Sunday, 21 May 2017 00:00

ኢቢሲ ለምን የህዝብ ሚዲያ ለመሆን ተሳነው?

Written by 
Rate this item
(14 votes)

   ጥናቶች ምን ይላሉ?
   የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ተጠሪነቱ ለህዝብ እንደራሴዎች ነው፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ የህዝብ ሚዲያ አልሆነም የሚሉ ትችቶችና ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግ በ10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ኢቢሲን ጨምሮ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ወገንተኛ መሆን እንዳልቻሉ አመልክቶ
ነበር፡፡ ከሰሞኑም ኮርፖሬሽኑ ያሉበትን ችግሮች የሚቀርፍ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያደርግ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ታዟል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የኮርፖሬሽኑ ዋነኛ ችግሮች ምንድን ናቸው? ለምን የህዝብ አመኔታ ማግኘት ተሳነው? እንዴትስ ተሻሽሎ የህዝብን ቀልብ መግዛት ይችላል? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህራንን አነጋግሮ አስተያየታቸውን
እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡
    
              “የአመለካከት ለውጥ ካልመጣ በቀር ሚዲያው ብቻ አይቀየርም”
               እንግዳወርቅ ታደሰ (በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር)

     ኢቢሲ እድሜ ጠገብና ግዙፍ ተቋም በመሆኑ በአሁን ውቅት በዘርፉ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራንን ትኩረት የሳበ ሆኗል፡፡ በርካቶች ጥናት ሰርተውበታል፡፡ እኔም ከነዚህ ጥናቶች ተነስቼ ነው አስተያየቶችን የምሰጠው፡፡
በአጠቃላይ ይህ የሚዲያ ነፃነት ችግር የአፍሪካ ሀገራት ችግር ነው፡፡ ደግሞ ከህትመቱ ይልቅ ብሮድካስት ሚዲያው ላይ ችግሩ ይጠነክራል። ጥናቶች ይሄን ያሳያሉ፡፡ የብሮድካስት ሚዲያ ያልተማረውን የህብረተሰብ ክፍልንም ስለሚያዳርሱና ለጠንካራ የሀሳብ መንሸራሸሪያነት ምቹ ስለሆኑ መንግስታት የበለጠ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጉባቸዋል፡፡ የኛም ሀገር ሁኔታ እንዲሁ ነው፡፡ ለምሳሌ የሬዲዮን ጉዳይ ብቻ ነጥለን ብንመለከተው፣ የአፍሪካ መሪዎች ሬዲዮንን በእጅጉ ይፈልጉታል፤ ስለዚህ ለማንም አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም። ይሄን ባህሪ ደግሞ የወረሱት ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነው፡፡ እኛ ሀገር ጣሊያን 5 ዓመት በቆየበት የወረራ ጊዜ እንኳን ይህቺን ልምድ ነው ትቶ ያለፈው፡፡ ሳንሱር ማድረግና ሬዲዮውን ለፕሮፓጋንዳ ጥቅም ማዋል የመሳሰሉ ልምዶችን ትቶልን ነው ያለፈው፡፡
