ጨርሰዋል፡፡

ፕ/ር ፓንክረስት እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ አራት ጀግኖች የሚታዩባቸው የአፈወርቅ የመጀመርያው የመስታወት የመስኮት ሥዕሎችና እንዲሁም ሌላው የመጀመርያው ጉልህ መታሰቢያነት ያለው የቅርፅ ሥራ ለሐረር የጦር አካዳሚ የተወጠነውም በዚሁ ቤተክርስትያን የማስዋብ ተግባር ላይ ሳሉ ነበር፡፡ አፈወርቅ ስለጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገልፁ አያሌ ሥራዎችን በቅርፃ ቅርፅ ለመስራት ቢተልሙም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሐረር ከሚገኘው (ራስ መኮንን በፈረሳቸው ላይ ሆነው ከሚያሳየው) አንድ ሐውልት በስተቀር ሌሎቹ አልተሰሩም፡፡

ከ1952 ዓ.ም ወዲህ ያሉት ዓመታት የእኚህ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ሰዓሊ የፈጠራ ተሰጥኦ በተፋፋመ እንቅስቃሴና በተለያየ መንገድ የተገለፁባቸው ዓመታት እንደነበሩ የሚያስታውሱት ፕ/ር ፓንክረስት፤ በሥዕል ንድፎችና በቀለም ቅቦች፣ በግድግዳ ላይ ሥዕሎች፣ ሞዛይኮች፣ የመስታወት ቅብ ሥዕሎችና ቅርፃ ቅርፆች፣ እንዲሁም የቴምብር፣ የመጫወቻ ካርታ፣ የአደባባይ ፖስተር፣ የባንዲራና የብሄራዊ ክብረ በዓል ልብሶች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሥነ ጠቢበነታቸውንና ዓለም አቀፍ ዝናቸውን እንዲናኝ ማድረጋቸውን ይገልፃሉ፡፡

በአፍሪካ አንድነት አዳራሽ መግቢያ ላይና በECA አዳራሽ የመስተዋት መስኮቶች ላይ በሰሯቸው ሥዕሎቻቸው ይበልጥ እንደሚታወቁም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በእነዚህ የሥነጥበብ ውጤቶችም ያለፈውን የአፍሪካን አሳዛኝ ታሪክ፣ የወቅቱን ትግልና የአፍሪካን የመጪ ዘመን ተስፋ እንዳንፀባረቁ ይነገርላቸዋል፡፡

በ1954 ዓ.ም በአዲስ አበባ የቀረበው የሰዓሊው ትዝታ ጠቀስ ትርኢት፤ በአገሪቱ የሥነጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ ምዕራፍ የያዘ ሲሆን በወቅቱ ከቀረቡ ሰባ ሦስቱ የቀለም ቅብ ሥዕሎች አንዷ የነበረችው “የመስቀል አበባ” ሥዕል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ በዚህ ትእይንት ስኬታማነት ባገኙት እውቅና የተነሳም በሩሲያ፣ በአሜሪካና በሴኔጋል ዓለም አቀፍ ትዕይንቶች ላይ ሥራዎቻቸውን ለማሳየት መንገድ ተከፍቶላቸዋል፡፡ በመቀጠልም የአፍሪካ አህጉርን ተዟዙረው የተመለከቱት አፈወርቅ፤ ከቅኝ ግዛት ሙሉ በሙሉ ያልወጡት አፍሪካውያን ለነፃነት ያደርጉት በነበረው ትግል ተነሽጠው “የአፍሪካ ስልጣኔ የጀርባ አጥንት”፣  “አፍሪካዊ አንድነት” እና ሌሎች አፍሪካዊ ይዘት ያላቸውን ሥዕሎች ሰርተዋል፡፡

በ1957 የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የመጀመርያው ብሄራዊ የሥነጥበብ ሽልማት ተሸላሚ የሆኑት አፈወርቅ፤ ዝናቸው ከአገር ውስጥ ባሻገር በውጭ አገራትም እየናኘ መጣ፡፡ የሥነጥበብ ትእይንት እንዲያቀርቡ ተጋብዘው ወደ ሩሲያ የሄዱት ሰዓሊው፤ እግረ መንገዳቸውንም በያኔዋ የሶቭየት ህብረት ግዛቶች እየተዟዟሩ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይሄን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስትም በዋሺንግተንና በኒውዮርክ የራሳቸውን የሥነጥበብ ትእይንት እንዲያቀርቡ ጋብዟቸዋል፡፡ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎችም ተመሳሳይ ንግግሮችን የማድረግ እድል አግኝተዋል - ሰዓሊው፡፡ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ትእይንቶችን በሴኔጋል፣ ቱርክ፣ ዛየር፣ የተባበሩት አረብ ሪፐብሊክ፣ ቡልጋሪያ፣ ሙኒክ፣ ኬንያና አልጀሪያ ማቅረብ እንደቻሉም ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

በ1974 ዓ.ም ሁለተኛውንና ትልቅ ግምት የተሰጠውን የሥዕል ትእይንት በሞስኮ ያቀረቡ ሲሆን በዓለም ዝነኛው የኡፉዚ ሙዚየም ከአፍሪካ የሥነጥበብ ባለሙያዎች ለመጀመርያ ጊዜ በር ከፋች አድርጐ “ራሱን በራሱ” (Self portrait) የተባለውን ሥዕላቸውን በመቀበል ተገቢ የክብር ስፍራ ሰጥቶታል፡፡

