Wednesday, 04 April 2012 10:56

“ነገ ውብ ነውና ወደ ነገ ተጓዙ” የትርዒቱ ቀን ማስታወሻ

Written by  ሳባውዲን ኑር
Rate this item
(0 votes)

ወደ ራሴ ልመለስ በርካታ ወራት ቃተትኩ። ከውስጤ የሚፈልቁና አንዳንዴም  ለራሴው እንግዳ የሆኑ ጣፋጭ ዜማዎችን መስማት ናፈቀኝ። በኔ ውስጥ የሚዘምረው እርሱ ወደ የት ተሰወረ? ነው ወይስ ዜማዎቹ  ነውጥና ጫጫታ ውስጥ ተውጠው ልሰማቸው ተሳነኝ?

ትናንት ትልቅ ነው ከተባለ የሥዕል ትርዒት ላይ ነበርኩ። በቀለም ውስጥ የተገለጠን ጣፋጭ ዜማ ላዳምጥ፤ከጫንቃዬ በላይ የሆነውን የጫጫታ ቁልል ‘እምሸከምበቱን ብርታት’ ልሸምት።

ግዙፉና የተዋበው የትርዒት አዳራሽ በግድግዳዎቹ ዘርፎች ከተሸከማቸው ሥዕሎች ጋር ዓይነተ ብዙ ዜማዎችን ያቀነቅናል።

ጎብኚዎች በጀማና በነጠላ እየሆኑ ሥዕሎችን ከብበው አፍጥጠዋል።

አንዳንዶቹ በእነርሱና በሥዕሉ መካከል ያለውን መሥመር አግኝተው በመንገዱ መመላለስ ጀምረዋል - ታድለው! ቀጫጭኖቹ መሥመሮች በብርሃን ፍጥነት እየተወነጨፉ የሚያመነጩትን ዜማ ስልት አግኝተዋል። ማየት ብቻ ሳይሆን ማድመጥ፤ማድመጥ ብቻ ሳይሆን በሚያደምጡት የብርሃን መሥመር ውስጥ መራመድም መቻል በጣም ያስቀናል። ሌሎች ደግሞ የሥዕሉም መሥመር ጠፍቷቸው ተጨንቀዋል። ብዙዎቹ ሥዕሎቹ መንገድ፣ ብርሃንና ድምፅ እንዳላቸው እንኳ አልተረዱም። ከበድን መሥመሮች ውስጥ ዜማ ሊያዳምጡ ጆሯቸውን የሚኮረኩሩ ብዙ ሰዎችንም አይቻለሁ-አያድርስ!

አንዳንዶቹም ምንተ-ዕፍረታቸውን ቀድሞም ነፍስ ያልፈጠረበትን የቀለም ድሪቶ እየጠነቆሉ “አያችሁ አይደል ሙቅ እስትንፋስ?... የጸባዖት መንገደኛ የቀስተ ደመና ዳንሰኛ?…” ይላሉ። ሰዓሊዎቹም “አዎ ልክ ነው፤ ቅኔና ሥዕል እንደፈቺው ነው። የስዕል ብጽእናው ከሰዓሊውም ቀድሞ እንዲህ የፍቺው ቋጠሮ ሲበዛ ነው” ይላሉ- አግኝተው ነው?

ለስላሳና ቀጭን የቫዮሊን ድምፅ፣ ትርዒቱን አጅባ ከአንዱ ጥግ ላይ ትስረቀረቃለች። ምናልባትም የዚህች ቫዮሊን ድምፅ ነው እዚህ አዳራሽ ውስጥ የታደሙትን ብዙዎቹን ተመልካቾችና ዜማ ናፋቂዎች አንድ ያደረጋቸው። በተቀረ ግን ያፈጠጡባቸው ሥዕሎች አለያይተዋቸዋል።

