Print this page
Saturday, 21 October 2017 13:15

ከመንቻካ ተሰናባች፤ ደህና ከዳተኛ ይሻላል

Written by 
Rate this item
(26 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት እናት ለልጅዋ፤
“ከጥቂት ቀን በኋላ ከቤታችን ብዙዎች ጫጩቶች ይኖሩናል” ትለዋለች፡፡
ልጇም፤ “ማነው የሚያመጣልን ወይስ አንቺ ልትገዢ ነው?” ይላታል፡፡
እናቱም፤ “የለም ማንም አያመጣልንም፡፡ እኔም አልገዛም፡፡ ጫጩቶቹ ግን ይፈለፍላሉ”
ልጅ፤ “እንዴት?” ብሎ እናቱን አፋጠጣት፡፡
እናትየውም ወደ አንዲት ትንሽ ክፍል ወሰደችው፡፡ አንዲት ዶሮ ዕንቁላል ታቅፋ ቅርጫት ውስጥ ሆና አሳየችውና፤
“ተመልከት፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከነዚህ ዕንቁላሎች ከየአንዳንዳቸው የሚያማምሩ ጫጩቶች ይወጣሉ” አለችው፡፡
“እንዴት ተደርጎ?” አለ መጠየቅ የማይታክተው ልጅ፤ “ከእነዚህ ውስጥ እንደምን ጫጩቶች ይወጣሉ?” የልጁን ግራ መጋባት ያስተዋለው አባት፤
“ና ወደዚህ፤ አንዲት እንቁላል ሳሕን ላይ አፍርጠን እንመልከት” አለና ዕንቁላል ሰብሮ ሳሕን ላይ ገለበጠው፡፡ ከዚያም፤ “ልብ በል ልጄ፤ ይሄ ከዚህ ቀደም እንዳየኸው ዓይነት ዕንቁላል ነው፡፡ ባልሰብረው ኖሮ ግን አንድ የምታምር ጫጩት ትወጣ ነበር፤ የቀሩትም ዕንቁላሎች ሁሉ እንደዚሁ ናቸው፡፡ ከሃያ ቀን በኋላ ከነዚህ ከያንዳንዳቸው አንዳንድ የሚያማሩ ጫጩቶች ይፈለፈላሉ፡፡”
“ለምን ሃያ አንድ ቀን ድረስ ይዘገያሉ?”
እናቱ ይሄኔ ወደ ዶሮ ቤት ሄደችና፣ ጭር ያለችውን እናቲት ዶሮ፣ ዕንቁላሎቹን ለማስታቀፍ አመጣች፡፡ ከዚያም “በሉ አሁን ዶሮዋ እንዳትፈራ ዘወር እንበልላት” አለች፡፡
ቦታውን ለቀው ራቅ አሉ፡፡
ዶሮዋ ይሄኔ ዘላ ከቅርጫቱ ገባችና ዕንቁላሎቹን ታቀፈቻቸው፡፡
“ከዚህ ቅርጫት ውስጥ ሃያ ቀን ሙሉ ሳታቋርጥ ዕንቁላሎቹን ትታቀፋቸዋለች፡፡ በመጨረሻም ቀን የሚያማምሩ ጫጩቶች እናት ትሆናለች፡፡”
“ሃያ ቀን ሙሉ አይርባትም?”
“እኛ የምትመገበውን አጠገቧ እናስቀምጥላታለን፡፡”
“ይቺ እናት ገና የሚወለዱትን ልጆቿን የምትወድ ትመስላለች” አለ ልጁ
ከሃያ ቀን በኋላ ከዕንቁላሎቹ ውስጥ ረቂቅ ድምፆች ይሰማሉ፡፡ እናቲቱ ባፏ ቀጭ እያደረገች፣ መውጫ በር ትሸነቁርላቸዋለች፡፡ አንድ በአንድ እየከፈተችላቸው አስወጣቻቸው፡፡ ፍንጥር ፍንጥር የሚሉ በአፋቸው መሬቱን ደቅ ደቅ የሚያደርጉ ጫጩቶች ተፈለፈሉ፡፡
ልጁ መጨቅጨቁን አላቋረጠም፡-
“ማነው ከነዚህ ዕንቁላሎች ውስጥ በዚህ በጥቂት ጊዜ ጫጩቶቹን የሰራቸው?” አለ፡፡
“ይህ ሚስጥሩ የማይመረመር ነገር ነው” ሲሉ መለሱለት፡፡
*      *     *
ዕውነት ነው፡፡ ዛሬ የማይመረመሩ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንድ ነገር ግን ሳይመረመር የሚገባን አለ። አዲሱ ማሸነፉ አይቀሬ ነው - The new is invincible ይለዋል የጥንቱ የጠዋቱ ፍልስፍና፡፡ አሮጌው እያረጀና እያገረጀፈ የመሄዱን ያህል፣ አዲሱ እየተፈለፈለ ማደሩ ግድ ነው!
የአልገዛም ባይነት ስሜት ከሥር እየጋለ መምጣቱና፣ የላይኛው ወገን እንደ ትላንቱ ካልገዛሁ የሚልበት ትንቅንቅ መቀጠሉ፣ በአሮጌው ተሸናፊነት እንደሚያበቃ ታሪክ ይነግረናል፡፡
አንድ ጃፖኒን (ክንድ የሌለው ካኒቴራ) ያደረገ ተከሳሽ ዳኛ ፊት ቀርቦ፣ እጁን ወደፊት አጣምሮ ሲቆም፤ ዳኛው “በማን ላይ ነው ጡንቻህን የምትወጥረው?” ይሉታል፡፡ ተከሳሹ ደንግጦ ሁለት እጆቹን ወደ ጀርባው አድርጎ አጣምሮ ሲቆም፤ አሁንም ዳኛው “በማን ላይ ነው ደረትህን የምትነፋው?”     ይሉታል፡፡ ከዚያም “ምንድን ነው ችግርህ?” ቢሉት