የሀገራቱ መንግስታትም ሚዲያን የሚያስፋፉት ከራሳቸው ሁነቶች ጋር በማስተሳሰር ነበር፡፡ ለምሳሌ ቴሌቪዥን የተጀመረው ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጋር በተገናኘ ነበር፡፡ ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ነበር እንጂ በእርግጥም ህዝባችን ሚዲያ ያስፈልገዋል ከሚል መነሻ አልነበረም፡፡ ይሄ ሁኔታ እያደገ መጥቶ ነው አሁን ያለው ችግር ላይ የጣለን፡፡ ጥናቶችም የሚያሳዩት ይሄንን ነው፡፡ አሁንም ጡንቻና አቅም ያለው አካል ሚዲያውን ለመሳሪያነት ይጠቀመዋል። የፕሮፓጋንዳና ፖሊሲ ስርፀት የሚሰራው ሚዲያውን አንቆ በመያዝ ነው፡፡
አንድ ኖርዬአዊ አቢሲ ላይ ያጠናው ጥናት አለ። በጥናቱ ላይ ሌሎች የመንግስት መገናኛ ብዙኃንም ተካተውበታል፡፡ ግለሠቡ በዚህ ጥናቱ፤ ላይቤሪያና ኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛታቸው መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ይጠቅሳል፡፡ ሚዲያዎቻቸው የሃገር ውስጥ ጉዳዮችን በስፋት እንደሚዘግቡ ያስቀምጣል፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገሮች ግን የትኩረት አቅጣጫቸው ከውጭ ሚዲያዎች የሚቀዳ ነው ይላል፡፡ ግን ይሄም ቢሆን ሚዲያው ነፃ እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ ከፍተኛ ክፍተት ያለውም አመራሩ ላይ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት እንዳለ ይገልፃል፡፡ እኔም ራሴ ጥናቴን የሰራሁት በዚህ ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ እንዴት ነው ነፃነት አላችሁ ወይ ብዬ ስጠይቅ፣ “ወቅቱ ክፉ ካልሆነ ነፃ ነን፤ ጠንካራ  ጉዳይ ከተነሣ ግን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ይኖራል” የሚል መልስ ነው ያገኘሁት፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች ባሉበት እንዴት ነው ‹‹ሪፎርም›› ይደረግ የሚባለው? አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቹ አመራሮች የሙያ ብቃትና ችሎታ ያንሣቸዋል። ታማኝ በመሆናቸው ብቻ ወደ አመራርነት ስለሚመጡ ብዙም ለውጥ አያመጡም፡፡ ኢቢሲ ሙያን የመረዳት ውስንነትና በራስ የመተማመን ችግር ያለበት አመራር እንዳለው ጥናቶች በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ አመራሩ ከገዥው መደብ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ዋናው ችግርም ይሄ ነው፡፡
ጋዜጠኞቹን ስናይ ሁለት መልክ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ለሙያው ብቻ ይተጋሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የዚህ ባህሪ የላቸውም፡፡ በሌላ በኩል በየክፍሉ  የተመደቡ ኤዲተሮች /አዘጋጆች/ አመዳደብም ተፅዕኖ እንደሚያደርግ ግልፅ ነው፡፡ አዘጋጅ ሆነው የሚቀመጡ ሰዎች ብቃት ወሳኝነት አለው፡፡
እኔ አጠቃላይ የአመለካከት ለውጥ ካልመጣ በስተቀር ሚዲያው ብቻ ይቀየራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኔ ለማስተምራቸው ልጆች የምነግረው ወገንተኛ እንዳይሆኑና ሙያውን እንዲያከብሩ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩ የኛ ጋዜጠኞች መጀመሪያ በኢኮኖሚ አቅማቸው በሁለት እግራቸው መቆም ይፈልጋሉ፡፡

