Saturday, 19 August 2017 14:54

ተቃዋሚ ፓርቲዎች - ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

   “ስብሰባ ስለተከለከልን ከህዝብ ጋር መገናኘት አልቻልንም”

      በቅርቡ የጋራ የፖለቲካ ተግባራትን ለማከናወን ተስማምተው እየተንቀሳቀሱ ያሉት ሠማያዊ እና መኢአድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላ ወይም
ከምርጫ 2007 በኋላ የመጀመሪያቸውን ህዝባዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ መብራት ሃይል አዳራሽ ሊያካሂዱ ቢያስቡም ከከተማ አስተዳደሩ አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኙ አስታውቀዋል፡፡
የፓርቲዎቹ አመራሮች፣ ከህዝብ ጋር ካልተገናኘን እንዴት የፖለቲካ ስራ መስራት ይቻለናል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይሄን ሃሳብ ይጋሩታል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ አለመሻሻሉ አሳሳቢ ነው ሲሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የፓርቲ አመራሮችንና የመንግስት አካላትን አነጋግሮ፣ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡

                         “ፓርቲዎች ለምርጫ እንዴት ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይችላሉ?”
                              ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (የመድረክ አመራር)

      በኢትዮጵያ አሁንም የፖለቲካ ምህዳሩ ከባድ ችግር ላይ ነው፡፡ የመሻሻል ምልክት እንኳን እያሳየ አይደለም፡፡ ለሁሉም ሜዳው ነፃ ያለመሆኑ ጥያቄ፣ አሁንም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላም እንዳለ ነው፡፡ ትልቁ ችግር ያለው ካድሬዎቹ ጋ ነው፡፡ አዋጁ ቢነሳም ካድሬዎቹ ለህግ እስካልተገዙ ድረስ ፓርቲዎች ህዝብን በአላማቸው ስር ለማሰለፍ የሚያደርጉት ጥረት የትም አይደርስም፡፡ ስብሰባ የመጥራት፣ ሰልፍ የማድረግ ጉዳይ፣በገዥው ፓርቲ አስተሳሰብ ውስጥ አስፈሪ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ  የማይሞከር ነው የሚሆነው፡፡
በድርድር እነዚህን መብቶች ለማስጠበቅ መሞከር ደግሞ ከህገ መንግስቱ አስተሳሰብ ውጪ ነው፡፡ የመሰብሰብ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የፖለቲካ ስራዎችን የማከናወን ተግባር በህገ መንግስቱ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በህገ መንግስቱ ለተቀመጠ ጉዳይ ድርድር አያስፈልገውም። “የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽ/ቤት መክፈት አይችሉም” የሚል ህገ መንግስቱ ላይ በሌለበት ሁኔታ፣ “ጽ/ቤት በየክልሉ እንዲኖራቸው ይደረጋል በሚል ተስማምተናል” መባሉ አስገራሚ ነው፡፡ አስቀድሞ ህገ መንግስቱ ላይ በሰፈረ ጉዳይ ላይ ምንድን ነው የሚስማሙት? እንደኔ፣ በዚህች ሀገር የፖለቲካ ፓርቲ ተግባራት እንዳይከናወኑ እንቅፋት የሚሆኑት ካድሬዎች ናቸው፡፡
ኢህአዴግ እንቅፋት ፈጣሪ ካድሬዎችን ከህዝቡ ላይ እስካላነሳ ድረስ በምንም መመዘኛ የተረጋጋ የፓርቲ ፖለቲካ ማከናወንም ሆነ ህዝብና ሀገርን የሚያረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም። አሁንም የሀገሪቱ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ያለው በኢህአዴግ እጅ ነው፡፡ ትንሽ የህዝብ እንቅስቃሴ ሲያይ እንመካከር ብሎ ይጠራናል፡፡ ግን እስካሁን ምንም የፈየደው ነገር የለም፡፡
መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ህገ መንግስቱ ነው መፈተሽ ያለበት፡፡ በምርጫ መንግስት እንዲለወጥና ህዝብ በምርጫ ሥርዓቱ እንዲተማመን ከተፈለገ፣ የምርጫ ቦርድን ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር መርጦ የማቅረቡ ጉዳይ ከህገ መንግስቱ መነሳት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ህገ መንግስቱን ይነካል፡፡ ትልቁ የዚህ ሀገር የፖለቲካ ካንሰር የምርጫ ቦርዱ አደረጃጀት ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ለመቀየር ፍቃደኛ እስካልሆኑ ድረስ ፓርቲዎችስ ለምርጫ ፖለቲካ  እንዴት ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይችላሉ? ህዝቡና ፓርቲዎች በዓላማ እንዴት ሊተሳሰሩ ይችላሉ?
እስካሁን እንደምናየው እነዚህን ለማረጋገጥ የኢህአዴግ የተግባር ቁርጠኝነት ያን ያህል አይደለም፡፡ ይህቺን ሀገር በዲሞክራሲ ፈር ውስጥ የማስቀመጥና ያለማስቀመጥ ጉዳይ ነው አሁን ከፊታችን የሚጠብቀን ፈተና፡፡ ፈሩን ለማስያዝ ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ወሳኝ ነው። እንደኔ የኢህአዴግ አካሄድ ለምንፈልገው ዲሞክራሲዊ አሰራርና አካሄድ አስቸጋሪ ነው፡፡ የዚህች ሀገር ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ አሰራርና አካሄድን ማስፈን ብቻ ነው፤ ዝም ብሎ ማምታታቱ የትም አያደርሰንም፡፡ እኛ ለውጥ በምርጫ ስርአት መሆን አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡ ይሄ እምነታችን እንዴት ወደ ውጤት ይምጣ ነው፣ አሁን የተጋረጠብን ፈተና፡፡

