Sunday, 11 June 2017 00:00

ለዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች አዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎት ተጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

 ሙያውን ያለስጋት ለማከናወን ያስችላል ተብሏል
                       
       ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀነራል ኢንሹራንስ፤ ዶክተሮችና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች ከአቅም በላይ በሆነ ክስተት በታካሚዎች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት የሚደርስባቸውን ህጋዊ ተጠያቂነት የሚታደግ አዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
የኢንሹራስ ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ በሒልተን ሆቴል ባዘጋጀውና አገልግሎቱን ይፋ ባደረገበት ሥነ ስርአት ላይ የኢንሹራንሱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሺመልስ ገ/ጊዮርጊስ እንደተናገሩት፤ ዶክተሮችና የህክምና ባለሙያዎች በሥራ ወቅት በሚያጋጥማቸው ችግር ሳቢያ ያላቸውን ህጋዊ ተጠያቂነት ለመታደግ የሚያስፈልግና ባለሙያዎቹ ሥራቸውን ያለሥጋት ለማከናወን እንዲችሉ የሚያደርግ አዲስ አይነት የኢንሹራንስ አገልግሎት ነው፡፡ አገልግሎቱ ታካሚዎች በሃኪሞቻቸው ላይ ሊያነሱ የሚችሉትን ህጋዊ የፍታብሔር ተጠያቂነት የሚሸፍን ሲሆን፡፡ ኢንሹራንሱ በወንጀል የሚነሳ ተጠያቂነትን አያካትት፡፡
በአሁኑ ወቅት ዶክተሮችና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ለታካሚዎቻቸው የህክምና አገልግሎት በሚሰጡበት ሂደት ውስጥ በሚያጋጥማቸው ከአቅም በላይ በሆነ ክስተት በታካሚዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት ወደ ህግ እየቀረበ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ፍ/ቤቱም የህክምና ባለሙያዎቹን የገንዘብ አቅም የሚፈታተን ከፍተኛ የካሣ ክፍያ እንዲከፍሉ ውሳኔ በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ባለሙያው ሥራውን ያለስጋት ማከናወን እንዳይችልና ለከፍተኛ ፍራቻና ሥጋት እንዲጋለጥ ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል፡፡
የኢንሹራንስ አገልግሎቱ ሁሉም ዶክተሮችና ከዶክተሮቹ ጋር ተያያዥ የሆነ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የጤና ተቋማትን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ባለሙያዎቹ በተናጠል በተቋምና በጋራ አገልግሎቱን መግዛት እንደሚችሉና ክፍያውም የአብዛኛውን የህክምና ባለሙያ አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር የኔነህ ጌታቸው በበኩላቸው፤ የኢንሹራንስ ድርጅቱ በአገሪቱ በአይነት አዲስ የሆነውን የህክምና ባለሙያዎች የኢንሹራንስ አገልግሎት መጀመሩ ባለሙያዎቹ ሥራቸውን ያለ ሥጋት እንዲያከናውኑ የሚረዳ ከመሆኑም ሌላ ተገልጋዩ ህብረተሰብም በሚሰጠው የህክምና አገልግሎት እንዲተማመን ያደርገዋል ብለዋል፡፡
አያይዘውም የዚህ አይነት አገልግሎት በተለያዩ የአለም አገረት የተለመደ ቢሆንም በአገራችን ከዚህ ቀደም የማይሰጥ በመሆኑ በርካታ ሃኪሞችና የጤና ባለሙያዎች በህክምና ሂደት ውስጥ በሚያጋጥማቸው ችግር ሳቢያ ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂ የሚሆኑበትን የካሣ ክፍያ ለመክፈል አቅም ሲያጥራቸው ቆይቷል፡፡
ይህ ሁኔታም ሃኪሞቹ በሚሰጡት የህክምና አገልግሎት ፍራቻና ሥጋት እንዲያድርባቸው ያደርጋቸዋል፡፡ የኢንሹራንስ አግልግሎት መኖሩ፣ ይህንን ሥጋት ለማስቀረት የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል - ዶክተር የኔነህ፡፡

Read 3933 times