Saturday, 07 April 2012 09:32

ጥበብ የጐደለው “የጥበባት ጉባኤ”

Written by  ደረጀ በላይነህ.
Rate this item
(0 votes)

በጥበብ አፀድ ውስጥ የዝማሬ ውብ ድምፆች በሞገስ እንዲፈስሱ…የደስታ ሳቆች እንዲፈኩ…እንመኛለን፡፡ ሰማይና ምድር በአድማሶቻቸው ተቃቅፈው ከከንፈሮቻቸው ዳርና ዳር ዜማ ሲፈልቅ፣ ተራሮች ማህሌት ቆመው ሲወዛወዙ ብናይ ደስ ይለናል፡፡ ጥበባትን የምንወድድ ሁሉ የልባችን ትርታና የነፍሳችንም ፉጨት ይኸው ነው!ታዲያ ይኸው ፍቅራችን በመጽሐፍት ቤቶች መደዳ፣ ሥጋ እንዳየ ጩሉሌ ያወዛውዘናል፡፡ በዚያ ውዝዋዜም መጻሕፍት ገዝተን በጉያችን ሸጉጠን እንከንፋለን፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዴ በሽፋናቸው ውበት ያማለሉን፤ በጀርባ አስተያየት ያባበሉን መጽሐፍት ጓዳ ገብተን ስንገልጣቸው እርቃን የቆሙ ግልቦች ይሆኑብናል! … እናም እንቆዝማለን!

ሰሞኑን በእጄ የገባው “የጥበባት ጉባኤ” የሚል መጽሐፍ የፈጠረብኝን ዝብርቅርቅ ስሜትና ትዝብት እንዳወጣ ያደረገኝም የዚሁ አይነት ገጠመኝ ነው፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ በብዕር ስምና በተፀውኦ ስም በርካታ የጋዜጣና መጽሔቶች ጽሑፍ፤ ጥቂት መጽሐፍትም ለአንባቢ ስላበረከቱ ጥልቀት እንኳ ባጣ ውበት አላጣም በሚል ወዲያው ነበር የገዛሁት፡፡

ደራሲው አቶ ጌታቸው በለጠ፤ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ስለሆኑም ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ መጠበቅ የግድ ነው፡፡ ጥልቅ ምርምርና ንባብ ሳያደርጉ ዘው ይሉበታል ብዬም መጠበቅ የለብኝምና አመንኳቸው፡፡

ይሁን እንጂ መጽሐፉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ቢይዝም፣ ቀደም ሲል በተለያዩ ፀሐፍት በተለይ በዩኒቨርሲቲ መምህራን የተሠራውን ሥራ በደረጃና በውበት ዝቅ አድርገው ከመድገማቸው ውጭ የሠሩት ሥራ አለ ማለት ይቸግራል፡፡ የተለያዩ ዘፋኞችን ሥራ ሰብስቦ በሲዲ እንደሚያሳትም አሳታሚ፣ ሰብሳቢ ናቸው ከማለት ያለፈ ምስክርነት የሚያሰጥ ሥራ የለበትም፡፡ ቢደገም እንኳ ቀደም ሲል ከተሠራው ጋር ተመጣጣኝነት ቢኖረው ወይም ክፍተት ቢሞላ ችግር ባልነበረው፡፡ ምክንያቱም ሳይንስና ቴክኒክ እንጂ የፈጠራ ሥራ ስላልሆነ፣ አንዱ ካንዱ በላቀ ሁኔታ እያሻሻለውና እያበሰለው ቢሄድ እሰየው የሚያሰኝ ነበር፡፡ “የጥበባት ጉባኤ” ግን ከቋንቋ አጠቃቀሙ ጀምሮ ንግግር እንጂ ጽሑፍ ነው ለማለት እንኳ ይከብዳል፡፡

ሌላው የሚገርመው ነገር ደራሲው ስለራሳቸው መጽሐፉ መግቢያቸው ላይ የፃፉልን ነገር ከመጽሐፉ ጋር ሲተያይ አራምባና ቆቦ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ እንዲህ ብለዋል፡- “ይህ መጽሐፍ ተነባቢ ነው፡፡ ለምን ቢሉ በትምህርት ዳብሯላ፣ በግል ንባብ ጐልብቷላ፣ ፀሐፊው ራሱ በዳሰሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተግባር ተፈትኗላ” ይላሉ፡፡ እውነት በሆነና ባሉ፤ ግን ካሉት ውስጥ የሚታይ እውነት የለም፡፡ የተማሩት፤ ያነበቡት በተግባር የተፈተኑት የማይጨበጥ ጉም ነው፡፡

ለነገሩ እውነት ቢሆን መጽሐፉን አንብበን ስናበቃ…በመደነቅ “እኒህ - ሰውዬ የተማሩ ናቸው!...እንደ ጉድ አንብበዋል…የሕይወት ተሞክሯቸው ውቅያኖስ ነው ብለን ፓ!” በማለት ከንፈራችንን መተኮስ የነበረብን እኛ ነን!...

