Saturday, 07 April 2012 09:52

ተቃዋሚዎች የአገሪቱ እድገት በኢህአዴግ እጅ ነው አሉ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

ደርግ መውደቁን ብደግፍም መንግስት የተጀመረውን ዲሞክራሲ አጨናግፏል - ዶ/ር መረራ  ጉዲና

የመንገድ ስራዎች እድገታቸው ጥሩ ነው - ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ

ዲሞክራሲያዊ መብቶች በህገ መንግስቱ ላይ መካተታቸው ጥሩ ነገር ነው - አቶ ሙሼ ሰሙ

መንግስት ልማት መስራቱ ግዴታው ነው - አቶ ግርማ ሰይፉ

በአገሪቱ እድገት ዙሪያ አንዳንድ ለውጦችና መልካም ተሞክሮዎች መኖራቸውን የገለፁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ ይሄ ተጠናክሮ ቢቀጥል ለውጥ እንደሚመጣ ጠቅሰው የአገሪቱ ዕድገት ያለው በኢህአዴግ እጅ ነው ብለዋል፡፡

የመድረክ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በሰጡት አስተያየት፤ ደርግ መውደቁን ብድግፍም መንግስት ብልጭ ብሎ የነበረውን ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ አጨናግፎታል ብለዋል፡፡ “አንዳንድ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ገና ከመነሻው ቢደረጉ ኖሮ እስካሁን የተሻለ ነገር ይታይ ነበር፤ ዲሞክራሲም ይስፋፋል” ያሉት ዶ/ር መረራ፤  ለዚህ ማሳያነት የ97 ምርጫን  ጠቅሰዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ ዲሞክራሲያዊ ነበር ባይባልም በኢትዮጵያ ከታዩት ምርጫዎች የተሻለ ነበር፤ ነገር ግን ብቅ ብሎ ተዳፈነ ብለዋል፡፡ በልማቱም ስራዎች ላይም መልካም ስራዎችን እንደሚያዩ የጠቀሱት ዶ/ር መረራ፤ ልማቱ በሙስና የተዘፈቀ መሆኑና በእርዳታ መሠራቱ ግን ችግሮች አስከትሏል ይላሉ፡፡ “ሆኖም አሁን ከሁሉም ጊዜ የተሻለ ነው፤ እነዚህ ለውጦች ተሻሽለው ቢቀጥሉ አገሪቱ ይበልጥ ታድጋለች” በማለት አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያነሷቸውን ችግሮች መንግስት ለመቅረፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ሆኖም ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በአንድ አይነት ሁኔታ ባይጨፈልቃቸው እንደሚሻል ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ፤ በልማት ረገድ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሲናገሩ፤ በከተሞች ትላልቅ መንገዶች መሠራታቸውን በማድነቅ ጥሩ ለውጥ ነው ብለዋል፡፡ ለ17 ዓመት የታገሉት ደርግ በመውደቁ ደስተኛ መሆናቸውን በማስታወስም፤ መንግስት ነፃነቱን ማስፋት አለበት ሲሉ አሳስብዋል፡፡

የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ በርካታ የመተግበር ጉድለቶች ቢኖሩም በህገ መንግስቱ ላይ ዲሞክራሲያዊ የሠው ልጅ መብቶች መካተታቸውን  እንደሚደግፉ ገልፀው፤ የኑሮ ውድነቱን ለማሻሻል መንግስት ያደረጋቸው ተግባራት የሚደገፍም የሚነቀፍም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የሲቪል ሠርቪስ ተቋማትን በተመለከተ የተንጣለለ ፎቅ ቢኖርም አሠራሩ የተቀላጠፈ አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ ሙሼ፤ ማህበረሠብን ለማገልገል፤ ቀናነትን በመፍጠር፤ ተመጣጣኝ ደሞዝና ጥቅማ ጥቅምን በማሻሻል አሁን ከሚታየው የተሻለ ነገር መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡ የህግ ስርአትን በተመለከተ የተለያዩ እና ያልተገናኙ ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚያወሱት አቶ ሙሼ፤ ማንም በዲሞክራሲያዊ መንገድ አሸንፎ ስልጣን እስከያዘ ድረስ ችግሮቹ መቀረፍ እንዳለባቸውና የተሻለ ውጤት መታየት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

የተሠሩ ስራዎችን መናገር አያስፈልግም የሚሉት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ኢህአዴግ ድልድይ መስራት ግዴታው ስለሆነ ድልድል ሠራ ብለው እንደማያመሠግኑት ገልፀው፤ ሆኖም አንድነት ድልድዩን ቢሠራው ኖሮ በፍጥነትና በቅልጥፍና ተጠናቆ ለአገልግሎት ይውል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

መንግስት መመዘን ያለበት በአደረጃጀትና ሥራውን በቅልጥፍና በመስራቱ መሆን እንዳለበት የገለፁት አቶ ግርማ፤ መንግስት መንገድና ድልድይ ሲገነባ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን መገንዘብ አለበት ብለዋል፡፡ የሊዝ አዋጁና የታክስ ስርአቱ እንዲሻሻል የጠየቁት አቶ ግርማ፤ ኢንቨስትመንቱም መስፋፋት እንዳለበት ጠቁመው፤ ሠዎች በአገራቸው በነፃነት የመኖር መብታቸው እስካልተከበረ ድረስ ምንም አይነት ፎቅና መንገድ ቢሰራ ዋጋ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኖች አገራቸውን ጥለው ሠው አገር እየተሠደዱ ስደተኝነታቸው እንዲፀድቅላቸው ይጠይቃሉ ያሉት አቶ ግርማ፤ ይሔ ለአገር አሳፋሪ ነው፤ አገሪቷ ሠው የሚሔድባት ሳይሆን ሌሎች በዲቪ የሚመጡባት እንድትሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡

 

 

Read 19939 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 14:22