---------------------

                     “ህዝብ ሰብስበን ስናወያይ ገዥው ፓርቲም ይጠቀማል”
                         ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የመኢአድ ፕሬዚዳንት)

      በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ብዙ ፖለቲካዊ ችግር አለ፡፡ መንግስት በሀገሪቱ ግርግርና ተቃውሞ ባጋጠመበት ወቅት “የፖለቲካ ምህዳሩ ይሰፋል” እያለ ቃል ሲገባ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደመሆናችን መጠን፤ የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ብለን የተሰባሰብን ነን፡፡ ለሰላማዊ ትግል እጅ የሰጠን መሆናችን በግልጽ እየታወቀ ነው፣ ስብሰባ ማድረግ አትችሉም የተባልነው፡፡ አሁን ስብሰባ ካላደረግን ታዲያ መቼ ነው ከህዝብ ጋር የምንሰበሰበው? መቼ ነው ለህዝብ አላማችንን አስታውቀን እንዲመርጠን የምናደርገው? እንዴት ነው የፓርቲ ፖለቲካ ልናካሂድ የምንችለው? እኛ ህዝብ ሰብስበን ብናወያይ እኮ ተጠቃሚዎቹ እኛ ብቻ አይደለንም፣ ገዥው ፓርቲም ተጠቃሚ ነው፡፡ እውነተኛውን የህዝብ ስሜት ሊያዳምጥ የሚችልበትን እድል ነው እንፍጠርልህ እያልን ያለነው፡፡ የአዳራሽ ስብሰባ ስንጠይቅ መቼም ከማንም የተደበቀ አይደለም፤ ለሁሉም ክፍት ነው። የኛ ጥረት፣ የሀገራችንን ፖለቲካ ከድንጋይ ውርወራ አላቀን፣ የውይይትና የክርክር በማድረግ ለማዘመን  ነው፡፡ በየአዳራሹ የሚደረጉ ስብሰባዎችን ብንጠራ፣ ህዝብ ነው የሚናገርባቸው፡፡ አሁን ፍቃድ የተነፈገን የአዲስ አበባው ስብሰባ አንዱ አጀንዳችን፣ በንግዱ ማህበረሰብ አካባቢ ያሉ ችግሮች ላይ መወያየት ነው። ይሄ  ውይይት ለኛ ብቻ ነው የሚጠቅመው ማለት ነው? አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ተቃዋሚዎች አንዱ ተግባራችን የመንግስትን ድክመቶች ማጋለጥ ነው፡፡ ይሄ መብት ነው፡፡ ታዲያ ይሄን መብት ከተነፈግን፣ እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ እንዴት ይመጣል? እኛ ባለን አቅም ነው የምንታገለው፡፡ መንግስት እንደ መንግስትነቱ ሆደ ሰፊ መሆን አለበት፡፡ ህዝብ የሚያቀርበውን ብሶት ማዳመጥ አለበት፡፡
“ስልጣን የሚመጣው ከአፈሙዝ ነው” የሚለው የማኦ ዜዱንግ አስተሳሰብ መቅረት አለበት፡፡ እኛ በሠላማዊ ትግል የምናምን ሰዎች ነን፡፡ ሠላማዊ ትግል ደግሞ ስብሰባ እና ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግን በዋናነት ያካተት ነው፡፡ በእነዚህ መንገዶች ከህዝብ ካልተገናኘን የፖለቲካ ስራ መስራት አንችልም፡፡ አሁንም ቢሆን ገዥውም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ማድረግ ነው ያለብን። የህዝብ ጥያቄ መስመር ስቶ ችግር ከመፍጠሩ በፊት በፓርቲዎች በኩል የሚሰባሰብን የህዝብ ድምፅና ብሶት የማዳመጥ ጉዳይ፣ከብልህ መንግስት የሚጠበቅ ነው፡፡
አሁንም ለዚህች ሃገር መፍትሄው የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ነው፡፡ ፓርቲዎች አስተሳሰባቸውን ለህዝብ ሸጠው በዙሪያቸው ዜጎችን መያዝና ሠላማዊ ትግልን ማለማመድ አለባቸው፡፡ ይሄ ካልተደረገ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡

