Wednesday, 04 April 2012 10:47

የጥበብ ዋርካዎቻችን አንረሳቸውም

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

የሀገር ጀግና - የልብ ሀውልት፣ የፈጠራም ጉልበት ይመስለኛል፡፡ ልጅነት፤ ገና ባልቆሸሸና በተራበ ፍላጐት ያገኙትን፣ የሚጐርሱበት ስለሆነ በተለያዩ ሰዎች እንደሚቀረጽ ጥሬ ድንጋይ ነው፡፡ ትልቅ ሆነው ወደ ኋላ በተመለከቱ ቁጥር ብዙ ድምፆች፣ ብዙ ንባቦች፣ ብዙ ቃሎች፣ በልብ ውስጥ ተጠራቅመው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ታላቅ ገጣሚ ዋልት ዊትማን፤ “በልጅነቴ ብድግ አድርገው ያቀፉኝ የአገሬ ጀግና ነገር እስከዛሬም አይረሳኝም፡፡ ደስታዬም አልቀዘቀዘም” ይላል፡፡ በተለይ ታዋቂ ሰዎች በልጅ ልብ ውስጥ በጐና ክፉ ነገር ለማኖር ቅርብ ናቸው፡፡ ተወዳጅ የሀገር ሰውማ ሁሌ ብርቅ ነው፡፡

የሩሲያ ደራሲያን “ሁላችንም የወጣነው ከጐጐል ካፖርት ነው” እንደሚሉት ሁሉ ቀዳሚዎች ያላቸው ሚና መቼም አይናቅም፡፡ ስለዚህ በዘመናት ሁሉ ቅን ልቦች ሲዘክሩባቸው ይኖራል፡፡ ያላለላቸው ደግሞ ድክመቶቻቸውን መዘው ለትውልድ የሰሩትን ስራ ሁሉ ጭቃ ይቀባሉ፡፡ ግና የቱም ሰው የየራሱ ድክመቶች እንዳለበት ማናችንም አንስተውም ብዬ አምናለሁ፡፡

ለምሳሌ ሊዮ ቶልስቶይና ጐርኪ ይግባባሉ፡፡ አብረው ያሳልፋሉ፤ ቶልስቶይ ሩሁሩህ፣ ቸር፣ ወፈፌና ግልጽም ነው፡፡ ለሁሉ አይመችም፡፡ ለሁሉ አይስማማም ግን ብርቅ ነው፡፡ ጣፋጭ ነው፤ ተመጥጦ የማያልቅ ከረሜላም ነው፡፡

ታዲያ ጐርኪ የፃፋቸው ዕለታዊ ማስታወሻዎች ላይ ስለ ቶልስቶይ ጽፏል፡፡ የፃፈው ለገፀ ንባብ እንዲበቃ አይደለም፡፡ የልቡን ነው፡፡ ግን ቅንነት የተሞላና አድናቆት ያላጣ ነው፡፡ የውስጥ ምጡን፣ ከቆዳው ስር የሚላወሰውን ስሜቱን ሁሉ ያጠና ይመስላል፡፡

ለማስታወስ ያህል:- “እጆቹ ላይ የፈጠጡት የደም ሥሮቹ በጣም ያስጠላሉ፡፡ የዚያኑ ያህል ግን ገላጭና የፈጠራ ሀይል ሞገድ ናቸው፡፡ ምናልባት የዚህ ዓይነት እ

ጆች ያለው ሊዎናርዶ ዳቬንቺ ይሆናል፡፡ እንደዚያ ባሉ እጆች ማንኛውም ጥበብ ሊሠራ ይችላል፡፡ አንዳንዴ ከበድ ያሉ ቃላት ከአንደበቱ ሲወጡ እጆቹ ይወራጫሉ፡፡ መልሰው ደግሞ ድንገት ቀጥ ይላሉ፡፡” ይላል፡፡

ጐርኪ እጆቹ ላይ ብቻ ዓይኑን ተክሎ ቶሌስቶይን፣ አይቷል አሳይቷልም፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የ”Meet Etv” አዘጋጁ ተፈራ ገዳሙ ያቀረበው ጋሽ ስብሃት፤ ቶልስቶይን አስታውሶኛል፡፡ ጋሽ ስብሃት በአይኖቹ፣ በእጆቹ፣ በከንፈሮቹና በግንባሩ ሁሉ ያወራ ነበር፡፡ በውስጡ የታመቀውን የዕውቀት ሃይል በብዙ ሽንቁሮች ለማውጣት፡፡