ድምፅ አልቦውን ዜማ ላዳምጥ ከአንድ ወጣት ሰዓሊ ሥራ ዘንድ ቀረብኩ። ሥዕሉ ውስጥ ጫጫታና የጣዕር እሪታ የለም ።መሥመሮቹ በስቃይ አይወራጩም። ሥዕሉ ውስጥ በእርግጥ ትግል አለ፤ ቢሆንም በደም እንባ አልተዋጠም።ከእያንዳንዳቸው ፍክ የቀለማት ኅብር ጀርባ ጉጉት አለ - የነገ ጉጉት!! ‘ነገ ውብ ነውና ወደ ነገ ተጓዙ።

ዛሬን በዛሬ ጭፍገት ሳይሆን በነገም ብርሃን ኖራችሁት ተሻገሩ። እዚህ የቀለማት ስብጥር ውስጥ የነገ መርከብ አለና ተሳፈሩበት’ ይላል ሥዕሉ።

እንዲህ የሚናገር ሥዕል በእርግጥም ካጋጠመ ይሳፈሩበት ለቸገራቸው አያሌዎች ታላቅ ስኬት ነው።

በዚህ ዘመን ክረምቱ ላይ ቆሞ መፃኢውን ብሩህ ፀደይ፤ ዝለቱን እየገሰጸ ከጠንካራ መዳፍ ውስጥ የምትፈለቀቀውን ውበት የሚኩል ሰዓሊ ማግኘት ከዕድሎች ሁሉ የላቀ ዕድል ነው።ወደሌላኛዎቹ ረድፎች ሔድኩ።

ከሰፊው የሰው ምሥል ፊት ለፊት ቆምኩ።የተፈጥሮ አድናቂ ብሆንም ከሥዕሎች ሁሉ የሰውን ፊትና የሰው ማኅበራዊ መሥተጋብራት የተኳሉበትን እመርጣለሁ።የተፈጥሮ ውበትም ቢሆን ከሰው ሕይወት፣ ሥነ ልቦናና ፍልስፍና ጋር ሲቆራኝ ዋጋው ከፍ ይልብኛል። የጥበብ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻው ለኔ ሰው ነው።

በእውነቱ አሁን አጠገቡ ያለሁበት የሥዕል ሸራ ነውጥና ትርምስ ይዞ ነው የጠበቀኝ። በየመሥመሮቹ መካከል ግራ መጋባትና መዋዠቅ ነግሷል።

ከአንድ ሰው ፊት ላይ የተለያዩ ድብልቅልቅ ስሜቶች ተበትነዋል። ሁለትና ሦስት እኔነት በአንድ ገፅ ላይ! ውጥንቅጡ የወጣ የተተረማመሰ ዜማ። ነገ እዚህ ውስጥ የለም።ነገውን የተሰረቀ ሰው እንደኛው አብሮን ያልቅስ - ቀለም ለምን ያነሳል? ከዚህ ሥዕል ዘንድ ተጨማሪ ጊዜ ማጥፋቱን ተጨማሪ እንባ እንደመሸመት ቆጠርኩት-አፍታም አልቆየሁበት።

ከአዳራሹ መውጫው በር አቅጣጫ ማዕዘን ጥጉ ላይ በተሰቀለ ሥዕል ዙሪያ በርከት ያሉ ሰዎች ተኮልኩለዋል። ወጣቷ ሰዓሊ በረጅም ቀጭን በትር ሸራውን እየነካካች የሥራዋን ሚስጥር ትተነትናለች።

ሰዎች ለገለጻዋ ምስ ይሆን ዘንድ አንገታቸውን እየነቀነቁ፣ በፈገግታና በመገረም ይከታተሏታል። አንዳንዶቹም በሥዕሎቹ ግርጌ ላይ የተለጠፉትን የመሸጫ ዋጋ እያዩ ሳያቅማሙ ገንዘባቸውን መዥርጠው በአንድ አፍታ የሥዕሎቹ ባለቤቶች ሆነዋል።

