Wednesday, 04 April 2012 10:16

ሶርያና ሊቢያ - ሁለቱ የነፃነት መንገዶች

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

አምስተኛው አምባገነን በሕዝባዊው አመፅ ይረቱ ይሆን?

በርካታ የህብረተሠብና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራንም ሆኑ የመስኩ ተንታኞች፤ ከአለማችን ሀገራት ድንገተኛ የሆነ ህዝባዊ አብዮት ሊነሳባቸው ይችላሉ ብለው ከሚገምቷቸው ሀገራት ውስጥ አረቦች የሚኖሩባቸው የሠሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የመጨረሻዎቹ ነበሩ፡፡ የእነዚህ ሀገራት ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት፣ የመሪዎቹ በውጪ ሀያላን መንግስታት የተደገፈ ጠንካራ የብረት ክንድና በአገዛዛቸው ላይ ለሚሠነዘር ማናቸውም አይነት ተቃውሞ ምህረት የለሽ መሆንና የህዝቡ በአገዛዙ የአፈና ቀንበር ሠጥ ለጥ ብሎ  ለአመታት መገዛት ለባለሙያዎቹና ለተንታኞቹ ግምት ዋነኛ መነሻዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡

የዛሬ ሁለት አመት ግን መላው አለም ሳይቀር ይሆናል ብሎ ያልገመተውና ያልጠበቀው ክስተት በሠሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውስጥ ለመታየት በቃ፡፡ በርካቶች የ”Arab Spring” የሚል የቁልምጫ ስም ያወጡለት ድንገተኛ ህዝባዊ አብዮት በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ፈነዳ፡፡

ሞሀመድ ቦአዚዝ የተባለ ወጣት፣ በፕሬዚዳንት ቤን አሊ አምባገነናዊ አገዛዝ ለዘመናት ሲቀበለው የኖረውን አፈናና የኢኮኖሚ ድቀት ለሌላ አንድ ተጨማሪ ቀን ሊሸከመው ባለመቻሉ ከሚችለው በላይ በመሆኑ፣ ከዚህ አበሳና አፈና እስከወዲያኛው ለመገላገል፣ እንዲሁም ለአገዛዙ ያለውን ከፍተኛ ጥላቻ ለማሳየት፣ በመኖሪያ ከተማው አውራ ጐዳና ላይ ራሱን በራሱ በእሳት አቃጥሎ ገደለ፡፡

የሞሃመድ ቦአዚዝ አሟሟት ”የታደለ” ሆነና ታሪክና ጊዜ በአንድ ላይ የተገጣጠሙለት ከፍተኛ የለውጥ አንቀሳቃሽ ሀይል ለመሆን በቃ፡፡ ለረጅም ዘመናት በከፍተኛ የነፃነት ጭቆናና አሠቃቂ የኢኮኖሚ ድቀት ስር ሲማቅቁ የነበሩት ቱኒዚያውያን፣ ሞሀመድ ቦአዚዝ በአሰቃቂ ሁኔታ ራሱን በራሱ እንዲገድል የተገደደበትን ዋና ዋና ምክንያቶች አንስተው ሁሉም እንደ አንድ፣ አንዱም እንደ ሁሉ በመነሳት በአንምባገነኑና በጨቋኙ መሪያቸው ቤን አሊ አገዛዝ ላይ በአመጽና በተቃውሞ ተነሱ፡፡

ከቱኒዚያ የተነሳው ህዝባዊ አብዮት ወደ ሌሎች የሠሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በከፍተኛ ሁኔታ በመዛመት፣ መቼም አይወድቁም እየተባሉ ሲነገርላቸው የነበሩትንና ለበርካታ ዘመናት ህዝባቸውን በከፍተኛ የጭቆናና የአፈና አገዛዝ ረግጠው ሲገዙ የነበሩትን አምባገነን መሪዎችን በየተራ ከስልጣን መንበራቸው መፈንገል ጀመረ፡፡

