Saturday, 07 April 2012 09:06

አሽተን ኩቸር ስቲቭ ጆብስን ለመተወን ተመረጠ

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

የአፕል ኩባንያ ዋንኛው መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረውን ስቲቭ ጆብስ በሚዘክር ፊልም እንዲተውን አሽተን ኩቸር መመረጡን ሎስአንጀለስ ታይምስ ዘገበ፡፡ የፊልሙ ቀረፃ በቀጣዩ ወር እንደሚጀመር ታውቋል፡፡ አሽተን ኩቸር የታዋቂውን የቴክኖሎጂ ምሁር የህይወት ታሪክ የሚዳስሰውን  ፊልም ለመተወን  በመልክ መመሳሰል፤ በሞባይልና ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ በሚሰራው ንግድና አጠቃቀሙ እንዲሁም በትወና ብቃቱ ተወዳዳሪ እንዳጣ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡  ከ37 በላይ የአፕል አፕሊኬሽኖች በመፈልሰፍና በታዋቂው የፒክሳር ኩባንያ መስራችነቱ የሚታወቀው የ56 ዓመቱ ስቲቭ ጆብስ ከ5 ወር በፊት በጣፊያ ካንሰር ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡

አንድ የቴክኖሎጂ ባለራእይን ለመተወን የተፈጠርኩ ነኝ ብሎ እንደሚያምን የተናገረው አሽተን ኩቸር፤ ስለስቲቭ ጆብስ የበለጠ ለማወቅ ከወዳጆቹ ጋር እየተገናኘ በመመካከር ላይ እንደሆነና ድምፁን በመለማመድ እና ፀጉሩን በማሳደግ ትወናውን ለማሳመር ዝግጅቱን እንዳጧጧፈ ታውቋል፡፡

 

 

Read 976 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:09