እንደኔ እንደኔ መጽሐፉን ለአንደኛና በመለስተኛ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች አዘጋጅተውት እንደሆነ ጠቆም ቢያደርጉ ደግ ነበር፡፡

ደራሲው በጠቅላላ ንባብ ውስጥ የሚደመጥ ድምጽ አላቸው፡፡ ያም የአንባቢውን ደረጃ ያለማወቅና ልክ እንደ ንግግር የቆጡን ከባጡ የመቀላቀል፤ በአንድ ጊዜ ከአንድ ሃሳብ ወደ ሌላ የመሄድ፤ ስለ ሂስ እያወሩ የታሪክ ፀሐፊ ሆኖ መገኘት!

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እንደሚመስለኝ የጠቀሱዋቸውን መጽሐፍት ሙሉ በሙሉ ያለማንበብ ችግር ያለ የሚያስመስሉ መረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአቶ ጌታሁን አማረን “ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋሰው”ን ሲያነብቡ፣ መስተፃምር በመስተዋድድ ውስጥ መካተቱን የሚገልፁ ጽሑፎችን በገጽ 48፣ 117፣ እና 161 እያሉ እርሳቸው ግን አሁንም መስተፃምርን ወደ ኋላ ተመልሰው ከነተክለማርያም ፋንታዬ ይጠቅሳሉ፡፡ ያለንጽጽር ለምን ተጠቀሰ እያልኩ ሳይሆን፤ ከ1987 ዓ.ም ወዲህ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም መስተዋድድን መስተፃምርን ውጦ ሁለቱን ሥራዎች መሥራት ከቻለ ደራሲው አሮጌ ፉርጐ ቀጥለው አንባቢውን ለምን ግራ ያጋቡታል ነው - ጥያቄዬ!

ይህንን በተመለከተ አቶ ጌታሁን አማረ (ረዳት ፕሮፌሰር) በዘመናዊ የአማርኛ ሰዋሰው ገጽ 48 ላይ የፃፉትን እንመልከት፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-

“በዚህ የስነ - ልሳን ምሁር (ፕ/ር ባዬ ይማም) የተዘረዘሩት የቃል ክፍሎችም 1 ስም፣ 2 ግስ፣ 3 ቅጽል፣ 4 መስተዋድድ፣ 5 ተውሳከ ግስ ናቸው፡፡

በነዚህ የቃል ክፍሎችም ውስጥ በቀደምት ሊቃውንት ስራዎች የምናገኛቸው ተውላጠ ስም፣ መስተፃምርና ቃለ አጋኖ የሚሉትን አናይም፡፡ እነዚህ ሦስቱ ከአምስቱ ጋር ያልተገለፁበት ምክንያት፣ ተውላጠ ስም የስም ንኡስ ክፍል በመሆኑ ስም በሚለው የቃል ክፍል ውስጥ ስለሚካተት ሲሆን መስተፃምር ደግሞ በባህሪው ከመስተዋድድ ጋር ስለሚመሳሰል በመስተዋድድ ውስጥ ስለተካተተ ነው፡፡

ይህ ከሆነ “የጥበባት ጉባኤ” እዚህ ላይ ምን አዳከራት? አልገባኝም! አቶ ጌታሁን አማረን ለምናውቅ ጥንቅቅ፣ ሙክክ ብለው የበሰሉ የሥነ ልሳን ምሁር ናቸው፡፡

“የጥበብ ጉባኤ” ስለ ደራሲ፣ ድርሰትና ተውኔት ያነሳውን ርዕሰ ጉዳይ፣ አቶ ዘሪሁን አስፋው በሚጥም ቋንቋ፣ በርካታ የሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ማስረጃዎችን ጨምረው “የስነ ጽሑፍ መሠረታዊያን” በሚል አሳትመዋል፡፡ እውነት ለመናገር የአቶ ዘሪሁን አስፋው መጽሐፍ በውበት በቋንቋ - የተቀባ ገጣሚ ያህል ጣፍጦና ተደራጅቶ የቀረበ ነው፡፡

ታዲያ ያንን ተራራ ለመገዳደር ሸለቆ ሆኖ መቅረብ ከግምት ውስጥ ከመውደቅ ውጭ ፋይዳው ምንድነው? በአንድ ነገር ተሽሎ ወይም ተለይቶ መቅረብ ካልተቻለ ምነው ቢቀርስ?