የቱኒዚያው ፕሬዚዳንትን ከሀገር መባረር ተከትሎ፣ ግብጾች ከአርባ አመታት በላይ አንቀጥቅጠው የገዟቸውን ፕሬዚዳንታቸውን ሆስኒ ሙባረክን ከስልጣናቸው መንግለው ወህኒ በማውረድ ፍርድ ቤት መገተር ቻሉ፡፡ ከዚያም ሊቢያውያን ቀጠሉ፡፡ ደም ባፋሠሠ የብረት ትግል አምባገነኑን መሪያቸውን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን ለአራት አስርት አመታት፣ በፈላጭ ቆራጭነት የተዘባነኑበትን ስልጣናቸውን ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውንም አሳጧቸው፡፡

የመናውያን በአልበገር ባይነት በተቃውሞአቸው በመጽናት፣ ለሠላሳ አንድ አመታት አንቀጥቅጠው የገዟቸውን ፕሬዚዳንት ሳላህን በህክምና ሠበብ ከስልጣን እንዲወርዱ ማስገደድ ቻሉ፡፡

የባህሬይን ህዝብ የተቃውሞ አብዮት በሳኡዲ አረቢያ ታንኮች ለጊዜው የተኮላሸ ቢሆንም የከናሳውን የንጉሱን አገዛዝ ዙፋን፣ የእሳት ላይ መቀመጫ እንዲሆን ማድረግ ችሏል፡፡

አሁን የመላው አለም አይኖች በአንክሮ የሚከታተሉት የሶሪያን ህዝባዊ የተቃውሞ አብዮትን ብቻ ነው፡፡ ሶሪያውያን ለዘመናት ከላያቸው ላይ ተጭኖ፣ በአፈናና በጭቆና ረግጦ በሚገዛቸው የ”አልአሳድ አናሳ” ስርወ መንግስት ላይ ህዝባዊ የተቃውሞ አብዮት ቀስቅሠው ለነፃነታቸው መታገል ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ሊቢያውያንን ወደ ነፃነት የወሠዳቸው መንገድ ለሶሪያውያን የተለየ መንገድ ሆኖባቸዋል፡፡ ሊቢያውያኖች በተጓዙበት የነፃነት መንገድ ላይ መንገዱን በመጥረግም ሆነ በመምራት የተባበሯቸውን የተለያዩ አለም አቀፋዊ ሀይሎች፣ ሶሪያውያን በጀመሩት የነፃነት መንገድ ላይ ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ እናም የነፃነቱ መንገድ ሁለት አይነት ሆኖባቸው ተቸግረዋል፡፡

ማንም ቢሆን በግልጽና በቀላሉ መረዳት እንደሚችለው የሊቢያም ሆነ የሶሪያ ህዝቦች የተነሱት ረጅም ዘመን ያስቆጠረውን የጭቆና አገዛዝ ለማስወገድ ነው፡፡ እዚህ ላይ መቅረብ የሚገባው ጥያቄ እንዲህ የሚለው ነው፡፡ ዋናው አላማ ይህ ከሆነ ታዲያ ከአንድ አመት በሁዋላም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በሁለት በእጅጉ በተለያዩ እውነታዎች ውስጥ የመኖራቸው ምስጢር ምንድን ነው?

የኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን አገዛዝ ለመገልበጥ ህዝባዊ የአመጽ ትግል ገና እንደጀመሩ ሰሞን በርካታ ሊቢያውያን በከፍተኛ ጭንቀት የአመጹን ሂደት ለመከታተል በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ አይናቸውን ተክለው የሚውሉበት በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ይህን በሚያደርጉበት ጊዜም ልክ እንደነሱው ሁሉ የጨቋኙን የአልአሳድን መንግስት ለመገልበጥ ሶሪያውያኑ የጀመሩትን ትግልም በእግረ መንገድ አብረው ይከታተሉ ነበር፡፡ ሊቢያውያን ያኔ ሶሪያውያን ለነፃነታቸው ያደርጉት የነበረውን ጩኸት በሚገባ ቢረዱትም፣ ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ ተቃዋሚዎቻቸውን ለመደምሠስ በሚወስዱት የጭካኔ እርምጃ የተነሳ የመላው አለም አይንና ልብ ከሊቢያ ወደ ሶሪያ ይዞራል በሚል በእጅጉ ይጨነቁና ይሠጉ ነበር፡፡ ሊቢያውያን ያኔ እንዴት ተሳስተው ነበር!