በተመልካችና በሥዕሉ መካከል በቃላት ኃይል ልትፈጥር ያሰበችው መሥመር የቅዠት መሆኑን አሰብኩና ለሥዕሉ፣ ለእርሷና ለእድምተኞቿ አዘንኩላቸው። ሥዕል ዜማ፤ ተመልካችም የእውነት ጆሮ ሲኖራቸው ሁለቱን ለማገናኘት አማላጅ አያሻም። ዓይን መሥመሮችን ከተረዳ መሥመሮችም ዕውን በሕይወት ካሉ ሁለቱን ለማገናኘት ሽመል ለምን? ቀለማት ለመራመድ አቅም ሲያንሳቸው ብትር ማስደገፍ አያሰኝም።

በነገራችን ላይ በሥዕል ትርዒት ቦታ በሙዚቃ መሣሪያ የሚንቆረቆሩ ሙዚቃዎች እንዲደመጡ ለምን እንደሚፈለግ የሚነግረኝ ሰው ይኖራልን? ወይም ግጥም እየተሰማ ጃዝ ለምን እንዳስፈለገ? ሥዕል ሙዚቃ፣ ዜማና ዜማን ለማግኘት የሚያበቃ ምናባዊ ኃይል…የለውም ማለት ነው? ወይስ ግጥም ውስጥ ጃዝ፣ ማሲንቆ፣ ታምቡር… ጠፋ?

እኔ ደካሞችን እያደጋገፉ እንደማስጓዝ እቆጥረዋለሁ። ሥዕልም ሌላ ሌላውም ለኔ በራሳቸው ምሉዕና ታላቅ አቅም ያላቸው ናቸው። ጓዝ አያስፈልጋቸውም። አጃቢ ካስፈለጋቸው ግን ገና ሥዕልም ግጥምም የመሆን አቅም ዘንድ አልደረሱም ማለት ነው። ግጥምን ግጥም ሥዕልን ሥዕል ማድረግ እንጂ ዘፈኑ ሲያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት እንዲል ያገሬ ሰው አንካሳን ምርኩዝ አስይዞ እዩት እንደጠያራ ሲወነጨፍ የማለት ያህል ነው - አጭበርባሪነቱ።ቢራ እየጠጡ አልኮል እየተጎነጩ በጃዝ ግጥምን መስማት ደስ እንደሚል ብዙዎች ነገሩኝ። ግን ዜማውን ለምን ለኔ አይተውልኝም? ከግጥም ውስጥ የሚገኘውን ትፍስህት በወይን ባላጅበውስ? ግጥም ውስጥ ያለውን ሰማያዊ ዜማ በታምቡር ድለቃ ባላደፈርሰውስ? ግጥም ራሱን የቻለ የሙዚቃ ‘ባንድ’ አለው’ኮ? ለዚያውም እርስ በርሱ የማይምታታና ፍጹም የሆነ። የትንፋሽ፣ የክር፣ የምት፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በሙሉ ‘ሚያካትት።

ይህን ብቃቱን መደምጠጥ ነው በቁሳቁስ ታምቡር ግጥምን ላጅብ ማለት። ታምቡርና ግጥም ሥዕልና ቫዮሊን ምንና ምን?

የቫዮሊኑ ተስረቅራቂ ድምፅ በአዳራሹ ይናኛል። እዚህ ከትርዒቱ ቦታ ያለን ጎብኚዎች ምናልባትም የጋራችን ከሆነ የምንጋራው የቫዮሊኗን ዜማ ብቻ ነው።ያም ቢሆን የጋራችን ስለመሆኑ ጥርጣሬ ገብቶኛል።

ከትርዒቱ ስወጣ ግን እላዬ ላይ ከነበረው ሸክም የሚበዛው ስለመውረዱ እርግጠኛ ነበርኩ። ቢያንስ ሸክሜን መጀመሪያ ያየሁት ሥዕል አቅልሎልኛል።

 

 

Read 1918 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 11:00