Saturday, 14 October 2017 15:14

ገበያ እንዴት ዋለ? ቢለው፤ አንዱ በአንዱ ሲስቅ!

Written by 
Rate this item
(20 votes)

  የምድር አውሬ ሁሉ መሰብሰቢያና መናገጃ አንድ ገበያ ነበር ይባላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አውሬ ሁሉ እገበያ ሲውል አያ ጅቦ ግን ሳይሄድ ቀረ፡፡ የማታ ማታ ገበያተኛ ሲመለስ ከጎሬው ወጣና ከመንገድ ዳር ተቀመጠ፡፡ ገበያ ምላሽ ሲሆን እንኮዬ ዝንጆሮ ስትመጣ፣ የገበያውን አዋዋል ጠየቃት፡፡ እንደምትቸኩል ነግራው፣ ጦጢትን ጠይቃት አለችው፡፡ ጦጢትን ጠየቃት፡፡ እሷም፤ እንኮዬ ሚዳቋን ጠይቅ ብላው ሄደች፡፡ ሚዳቆን ጠየቃት፡፡ እቸኩላለሁ፤ እንኮዬ አህዪትን ጠይቃት አለችው፡፡
በመጨረሻው አህዪት መጣች፡፡ ገበያው እንዴት ዋለ? አላት፡፡ “ቆይ ቁጭ ብዬ ላጫውትህ!” ብላ ተቀመጠች፡፡ ሁሉን ካወራችለት በኋላ፤ “እንደኔ ይሄን ገደል እመር ብለሽ ማለፍ ትችያለሽ?” አለና ጠየቃት፡፡
“አሳምሬ!” አለችው፡፡
አጅሬ የሞት ሞቱን እንጣጥ ብሎ ዘለለው፡፡ አህዪት ግን እዘላለሁ ብላ ወርዳ ተከሰከሰች፡፡ አያ ጅቦ ሆዬ፤ ታች ወርዶ ሆዷን ዘንጥፎ ይበላ ጀመር፡፡ ይሄኔ ውሻ ከአፋፍ ብቅ አለች፡፡ ስታስተውል አበላሉ አስጎመዠትና፣ ምራቋ ጠብ ጠብ ሲል አናቱ ላይ አረፈ፡፡፡ ቀና ብሎ ቢያይ፤ ውሺት አለች፡፡
“በይ ነይ ውረጂና እየመተርሺ አብይኝ” አላት፡፡
“እሺ ጌታዬ” ብላ ወርዳ እየመተረች ስታበላው ቆይታ፤ አያ ጅቦ ዞር ሲልላት የአህዪትን ልብ ዋጥ ስልቅጥ አደረገችው፡፡ ጅቦ መለስ ብሎ ቢያይ ልቧን አጣው፡፡
ውሾን፤
“ልቧ ወዴት ሔደ?” ብሎ ጠየቃት፡፡
“ልብ ባይኖራት ነው እንጂ ልብማ ካላት አንተ ዘንድ መጥታ መቼ ትቀመጥ ነበር?” አለችው፡፡
አያ ጅቦ ግን፤ “ቅድም አይቼው ነበር፡፡ ታመጪ እንደሆን አምጪ፡፡ አለበለዚያ፤ አንቺንም እበላሻለሁ” አላት፡፡
“ምነው አያ ጅቦ፤ እኔን በቅቤና በድልህ አጣፍጠህ ነው እንጂ፣ እንደ አህዪት ደረቁን ትበላኛለህ?” አለችው። ሆዳሜ ዕውነት መሰለውና፤
“ቅቤውና ድልሁ ከየት ይመጣል?” አለና ጠየቃት፡፡
“ከእመቤቴና ከጌታዬ ቤት እኔ ሄጄ አመጣዋለኁ” አለችው፡፡
“ሄደሽ የጠፋሽ እንደሆነ ማ ብዬ እጠራሻለሁ?”
“እንኮዬ ልብ-አጥቼ፤ ብለህ ትጠራኛለህ!”