ነገር ግን ለውጭ ታዛቢዎች ሽክ ብለው ከሚለብሱትና በተመጠነ ድምጽ ከሚናገሩት ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ ይልቅ ዓለም በሙአመር ጋዳፊ ላይ ለመተባበርና ከስልጣናቸው ለመገርሰስ እንዴት ቀለለው? በእርግጥ ያኔ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የውጭ ወታደራዊ ሀይሎች፣ በሊቢያ ጣልቃ እንዲገቡና የፕሬዚዳንት ጋዳፊን ሀይል በጦር ሀይል እንዲደበድቡ የሚያስችል ውሳኔ ማስተላለፍ የቻለው ያለ ብዙ የዲፕሎማሲ ውጣ ውረድ ነበር፡፡

ያኔ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለተከታተለ፣ የተደረጉት ነገሮች ሁሉ በቀላሉ የተደረጉ መስለው ሊታዩት ቢችሉም፣ በርካታ ጉዳዮች በጨዋታው ውስጥ ነበሩ፡፡ የነፃነቱን መንገድ ሁለት እንዲሆን ያደረጉትም እነዚሁ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ፣ በአረቡ አለም የተቀጣጠሉት ህዝባዊ አብዮቶች ሁሉ የነፃነት ፍለጋን ገመድ በአንድነት የተጋሩ ቢሆኑም፣ የነፃነት ፍለጋው ገመድ አስተሳሠር ግን ለየቅል ነበር፡፡ ነፃነትን ፍለጋና ከጭቆና ለመገላገል በሶሪያና በሊቢያ የተቀሰቀሱት ህዝባዊ አብዮቶች ተመሳሳይ ነበሩ፡፡ ሁለቱም አብዮቶች ከሀይማኖት ልዩነትና ይህም ልዩነት ከሚፈጥረው አደገኛ ጥልፍልፍ ነፃ ነበሩ፡፡ አብዛኛው የሊቢያ ህዝብ፣ የነፃነቱን ትግልና ለድጋፍ የተሠማራውን የውጪ ወታደራዊ ሀይል ደጋፊ ነበር፡፡

ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሶሪያ ያለው አመለካከት ግን የተለየ ነው፡፡ በሊቢያ እንደተደረገው የውጪ ወታደራዊ ሀይሎች በሶሪያ የመግባት ሁኔታን ሶሪያውያን የሚያስቡት እንደ ሊቢያኖች ሳይሆን በኢራቅና በሊባኖስ በውጭ የጦር ሀይሎች ጣልቃ ገብነት አማካኝነት የተፈጠረውን ምስቅልቅልና የእርስ በርስ እልቂት በማሰብ ነው፡፡ የሶሪያውያንን እንዲህ ያለ ጭንቀትና ፍርሀት አንዳንድ የውጪ ሀይሎችም ይጋሩታል፡፡

ለምሳሌ የጋዳፊን የጦር ሀይል በማንበርከክ በኩል ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱት ሀገራት አንዷ የሆነችው የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አለን ዡፔ፤ የፕሬዚዳንት በሻር አል አሳድን ተቃዋሚዎች የማስታጠቅን ጉዳይ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፤ “ማጣፊያው የሚያጥር የእርስ በርስ እልቂት ያስነሳል” የሚል ነው፡፡

