ሰሞኑን የፊልሙ ፕሮዱዩሰሮች በሰጡት መግለጫ፤ ማንዴላን ለመተወን ከደቡብ አፍሪካዊ ውጭ ሌላ ተዋናይ አንፈልግም ማለታቸውን የዘገበው ጋዜጣው፤ የማያሳምን ውሳኔ በሚል ነቅፎታል፡፡ የ”ጎልደን ግሎብ” ተሸላሚው ኢድሪስ ኤልባ በፊልሙ ላይ ማንዴላን ለመተወን ዋና እጩ እንደነበር የጠቀሰው “ዘ ጋርድያን”፤ የ39 ዓመቱ የፊልም ተዋናይ የደቡብ አፍሪካ ትውልድ ቢኖረውም በዜግነቱ እንግሊዛዊ በመሆኑ እድሉን እንዳጣ አመልክቷል፡፡ ፊልሙን በተሳካ መንገድ ለመስራት ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ተዋናዮች መወዳደር ነበረባቸው ያለው ጋዜጣው፤ በቂ ልምድ የሌላቸው የደቡብ አፍሪካ ተዋናዮች ይሰሩታል መባሉንም አጣጥሎታል፡፡ ከእስር ከተፈቱ 22 ዓመት በሆናቸው የ94 ዓመቱ ኔልሰን ማንዴላ ህይወት ዙሪያ የተለያዩ ፊልሞች የተሰሩ ሊሆን ማንዴላን በመተወን ትላልቅ የሆሊውድ ተዋናዮች መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡ ከተዋናዮቹም መካከል ዳኒ ግሎቨር፤ ሲድኒ ፖይተርና ሞርጋን ፍሪማን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