“በይ እንግዲያውስ ሄደሽ አምጪ” አላት፡፡
“እሺ ታዛዥ ነኝ!” ብላ ሄደች፡፡
ሄደችና ቅርት አለችበት፡፡
“ኧረ እንኮዬ ልብ-አጥቼ” እያለ ተጣራ፡፡
“ከእመቤቴና ከጌታዬ ቤት ለምን ወጥቼ!” ብላ፤ የስድብ ወርጂብኝ አወረደችበት፡፡
ከጊዜ በኋላ ግን ውሺት ስትልከሰከስ፤ አያ ጅቦ ያዛት፡፡ ዐይኗ ፈጠጠ፡፡
አያ ጅቦም “ዐይንሽ በምን እንዲህ አማረ?” አላት፡፡
“ጌታዬ፤ በአሥር የአጋም እሾህ ተነቅሼ ነዋ!” አለችው፡፡
“እባክሽ እኔንም ንቀሺኝ?”
ውሺት፤ አጋም እሾህ ሰብራ አመጣችና ዐይኖቹን ትጠቀጥቃቸው ጀመር፡፡
“ኧረ አመመኝ ውሺት”
“ሲያጌጡ ይመላለጡ ነው! ማማር እንዲያው ይገኝ መሰለህ?”
ብላ ሁለቱንም ዐይኑን አሳወረችው፡፡ ከዚያም ሠንጋ ጥለው፣ በጎድን ተዳቢት የሚደባደቡ ሰዎች ጋ ልውሰድህ ብላ ለገበሬዎች አሳልፋ ሰጥታ አስገደለችው!
*    *    *
“ያሰቡትንና ያቀዱትን ቸል ሳይሉና ሳይታለሉ ከፍፃሜ ማድረስ፣ የአስተዋይ ተግባር ነው፡፡ እኩይ ያልሆነ ጓደኛ መያዝ፣ ነገርን ሳያመዛዝኑና ሳያሰላስሉ ፈጥኖ ማመንና መቀበል የሚያስከትለውንም አለማሰብ፣ ከየዋህነትና ከቂልነት አስቆጥሮ ከጥቃት ያደርሳል፡፡ አታላይ ለጊዜው በመብለጥለጥ ምኞቱን ቢያረካም የፈፀመው ደባ እንደሚደርስበት የጅቡን አወዳደቅ መመልከት ይበቃል፡፡ ከእንስሳትም ውስጥ በአስተዋይነታቸውና በብልህነታቸው የሚመሰገኑ ፍጥረታት ይገኛሉ፡፡ እነሆ ውሻይቱ፤ በዘዴ ከአደጋ ከአመለጠች በኋላ፤ ኃይለኛ የሆነ ጠላቷን አሞኝታ ከሞት አደጋ አድርሳዋለች”፡፡ (ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀል) አቅደን በዕንጥልጥል የተውነው ስንት ጉዳይ ነበረን? የማያዋጣ ጓደኛ ምን ያህል ጊዜ ያዝን? ምን ያህል ደባዎች ተፈፀሙብን? ከዚያስ ምን ያህል ተማርን? እነዚህን ጥያቄዎች ደጋግመን ብንጠይቅ፣ ብዙ ችግሮችን ለማስወገድ እንችላለን!