“እኛን የቸገረን እጃችንን የምናስቀምጥበትን ቦታ የሚጠቁም አንቀፅ ነው!” አላቸው አሉ፡፡ ፍትሕ ሲዛባ ሁሉ ነገር ቅጥ-አንባሩ ይጠፋል፡፡ ሰብዓዊ መብት ይረገጣል፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብት የግለሰብ አንባገነኖች መጫወቻ ይሆናል፡፡ ይሄኔ የህዝብ ምሬት ያጥጣል! ብሶቱ ጣራ ይነካል! የአልገዛም ባይነት ስሜት እየመረረና እየከረረ፣ ሥርዓቱ እንደ ወትሮ በወዙና በወጉ መጓዙ እያዳገተ መንገጫገጭ ይጀምራል። ትናንሽ ካፊያ እየተጠራቀመ ውሽንፍራም ዝናብ ይሆናል፡፡ ከዚያም ጎርፍና ወጀብ ይበረታል፡፡
የሥነ አዕምሮው ሊቅ፤ ዣን ፒያጄ፤ ስለ ራስ-ተኮር ማዕከላዊነት ሲፅፍ፤
“እኛ ሳናቋርጥ የውሸት ሀሳቦችን ፈልፍለናል፡፡ ቅጥፈቶችን ተናግረናል፡፡ ቅዥቶችን ሰንቀናል። ምትሃታዊ የመሰሉ ገለፃዎችን አድርገናል፡፡ ጥርጣሬዎችን ቀፍቅፈናል፡፡ ቅጣምባራቸው የጠፋ ራዕዮችን ቀበጣጥረናል፡፡ ሁሉም ዕውነተኛ ሰዎች ፊት ሲቀርቡ በንነው ጠፊ ናቸው” ይለናል፡፡ ጊዜያዊ መፍትሔዎች ለጊዜው ቁጣን ሊያበርዱ ይችላሉ እንጂ ውለው ሲያድሩ እዚያው የድሮ ቦታቸው ይመጣሉ፡፡ አሁን ግን ግዘፍ-ነስተው፣ ኃይል አደርጅተው ነው ብቅ የሚሉት፡፡ በሃይል ለመመለስም በጄ የማይሉት ምዕራፍ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ገዢው ወገን እንዳረጀ ጥርስ እየተሸራረፈና እየተነቀለ ፈፅሞ ማኘክ የማይችልበት ሁኔታ ላይ ይወድቃል፡፡ “ኤጭ” አይባል የአገር ጉዳይ ይሆንና ሁሉንም ያነካካል። አንዱ አንዱን እየገፋ የሚጥልበት የዶሚኖ-ጨዋታ አወዳደቅ ይከሰታል- Dominos-effect ይሉታል ተንታኞቹ!
በአንድ አፍታ ለመበልፀግ የሚፈጠሩ ስግብግብ አካሄዶች ፍፃሜያቸው የህዝብ ተጠያቂነት ነው። አይነቃብኝም ተብሎ በስልጣን ሽፋን የሚዘረፍ ንብረትና ገንዘብ፣ የማታ ማታ ነገሮች ሲጠሙ ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀሬ ነው፡፡
የወርቅ ዕንቁላል የምትወልደውን ዶሮ አትገደላት! አትረዳትም፡፡ ለአንድ ቀን የምታገኘው ዕንቁላል፤ የሁልጊዜዋን ዶሮ አይተካልህምና፤ ነው ነገሩ፡፡
የህዝብ አመፅ እየተጋጋለ እየሄደ፣ ኑሮ ውድነቱን ማባባስ የለውጥ ፍንዳታን እንደማፋጠን ይቆጠራል። ዱሮ በ1966 ዓ.ም የፈነዳውን አብዮት ያቀጣጠሉ ረሀቡ፣ የነዳጅ ዋጋ  ጭማሪ፣ የዕለት - ሠርክ የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ አለቅጥ ማሻቀብ፣የመምህራን ጥያቄ፣ የጦሩ በየቦታው የደሞዝ ጥያቄ ማንሳት፣ የተራ ወታደሮች በአለቆቻቸው ላይ በእምቢ-ባይነት መነሳት፣ የባለሥልጣኖች “እሱ ነው፣ እሱ ነው” እያሉ የጥፋተኝነት ወንጀል አንዱ በአንዱ ላይ ማላከክ፣ በሥልጣን መባለጉ ከራሰ እስከ ግርጌ ማመርቀዝ - በጠቅላላው የላዕላይ መዋቅሩ (Superstructure) መናጋት፤ አንድ -አሙስ የቀረውን መንግሥት መፈንገል ጠቋሚ ምልከቶች ነበሩ፡፡ የፈረንሣይዋ ንግሥት ሜሪ አንቷኔት ህዝቡ ዳቦ እያለ ተሰልፎ እያለ “ለምን ኬክ አይበሉም?” ማለቷን ማላገጥ እናስታውስ! ነገሮች ወደ ፍንዳታ-ነጥብ- Tipping point፣ ሲቃረቡ አላየንም ብለው ዐይናቸውን የሚጨፍኑ የዋሃን ናቸው! ሰበቦች ቢደረደሩ፣ የበሰለውንና አገር ያወቀውን ነገር መልሶ ጥሬ ማድረግ አይቻልም፡፡ “ከመንቻካ ተሰናባች፣ ደህና ከዳተኛ ይሻላል” የሚባለው ለዚህ ነው!!

Read 7783 times
Administrator

Latest from Administrator