------------

                     “የኢቢሲ ጋዜጠኞች ነፃነታቸውን ማስከበር አለባቸው”
                       ሄኖክ ንጉሴ (በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር

      ኢቢሲ የጋዜጠኝነትን ንድፈ ሀሳብ ከመከተል አኳያ ብዙ ችግር አለበት፡፡ በ2008 እ.ኤ.አ የመንግስት ሚዲያ ልማታዊ ጋዜጠኝነት እንደሚከተል ታውጆ ነበር፡፡ ኢቢሲም ይሄን እንዲከተል ነው የተባለው። ግን ከልማት ጋዜጠኝነት አተገባበሩ ጋር በተያያዘ ብዙ ጉድለትና ክፍተት አለበት፡፡ አንደኛ የልማት ጋዜጠኝነት በተለያዩ ሀገራት የተለያየ አተረጓጎምና አተገባበር ነው ያለው፤ ቁርጥ ያለ መርህ የለውም። መንግስታት በራሳቸው አካሄድ እንዲተረጉሙት መንገድ የሚከፍት ነው፡፡
ለምሳሌ የፊሊፒንስ መንግስት የልማታዊ ጋዜጠኝነትን በራሱ የፖለቲካ አስተሳሰብ በመተርጎም፣ ያንን ለጋዜጠኞች በመስጠት እንዲመሩበት ያደርጋል። የኛም ሀገር እንዲህ ያለ ባህሪ ነው ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ ለባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት በር ይከፍታል፡፡ ጋዜጠኛውን ነፃነት የማሳጣት ነገሮች እንዲበራከቱ ያደርጋል፡፡ ኢቢሲም የዚህ ችግር ተጠቂ ሆኖ ነው የምናየው፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ለእንደዚህ ያለ ጣልቃ ገብነት የተጋለጠ ነው፡፡
ኢቢሲ ለፓርላማው በሰጠው ማብራሪያ ጣልቃ እየተገባብኝ ነው ማለቱም ከዚህ አንፃር የሚፈጠር ነው፡፡ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ፅንሰ ሀሳብን ለመተግበር ከተፈለገ በራስ ብቻ ከመተርጎም ይልቅ ምሁራንን በሚገባ አነጋግሮ፣ ጋዜጠኞችንም አማክሮና በሚገባ አሰልጥኖ ወደ አሰራር ማምጣት ቢቻል  ውጤታማ ለመሆን ይቻል ነበር፡፡
ለኔ በዋናነት በኢቢሲ የሚታየኝ ችግር የልማታዊ ጋዜጠኝነት ፅንሰ ሀሳብን አዛብቶ ተርጉሞ የመተግበር ነገር ነው፡፡ እኛ በቅርብ ጊዜ በመንግስት ሚዲያዎች ላይ ያከናወንናቸው ጥናቶች ሳይቀሩ የመንግስት ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት እንዳለ ያረጋግጣሉ። ጋዜጠኛው ነፃ እንዲሆን አልተደረገም። ነፃነት ደግሞ ለጋዜጠኛ ዋናው መርህ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ አሁን እየተተገበረ ነው የሚባለው የልማታዊ ጋዜጠኝነት ሞዴል በድጋሚ ለውይይት  ሊቀርብ ይገባል፡፡
የልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ያቀጭጫል የሚሉ ክርክሮች አሉ። በእርግጥም ይሄን በኛ ሃገርም እየተመለከተነው ነው፡፡ አንድ ባለስልጣን በዚህ ደረጃ ጣልቃ ገብነት ካለው የምርመር ጋዜጠኝነትን ለመስራት አስቸጋሪ ነው ማለት ነው፡፡
ኢቢሲ ውስጥ ባለስልጣናት ጣልቃ እንዳይገቡ የሚገድብ ህግ መኖር አለበት፡፡ ሌላው አቢሲ የህዝብን ፍላጎት አዳምጦ የመዘገብ ባህል ማዳበር አለበት፡፡ ያን ጊዜ ነው ኢቢሲ የህዝብ ነው የሚባለው፡፡ ግጭት ሲኖር የመንግስት ጥቅም እንጂ የህዝብ ጥቅም ሲንፀባረቅበት አይታይም። መነሻቸው የመንግስት ምላሽ ነው እንጂ የህዝብ ቅሬታ አይደለም፡፡ ይሄ ሁሉ የሚስተካከለውና ጣቢያው በተግባር የህዝብ የሚሆነው ነፃነቱን ሲያረጋግጥ ነው፡፡
በሌላ በኩል የኢቢሲ ጋዜጠኞች ራሳቸውን ከባለስልጣናት ጣልቃ ገብነትም ሆነ ከሌሎች አካላት ለመከላከል የሙያ ማህበር ሊመሰርቱ ይገባል። በአጠቃላይ የሙያው ማህበራት መጠናከርና የራሳቸውን ነፃነት ማስከበር አለባቸው። የጋዜጠኝነት ትልቁ መርህ ነፃነት ነው፡፡ ነፃነትን የምታመጣው በጋራ ሆኖ በመንቀሳቀስ ነው፡፡
አንድ በቅርቡ የተጠና ጥናት፤ በመንግስት ሚዲያዎች ያሉ ጋዜጠኞች የፓርቲ አባላት እንደሆኑና ሙያዊ ጉዳዮችን ሲነጋገሩ፤ ከፓርቲያቸው አሸማቃቂ ትችቶች እንደሚደርስባቸው ያትታል፡፡ ስለዚህ ለሙያው ሳይሆን ለድርጅታዊ መርህ ታማኝ መሆንና እንጀራዬን አጣለሁ ብሎ የመስጋት ችግር እንዳለ ያመላክታል፡፡ ስለዚህ የሙያ ማህበራት መቋቋምና መጠናከር አለባቸው፡፡ ከጣልቃ ገብነትም ራስን ለመከላከል አንዱ መሳሪያ ነው፡፡