ቶልስቶይ ለሩስያ እንደሆነ ሁሉ ጋሽ ስብሃት ለኢትዮጵያ ነው፡፡ ብዙ አንብቧል፤ ብዙ ያውቃል፡፡ ሕይወቱም በብዙ ውጣ ውረድ ተዛንፏል፡፡ ባያደርጋቸው ብለን አፉን ይዘን ልናስቀራቸው፤ ያለነቀፋ በሁሉም ፊት ውብ እንዲሆን የምንመኛቸውን ውበቶች ባናገኝም፤ ውብ ብዕር እንደነበረው አንክድም፡፡ በማህበራዊ ህይወቱም ሰዎችን የማይነካ፣ ያለውን የሚያካፍል፣ የለበሰውን ልብስ እንኳን አውልቆ የሚሰጥ እንደሆነ አናውቃለን፡፡ ግን እነዚህንም ባያደርግ ጀግና ነው፡፡ ምናልባት ስለዚህ ጥሩ የሚያወራልን የአለማየሁ ገላጋይ “ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ሕይወትና ክህሎት የተሰኘው መፅሃፍ ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደ ሽንኩርት ልጣጭ ተልጠው ሊነሱ የሚገባቸው፣ ትልቁን ሃሳብ የማይመጥኑ ምዕራፎች ቢኖሩም አለማየሁ ለአንድ አገር ጀግና የሚሰራውን ስራ ሊሰራ ሞክሯል፡፡ የበሰሉ ሃሳቦችን፣ ክመቼት ጋር የተገናኙ ሁነቶችንና የአጻጻፍ ስልቱን ምንጭ ፍለጋም ደክሟል - ሸጋ ነው፡፡ የስብሀትን አንቀፆች ጣዕም፣ በዚያ ብዙዎች በሚከብደን (ሀራም) ውስጥ እንኳን ልብ ካልን ትልልቅ ሃሳቦች አሉ፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ፤ ሙሉ ሕይወቱንና ሥራውን “ማስታወሻ” በሚለው መጽሐፍ ለህዝብ በማስተዋወቅ የሠራው ሥራ፤ ትልቅና ዘመንና ትውልድ የማይረሳው ነው፡፡ ወደፊት ከዚህ በተሻለ ሊሠራ እንደሚችልና “ማስታወሻ”ንም ደግሞ እየፃፈ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡

ስለ ጋሽ ስብሃት ካነሳሁ፣ ሉድዊግ ቤትሆቨንን በአንድ ጉዳይ አነፃጽራለሁ፡፡ ቤትሆቨን በልጅነቱ በገጠመው የጤና እክል የተነሳ፣ ብዙ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ታድያ ስለዚህ ቀውስ እንዲህ ይላል፤ “ከህፃንነቴ ጀምሮ ልቤና አዕምሮዬ በመልካም ሃሳብ የተሞሉ ነበሩ፡፡ ትልቅ ነገር ለመስራትም ዝግጁ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን ለበርካታ ዓመታት ከጆሮ ህመም ጋር ስታገል ኖርኩ፡፡ በሀኪም ታየሁ፤ ከጊዜ ጊዜ በተስፋ ዳከርኩ፤ በኋላ ግን በተሟጠጠ ተስፋ ያለመስማቴን ችግር ተቀበልኩት፡፡ ልጅነቴን ገለልተኛና ብቸኛ ሆኜ ኖርኩ፡፡ በኋላም ሰዎችን ጮክ ብላችሁ አውሩ፤ ደንቆሮ ነኝ ማለት አስጠላኝ፡፡”

በህይወቱ በደረሰው መከራና ጣጣ ምክንያት ሰዎች አልተረዱትም ነበር፤ ስለዚህ “አልተረዳችሁኝም ችግሬ አልገባችሁም፡፡ ስሞት ሁሉን ስታውቁ ትፀፀታላችሁ” ይል ነበር፡፡ ወደ ፈጣሪም መለስ ብሎ “ፈጣሪ ሆይ፤ የልቤን ውስጥ እየው፤ ለሰው ልጆች ያለኝን ፍቅርና ከነሱ ጋር በሰላም ለመኖር ያለኝን ፍላጐት አንተ መዝነው” ሲል ፀልይዋል፡፡

