Sunday, 27 August 2017 00:00

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በጣሊያን እየተሰቃዩ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

የመጨረሻ ዕጣፈንታቸውን ገና አላወቁም
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ የጣሊያን መንግሥትን እርምጃን አውግዘዋል
በሳኡዲ የሚገኙ ግማሽ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አደጋ ተጋርጦባቸዋል

   ለበርካታ አመታት በስደት ጣሊያን ሮም ውስጥ የኖሩ ከ800 በላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የጣሊያን መንግስት በጀመረው የፀረ ሽብር ዘመቻ ሰበብ፣ በጋራ ከሚኖሩበት ህንፃ ያለአንዳች ማስጠንቀቂያ በኃይል እንዲለቁ የተደረገ ሲሆን እርምጃውን የተቃወሙ ስደተኞች፤ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው ለድብደባና ለእንግልት እንደተዳረጉ አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
ከ4 ዓመት በፊት ጀምሮ ይኖሩበት ከነበረው “Piazza Indipendenza” የተሰኘ ህንፃ በኃይል እንዲወጡ ከተደረጉ ስደተኞች መካከል በርካቶቹ ከቅዳሜ ጀምሮ በጎዳና ላይ እያደሩ ነው ተብሏል። ጥገኝነት ጠያቂ የሆኑ አብዛኞቹ ህፃናትና ሴቶች በአቅራቢያ በሚገኝ ህንፃ በጊዜያዊነት እንዲጠለሉ ተፈቅዶላቸው የነበረ ቢሆንም በህንፃው መስኮቶች ላይ “እኛ አሸባሪዎች አይደለንም” የሚል መፈክር ሰቅለው ነበር ተብሏል፡፡ ጥቂት ስደተኞችም የውሃ ኮዳዎችን ጨምሮ ድንጋይ ፖሊስ ላይ መወርወር ሲጀምሩ ግን ከህንፃው እንዲወጡ ተደርገው፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸው ታውቋል። ፖሊስ የስደተኞቹን አድማ ለመበተን ኃይለኛ ውሃ መጠቀሙን፤ በቆመጥም ድብደባ መፈፀሙ ስደተኞቹ ይናገራሉ፡፡
በሃይል እርምጃውም 13 ስደተኞች መቁሠላቸውንና ሁለቱ ወህኒ ቤት መውረዳቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡ የጣሊያን መንግስት ባለስልጣናት፣ ስደተኞቹን ከህንፃው የማስለቀቁ ተግባር የፀረ ሽብር እርምጃ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ጥገኝነት ጠያቂዎች አብዛኞቹ ሴቶችና ህፃናት መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን የሃገሬው መንግስት ከህንፃው ካስለቀቃቸው በኋላ እናትና ልጅን እንዲሁም ባልና ሚስትን እየነጣጠለ ወደተለያዩ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች በሃይል ማሠማራቱ በስደተኞቹ ተነቅፏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን፣ ዩኒሴፍ እና ሌሎች አለማቀፍ የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፤ የጣሊያን መንግስት በስደተኞቹ ላይ ያለማስጠንቀቂያ የወሰደውን ከመኖሪያቸው የማፈናቀል እርምጃ በፅኑ አውግዘዋል፡፡
“አማራጭ የመኖርያ ቤት መፍትሄ ያለመኖሩ ብጥብትና ሁከት መፍጠሩ አሳፋሪ ነው” ያለው ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን፤ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ስደተኞች “ክብራቸውን የሚጠብቅ መፍትሄ” እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል “የመኖሪያ ፈቃድ የሌላችሁ ህገ ወጦች ሃገሬን ለቃችሁ ውጡ” በማለት ቀነ ገደቡን ለሁለተኛ ጊዜ ያራዘመው የሣኡዲ አረቢያ መንግስት፤ ከእንግዲህ በኋላ እርምጃ ወደ መውሰድ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡ ይህን መነሻ አድርጎ በኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከትናንት በስቲያ ሰፊ ሪፖርት ያወጣው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ በህገ ወጥ መንገድ በሳኡዲ ከሚገኙ 10 ሚሊዮን የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መካከል ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ጠቁሞ፣ የእኒህ ኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ በኃይል ከሀገሪቱ መባረር እንደሚሆን ገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ አሁንም ኢትዮጵያውያኑን ከሀገሪቱ ለማስወጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁሞ, በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ግን አሳሳቢ መሆኑን ሳይገልፅ አላለፈም፡፡
በመላው ዓለም በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ቤት የሚልኩ ሲሆን በ2015 የወጣ ሪፖርት፤ በአመት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ (ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ) እንደሚልኩ ይጠቁማል፡፡ አይኦኤም የተሰኘው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም ባቀረበው ጥናት ደግሞ በመላው አለም በስደት ላይ የሚገኙ 3 ሚ. ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት ከሚልኩት ገንዘብ ውስጥ 78 በመቶው በህገ ወጥ መንገድ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ 

Read 4493 times