---------------

                   “በህዝብ ተአማኒነት ያጣ ሚዲያ እንደሌለ ነው የሚቆጠረው”
                   በለው አንለይ (በሐዋሣ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር)

      በአንድ ሀገር ውስጥ የዲሞክራሲ ስርአት ለመገንባት፤ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ሙስናን ለመከላከል፣ የመገናኛ ብዙኃን ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በሀገራችን በመንግሥት ስር በርካታ መገናኛ ብዙኃን አሉ፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ከፓርቲ ፍላጎት ነፃ ሆነው እንዲሰሩ ቢደረግ የተጠቀሱትን ህዝባዊ አገልግሎቶች መስጠት ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢቢሲ ህዝብ የሚፈልገውን ማድረግ አልቻለም፡፡ “የብዝኃነትና የህዳሴ ድምፅ” የሚል መሪ ቃል ባለቤት ቢሆንም ተግባሩ መሪ ቃሉን በትክክል የሚገልፅ አይመስለኝም፡፡
የህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ንፁስ አንቀፅ 5፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችንና ሀሳቦችን ለማስተናገድ በሚያስችል ሁኔታ እንዲሰራ ይደረጋል ነው የሚለው፡፡ እንግዲህ ኢቢሲም የተመሰረተበት አላማ ይሄው ነው፡፡ በህገ መንግስቱ ኢቢሲ የህዝብ መሆኑ በግልፅ ተቀምጧል። ጥያቄው እንደ ህዝብ መገናኛ ብዙኃንነቱ የህዝብ ሆኗል ወይ የሚለው ነው። እንደ መሪ ቃሉ የብዝኃነት ድምፅ መሆን ችሏል ወይ? ጣቢያው የህዝብ ፍላጎቶችን እያንፀባረቀ አይደለም፡፡ ለዚህም ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በመንግሥት እንደሚነገረው፤ ሙስና በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ተከታትሎ ለህዝብ ማጋለጥ ያለበት ደግሞ የህዝብ የተባለው ኢቢሲ ነው፡፡ እኔ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፤ እስካሁን ኢቢሲ አጋልጦት የታሰረ ወይም ከስልጣኑ የተባረረ ባለስልጣን አናውቅም፡፡ ምናልባት መንግሥት ራሱ ባለሥልጣን ካሰረ በኋላ ነው ከስር ከስር የሚዘግበው እንጂ አስቀድሞ አጋልጦ ሲያቀርብ አላየሁም፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሙከራ ሊኖር ይችላል እንጂ በተግባር በሚገባ ሲውል አናይም፡፡ ይሄ የሚያሳየው የፓርቲ ወገንተኝነት እንደሚያጠቃው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የህዝብ ተአማኒነትን ያሳጣዋል፡፡ እንዲህ ያለ ተአማኒነትን ያጣ ሚዲያ ደግሞ እንደሌለ ነው የሚቆጠረው፡፡ ለአንድ ሚዲያ ተአማኒነትን ከማጣት በላይ የሚጎዳው ነገር የለም፡፡
አሁን ኢቢሲ እንደሚመራበት ጋዜጠኝነት፣ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ብቻ ነው ብልን ከተረጎምነው ትልቅ አደጋ አለው፡፡ ይሄ ኢቢሲ ከተመሰረተበት የህገ መንግስቱ አላማ ጋርም ይጋጫል፡፡ ጋዜጠኝነት ልማታዊ ጋዜጠኝነት ብቻ አይደለም፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ቁንፅል ነው፡፡ በኛ ሃገር ልማታዊ ጋዜጠኝነት ለመንግስት እንዲጠቅም ተደርጎ ነው የተተረጎመው፡፡ ጋዜጠኝነት ማለት ሃሳብን መግለፅ ማለት ነው፡፡ ሃሳብን መግለፅ ደግሞ ስለ ልማት ብቻ ማውራት አይደለም፡፡ ይሄ የሚዲያን ታሪካዊ ሚና ወደ ጎን ገሸሽ የሚያደርግ ነው፡፡
ኢቢሲ የህዝብ ሚዲያ እንዲሆን ከተፈለገ ብዙ መድከም ሳያስፈልግ ህገ መንግስቱ ላይ ያለውን ነገር ወደ ተግባር ማውረድ በቂ ነው፡፡ ብዝኃነት ስንል የአስተሳሰብ ብዝኃነትም ስለሆነ የተቃዋሚ ድምፆች እንዲሰሙ ማድረግ የመሳሰሉትን በሙሉ ሽፋን መስጠት አለበት፡፡ይህን ለማድረግ ይሄ ሚዲያ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች መመራት አለበት፡፡ ሁለተኛ በፓርቲና በመንግስት መካከል ያለው ልዩነት በግልፅ መታወቅ መቻል አለበት፡፡
ፓርቲ የራሱን ሚዲያ መመስረት መቻል አለበት። መገናኛ ብዙኃንን የፓርቲ፣ የህዝብ/የመንግስት ወይም ነፃ ሚዲያ ብለን በሶስት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ መንግስታዊ/ ህዝባዊ ሚዲያ የምንለው ሙሉ ነፃነት ሊኖረው ይችላል፡፡ የፓርቲ ሚዲያ ግን የፓርቲው አቋም ብቻ የሚንፀባረቅበት ነው የሚሆነው፡፡ ከፓርቲ አመለካከት ውጪ ከሆነ ፓርቲው የራሱን እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር የኛ ሃገር ችግር የፓርቲና የመንግስት/ህዝብ ሚዲያ ልዩነት ጠርቶ አለመቀመጡ ነው፡፡ ይሄ መስመር ከጠራ ብቻ ነው ኢቢሲ ትክክለኛ የህዝብ ሚዲያ መሆን የሚችለው፡፡

