Sunday, 30 July 2017 00:00

ትናንሾቹን ዓሳዎች እኛ እንይዛቸዋለን፤ ትላልቆቹ እርስ በርስ ይበላላሉ

Written by 
Rate this item
(25 votes)

 አንድ የሩሲያ ተረት እንዲህ ይላል፡-
ባልና ሚስት ዓሳ ሊያጠምዱ ወደ አንድ ሀይቅ ይወርዳሉ፡፡ ገና መንገድ ሳሉ፤
ሚስት፤
“የሚያዙት ዓሳዎች ግማሾቹ ለልጆቻችን ምግብ ይሆናሉ፡፡ ግማሾቹን ደግሞ ወደ ገበያ ወስደን እንሸጣቸውና፤ ሌሎቹ ኑሯችንን ማሟያ ገንዘብ ያመጣሉ፡፡” ትላለች
ባል፤
“እስቲ መጀመሪያ ዓሳዎቹ ይገኙ፡፡ ከዚያ ደግሞ መረባችን የሚይዘውን ብዛት እንይ፡፡ የዛሬ ዓሳዎች እኮ እንደ ድሮዎቹ ዓሳዎች በማንኛውም መረብ ውስጥ ተንደርድረው ጥልቅ አይሉም”
ሚስት፤
“ዓሳ ዓሳ ነው፤ ብርብራ ካየ ዘሎ ጥልቅ ማለቱ አይቀሬ ነው”
ባል፤
“አይምሰልሽ፤ እኛ ያለን የዱሮ መረብ ነው፡፡ ዓሳዎቹ የአሁን ጊዜ ናቸው፡፡ የዱሮ መረብ በቶሎ ይበጣጠሳል፡፡ ወይ መረቡ በአዲስ ክር መሰራት አለበት፤ አሊያም ሙሉ በሙሉ ተለውጦ አዲስ መሆን አለበት፡፡ እንጂ የዛሬን ዓሶች ችሎ አፍኖ አያስቀምጥም”
ሚስት፤
“ግዴለህም ባሌ፤ አታስብ፡፡ ሀይቁም ያው የዱሮው የምናውቀው ሀይቅ ነው፡፡ ዓሳዎቹም የዱሮዎቹ ዓሳዎች ናቸው፡፡ ድንገት ተነስተው ብልጥ ዓሳዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እኛ ተጃጅለን፤ ቅልጥፍና አንሶን የማምለጥ እድል ካልሰጠናቸው ባንድ አፍታ እጃችን እናስገባቸዋለን”
ባል፤
“እስቲ ይቅናን! ወዳጄ”
ተያይዘው እሀይቁ ዳርቻ ደረሱ፡፡ መረቡን ዘረጉት፡፡ የተያዙት ግን በጣም ደቃቃ ደቃቃ ዓሳዎች ብቻ ናቸው፡፡
ሚስት፤ በጣም ገረማትና፤
“ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል፤ መረቡ ትናንሽ ዓሳዎችን ብቻ እየመረጠ ነው እንዴ የሚይዘው?” ስትል ባሏን ጠየቀችው፡፡
ባሏም፤
“ይሄውልሽ ጊዜው እንደዚህ ሆኗል፡፡ ትናንሾችን ዓሳዎች እኛ እንይዛቸዋለን፤ትላልቆቹ እርስ በርስ ይበላላሉ!!”
*       *      *
ዘመኑ እንደዚህ ነው! ትላልቆቹ ሌቦች አይነኩም፡፡ ትናንሾቹ ብቻ ይጠመዳሉ፡፡ ባለ ከፍተኛ ንግድና ሀብት ባለቤቶች የሚነካቸው የለም፡፡ ትናንሾቹ ጉልት ቸርቻሪዎች፣ ከገቢ ገማች እስከ ወንጀል መርማሪ ይፈራረቅባቸዋል፡፡ ይህንን ዕውነታ መለወጥ የትራንስፎርሜሽን ያህል ከባድ ነው፡፡ ምነው ቢሉ፣ ከባድ ከባድ፣ ንክኪ በሥሩ አለ፡፡ አብ ሲነካ ወልድ ይነካ ነው!
ስለሆነም የላይኞቹ ክፉኛ ይጮሀሉ!! የታችኞቹ ወንጀሉ የዓለም መጨረሻ እንደሆነ አድርገው ያወራሉ፤ ይጮሃሉ! ባለ ፎቆቹ፣ ባለ ቪላዎቹ፤ ባለ ብዙ ኤከር መሬት ባለቤቶቹ፤ ንፁሀን ሆነው ቁጭ ይላሉ! በየሸንጎውም ላይ ጨዋዎቹ እነዚህ ባለፀጎች ይሆኑና የክብር እንግዶች ተብለው ክብር ትሪቡን ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ አዳዲስ ተቋም ሲመረቅ መድረኩን ይሞላሉ፤ ግንባር ግንባር ቦታውን ያጣብባሉ! በደህና ጊዜ የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ እያሉ፣ የአንበሳውን ድርሻ ሲቀራመቱ የነበሩ ናቸው፡፡
