Sunday, 27 August 2017 00:00

በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የንግድ አድማ 4ኛ ቀኑን ይዟል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

• ክልሉ የተቃዋሚ አመራሮችን ለማስፈታት ከአቅሜ በላይ ነው አለ

በማህበራዊ ሚዲያዎች ከረቡዕ ጀምሮ ለ5 ቀናት የተጠራው የንግድ መደብሮችን የመዝጋትና የትራንስፖርት አገልግሎትን የማቋረጥ አድማ፣ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ዛሬ 4ኛ ቀኑን እንደያዘ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡   
የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮን ጨምሮ አፍሪካን ኒውስ ድረ-ገፅ እንደዘገቡት፤ በአንዳንድ ከተሞች የንግድ መደብር ባለቤቶችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በግድ እንዲሰሩ የተደረጉ ቢሆንም በአብዛኞቹ ከተሞች ግን የንግድ  አድማው ቀጥሏል፡፡ ንግድ ቤቶች ተዘግተውና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ፣ ከቤት ባለመውጣት ለሚደረገው አድማ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል፣ “በነጋዴው ላይ ከአቅም በላይ ግብር ተጥሏል”፣ ”የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ”፣ “ፖለቲካዊና ማህበራዊ የህዝብ ጥያቄዎች ይመለሱ” የሚሉ እንደሆነ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል። አድማው በተጨማሪም፤ “የታሰሩት የኦፌኮ አመራሮች ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በቀለ ገርባ ይፈቱ”፣ “የድንበር ግጭት ይቁም” የሚሉ ጥያቄዎችን ያነገበ እንደሆነም የተለያዩ ዘገባዎች  ጠቁመዋል፡፡
በተለይ በሰበታ፣ ቡራዩ፣ ወሊሶ፣ አምቦ፣ ነቀምት፣ ሮቤ፣ አወዳይ፣ ጭና ቅሰን፣ ሻሸመኔና በሌሎችም ከተሞች አድማው ሲደረግ መሰንበቱ ታውቋል፡፡ በአብዛኞቹ የክልሉ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ መዳከማቸውም ተጠቁሟል፡፡   
 “በአድማው መሳተፍም አለመሳተፍም ጭንቅ ሆኖብናል” ያሉ አንድ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ፤ ”የመንግስት ኃይሎች በግዳጅ ወደ ስራ ውጡ ይሉናል፤ አድማ ጠሪዎችም በፊናቸው የአድማው ተባባሪ ያልሆነ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፤ በእውነቱ ግራ የሚያጋባ ሆኖብናል” ብለዋል- ለአዲስ አድማስ፡፡
ከዚሁ አድማ ጋር በተያያዘ ባለፈው ረቡዕ፣ በሃረር አወዳይ፣ ሲንቀሳቀስ ነበር የተባለ አንድ ተሽከርካሪ ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከትናንት በስቲያ እኩለ ቀን ላይ በጅማ ከተማ የፈነዳ ቦምብ፣ በ13 ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ታውቋል፡፡ ቦምቡ ባልታወቀ ግለሰብ፣ በሁለት ህንፃዎች መካከል ተወርውሮ፣ በአካባቢው ሲተላለፉ በነበሩ ግለሰቦች ላይ ቀላል ጉዳት አድርሷል - የዜና ምንጮች እንደዘገቡት፡፡   
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየታየ ያለው ውጥረት አሳሳቢ መሆኑን የሚገልጹ አንጋፋ ፖለቲከኞች፤ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ፣ አፋጣኝ መፍትሄዎችን መሻት እንዳለበት መክረዋል፡፡
ህዝቡ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በቅርቡ ሲናገሩ፤ “የህዝባችንን ጥያቄዎች እግር በእግር እየተከተልን መፍትሄና ምላሽ ከመስጠት ውጭ አማራጭ የለንም” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ በኦሮሚያ ከተሞች ከረቡዕ ጀምሮ የተጠራው አድማ፣ እንደተባለው በ5 ቀናት የሚያበቃ ከሆነ፣ ነገ እሁድ የመጨረሻው ቀን እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡  
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ፤ትናንት ማምሻውን በማህበራዊ ድህረ-ገፃቸው ባሰራጩት መረጃ፣ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ 315 ወረዳዎች ውስጥ በ29 ወረዳዎችና  በ4 ትልልቅ የክልሉ ከተሞች አድማ መካሔዱን አረጋግጠዋል፡፡
ከአድማው አጀንዳዎች መካከል የታሰሩ የኦፌኮ አመራሮች ይፈቱ የሚለው አንደኛው መሆኑን የገለጹት አቶ አዲሱ፤ የአመራሮቹ የህግ ጉዳይ በፌደራል ደረጃ ያለ መሆኑን ፣ ነገር ግን ነቀምት ላይ ተካሄዶ በነበረው ስብሰባ የአካባቢው ማህበረሰብ ለጠይላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ጥያቄውን አንስተውላቸው “ለጉዳዩ መፍተሔ የሚሰጠው ህግ ነው” የሚል ምላሸ መስጠታቸውን በመጠቆም የአመራሮቹ የእስር ጉዳይ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ይቅርታ ትልቅ ቦታ እንዳለው ያምናል› ያሉት አቶ አዲሱ፤ በዚህም መሰረት በክልሉ ከአመፅ ጋር በተገናኘ፣በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ከ22 ሺ በላይ እስረኞችን በይቅርታ መፍታቱን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ተጨማሪ ምክንያቶች ለሆኑት የግብር ጉዳይና በኦሮሚያ እና ሶማሊያ ድንበር መካከል ስላለው ግጭቶች የክልሉ መንግስት በየደረጃው እልባት በመስጠት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡


Read 7547 times