Wednesday, 04 April 2012 11:02

ተሸላሚዎቹ የቴአትር ኮከቦች ምን አሉ?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“ተስፋ ኢንተርቴይመንት” ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የቴአትር ፌስቲቫል ባለፈው ሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2004 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን 10 ቴአትሮችን አወዳድሮ ኮከብ ተዋንያን፣ አዘጋጅ፣ ደራሲና በአጠቃላይ አቀራረብ በሚሉ ዘርፎች 14 ተሸላሚዎችን በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አዳራሽ ሸልሟል፡፡ ተመልካች የሰጠው ድምጽ 60 ከመቶ፣ የባለሙያዎች ግምገማ 40 ከመቶ ዋጋ ተሰጥቶት የተሸላሚዎች ምርጫው እንደተካሄደ በእለቱ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ በመታየት ላይ ካሉ 25 ቴአትሮች 10ሩ በምን መመዘኛ ለውድድር እንደተመረጡ የተገለፀ ነገር የሌለ ሲሆን፤ ባለሙያዎች ቴአትሮቹን የገመገሙበት ሂደትና መስፈርትም ይፋ አልተደረገም፡፡ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ዘግይቶ ቢጀምርም ሳይንዛዛ በፍጥነት በመጠናቀቁ ታዳሚውን ከምሬት ታድጓል፡፡ የውድድሩ አሸናፊዎች የኮከብ ምስል የተቀረፀበት ዋንጫና የ10ሺህ ብር ሽልማት ያገኙ ሲሆን፤ በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ላይ ተሸላሚዎች የተሰማቸውን ስሜትና አስተያየት ለዝግጅቱ ተካፋዮች ገልፀው ነበር፡፡

ተሸላሚዎቹ የቴአትር ኮከቦች ምን አሉ?

ምርጥ የቴአትር ደራሲ - ኃይሉ ፀጋዬ

ምርጥ ሴት አዘጋጅ - የሻሽወርቅ በየነ

ምርጥ ወንድ አዘጋጅ - ዳግማዊ ፈይሳ

በአጠቃላይ ዝግጅት - አዜብ ወርቁ

የ”ዕጣ ፈለግ” ኮከብ ተዋናይ - ታጠቅ ነጋሽ

የ”ቤተሰቡ” ኮከብ ተዋናይ - ሄኖክ ብርሃኑ

የ “ገፅ ሁለት” ኮከብ ተዋናይ - ደምሴ በየነ

የ“እልበት” ኮከብ ተዋናይት - ሜሮን ጌትነት

የ”ሰማያዊ ዓይን” ኮከብ ተዋናይ - ተስፋ ብርሃኔ

የ “ረመጥ” ኮከብ ተዋናይት - ባዩሽ አለማየሁ

የ”ሦስተኛው ችሎት” ኮከብ ተዋናይ - አበበ ፈለቀ

የ”ጓደኛሞቹ” ኮከብ ተዋናይ - ሸዋፈራሁ ደሳለኝ

የ”ሚስት ያለህ” ኮከብ ተዋናይ - ሽመልስ አበራ

የ”ደመነፍስ” ኮከብ ተዋናይ - አለማየሁ ታደሰ

በዘካሪያስ ብርሃኑ የተደረሰው “ዕጣ ፈለግ” በሁለት ባለሙያዎች ነው የተዘጋጀው -በደራሲውና ከተዋናዮቹ አንዱ በሆነው በታጠቅ ነጋሽ፡፡ የቴአትሩ ኮከብ ተዋናይ በመሆን ያሸነፈውም ታጠቅ ነጋሽ ነው፡፡ ተዋናዩ ለሽልማቱ በመብቃቱ የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ “ጤናና ዕድሜ ሰጥቶኝ ለዚህ ያደረሰኝ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ “ዕጣ ፈለግ” ከመነሻው ጀምሮ ብዙ ደክመንበታል፡፡ በተለይ ለደራሲው ልዩ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ወዳጆቼን በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡” ብሏል፡፡

 

በደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ የቀረበው “ቤተሰቡ” ቴአትርን ያዘጋጀው ዳግማዊ ፈይሳ ነው፡፡ የዚህ ቴአትር ኮከብ ተዋናይ ሆኖ የተሸለመው ሄኖክ ብርሃኑ ደግሞ “ደራሲውንና አዘጋጁን አመሰግናለሁ፡፡ ለዚህ ክብርና ማዕረግ ላበቃኝ ለድንግል ልጅ ክብርና ምስጋና ይግባው” ሲል ስሜቱን ገልጿል፡፡

የ“ገጽ ሁለት” ደራሲያን ተሻለ ወርቁ፣ ባዩሽ አለማየሁ፣ ዝናሽ ጌታቸውና ብሌን ጌታቸው ሲሆኑ ቴአትሩን ያዘጋጁት ዓለምፀሐይ እጅጉና አብዱልከሪም ጀማል ናቸው፡፡ በዚህ ቴአትር ኮከብ ተዋናይ ሆኖ የተመረጠው ደምሴ በየነ ስሜቱን ሲገልጽ፤ “ሞዴል ከማደርጋቸው ከአለማየሁ ታደሰ፣ ከሽመልስ አበራና ከፈለቀ አበበ ጋር እዚህ መድረክ ላይ መቆም በመቻሌ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፡፡”

“እልበት” በዳንኤል ሙሉነህ ተደርሶ በአልአዛር ሳሙኤል የተዘጋጀ ቴአትር ሲሆን  ኮከብ ተሸላሚ የሆነችው ተዋናይት ሜሮን ጌትነት እንዲህ ብላለች፤ “እጅግ ከማከብራቸው አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር ሞገስ ሰጥቶ ላቆመኝ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ ሁሉም ቴአትር በራሱ ትምህርት ቤት ነውና አምነውብኝ ቴአትር ላሰሩኝ፣ ድምፁን ለሰጠኝ ሕዝብና ይህንን መድረክ ያዘጋጃችሁትን ሁላችሁንም አመሰግናለሁ፡፡”

ተስፋዬ ሽመልስ የ”ሰማያዊ ዓይን” ደራሲ ነው፡፡ ቴአትሩን ያዘጋጀው ተስፋ ብርሃኔ፤  ኮከብ ተዋናይ ሆኖ በመመረጡ የተሰማውን ስሜት ሲገልፅ፤ “ክብሩ ሁሉ አምላክ ተክለሃይማኖትና የእናቴ ኪዳነምህረት ይሁን” ካለ በኋላ፣ በመውደቅ መነሳቱ ውስጥ ያልተለዩት ጓደኞቹን አመስግኗል፡፡ ወጣት ባለሙያዎችን በማበረታታት ላይ ለሚገኘው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ያለውን አድናቆትም ገልጿል፡፡

በሕይወት አራጌ የተዘጋጀው “ረመጥ” ቴአትር ደራሲዋ ባዩሽ አለማየሁ፣ በኮከብ ተዋናይነት በመመረጧ የተሰማትን ስሜት ስትገልጽ፤ “ሽልማት፣ ክብርና በሰው ፊት ሞገስ እንዳገኝ የረዳኝ አምላክና እናቱ የተመሰገኑ ይሁኑ፡፡ ለዚህ አሸናፊነት ድምፁን የሰጠኝን ተመልካች፣ የቴአትር ቡድን አባላት፣ ባለቤቴንና ቤተሰቦቼንም አመሰግናለሁ፡፡” ብላለች፡፡በአያሌው ሞገስ የተደረሰውን “ሦስተኛው ችሎት” ቴአትር መሠረት ሕይወትና ፍሬሕይወት ተሻለ ያዘጋጁት ሲሆን በኮከብ ተዋናይነት ፈለቀ አበበ ተመርጦበታል፡፡

“ከሁሉም አስቀድሞ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ አድናቂዎቼን፣ የልጄን እናት፣ ልጄን እወዳችኋለሁ፡፡ ባለፈው ዓመት በፊልም ሙያ ላይ ያገኘሁትን ሽልማት ወደ ፊልም ሙያ ለሚመጡ ወጣቶች አበርክቼው ነበር፡፡ የዛሬውን ሽልማት ደግሞ በቴአትር ሙያ ውስጥ ለኖሩ አርቲስቶች መታሰቢያ አድርጌዋለሁ፡፡”

የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ትርጉም ሥራ ነው “ጓደኛሞቹ”፡፡ ቴአትሩን ያዘጋጀችው ገነት አጥላው ስትሆን በቴአትሩ በኮከብ ተዋናይነት የተመረጠው ሸዋፈራሁ ደሳለኝ ነው፡፡ “እኔን ታናሹን በእናንተ ታላላቆች ፊት ክብር ለሰጠኝ ለእግዚአሔር ምስጋና ይግባው፤ ከምማርበት ትምህርት ቤት ከዴክስ ላይ አስነስቶ ወደዚህ ሙያ ያመጣኝ ዳግማዊ ፈይሳ በተሸለመበት መድረክ ላይ ቆሜ መሸለሜ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው፡፡” ሲል ሸዋፈራሁ አስተያየቱን ተናግሯል፡፡

አዜብ ወርቁ “የሚስት ያለህ” የተሰኘው ትያትር ተርጓሚና አዘጋጅ ናት፡፡ በቴአትሩ ኮከብ ተዋናይ ሆኖ የተመረጠው ሽመልስ አበራ ሲሆን ለሽልማት መመረጡን አስመልክቶ ሲናገር፤ “የወደቀን የሚያነሳ የድንግል ልጅ ክብሩ ለዘላለም ይሁን፡፡ አባቴ ለ31 ዓመታት በሰራበት መድረክ ላይ ቆሜ ተሸላሚ በመሆኔ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ‘አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም’ እንደሚባለው ቴአትርን በተመለከተ መንግስት የተኛ ስለሚመስለኝ፣ እንዲነቃ ይህንን መድረክ በማዘጋጀታችሁ አመሰግናለሁ፡፡” ብሏል፡፡

የሻሽወርቅ በየነ ያዘጋጀችው “ደመነፍስ” ትያትርን ወደ አማርኛ የመለሰው አለማየሁ ታደሰ ሲሆን ተርጓሚው በኮከብ ተዋናይነት ተመርጦበታል፡፡ እንደ ብዙዎቹ በቅድሚያ አምላኩን ካመሰገነ በኋላ “እንኳንም የመድረክ ተዋናይ ሆንኩ ባልኩበት ቴአትር በመሸለሜ ተደስቻለሁ…ሄደ መጣ ሲባል እስካሁን የዘለቀው የኢትዮጵያ ቴአትር ተመልካችንም አመሰግናለሁ፡፡

“የዚህን መድረክ አዘጋጆች በተለይ ማመስገን አለብን፡፡  በ1988 ዓ.ም ኢቴቪ እና ሜጋ ያዘጋጁት ሽልማት ታይቶ ነበር ጠፋ፡፡ በ1994 ዓ.ም አክሲማሮስ የሚባል ድርጅት አንድ ዙር የሽልማት መድረክ አዘጋጅቶ በዚያው ቀረ፡፡ በ1996 ዓ.ም በየትም አገር ያልታየና የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ለመሸለም ተሞክሮ በዚያው ተቋረጠ፡፡ አሁን ይህ ዝግጅት አንድ ብሎ ጀምሮ ሁለተኛውን መቀጠሉ ያስመሰግነዋል፡፡” ሲል አስተያየቱን አቅርቧል፡፡

ከ10ሩ ቴአትሮች የተመረጡ 10 ኮከብ ተዋናዮች ሽልማት ካበቃ በኋላ አራት ተጨማሪ ሽልማቶች ተበርክተዋል፡፡ በምርጥ የቴአትር ደራሲነት ኃይሉ ፀጋዬ የተሸለመ ሲሆን የተሰማውን ሲገልጽም “ሴቷ ልጄ ዩኒቨርስቲ ገብታ ቴአትር እያጠናች ነው፡፡ እኔን ለመተካት ያሰበች ይመስላል፡፡ አንድ ቀን እዚህ መድረክ ላይ ትቆሚያለሽ፡፡ በርቺ - መግለጽ የምፈልገው ሌላው ነገር፣ የቅርብ ወዳጄና ሚዜዬ ባለፈው ሳምንት በሞት ተለይቶናል፡፡ ይህንን ሽልማት ለሱ መታሰቢያ አድርጌዋለሁ፡፡” ብሏል፡፡

