Sunday, 28 May 2017 00:00

በውሃ የሚያቦኩበት አገር መጥፎ ነው ብላ፣ በምራቅ የሚያቦኩበት አገር ደረሰች

Written by 
Rate this item
(14 votes)

  ከእለታት አንድ ቀን አንድ ዛፍ ቆራጭ ከወንዝ ዳር ዛፍ እየቆረጠ ሳለ፣ መጥረቢያው ከእጁ ወጥቶ፣ ግንዱ ላይ ነጥሮ ወንዙ ውስጥ ወደቀበት፡፡ በወንዙ ዳር ቆሞ፣
“አዬ ጉድ! የእንጀራ ገመዴ ተበጠሰ!” እያለ ሲያለቅስ፤ የውሃው አማልክት መልክተኛ ሜርኩሪ ብቅ አለና፤
“ምን ሆነህ ታለቅሳለህ? ለምን አዘንክ?” አለው፡፡
“የሥራ መጥረቢያዬ ወንዝ ውስጥ ገባብኝ” አለው፡፡
ሜርኩሪ ወደ ውሃው በዋና ጠለቀና አንድ የወርቅ መጥረቢያ ይዞ ወጣ፡፡ ከዚያም፤ይሄ መጥረቢያ ያንተ
ነውን?” ሲል ጠየቀው፡፡
ዛፍ ቆራጩም፤
“የለም ይሄ የእኔ መጥረቢያ አይደለም” አለና መለሰ፡፡
ሜርኩሪ ለሁለተኛ ጊዜ በዋና ወደ ወንዙ ጠለቀና አንድ ሌላ ከብር የተሰራ መጥረቢያ ይዞ ብቅ አለ፡፡
“ይሄስ ያንተ ነውን?” አለና ጠየቀው፡፡
“እረ የለም፤ ይሄ የእኔ አይደለም” አለ ዛፍ ቆራጩ፡፡
ሜርኩሪ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ውሃው ጠልቆ ሌላ ተራ መጥረቢያ አወጣ
“ይሄስ?” አለው
ዛፍ ቆራጩ፤“በትክክል ይሄኛው የእኔ መጥረቢያ ነው!” አለ በከፍተኛ ሐሴት ተውጦ፡፡ “እጅግ አድርጌ
አመሰግናለሁ!” አለ፡፡
ሜርኩሪም በጣም ረክቶ፤
“ስለ ታማኝነትህ እነዚህን ሁለት መጥረቢያዎች - ከወርቅ የተሰራውንና ከብር የተሰራውን፤ ሸልሜሃለሁ!”
ብሎ ሰጠው፡፡
ዛፍ ቆራጩ ወደ ሰፈሩ ሲደርስ፤
“ዛሬ ትልቅ ፌሽታ ነው ያጋጠመኝ!” ብሎ የሆነውን ሁሉ ለባልንጀሮቹ ነገራቸው፡፡
ከዛፍ ቆራጮቹ አንዱ ቅናት ይይዘዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ወንዙ ሄዶ፣እሱም እድሉን ለመሞከር ይወስናል፡፡
ቀናተኛው ዛፍ ቆራጭ፤ አንድ ከወንዙ ዳር ያለ ዛፍ መቁረጥ ይጀምራል፡፡ ከዚያም አውቆ ወደ ውሃው
መጥረቢያውን ይወረውረውና፤
“ወይኔ መጥረቢያዬ! ወይኔ የሥራ መሣሪያዬ!” እያለ ይጮሃል፡፡
ይሄኔ ሜርኩሪ ብቅ አለ፡፡
“ምን ሆነህ ነው የምትጮኸው?”
“መጥረቢያዬ በሥራ ላይ ሳለሁ ውሃ ውስጥ ወደቀብኝ” አለ፡፡
ሜርኩሪ ወደ ውሃ ውስጥ ጠለቀና አንድ የወርቅ መጥረቢያ ይዞ ብቅ አለ፤ ከዚያም
“የጠፋብህ መጥረቢያ…” ብሎ ሊጠይቀው ሲጀምር፤
ዛፍ ቆራጩ በስግብግብነት፤
“አዎን፡፡ የኔ የራሴ መጥረቢያ ነው! የገዛ ራሴ መጥረቢያ ነው!!” አለና ሁለት እጆቹን ዘረጋ፡፡
ሜርኩሪ የማይታመን ሰው በመሆኑ በጣም በመከፋት፤
“አንተ ታማኝ አይደለህም! ስለዚህም እንኳንስ፤ የወርቅ መጥረቢያ፣ ውሃ ውስጥ የጣልከውን የራስህን
ተራ መጥረቢያም፣ አታገኝም!” አለው፡፡
*   *   *
ታማኝነት የህይወታችን መሰረት መሆን አለበት፡፡ ለሥራ ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለእውቀት ታማኝ
መሆን አለብን፡፡ ለፖለቲካ ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ታማኝ መሆን አለብን፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ ለሀገራችንና ለህዝባችን ታማኝ መሆን አለብን፡፡ በሌሎች ላይ ልናደርገው ያሰብነውን ወይም ያደረግነውን በራሳችን ላይ ሲሆን የምንሸሽ፣ አሊያም መመሪያ የምናወጣበት ከሆነ፣ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡ “ሲያቃጥል በማንኪያ፣ ሲበርድ በእጅ” የምንል ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የምንል ከሆነ፣ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡
ጐር ቫይዳል ምቀኝነትን ሲገልፅ፤ “ጓደኛዬ ሲሳካለት፣ አንድ ነገር ከውስጤ ይሞታል/ይቀንሳል”
እንዳለው፤ ጓደኛችን የተሻለ አገኘ ብለን ዐይናችን የሚቀላ ከሆነ፣ ታማኝነት የጐደለው መንፈስ ነው። “ጐረቤታችን ጫጩት ሲያረባ ስናይ፣ እኛ ሸለምጥማጥ ማርባት የምንጀምር” ከሆነ፣ ፍፁም ታማኝነት የጐደለው የምቀኝነት ድርጊት ነው፡፡ ለእድገት የበቃ ባልደረባችን በደስታ ሲጥለቀለቅ ስናይ፣ እንባ የሚተናነቀን ከሆነ ፈርዶብናል ማለት ነው፡፡ የ”ተያይዘን እንለቅ” ፍልስፍና የትም አያደርሰንም - እርግማን ነው፡፡ በሌሎች ደስታ ውስጥ የእኛን ደስታ ለማየት መቻል አለብን፡፡ ደስታችንን ለሌሎች እናጋራ፡፡ ራስ ወዳድነትን እንታገል!
“ደስታን ከራሱ ጋር፣ አጥብቆ ያሰረ
ክንፍ - ያላትን ህይወት፣ ትንፋሽ አሳጠረ፡፡
ደስታ እየከነፈች፣ የሳማት ሰው ግና
የዘለዓለም ፀሀይ ይሞቀዋል ገና”፤ እንዳለው ነው ዊልያም ብሌክ፡፡
ደስታችን የአገር ይሁን እንደ ማለት ነው፡፡ ደስታ የእኔና የእኔ ብቻ ይሁን ብሎ የሙጥኝ አለማለት ነው። ከአገር ካዝና የወጣ ደስታ፤ የአገር ነውና ለህዝብ እናዳርሰው፡፡ ለራሳችን ሸሽገን አንቀራመተው ማለት ነው። የጋራ ቤታችንን እናስብ፡፡ በፓርቲ አጥር አንታጠር፡፡ ደፋር - መሀይም ብቻ ሳይሆን፣ ጭምት - ምሁር የሚኖርባትም አገር እናልም! ዕቡይ - ምሁር ብቻ ሳይሆን ያልተማረ - ጨዋ ህዝብ ያላት አገር እናስብ። ከፓርቲም ውጪ በቤተሰብ፣ በቢሮ፣ በተቋም፣ በንግድ ድርጅት ውስጥ የሚኖር ነፃ ዜጋ አለ ብለን፣ ከሳጥን ውጪ እንመልከት! ቢያንስ ባስበው ያስበኛል ብሎ ግንዛቤ መውሰድ ያባት ነው፡፡ “የእኔ ወንበር እስካልተነካች ድረስ” የሚል እሳቤ፤ ኃላፊነትን ዘንግቶ አጥር ማጠር፣ ረጅም ጊዜ መኖርን ከዘለዓለማዊነት ጋር ማምታታት ነው (Mistaking Longevity for immortality እንደ ማለት ነው)፡፡ በዚህም እሳቤ ምክንያት ነው መተካካትን ከብወዛ ጋራ አንድ አድርገን (Mistaking Replacement for Reshuffling እንደ ማለት) የምናየው፡፡ ወደድንም ጠላንም ቢያንስ ማንም ሰው ሊተካ የሚችል ነው፤ የማይተካ የለም (No one is indispensable) የሚለውን ሁለንተናዊ መርህ ያለ ራስ ወዳድነት፤ ያለ ምቀኝነት እንቀበል፡፡
ከአጠቃላይ ነባራዊ እውነታው፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፤ አናመልጥም፡፡ እውነታውን ተቀብሎ መፍትሄውን መሻት ከአላስፈላጊና ከማናመልጥበት ሽሽት ይገላግለናል፡፡ አገርም ለቅቀን እንሽሽ ብንል አይሆንም፡፡ ከራስ የህሊና ቁስል ማምለጥ አይቻልምና፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የናዚም ወታደር ይያዛል፤ ተብሏል፡፡ በመሸሽ፣ በመሸሸግና ሌላ አገር በድሎት ከመኖር ጋር ራስን ማስተሳሰር ቢያንስ የዋህነት ነው። እንኳን በባሌ በቦሌም ምቾት ቅርብ አደለም፡፡ ምቾትና ነፃነትን በሌላ ምድር ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ በሰሜንኛ፤“ጠላ አገኛለሁ ብለህ ውሃ ረግጠህ አትሂድ”ይባላል፡፡ በወላይትኛ ደግሞ፤“በውሃ የሚያቦኩበት አገር መጥፎ ነው ብላ፤ በምራቅ የሚያቦኩበት አገር ደረሰች”ማለት ነው፡፡ በማህል አገርኛ፤“ከድጡ ወደ ማጡ” ብለው ያጠቃልሉት ይሆናል፡፡ ብቻ ከዚህ ይሰውረን!!

Read 6256 times