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት፣ በተደጋጋሚ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ቻይናና ሩሲያ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸው ውድቅ ያደረጉበት ምክንያትም በዋናነት ይሄው ስጋት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሶሪያውያንነ የነፃነት መንገድ ከሊቢያውያን መንገድ ጋር የተራቀቀ እንዲሆን አድርጐባቸዋል፡፡ የነዳጅ ዘይት ጉዳይም ሌላው ከባድ ተጽዕኖ የፈጠረባቸው ጉዳይ ነው፡፡ የምዕራቡ አለም የሊቢያ ጦርነት በአለም የነዳጅ ዘይት አቅርቦትና ገበያ ላይ የሚፈጥረውን ከባድ ቀውስ በዝምታ ለማለፍ ጨርሶ ፍላጐት አልነበራቸውም፡፡ በሊቢያ ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለመፈፀም ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የወሰዱት፣ ለወጉና ለአለማቀፉ ዲፕሎማሲ ይሉኝታ ብለው እንጂ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጣልቃ የመግባታቸው ጉዳይ ጨርሶ የማይቀር ነበር፡፡ የአሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ልብ መምታት የሚችለው በነዳጅ ሲሆን የሚረጨውም ደም ሳይሆን ነዳጅ ነው፡፡ እናም ከደረሠበት መንኮታኮት እንዲያገግም “ማሪያም ማሪያም” እያሉ ሱባኤ የገቡለት ኢኮኖሚያቸው ሙአመር ጋዳፊ በተባለ፣ ቀን ጊዜና ህዝብ በከዳው መሪ አጓጉል ድርጊት የባሠ እንዲንኮታኮት አሜሪካም ሆነ አውሮፓ የአፍታ እድሜና እድል ይሠጡታል ብሎ ማሠብ፣ በወቅቱ ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ጨርሶ የማይሞከር ነበር፡፡ ጋዳፊን በማስወገዱ ትግል ውስጥ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ያደረጉትን ያደረጉትም በዚህ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ይህም ድርጊታቸው የሊቢያን የነፃነት ትግል የራሱን የተለየ መንገድ ይዞ እንዲጓዝ አድርጐታል፡፡

ሶሪያ ግን ምን አላት? ይህ ጥያቄ ለሶሪያና ህዝቧ ሞራል ነክ የሆነና በሰላሙና በመልካሙ ቀኗ ቢሆን ኖሮ ጨርሶ ልትጠይቀው የማትችለው ጥያቄ ነበር፡፡

ግናስ ሶርያ ምን ማድረግ ይቻላታል? የዚህ ጥያቄ ተደራራቢ ክፋቱ መልሱም የጥያቄውን ያህል አሳዛኝ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥም ሶሪያ የምዕራብ ሀያላን መንግስታት፣ የጀመረችውን የነፃነት ትግል ከጥቅማቸው አንፃር አይተውና ገምተው በሊቢያ እንዳደረጉት አይነት ቀጥተኛ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትና ዙሪያ መለስ እርዳታ እንዲያደርጉላት የሚያስገድድ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅም የላትም፡፡ ይልቁንስ የበሸር አል-አሳድን መንግስት ለመጣል ለሚታገሉትና ከሞራል አኳያ እነሱን ለመርዳት እያሰላሰለ ለሚገኘው ለምዕራቡ አለም፣ ጣጣውና ዳፋው በቀላሉ የማይበርድ የዲፕሎማሲ የፈንጂ ወረዳ ናት፡፡ እናም ታዲያ እንዲህ የፈንጂ ወረዳ ውስጥ ከሞራልም አኳያ ቢሆን አይን እያየ ገብቶ፣ ስምና ሰበብ የሌለው የሞኝ መስዋዕትነት የሚከፍል ሀገር እግር እስኪነቃ ቢሄዱስ፣ ከእንዴት ያለው አለም ማግኘት ይቻላል?