ጋሽ ስብሃትም መጠጥ መቼ እንደጀመረ ካወቅን፤ በትዳሩ ላይ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ እራሱን መጠበቅ መተውን፣ ከረባትና ኮቱን አሽቀንጥሮ መጣሉን ከተረዳን ብዙ ነገሮቹ ያሳዝኑናል እንጂ አያናድደንም፡፡ ስለ ሚስቱ የነበረው ፍቅርን ሲያጣ፣ ልጁ ሲለየው የሚሰማውን ስሜት በእርሱ ቦታ ሆነን ካየነው፣ ህመሙ የቤትሆቨንን ያህል ይሰማናል፡፡

ብቻ የቱም ይሁን ማንም፤ የሀገር ጀግና ድክመቶቹን አርመን፣ የማንወድለትን ትተን፣ የምንወደድለትን ልናከብርለት ይገባል፡፡ የጋሽ ስብሃት የአዲስ ዘመን፣ የአዲስ አድማስና የሌሎች ጋዜጦች ሥራዎች የነበራቸው ውበትና ጠቀሜታ የሚረሣ አይደለም፡፡

ስለ ታላላቆቻችን ሳስብ፣ የጋሽ ማሞ ውድነህም ነገር በእጅጉ ሆዴን አባብቶታል፡፡ እሳቸውም በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ውስጥ የቆዩ ዋርካ ስለሆኑ፣ ከዋርካው ስር ያደግን ሁሉ ጥላው ሲነሳብን ጭርታ ይሰማናል፡፡ ጋሽ ማሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ላደገና ማንበብ በሚችል ሰው ልብ ውስጥ ሁሉ ያሉ የንባብ መምህር ናቸው፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ወይም ኮሌጅ ተማሪ ሆኖ፣ የሳቸውን የስለላ መጽሐፍ ያላነበበ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለንባብ አስታውሶ ጋሽ ማሞን መርሳት የማይቻል ነው፡፡ በተለይ የስለላ መጽሐፍትን አንብቦ ለመለማመድ ያልሞከረ፣ አድናቆት ያልተፈጠረበት ይኖራል ብዬ አልጠረጥርም፡፡ ጋሽ ማሞን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች እንደሚሉት፤ ጋሽ ማሞ ሁሌ የሚተረጉሙት ትኩስ መጽሐፍ ነው፡፡ በየት እና እንዴት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገቡ አይታወቅም፡፡ ግን ታታሪ ናቸው፡፡ አነፍናፊ ናቸው፡፡ ስለዚህም ጋሽ ማሞ ባለውለታችን፣ በትውልድ ልብ ሊቀመጡ የሚገቡ ብርቅ ናቸው፡፡ ዛሬ የቱንም ያህል እናንብብ፣ የቱንም ያህል እንወቅ ግን ዳዴ ወፌ ቆመች ብለው መራመድ ያስለመዱንን አባቶች አንረሳም፡፡ ክብራቸውንም አንነፍግም፡፡

ከበደ ሚካኤል የሚፃፉት የወል ቤት ግጥም፣ ዛሬ ምጡቅ ሆነም አልሆነም፤ ዘመኑ ገጠመ አልገጠመ ለሳቸው ያለን አድናቆት ቤት በመምታት - መድፋት ዜማ ፈጥረው የልጅ ልጃችንን እያጨዋወቱ፣ አንዳች ቁም ነገር ወደምናገኝበት አምባ የመሩንን አባት ዛሬም በበጐ መዘከራችን ግድ ነው፡፡ የፍቅር ግዴታ ማለቴ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የኪነ ጥበቡን ማህሌት በብዕር ያደመቁና በንባብ ልምድ የበሰሉ ሰዎች፤ ዛሬ ዛሬ እየሳሱ መምጣታቸው በእነዚህ ብርቆቻችን ከጐናችን መጥፋት ይበልጥ እንድንብሰለሰልና እንድንቆጭ የሚያደርገን ይመስለኛል፡፡ ምን አልባትም ችግሮቻቸውና ጉድለቶቻቸው ላይ ስናጠነጥን ብስለታቸውን ሳንቀዳ፣ ንባባቸውን ሳንወርስ እንደተታለልንም እጠራጠራለሁ፡፡ ባልሳሳት የቀደሙት ደራሲያን በፍልስፍና፣ በኪነ ጥበብ፣ ጠቅላላ ሳይንስ፣ በታሪክና በቋንቋ ዕውቀት የተሻለ ሙላት ነበራቸው፡፡ ሲናገሩ በመረጃ፣ ሲጽፉ በመረጃ ስለነበር የሚያስቀና ነገር አስተውዬባቸዋለሁ፡፡