በሌላ ወገን፤ ዝቅተኛው መደብ፣ ሱቁ ሲመዘበር፣ ያልሆነ ዋጋ ሲተመንበት፣ ሰሚ ያጣ ጩኸት ሲጮህና የአገር ያለህ፣ የመንግሥት ያለህ ሲል፤ “ስህተት ያለ ነገር ነው፤ ለቅሬታ ሰሚ አመልክት እንጂ ምን ታካብዳለህ” ይሆናል የምላሹ ዘይቤ! ሱቃቸውን ዘግተው የጠፉ፣ ዕቃቸውን ያሸሹ፣ ንብረት አናስገምትም ያሉት ዕውን ከግንዛቤ ማነስ ነውን? ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጎስ፣ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው ተመልሰዋል ማለት ዕውን ነባራዊው ሀቅ ነውን? መሬትና ሰማይን ያነካካ ገመታ፣ የምስኪኑ ችርቻሮ ነጋዴ ደስታ ሊሆን ይችላልን? ግልፁ ጨዋታ ሌባው በወርቅ አልጋ፣ በእርግብ ላባ ላይ፣ ከዝሆን ጥርስ በተሰራ ፎቅ ውስጥ መኖሩ ነው! ማን ይንካው? የማይታረቁ ግጭቶች ተፋጠው ይገኛሉ!! የማይታረቁ ግጭቶችን ለመፍታት ቢያንስ ገጣሚና ፀሐፌ - ተውኔት መንግሥቱ ለማ፤ በባ‘ለ ካባና በባለዳባ’ ተውኔታቸው ውስጥ፡-
“ቀማኛን መቀማት፣ ከሌባ መስረቅ ……….. (‘ቅ’ ይጠብቃል)
ከማቅለል ከሆነ፣ የድሆችን ጭንቅ ………….. ( ‘ቅ’ ይጠብቃል)
በእኔ ቤት፣ ፅድቅ ነው፣ አንድ ሰው ይሙት …………(‘ሙት’ ይጠብቃል)
አንድ መቶ ሺ ሰው፣ ኪኖር በምፅዋት!!” …..…………(‘ዋት’ ይጠብቃል)
ያሉትን ማስታወስ ግድ ይሆናል!!
“እገሌ የእኛ ወገን ነው አይነካም”፤ “እገሌ የሌላ ወገን ነው፤ በለው!”፤ “እገሌ የማንም አይደለም ጊዜውን ይጠብቅ” …. “እነ እገሌን ተውዋቸው የኛ ናቸው” … “እነገሌን ግፏቸው ጠላት ናቸው” … ዓይነት አካሄድ፤ ቢያንስ ‹ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ› አለማወቅ ይሆናልና ልብና ልቦና ይስጠን!!
የሀገራችን አንድ ፈታኝ የሆነ ችግር፣ “ህዝቡ አያውቅም” የሚለው መላምታዊ ድንቁርና ነው፡፡ የነቃው፣ ህዝቡን በትግሉ ሲያግዝ የኖረው፣ በቀውጢው ሰዓት ታጋዮችን ከክልል ክልል ሲያሳልፍ የከረመው፤ ትልቅ አድናቆት ሲቸረው የኖረ ህዝብ፤ ድንገት ድንቁር ሊል ፈፅሞ አይችልም፡፡ እንደ ሁልጊዜው የግምት ስህተት አለ!! “ይሄን ስናሰላ፣ እንዲህ እንዲህ ያለ ችግር ነበረብን” የምንለውን እንኳ ዛሬ ስለተውነው፤ ከስህተት መታረም የሚለው ቁም - ነገር ጨርሶ ጠፍቷል፡፡ ከዚህ ይሰውረን!!
ትናንሾቹን ዓሳዎች አሳዶ የሚበላቸው አይጠፋም - አቅም የላቸውምና! ትላልቆቹ ግን እርስ በርስ እስኪበላሉ መጠበቅ ነው! ከዚህም ያውጣን!!

Read 7025 times