ከአባታቸው በቀጥታ የወረሱትን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ይዘው ላለፉት አስራ አንድ አመታት ሶሪያን በጠንካራ አምባገነናዊ ክንድ ሰጥ ለጥ አድርገው የገዙት ፕሬዚዳንት በሻር አል-አሳድና መንግስታቸው፣ በኢራንና በሊባኖሱ ሂዝቦላህ ውስጥ ሁነኛና ጠንካራ ወዳጆች አላቸው፡፡ የሶሪያ የቅርብ ጐረቤት የሆነችው የሊባኖስ መንግስት እንደ ሂዝቦላ በሻር አል-አሳድን በግልጽ ባይደግፍም፣ ዳፋው ለእሱም የሚተርፍ አደገኛ የእርስ በርስ ጦርነት ይነሳል በሚል ስጋት በጥፍሩ የቆመ በመሆኑ፣ አማጺያኑን ለመደገፍም እንዲህ በቀላሉ የሚያደርገውና የሚሆንለትም አይደለም፡፡ በሶርያ የእርስ በርስ ጦርነት ከተነሳ መዘዙ በተለይ ለሊባኖስ አያድርስ ነው፡፡ እንኳን የእርስ በርስ ጦርነት ተነስቶ ይቅርና፣ በየቀኑ ወደ ሀገሩ የሚገቡትን የሶሪያ ስደተኞችን በወጉ ለማስተናገድ የሊባኖስ መንግስት ከባድ ፈተና ገጥሞታል፡፡ የሊባኖስ ህዝብም ቢሆን የተቃዋሚውን የሶሪያ ነፃ ወታደሮች (Free Syrian Army-FSA) ለመርዳት በመፈለግና ሌላ አዲስ የተቀጥላ ጦርነት በሀገራቸው ውስጥ እንዳይነሳ ባላቸው ፍርሀት መሀል ልባቸው ለሁለት ተከፍሎ ከወዲያ ወዲህ እየዋለለ ይገኛል፡፡

ሌላም ተጨማሪ ጉዳይ አለ፡፡ እድሜ ለክፉ አማካሪዎቻቸውና ከሁሉም ይልቅ ደግሞ ምስጋና ለማይጨበጠውና ለቅዥት አስተሳሰባቸው ይሁንና፣ የሊቢያው አምባገነን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ፤ በስልጣን በዘለቁበት አብዛኛው ዓመታት፣ ያለ ሌላ የውጪ ግፊትና ተጽእኖ ራሳቸውን በራሳቸው ከተቀረው አለም ለይተውና አግልለው የኖሩ፣ በቅጡ ለመግለጽ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ መሪ ነበሩ፡፡ ከተቀረው አለም በተሻለ እንደ ወገን ሊያያቸው ይችላል በሚባለው የመካከለኛው ምስራቅ ያሉ የአረብ ሀገራት መሪዎችም ለጋዳፊ ያላቸውን ጥላቻ በግልጽም ይሁን በሹክሹክታ ለዘመናት ሲገልፁት የኖሩ በመሆኑ፣ የህዝባዊው አመጽ እሳት ከትሪፖሊ አልፎ የትውልድ ከተማቸውንና የመጨረሻ መሸሸጊያ ያደረጓትን ሲርትን መለብለብ ሲጀምርም እንኳን፣ የመታደጊያ እጁን የዘረጋላቸው “አላህ በወጉ ይግደልህ” ያላቸው እንኳ አልነበረም፡፡