እላይ ከጠቀስኳቸው ሁለት ታላላቆቻችን በተጨማሪ፣ በንባብ ልምዱ የማደንቀውና የበሰለ ተመክሮ የነበረው አብርሃም ረታ፤ በሙዚቃ ላይ የነበረው ዕውቀት ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን አብርሃም የዜማና ግጥም ደራሲም እንደነበረ ይታወቃል፡፡

አብርሃም ለዚህ ብቃቱ መጐልበት ምክንያት እንፈልግ ከተባለ፣ ልዩነት እንዲፈጥር ያደረገው ሳያሰልስ ማንበቡና ሙዚቃዎች እያዳመጠ መተንተኑ ነው፡፡ በህይወት በነበረ ጊዜ መኖሪያ ቤቱ ሄጄ እንዳየሁት፣ ከአንድ ሺ የሚበልጡ የዘፈን፣ የመዝሙርና የመንዙማ ካሴቶች ነበሩት፡፡ የመጻሕፍቱ ነገር አይጠየቅም፤ ገበያ ላይ የሌሉ መፃሕፍት እርሱ ቤት አይጠፉም፡፡ ስለዚህም አብርሃም በሂሱ ጥበብ ላይ ሻል ያለው ዕውቀት ነበረው፡፡

እንደ እኔ እንደ እኔ አብርሃም ረታም ለትውልዱ አርአያነት ያለው ስራ የሠራና ካጣናቸው በሳል ሰዎች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ምክንያቱም ከደራሲነት ጋር የዕውቀት ጐተራቸውን ያሳበጡ ሰዎች፣ እንደ ሰሜን ዋልያ በቁጥር የተመናመኑ ስለሆነ በስጋት የምንሳሳላቸው ናቸው፡፡ ከአብርሃም ረታ ቀደም ሲል ከዚህ አለም በሞት የተለዩን መስፍን አለማየሁ፣ ባሴ ሃብቴና ከአብርሃም በኋላ የተለየን ደምሴ ጽጌ ልናስባቸው የሚገቡ ምሳሌዎቻችን ናቸው፡፡ ደግሞ እንዴት እንተካቸው? እንዴት እንምሰላቸው? በማለት የሚያስቀና ነገራቸውን የምንመዝላቸው ናቸው፡፡ ታላላቆችን ስለመዘከርና ስራቸውን ስለማድነቅ ካነሳሁ አይቀር፣ የፌደራል ፖሊስን በጐ ጐን ልጠቁም፡፡ ፌደራል ፖሊስ በቅርቡ ደራሲ ማሞ ውድነህን በአክብሮት ዘክሯል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ከደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ጋር ባጋጣሚ ተገኝቼ ነበር፡፡ ደስ ያለኝና በፕሮግራሙ ላይ የተገኘሁት ከሞቱ በኋላ በመዘከራቸው አይደለም፡፡ በህይወት እያሉም ሲያስታውሱዋቸው ስላየሁም እንጂ፡፡ የፖሊስ ፕሮግራም ደራሲና ተርጓሚ ማሞን ለገና በዓል እንግዳ አድርጓቸው ነበር፡ፌደራል ፖሊስ የጥበብ ሰዎችን ብቻ አይደለም፣ በጡረታ የተገለሉ የቀድሞ ባለውለታዎቹን ሲዘክር በተደጋጋሚ አይቻለሁ፡፡ ከዚህ የተነሳም እኔ ለፌደራል ፖሊስና ለፕሮግራሞቻቸው ያለኝ ከበሬታ እጅግ የላቀ ነው፡፡

ከፖሊስ እኔ እናንተም፣ ሁላችንም የምንማረው ብዙ ነገር አለ፤ ጀግኖች ማክበር፤ የሀገር ባለውለታዎችን መዘከር!

 

 

Read 2454 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:50