አቶ ጌታቸው በገጽ 105 ላይ ደርግን ያለ አግባብ የኮነኑበት ሰበብም ደስ አላለኝም፡፡ በነገራችን ላይ ደርግን ሁሌ እንደጭራቅ መቁጠር ያለብን አይመስለኝም፡፡ በተለይ ከአግባብ ውጭ፡፡

ከሁሉ ይብስ ግን “ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስር እናደርጋለን” ያለ መንግስት ተፈጥሮን አይወድምና አይንከባከብም ብሎ ማሰብ ከደራሲው ደረጃ በታች ያለ ጭፍን ሰው አስተሳሰብ እንጂ የእርሳቸው መሆኑ የሚገርም ነው፡፡ ይህንን ያለው ደርግ ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች፣ እንዲሁም ከአሥር ዓመት ወዲህ የታተመውስ “American Culture” ስለ አሜሪካን ባህል ሲያወራ፤ በስራ እንጂ በዕጣ ፈንታ አናምንም አላለም እንዴ? ታዲያ ደርግ “ሀገር እናልማ” ማለቱን ለምን ሌላ ሰበብ ፈለጉለት? ደርግ እንደማንኛውም መንግስት ክፉም በጐም ገፅታ እንዳለው መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡

ደራሲው አቶ ጌታቸው፤ አንድ መጽሐፍ ለመፃፍ የተዘጋጀ ሰው ቀርቶ ለጋዜጣ ጽሑፍ የሚደረገውን ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረጋቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ የጠረጴዛ ዙሪያ የሻይ ቡና ገራገር ጨዋታ መስሏልና፡፡

ሌላው እጅግ የገረመኝ ነገር.፣ ደራሲው በዚህ አቋምና ዝግጅት፤ አቶ ብርሃኑ ገበየሁ በጥልቀት የሰራበትን “የአማርኛ ስነ ግጥም” አይናቸውን ጨፍነው መቧጠጣቸው ነው፡፡ አቶ ብርሃኑ መጽሐፉን ለማስተማሪያነት መረጃ አስቆንጥጠው፣ ጥናት አስጨብጠው ብቻ አይደለም የሠሩት፤ እንደ ግጥም አጣፍጠው፣ ደመና አስረግጠው ነው፡፡ መጽሐፉ ዕውቀቱ ብቻ ሳይሆን ውበቱ መሳጭ ነው፤ ተነብቦ አይጠገብም ፡፡ ቋጥኙን ፈላልጦ፣ ለግንብ የሚሆን ድንጋይ፣ አሸዋ፣ የሲሚንቶ ያህል የላመ አድርጐ ሠርቶታል፡፡ ታዲያ አቶ ጌታቸው ከዚህ የሚተካከል፣ ወይም የሚጠጋጋ ምን ይዘው ደፈሩ? ወይስ እፍኝ እንትን ይዘህ..እንደሚባለው ሆኖ ነው?

ስለ ግጥም ደፍረው ጀመሩ እንበልና እንመልከተው፡፡ ግጥምን “አንጋፋ” ብለውታል፡፡  ደግ፤ ግን ለአንጋፋነቱ መረጀ አልሰጡንም፡፡በመሠረቱ ግጥም አንጋፋ ነው ስንል ብቻውን ተንጠልጥሎ አልነበረም የተወለደው፡፡ በግራና በቀኝ አቅፈው ያንጠለጠሉት መንትያ ጥበባት አሉ፡፡ የተወለደውስ የት ነው? ለዚህም መልስ አልሰጡንም፡፡ የት ሀገር? ሦስት ሀገራት አሉት፡፡ የኢትዮጵያ ስነግጥምስ?

ይህንን ካልነገሩን ለምን ፃፉት? ለመድገምም ከሆነ በወጉ ቢደግሙልን ምን ነበረበት?

ሌላው ቀርቶ ስለ ግጥም፤ ስነ ግጥምና ቅኔ እንኳ ሲያወሩ፣ ልዩነቱን የወሰዱት ቀጥታ ከብርሃኑ ገበየሁ ነው፡፡ የአረፍተ ነገሩን መልክ ከመለየት በቀር፡፡ የደራሲና ገጣሚ አበራ ለማ አመለካከት የሚለይ ስለሆነ የእርሱን እንኳ ይዘው ቢመጡ ምን ነበረበት? ግድ የለም ንቀውናል!