ጉዳዩ ጠቅለል ባለ አነጋገር ሲገለጽ፤ ጋዳፊ ራሳቸውን በራሳቸው ያገለሉ፣ ራሳቸው በራሳቸው ለቁጥር የሚያስቸግር የውስጥና የውጭ ጠላት ያፈሩና ለክፉ ቀን ጥላ ከለላ ወይም መሸሸጊያ የሚሆን አንድም የጐረቤት ወዳጅ እንኳን ማፍራት ያልቻሉ ብቸኛና ተቅበዝባዥ መሪ ነበሩ፡፡ እንደ ጥቂት የቤተሰባቸው አባላት፣ ስልጣናቸው እስከ ወዲያኛው ድረስ መበጠሱን ካወቁ በኋላ፣ እንዲሁም ሞት ህይወታቸውን ሊቀማ እግራቸው ሥር ሲያነፈንፍ፣ ወደ ውጪ አምልጠው መውጣት ያልቻሉትና በአይጦች ጉድጓድ ውስጥ ለአሳዛኝና አዋራጅ ሞት የበቁትም በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡ ይህንን እውነት እስከመጨረሻዋ ሰአት ድረስ አብሮአቸው ሲጋደል የነበረውና ቆስሎ የተማረከው አጃቢያቸው፣ ለማራኪ ጠላቶቹ በሰጠው ቃል አረጋግጦታል፤ “ሁሉ የሊቢያ ድንበሮች ጨርሰው በአማጽያኑ ተዋጊዎች ከመዘጋታቸው በፊት ወደ ኒጀር ወይም ወደ ቱኒዚያ ማምለጥ እንችል እንደሁ ስንነጋገር፣ ሙአመር ጋዳፊ እንዲህ አሉን:- ማንም ሀገር እኔን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም፤ ማንም! አንድም እንኳ የለም፡፡ ስለዚህ ወደ ሲርት እሄዳለሁ፡፡ ሲርት ተወልጄ ያደኩባት፣ እትብቴም የተቀበረባት ከተማ ናት፤ ወደ እዚያ ሄጄ በዚያ እሞታለሁ” መሪያችን ሙአመር ጋዳፊ ይህን ከተናገሩን በኋላ ሳምንቱን ሙሉ ለብሰውት የነበረውን ቡናማ ቀለም ጀለቢያ አውልቀው በመጣል፣ ግራጫ ቀለም ያለው ካኪ ሱሪና እጅጌ አጭር የሆነ ተመሳሳይ ቀለም ያለው ሸሚዝ አድርገው፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃቸውን አንስተው ወደ ሰማይ በርካታ ጥይት ተኮሱ፡፡ ሲተኩሱ እጃቸው በእልህ ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ወደ ሲርት ጉዞ ስንጀምር፣ እንባቸው በጉንጫቸው እየወረደ እንደነበር አየሁ፡፡ በመጨረሻም የሆነው ሁሉ ሆነ…እሳቸውም ቀደም ብለው እንዳሉት ይሄው እዚያ ያዛችሁአቸው፡፡”

“እኛም ሆነ የተቀረው አለም ደም ባላፋሰሰ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት፣ ንጉስ ኢድሪስን ገልብጠው ከአርባ አመታት በላይ ሊቢያንና ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት  ሀብቷን ልክ እንደግል ንብረታቸው በፈላጭ ቆራጭነት የገዙትን የፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊን መጨረሻ ያየነው ልክ አጃቢያቸው እንደተናገረው ነው፡፡ እድሜ ልካቸውን አብሯቸው በዘለቀውና ብዙዎቹ “ወፈፌ” በሚሉት የማይጨበጥና ጨርሶ ግራ በሚያጋባ አስቸጋሪ ባህሪያቸው የተነሳ ጋዳፊ እጅግ መጠነ ሰፊ የተለያዩ ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎችን ለዘመናት በማከማቸት፣ ድንገት በነሸጣቸው ቀን እንኳን በጐረቤቶቻቸው በመላው አለምም ላይ ጦርነት ከፍተው፣ ማንንም ሀገር አይቀጡ ቅጣት መስጠት እንደሚችሉ ሲዝቱ ኖረዋል፡፡ ይህ ዛቻቸው ግን በጐ ነገር አላተረፈላቸውም፡፡ ጐረቤቶቻቸውም ሆኑ ሌሎች የአለም ሀገራት ሰውዬው ከእነታጠቁት የጦር መሳሪያ እንዲወድሙላቸው በመመኘት፣ ጣልቃ ለመግባትም ሆነ ተቃዋሚዎቻቸውን ለመርዳት እንደ አንድ ምክንያት ሆኖ ሲያገለግላቸው፤ ለተቃዋሚቻቸው ደግሞ የጦር መሳሪያ ፍለጋ የትም ሳይባዝኑና ሌሎችን ደጅ ሳይጠኑ፣ ጋዳፊን ራሳቸው ባከማቹት የጦር መሳሪያ ከስልጣናቸው ገልብጠው እንዲገድሏቸው አስችሏቸዋል፡፡

የጋዳፊን ነገረ ስራ እያሰባችሁ ደማስቆ ሶሪያ ስትገቡ የሚያጋጥማችሁ፣ የጋዳፊ ቀጥተኛ ተቃራኒ የሆነ መሪ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ አንዲትም ነገራቸው ከጋዳፊ ጋር መመሳሰል ቀርቶ በሩቅ ርቀትም እንኳ አይገናኝም፡፡ የሊቢያ ህዝብ በጋዳፊ ላይ አምጾ ሲነሳና የሀገሪቱ ሁለተኛ ታላቋ ከተማ የሆነችውን ቤንጋዚን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የፈጀባቸው ጊዜ እንደ ብርሃን ፍጥነት የሚቆጠር ነበር፡፡