በምርጥ ሴት አዘጋጅነት ለሽልማት የበቃችው የሻሽወርቅ በየነ በበኩሏ፤ “ጥበብና የጥበብ ፍቅር የሰጠኝ እግዚብሔር ይመስገን፣ ቴአትር የቡድን ሥራ ነው፡፡ በሕብረት ለሰራነው ለሁሉም አባላት ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ቀደምት ባለሙያዎች በብዙ መስዋዕትነት ጥበቡን ለዚህ አድርሰውታል፡፡ እኛ ከእነሱ በተሻለ እየተከፈለን እየሰራን ነው፡፡ ነገ ከዚህም የተሻለ ዘመን እንደሚመጣ የዚህ መድረክ አዘጋጆች አሳይታችሁናል፡፡” ስትል ስሜቷን ገልፃለች፡፡

በምርጥ ወንድ አዘጋጅነት የተሸለመው ዳግማዊ ፈይሳ በበኩሉ፤ “ሰዓሊ መስፍን ሀብተማርያም ጥበብን በትርፍ ጊዜ ሥራነት በሚያዩ ሰዎች ይናደድ ነበር፡፡ እኔ ከቴአትር ወጥቼ ወደ ሚዲያ ሄጃለሁ፡፡ አሁን የተሸለምኩት በትርፍ ጊዜዬ በሰራሁት ሥራ ነው፡፡ ይህ ለእኔ ምፀት ነው፡፡ ለቴአትር ሥራ ሙሉ ጊዜያችንን እንዳንሰጥ ያደረገን የድካማችንን ስላላገኘን ነበር፡፡ እንዲህ መመስገንና መሸለም ካለ ከመድረኩ የጠፉ ሌሎች ባለሙያዎችም ይመለሳሉ፡፡ ባለሙያዎችን ከመድረክ እያሸሸ ያለው የታክስና ቀረጡ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የዚህን መድረክ አዘጋጆች፣ የቡድኔን አባላትና ጓደኞቼን አመሰግናለሁ፡፡”

በአልባሳት፣ በመብራት፣ በመድረክ ቅንብር በአጠቃላይ ዝግጅት ለሽልማት የተመረጠችው አዜብ ወርቁ በተመሳሳይ መልኩ አምላኳን ማመስገኑን አስቀድማ “መተርጐም፣ ማዘጋጀት ትችያለሽ ብሎ ለዚህ ያበቃኝ ባለቤቴ ነው፡፡ ቴአትሩ ምርጥ ተሸላሚ የሆነው የትወና፣ የድምጽ፣ የመብራት፣ የመድረክ…ባለሙያዎች ዕውቀትና ችሎታ ታክሎበት ስለሆነ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ” ብላለች፡፡

ለተሸላሚዎች የተበረከተውን የገንዘብ ስጦታ ከሰባት ስፖንሰር አድራጊዎች ለመሰብሰብ እንደተሞከረ የገለፁት የፌስቲቫሉ አዘጋጆቹ፤ 125 ሺህ ብር መዋጣቱንና ገንዘቡ በቂ ባለመሆኑ ሳምሶን አድቨርታይዚንግ መጠኑ ያልተገለፀ ብር ጨምሮበት ሽልማቱ እንደተዘጋጀ አስታውቋል፡፡ አዘጋጆቹ እንደተናገሩት በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው ሥነሥርዓት በሽልማትም ሆነ በስፋቱ ከዚህ የተሻለ ይሆናል፡፡ በዕለቱ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁና አቶ ሙሉ ገበየሁ የምሽቱ የክብር እንግዶች ነበሩ፡፡

 

 

Read 1960 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 11:12