Print this page
Saturday, 02 September 2017 11:45

“በክልሎች የግል ሬዲዮ ጣቢያ ለመክፈት ፍላጎት ያለው አመልካች አልተገኘም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    የሬድዮ እናቴሌቪዥን ፍቃድ የመስጠትና የመቆጣጠር ተግባር የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በተደጋጋሚ ለአመልካቾች ማስታወቂያ ቢያወጣም በክልል የግል የንግድ ሬድዮ ጣቢያ ለመክፈት ፍላጎት ያለው አካል አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ ከሠሞኑ የግል ሚዲያዎችን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ዳሠሣዊ ጥናቱ ላይ የሬድዮ ፍቃድ መስጠት ከተጀመረ ጀምሮ 10 የግል ሬድዮ ጣቢያዎች በአዲስ አበባ ፍቃድ የወሠዱ ሲሆን አንደኛው እስካሁን ስራ አልጀመረም ተብሏል፡፡
በተደጋጋሚ በየክፍልቹ የግል ሬድዮ ጣቢያ ለመክፈት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የውድድር ማስታወቂያዎች ማውጣቱን የጠቆመው ባለስልጣኑ እስከዛሬ አንድም አካል ፍቃድ ወስዶ ለመስራት ፍላጎት አላሣየም ብሏል፡፡
በአዲስ አበባ የተከፈቱ የግል የሬድዮ ጣቢያዎችም ቢሆኑ ብዙ ርቀት የማይደመጡ በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የተወሠኑ ከመሆናቸውም በላይ የይዘት ችግር አለባቸው ብሏል ባለስልጣኑ፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ የኤፍ ኤም የግል ሬድዮ ጣቢያዎች የአየር ጊዜያቸውን በአመዛኙ በስፖርት እና በመዝናኛ ጉዳዮች እንደሚሸፍኑ የጠቆመው የባለስልጣኑ ዳሠሣዊ ጥናት በዚህም በሃገሪቱ የሚፈልገውን ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር በኩል የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት አልቻሉም ብሏል፡፡
በይዘታቸው በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ በየጊዜው ባለስልጣኑ ከብሮድካስተሮቹ ጋር እየተመካከረ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ብሮድካስት ባለስልጣን ፍቃድ ከሠጣቸው 5 የሃገር ውስጥ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሶስቱ ስራ መጀመራቸውንና ሁለቱ እስካሁን ወደ ስራ ለመግባት እንዳልቻሉ ተመልክቷል። ተጨማሪ 5 የሣተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ ተቀማጭነታቸው ከሃገር ውጭ አድርገው እየሠሩ መሆኑን ከብሮድካስት ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ፕሬሶችን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት 18 ጋዜጦች እና 43 መፅሄቶች ገበያው ላይ አሉ ያለው ብሮድካስት ባለስልጣን ከ18 ያህሉ ጋዜጦች ወጥነታቸውን ጠብቀው ሣያቋርጡ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጋዜጦች በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው ብሏል፡፡


Read 1433 times
Administrator

Latest from Administrator