የዛሬ አንድ አመት የበሽር አልአሳድ አምባገነን መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ በመጠየቅ በተቃውሞ ወደ አደባባይ የወጡ ሶሪያውያን ዛሬ የት እንደሚገኙ ብትጠየቁ መልሱን ማግኘት የምትችሉት ከሶሪያ መንግስት ሳይሆን ከዘመድ አዝማዶቻቸው ብቻ ነው፡፡ ከእነዚያ ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ በፕሬዚዳንት አሳድ ወታደሮች ጥይት በጭካኔ ተገድለዋል፡፡ ከፊሎቹ እድለኞች የተባሉት ደግሞ ወህኒ ሲታጐሩ ቀሪዎቹ እምጥ ይግቡ እስምጥ የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ይሁን እንጂ ለነፃነታቸው የከፈሉት ከባድ ዋጋ እንዲሁ በከንቱ አልቀረም፡፡ የተቀሩት ዘመዶቻቸው የወታደሮቹን የታንክና የመትረየስ ጥይት ከምንም ሳይቆጥሩ ነፃነታቸውን ፍለጋ በተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውን አላቆሙም፡፡ እነዚህ ህዝቦች በዚህም ሆነ በወዲያኛው ጠርዝ ቢቆሙ ሞት የማይቀርላቸው ድግስ መሆኑ ገብቷቸዋል፡፡

እናም ለነፃነታቸው እየጮሁ መሞትን መርጠዋል፡፡ እንደነዚህ ህዝቦች ሁሉ የጦር ሀይሉን ከድተው፣ የሶሪያ ነፃ ወታደሮች ቡድንን ለተቀላቀሉት ወታደሮችም ወደ ኋላ የመመለስ እድል ጨርሶ የለም፡፡ በምንም አይነት ሁኔታና አጋጣሚ እንዲህ ካደረጉ፣ ራሳቸውን በራሳቸው የማጥፋት እርምጃ ወሰዱ ማለት ነው፡፡ ከፍ ብለን እንደገለጽነው የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝርዝር ባየናቸው ምክንያቶች የተነሳ፣ አሜሪካና አውሮፓም ከጥቅምና ጉዳት ምዘና ቅኝት የተነሳ የፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድን መንግስት ከማውገዝ ባለፈ መንቀሳቀስ አልተቻላቸውም፡፡ ይህን በትክክል የተረዱት ፕሬዚዳንት አልአሳድም ተቃዋሚዎቻቸውን ያለአንዳች ማወላወልና ርህራሄ በእጃቸው በገባው መሳሪያ፣ በተናጠልም ሆነ በጅምላ መግደላቸውን እስካሁን ድረስ አላቆሙም፡፡ ይህንን ሁኔታ እንደአለመታደል አሊያም እንደ ክፉ አጋጣሚ ወይንም ደግሞ እንደፈለጋችሁት አድርጋችሁ ልትተረጉሙት ትችላላችሁ፡፡ በዚያም ሆነ በዚህ ብትሉ ልትለውጡት የማትችሉት እውነት ግን ነገርዬው ለሶሪያና ለነፃነቱ ለሚታገለው ህዝብ ተስፋ አስቆራጭ የሆነ ስሜት መፍጠሩንና የሶሪያን የነፃነት ጉዞ ረጅምና በእጅጉ አስቸጋሪ እንዲሆን ማድረጉን ነው፡፡

ከአምባገነን አገዛዝ ለመላቀቅና ነፃነታቸውን ለመጐናፀፍ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የሚታገሉት ሶሪያውያን፤ አሁን ተስፋቸውን የጣሉት በሁለት ነገሮች ላይ ብቻ ነው - በአምላካቸው በአላህ እና በጊዜ፡፡

 

 

Read 3455 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:34