Sunday, 21 May 2017 00:00

ጉድ‘ኮ ነው! አሰፋ ጫቦ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

  ሲያስቡት? ጉድ! እንዲያው ጉድ እኮ ነው!
ያንዱ ሥጋ ወነፍስ፣
የሌላው ቀለብ፣ ድግስ፤
ምሳ ራት ቁርስ፡፡
እኔኮ የሚገርመኝ፣
የሚከነክነኝ፣
      ይኸ ሰርቶ አፍራሹ
ፈጣሪው ደጋሹ     
ከያሊው ፈዋሹ፡፡
ያኔ ሲነገር፣ ስንማር፣ ስንመከር፣
ምሉእ በኩሌሐ
ወይትባረከ ሰመ ስብቲሐ
እስመ አልቦ ነገር አሚረ ኩሉ
መአቱ የራቀ ምህረቱ ሙሉ
ብለው አሳምነው አልነበር?
ያልነገሩን ተረፈሪ ሚስጥር ነበረ?
ምነው ልቤ ጠረጠረ?
ሰማይን ያለባላ፣ ያለምሶሶ
ምድርን ያለካስሚያ፣
የዘረጋ፣ የወጠረ፣
ኁልቆ መሳፍርቱን የፈጠረ፣
ዝንፍ፣ እልፍ የማይል
      የማይልበት
የወርቅ ሚዛን ያለው፣
     የሚለካበት፣
የውሃ ልክ ያለው የሚለስንበት፣
             የተባለለት፡፡
አድሎ የሌለበት፣
ከዘላለም በፊት የነበር፣
ከዘላለም በኋላም የሚኖር፣
ህጸጽ አልባ ሚስጢር፣
ነው-ው-ው! ተብየም አልንበር?!
እና!? እኮ!? ያ ሁሉ የት ሔደ?
እንደጉም በነነ? እንደኬላ ተናደ?
ይኸው ነው የዚያ ሁሉ ስብከት ውጤት?
አንዱ የሌላ ቁርስ ምሳ ራት
ማነው ስቶ ያሳተኝ?
ካናቱ ወደ ደቀ መዛሙርታት?
 
ልቤ የሚጠረጥረው?
እንዲያው ድንገት ለምናልባት፣
ባራያ በምስሉ የፈጠረን ለት፣
ሲወጥር፣ ሲተክል፣
ሲያቆም ሲጥል፣ ሲነቅል፡፡
ሲዘረጋ፣ ሲሸበሽብ፣
ጎንበስ ቀና እስኪያልብ፡፡
ቀና ደፋ ሲል ደክሞት፣
ታክቶት፣ ሰልችቶት፣
የሰአት እላፊም ደርሶበት፣
ሲጣደፍ ኮታ ለመሙላት፣
ጀምበር ጠልቆ፣ መሽቶበት፡፡
አላልቅ ብሎ ሲጣደፍ፣
ለሚኒሞው ገረፍ ገረፍ፣
በዊክ ኤንድ ለማረፍ፡፡
በድንግዝግዙ ለድንገት ዞር ባለበት፣
ሚዛኑ ላፍታ፣ ለድንገት
ደፋ፣ ቀና፣ አለበት?
ተንጋዶ? ሔድ መለስ አለበት?
ላንዳች ቅጽበት፣ ሰውን ፈጠርኩ ባለበት?
እንጅማ!
እንደ መሸታ ስራ ሠንካላ፣
በቅጡ ያልበሰለ ያልተብላላ፣
ተሟሽቶ ያልተሞከረ፣ ያለየ፣
ጉዳት ጠቀሜታው ያልታየ፣
ሰንካላ፣ ግርድፍ፣ ያልተበራየ፡፡
በቃ ሂድ፣ ወግዱ፣
ከዚህ ጥፉ፣
ብሉ፣ ተባሉ፣
ምድርንም አጥፉ!
ይኸውልህ! እች ያንተ ነፍስ፣
ትሁን ለነንትና ድግስ፤
ምሳ፤ራት፣ቁርስ፣
ነውር አይደለም እንዴ በኔ ሞት!?
ተፈቶ ይለቀቃል እንዴ መጠፋፋት?
መተላለቅ መሟሟት?
ደሞም!
ስራውን አያቅም፤
አይችልምም አልተባለም!!
እኔማ የሚገርመኝ
መንጋ ጉሮሮ ከፍቶ፣
መዝጊያ፣ መቀርቀሪያ ሳይሰራ ትቶ
ግበረ-በላ አብዝቶ፣ ለቆ ፈቶ፣
ቀለብ ሳይሰራለት፣ ሳይቀርጥለት፣ ሳይሰፍርለት፣
እንዲኖር ተናንቆ፣
ተነጣጥቆ፣
ተጠባብቆ፡፡