አብዛኞቹ ግለሰቦች በፓርቲ የፖለቲካ ህይወታቸው የመታለል እጣ ይገጥማቸዋል፡፡ በትልቅነታቸውና ሆይ ሆይ በሚባሉበት ሰዓት፣ ከቶም መውደቅ የሚል ነገር እንዳለ ትዝ አይላቸውም! በታሪክ የነበሩ መሪዎች፣ የፖለቲካ ኃላፊዎች፣ ታላላቅ ሰዎች እንዴት ወደቁ? የእኔስ አካሄድ ምን ይመስላል? አለማለት፤ ቢያንስ የዋህነት ነው! ከታሪክ አለመማር ነገን ለመገመት አለመቻል ነው፡፡ ነገን አለመገመት የራስን ፍፃሜ አለማጤን ነው፡፡ ስለሆነም የድንገቴ አወዳደቅ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ማጣፊያው ያጥራል! በደጉ ሰዓት ያላቆዩዋቸው ጓደኞች፣ በክፉው ሰዓት አይኖሩምና፤ የማታ ማታ አጋዥ ደጋፊ ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡ ህዝብ የደገፈን ሲመስለን ጥንቃቄ ስለማናደርግና የእኔው ነው ብለን ስለምንኮፈስ ነው! ሲመሽብን ግን በምን ያህል ፍጥነት እንደሚተፉን፣ በምን ያህል ፍጥነትስ ገፍትሮ እንደሚጥለን ሳንገነዘብ ከአደባባይ ሸንጎ እንወገዳለን። የሚገርመው ስንወድቅም ህዝብ ከድቶናል ብለን አለማመናችን ነው!! ከአንገት በላይ ፍቅር ከአንገት በላይ ይቀራል! የህዝብን መሠረተ-ነገር አለማጤን ክፉ ማጥ ውስጥ ይከታል!!
ማንኛውም ነገር ያረጃል፡፡ ያፈጃል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ፍቅርም እንደዚያው ነው፡፡ ትላንት የደምና የመስዋዕትነት ጓዶች የነበሩ ዛሬ በኢኮኖሚ ተፅዕኖ፣ አዳዲስ ወዳጅ በማፍራት፣ ሀቀኛ የነበረው ዓላማ ጊዜውን ጨርሶ በአዳዲስ ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ ሲዋጥ፤ አሊያም የህዝብ ብሶትና ምሬት መቆሚያ መቀመጪያ ሲያሳጣው ወይም አጠቃላይ ሁኔታው ምቾት ሲነሳንና፤ ከውጪም ከውስጥም ስንወጠር፤ የዱሮው እኛነታችን ያከትማል፡፡ ከጥንት ወዳጆቻችን ጋር በሰላም ከተለያየን እሰየው ነው! በተቃራኒው ሆድና ጀርባ ሆኖ መለያየት ከመጣ ግን ወደማናውቀው ጠብ፣ መጠላለፍ እና መጠፋፋት ደረጃ እንደርሳለን! ከዚህ ይሰውረን!
ከነገራችን ሁሉ እጅግ አሳሳቢ፤ ነግ በእኔን አለማወቃችን ነው!! እኔ የተሻልኩ ስለሆንኩኝ እንደሱ አልወድቅም፣ ማለት ሁሌም እንዳታለለን አለ፡፡ ይልቁንም የወደቀውን ሰው ወንበር መሻማት፣ እሱ ባያውቅበት ነው የሥልጣንን አያያዝ፣ እያሉ፣ እዚያው ገደል ውስጥ መውደቅ የተለመደ ሆኗል! አይጣል ነው! ታማኝነትን ከአድር-ባይነት አለመለየት እርግማን ነው! ዘላቂነትን ከዘልዓለማዊነት ጋር ማምታታት የባሰ መርገምት ነው። “ጓደኛህን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ!” የሚለውን ተረት አንርሳ፡፡
“ትላንትና ሞቼ፣ ቀረሁ ሳልቀበር
እኔም የፈራሁ፣ ይሄንኑ ነበር!”… የሚለውን ግጥምም ልብ እንበል፡፡ አለመቀደም መልካም ነገር ነው። ቀድሞ መመታት እንዳለ ግን አንዘንጋ! ትላንት አለቃ የነበረው ዛሬ ምንዝር ሲሆን ማላገጡንና መሳለቁን ትተን፣ ይህ ሂደት የት ያደርሰን ይሆን? ብለን እንጠይቅ፡፡ ሁኔታዎች ካልተሻሻሉ፣ ነገሩ ሁሉ እየከፋ ይሄዳል፡፡ ጥንት “ወሎ መሰደድ ልማዱ ነው” ያሉ ባለሥልጣናት፤ እራሳቸው መቀመቅ ወርደዋል፡፡ “ገበያ እንዴት ዋለ?” ቢለው፤ “አንዱ በአንዱ ሲስቅ” የሚለው ተረት ትምህርት ካልሆነን፤ ከምን ልንማር ነው?!

Read 5551 times