---------------------

                              “እኛም የሃገሪቱ የመፍትሄ አካል መሆን እንፈልጋለን”
                                 አቶ የሸዋስ አሰፋ (የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር)

      አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቷል ተብሏል፡፡ ህገ መንግስቱ የመሰብሰብ መብት አጎናጽፎናል። መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን አስተካክላለሁ ብሎ ቃል ገብቷል፡፡ በዚህ ወቅት የአዳራሽ ስብሰባ መከልከላችን ብዙ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርግ ነው፡፡ ስብሰባ ማድረግ የምንከለከል ከሆነ፣ እንዴት ነው የፖለቲካ ስራ የምንሰራው? ህዝቡንስ እንዴት ማረጋጋትና ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ማምጣት ይቻላል?
እኔ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ሁልጊዜ ምርጫ ሲደርስ፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ሌላው፣ ”ተቃዋሚዎች ምንም አማራጭ ሀሳብ የላቸውም፤ ዝም ብለው ነው” ሲሉ ይሰማል፡፡ ይሄ የሚባለው እንግዲህ አማራጫችንን እንዳናቀርብ እየተከለከልን ነው፡፡ እኛ ዝም ብለን ጊዜ ለማጥፋት አይደለም የተሰባሰብነው፡፡ ለምንወዳት ሀገራችን ይበጃል ያልነውን አማራጮች ይዘን ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ፣ ሀገር በሚያተራምስባቸው ጉዳዮች ሳይቀር አማራጮችን ለማቅረብ ዝግጁ ነን፤ ግን ይሄ ያለ ሚዲያ፣ ያለ ህዝባዊ ስብሰባ እንዴት ይሆናል? ሁለቱም ለኛ ክልክል ናቸው፤ ለገዥው ፓርቲ ግን የተፈቀዱ ናቸው፡፡ ታዲያ እንዴት ህዝቡ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ አማራጭ ውጭ ያለውን ይስማ? በየት በኩል ህዝቡን እናግኝ? እናውቃለን፤ገዥው ፓርቲ ፍርሃት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ፍርሃት ተይዞ፣ እኛንም ለህዝባችን ምንም አማራጭ እንዳናቀርብ እያደረገን ነው፡፡ ያ ደግሞ ሀገሪቱን ችግር ላይ የሚጥል ነው፡፡
መንግስት ለህዝብ ማሰብ አለበት፡፡ የፓርቲዎችን ተግባር ማክበር አለበት፡፡ እኛም እኮ ህዝባችንን ማረጋጋት እንፈልጋለን፡፡ ይሄን እድል ለምን እንነፈጋለን? እኛ ህገ መንግስቱን በማክበር ነው የአዳራሽ ስብሰባ ፍቃድ እየጠየቅን ያለነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ሲሆን ግን ማሳወቅ በቂ ነው፤ ይሄኛው በር ከተዘጋ እንግዲህ ወደ ሰላማዊ ሰልፉ ልንሄድ እንችላለን ማለት ነው፡፡
ፓርቲዎች ሲቋቋሙ አንዱ አላማቸው በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍ ነው፡፡ ለማሸነፍ ደግሞ ህዝብን በአመለካከታችን ላይ ማሳመን አለብን፡፡ ማሳመን የምንችለው ደግሞ እንዲሁ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠትና ቢሮአችን በመቀመጥ አይደለም። በተለያዩ አማራጮች ከህዝብ ጋር በመገናኘት ነው። የመገናኛ መንገዶች በሙሉ ከተዘጉብን ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን? ከሠላማዊ ትግል ውጪ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ችግራችንን በሚዲያ ለህዝብ ማሳወቃችን ምክንያቱም ይኸው ነው፡፡ ያለን አማራጭም ይኸው ብቻ ነው፡፡
አሁን ላይ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ጥሩ አይደለም፡፡ ገዥው ፓርቲ ከካድሬዎቹ ጋር ካልሆነ በቀር  ከህዝብ ጋር እየተገናኘ አይደለም፡፡ ይሄ የራሱ የፖለቲካ ስልት አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ግን ጉልበታችን ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ፕሮግራማችንን አይቶ እንዲተቸን እንፈልጋለን፡፡ መቼም የታመመ ሰው በማስታገሻ ሊድን አይችልም፤ በፈዋሽ መድሃኒት እንጂ፡፡ እንግዲህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስታገሻ ነበር፤ አሁን ደግሞ ፈዋሽ መድሃኒት ያስፈልጋል፡፡ ከመድሃኒቱ አንዱ ከህዝብ ጋር የሚደረግ ነፃ ውይይት ነው፤ እኛ ደግሞ የሃገሪቱ የመፍትሄ አካል መሆን እንፈልጋለን፡፡ የሃገሪቱ የፖለቲካ በሽታ መድሃኒቱ፣ በውይይት የህዝብን ስሜት ማዳመጥ ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም ያለን አንድ ሃገር ነው፡፡ ስናስብ እንደ ሃገር ነው መሆን ያለበት፡፡