ጎብዝ! እኔ የምለው!
ምነ አንድ እድል ቢሰጠን፣
ያለፈውን፣ ያለውን፣
ሙከራ ነበር! ተሞክሮ ነበረ፤
አልተሳካም ከሸፈ ከሰረ!
ፋይሉም ፋብሪካውም ይዘጋ፣
ይቆጠር እንዳልነበረ፡፡
እናም እንዳያዳግም፣ እንዳያደጋግም፣
በትርፍ ሰአት ክፍያም ቢሆንም፡፡
ስድስቱ ቀን ቀርቶ፣
አዲስ ተዘርቶ፣ ታጭዶ፣ ተወቅቶ፣
አብሲት ተጥዶ፣ በቅጡ ቦክቶ፣
ስምንትም ይሁን ሰማኒያ ቀን ተፈጭቶ፣ ተፋጭቶ፣
ሰውን የሚያክል ነገር አደል?
የፍጥረታት የበላይ አካል?
የሚፈጠር ባምላክ አምሳል?
አዲሱ ሰው ይሰራ ቢባል!?
አንገቱን ረዘም መለል ማሰኘት፣
ተነቃናቂ ተጣጣፊ ብሎ ማስገባት፣
ለስላሳ ኩሺኔትም ጨምሮ መክተት፣
ዙርያ-ገቡን ሁሉ-ገቡን እንዲያይበት፣
እዝነ ልቦናውም አይነ ልብናውም፤
ዳጎስ፣ ጎላ ቢልለት፤
የሰማው ያየው፤ እንድያርበት፣ እንዲያድርለት፤
እንዲሰነብት፤ እንዲሰነባብት፡፡፡
ዘኃለፈ ሰርየትም እንዲለበት፣
ከማት አምጭነት እንዲታቀብበት!
ሰፋፊ ልብም፣ ልቦናም የሰጠው!
ትልቁ ቱቦ፣ ትልቅ ቧንቧ ያለው፤
ሰው የሚሔድበት፤
ሰው የሚመጣበት፡፡
ሰው የሚመላለስበት፣
ሰው አድሮ የሚውልበት፣
ሰው የሚታቀፉበት፣
ሰው የሚታቀቡበት፣
…. የሚሰነባብትበት!
የሰራ አካላቱ እንዲሁ፣
…. ዚኒ ከማሁ፡፡

ወይስ ከነአካቴው!
እንበል እንዴ ሰሪም ተሰሪም፣
ፈጠሪም ተፈጣሪም አልነበረም!?
ይኽ ክርቲካል ማስ ያሉት ሲገጣጠም፤
ሰኔና ሰኞ ፍጥምጥም!
አስቀድሞ የነበር፣ ያልነበር አንድ ትልቅ ዝም!
አንድ ቀን ቡም! ቡም! ቡ-ም-ቡ-ም!
………… ቡምቡም!
መሰባሰብ! መጠረቃቀም!
ከመሀል አልቦ የትም!
ወደዝንተ አለም ምንም!
ወደ ዘላለም እርም!
…. አበስኩ! ገበርኩ!
April 1,1995
Los Angeles, California, USA

Read 2227 times