ከመቶ የማያንሱ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን እንዳገኙ የሚነገርላቸው እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ፤ በ1989 ዓ.ም በፈረንሳይ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ውድድር አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ሰዓሊው የአራት ዓለም አቀፍ የሥነጥበብ አካዳሚ አባል እንደሆኑ ሲታወቅ ከእነዚህም ውስጥ የፈረንሳይ ዓለም አቀፍ የሥነጥበብ አካዳሚና የሩሲያ የስነጥበብ አካዳሚ አባልነታቸው ይጠቀሳል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ያሉ ጀግኖች የሚታዩበት የጥበብ ፕሮጀክታቸው “ይቻላል” ከሚል መግለጫ ጋር በተለያዩ የመዲናዋ ስፍራዎች ተሰቅሎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ሰዓሊው በህይወት ሳሉ ስለዚህ ተጠይቀው ሲያስረዱ፤ “ጨለምተኛ አይደለሁም፤ ሰዎች ሥዕሌን አይተው ተስፋ እንዲያገኙ እፈልጋለሁ፤ ሰዎች ስለኢትዮጵያ፣ ስለአፍሪካ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው እሻለሁ… ከሁሉም በላይ ደግሞ ‘ይቻላል’ ብለው እንዲያስቡ እፈልጋለሁ” ብለው ነበር፡፡

ሰዓሊው መኖርያ ቤታቸውን፣ እንዲሁም ስቱዲዮና ጋለሪ ያካተተውን “ቪላ አልፋ” የተሰኘ ህንፃ ራሳቸው ዲዛይን ማድረጋቸው ሲታወቅ፤ 15 ዓመት እንደፈጀባቸው የሚነገርለት ባለ 22 ክፍሎች ህንፃ ጥንታዊቷን አክሱም፣ የጐንደር ቤተመንግስትንና የሐረር ግንብን በሚያንፀባርቅ መልኩ የታነፀ ነው፡፡ ሰዓሊው “ቪላ አልፋን” የገነቡት በውጭ አገራት ከሚያቀርቡት እያንዳንዱ ትእይንት ከሚያገኙት ገቢ 1/3ኛውን ለህንፃ ግንባታው በመመደብ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከህልፈታቸው በኋላ ባለፈው ረቡዕ ምሽት በኢቴቪ በተሰራጨ ዘገባ፤ ሰዓሊው በህይወት ሳሉ የሥዕል ስራዎቻቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ በቅርስነት እንደሚያወርሱ ቃል መግባታቸው የተጠቆመ ሲሆን ለቅርሱ ደህንነት ሲባል “ቪላ አልፋ” በፖሊስ እንደታሸገ ተገልፆ ነበር፡፡ ከባህል ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተመሰረተው ጊዜያዊ ኮሚቴ፤ “ቪላ አልፋ” ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ክፍት እንደሚሆን ባለፈው ሐሙስ አስታውቋል፡፡

በ”ቪላ አልፋ” የሚገኙትን የሥዕል ሥራዎች ማንም ሊያደራጀው ከሚችለው በላይ አርቲስቱ አደራጅተውት እንዳለፉ የመሰከረው ሰዓሊ በቀለ መኮንን፤ ጋለሪው ጥበቃ ተደርጐለት ለህዝብ ግልጋሎት እንዲሰጥ ይፈልጉ እንደነበር ጠቅሶ፤ ይህም ሊከበርላቸው ይገባል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ እንዲሁም የዓለም የሥነጥበብ ኩራት እንደነበሩ የሚነገርላቸው የሥነጥበብ ሊቁ፣ የህይወት ታሪክ ተፅፎ ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጋር ወደ ጨረቃ ተልኳል - ከሌሎች 200 የዓለም ታላላቅ ሰዎች ታሪክ ጋር በመሆን፡፡

“አፈወርቅ እስካሁን ያበረከቱትን የፈጠራ ውጤቶች መጠን ስንገመግም የፈጠራ ርቅቀታቸውንና እውቀታቸውን በስራ ላይ ማዋላቸውና ብርቱ ሠራተኛነታቸው ራሳቸው ለነበሩበት ትውልድ አርአያ አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደምረው በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሰዓሊነታቸው ብቻ ሳይሆን በ20ኛው መቶ ክ/ዘመን የሥነጥበብ ዓለም ውስጥም ያላቸውን ጉልህ ስፍራ ጭምር አብስረውላቸዋል” ብለዋል - ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለ ሥነጥበብ ሊቁ በከተቡት የምስክርነት ፅሁፋቸው፡፡

በጨጓራ አልሰር በሽታ በካዲስኮ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ የህክምና ክትትል ሲያደርጉ የነበሩት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ሥነስርዓታቸውም ዛሬ ከቀኑ በ9 ሰዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን እንደሚፈፀም ታውቋል፡፡ “አርቲስቱ በማለፉ የሞያው ሰፈር ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አገር ልታዝን ይገባል” ያለው ሰዓሊ በቀለ መኮንን፤ “አገር አዘነች ማለት አገር ትቀብረዋለች ማለት ነው” ብሏል፡፡

 

 

Read 20365 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:17