-----------------

                         “የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ ዜጎች መበረታታት አለባቸው”
                            ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራት (የኢዴፓ ም/ፕሬዚዳንት

      አስቀድሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀበት ዋነኛ ምክኒያት፣ በአጠቃላይ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታችን በጥሩ ሂደት ላይ ስላልነበረ፣ ህዝቡ በራሱ መንገድ እነዚህን መብቶቹን ለመጠየቅ እንቅስቃሴ በማድረጉ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ደግሞ የችግሩን ምክንያት አውቆ መፍትሄ ለማበጀት ጥረት አልተደረገም፡፡ ከሰሞኑም የምሰማቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች መነሻቸው ይሄው ነው፡፡
አሁንም ቢሆን በህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን በቁርጠኝነት ለመመለስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ግን ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ያለ አይመስልም፡፡ ህዝብን በፓርቲ ጥላ ስር ለማሰባሰብና የተበታተነን ለዲሞክራሲ የሚደረግ አደገኛ አካሄድ ለመሰብሰብ፣ ፓርቲዎች ጉባኤ እንዲያካሂዱ ምቹ ሁኔታ አለመፈጠሩ የሀገሪቱ ፖለቲካ አንዱ ችግር ነው። እስካሁንም ድረስ አንዳንድ የፓርቲ አባሎቻችን ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው፡፡ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ፣ ለፓርቲ የፖለቲካ ክንዋኔዎች በመጠኑ እንኳ ገርበብ ያለ ሁኔታ አለ ማለት አይቻልም። በሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርአትን ለማጎልበት፣ የጉባኤ ፖለቲካ አንዱና ወሳኙ ነው፡፡ ከህዝብ ጋር ጉባኤዎች መደረግ አለባቸው፡፡
በእርግጥ ከገዥው ፓርቲ ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር ጅምሩ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎችንም በሚያካትት መልኩ መካሄድ አለበት፡፡ ይህ ከተደረገ የመድብለ ፓርቲ ስርአቱን አንድ እርምጃ ማራመድ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግስትም የገባውን ቃል መጠበቅ አለበት፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን አንጥሮ በማውጣት በኩል መንግስት ያሳየው ድክመት፣ አሁንም ከስጋት እንዳንላቀቅ አድርጎናል፡፡ እርግጥ ነው አሁንም አልረፈደም፡፡ መንግስት አዲስ አይነት ስልት መንደፍ ይችላል፡፡
የሀገሪቱ ፖለቲካ የተረጋጋ እንዲሆን ዋነኛ መፍትሄው፣ ገዥው ፓርቲ የመረጠውንም ያልመረጠውንም ህዝብ ሀሳብ መቀበል ነው፡፡ እስከ ዛሬ የሚያደርጋቸው የውይይት መድረኮች ባህሪ መቀየር አለበት፡፡
ችግሮችን በትክክል አንጥረው የሚነግሩትን ነው ማወያየት ያለበት፡፡ የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ ዜጎች መበረታታት አለባቸው፡፡ ሀሳባቸውን በነፃነት የሚያራምዱ ዜጎች በእስር የሚሸማቀቁ ከሆነ ችግሩን መፍታት አይቻልም፡፡ ስለዚህ መንግስት ሆደ ሰፊ በመሆን ህዝብን በማንኛውም ጉዳይ ላይ ማወያየት አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ የሀገሪቱ ሁኔታ አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ 

Read 4722 times