ስለ ስህተት ካነሳን አይቀር፣ ገጽ 216 ላይ ስለ ሀረግ ያነሱት ነገርም ግራ ገብቶኛል፡፡ እንዲህ ይላሉ፡- “ስለ ሐረግ ምንነት ቀደም ባሉት ክፍሎች ውስጥ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በግጥም ውስጥ ሐረግ ሙዚቃዊ ቃና ባለው አንድ የአነባበብ ትንፋሽ የሚነገር ወይም የሚነበብ ነው፡፡ የስንኝ እኩሌታም ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ስለ ሐረግ ብያኔ መንግስቱ ለማ በ1963 ዓ.ም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል - “ሐረግ የስንኝ እኩሌታ ነው ተብሎ ነበር፡፡ ይህ ግን የሚሆነው በአንድ አይነት ስልት ሲሰናኝ ብቻ ነው፡፡ ሁለት ሶስት አይነት የስንኝ ስልት ባንድ ቤት ሲደባለቅ ግን አንዱ ሐረግ ከአንደኛው ሐረግ መርዘሙ ወይም ማጠሩ የግድ ስለማይቀር፣ ሐረግ የስንኝ እኩሌታ ሊሆን አይችልም፡፡”

አቶ ብርሃኑ ገበየሁም፤ ሐረግ የስንኝ እኩሌታ ነው የሚለው ሀሳብ ትክክል እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡

እናም አሁን ጥያቄዬ ደራሲው፣ የተለወጠን አዲስ ነገር ካላሳወቁ፣ ካላነፃፀሩ … መጽሐፍ ለምን ፃፉ? ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ገጽ 218 ላይ አቶ ጌታቸው በለጠ፤  በሰንጠረዥ የግጥም ምደባዎችን ሲያስቀምጡ፤ የመርስኤ ሐዘን እና የብርሃኑ ገበየሁ በሚል ረድፍ አስይዘዋቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም መንግስቱ ለማ ከባላንባራስ ተውሰው የጨመሯቸውን በበገና የሀዘንት ምት፣ አባባዬ ሆይ ዘፈን፣ በመሰንቆ መዲና ግጥም፣ የጥምቀት ዘፈን ግጥምንና የመሳሰሉት በኢትዮጵያ ግጥም ውስጥ የነበራቸውን ሥፍራ ጭራሽ አልጠቀሱም፡፡ (ይህንን ያስተምሩ አይደለም! “ነበሩ” ብለው እንኳን አላሰቡዋቸውም፡፡)

እንደእኔ እንደኔ መቀነት በሌለው ብዕርና በተልፈሰፈሰ ገለፃ፣ ግጥምን ባይነኩት ጥሩ ነበር፡፡

ከሁሉም የጥበባት ዘውጐች በወጉ ቢጽፉበት ኖሮ፣ የወግ ጽሑፍ ያልተነካ ስለሆነ ጥሩ አጋጣሚ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምን ነካኩት የሚል ተቃውሞም የለኝም፤ በጥቂቱም ቢሠሩት ከባዶ ይሻላልና ደግ አድርገዋል!

የሂስ ጥበብን ጉዳይም በወጉ ቢሠሩት እንደዚሁ ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊና ምንም ያልተፃፈበት የጥበብ ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ እሱንም በደሴት ዙሪያ እንደሚዞር ወንዝ ዙሪያውን ዞሩ እንጂ አልነኩትም ወይም አልተዘጋጁበትም፡፡

ስለሂስ ሲያነሱ ጀማሪው አርስቶትል መሆኑንና የመጀመሪያው ሥራ “ፖኤቲክስ” መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከዚያም ፕሌቶንና ሌላ ሕንዳዊ ሃያሲን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአርስቶትልና በፕሌቶ ሂሶች መካከል ያለውን የባህርይ መልክ ትንፍሽ አላሉም፡፡ በቅርጽ በአመክንዮ የማ በሞራል ደግሞ የማን እንደሆነ ካልነገሩን ምን ይጠቅመናል?  ለዚህ ለዚህ ባይነግሩንስ ያስብላል፡፡

ገጽ 344 ላይ የሂስ አይነቶችን አስመልክተው አምስት ያህሉን ከጠቀሱ በኋላ ዋና ዋና ዋናዎቹን ማለፋቸው ገርሞኛል፡፡ ሌላው ቢቀር በሀገራችን እጅግ የተለመደውን “ቅርፃዊ ሂስን” እንኳ እንዴት አይነግሩንም?  ይልቅ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የቅኔ፣ የዜማና የአቋቋም ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመምህራኑና በተማሪዎች መካከል ስለሚካሄደው የተጧጧፈ የሂስ ጦርነት የተናገሩት አዲስና ደስ የሚል ነው፡፡

በተረፈ ስለቀደሙት የብዕር ስሞችና ፀሐፍት የፃፉት፣ ለታሪክ ሰነድ ማጠርቂያ ስለሆነ በጐ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡

ከዚህ ውጭ ግን በበረታ ንባብና በጠና ጥሞና ላይ ያልተመሰረተ የሞያ መጽሐፍ መጀመር፣ በባዶ ሆድ ሚዛን ላይ እንደመቀመጥ ወይም እንደ ፀጉራም በግ አሉ እየተባሉ መሞት ነውና ለሌላ ጊዜ ደራሲው ከልብ ሊያስቡበት ይገባል ባይ ነኝ፡፡

 

 

Read 2273 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:37