-------------

                “የጋዜጠኞች ገለልተኛ አለመሆን ትልቁ ችግር ነው”
                አስማማው አዲስ (በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ጋዜጠኝነት መምህር)

      በቅርቡ የምሁራንንና የሚዲያዎች ግንኙነት ላይ ያተኮረ አንድ ጥናትእያጠናሁ በነበረበት ወቅት ኢቢሲ ተአማኒነቱን ማጣቱን ከጥናቴ ውጤት ተገንዝቤአለሁ፡፡ ለጣቢያው ተአማኒ አለመሆን ዋናው መንስኤ ደግሞ የጋዜጠኞች ከመንግስታዊ አካል ተፅዕኖ ነፃ አለመሆን ነው፡፡ ሁለተኛው ሚዲያው የሚመራበት ፍልስፍና ችግር ነው። ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው የሚለው፡፡ ግን ይሄ በትክክለኛው ትርጉም አልተያዘም፡፡ በመሰረቱ ልማታዊ ጋዜጠኝነት በሶስት ይከፈላል፡፡ አንደኛው Pro-process የሚባለው ነው፡፡ ይሄ ለሂደቱ ድጋፍ ማድረግ የሚል መርህን ያነገበ ነው፡፡ ከመንግስት ጋር በመሆን ለመንግስት ስትራቴጂዎች አስተዋፅኦ ማድረግ የሚል ነው፡፡  
መንግስት የሚሰራውን ከስር ከስር እየተከታተሉ መዘገብ ማለት ነው፡፡ ሌላኛው የልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ Pro-participation የሚባለው ነው፡፡ ይሄ ዜጎች መብታቸው እንዲከበር አተኩሮ የሚሰራ መርህ ነው፡፡ ሌላኛውና ሶስተኛው Pro-government የሚባለው ነው፡፡ ይሄኛው በመንግስት ፖሊሲ ጥላዎች ስር ሆኖ የመንግስትን ፖሊሲዎች ማስፈፀም ነው፡፡ የኛ ሀገር ሚዲያ በዚህ ስር ያለ ይመስለኛል፡፡ ይሄ በራሱ የጣቢያው ችግር ነው፡፡
በሌላ በኩል የጣቢያው ፕሮግራም ይዘቱ አሰልቺ ነው፡፡ ተደጋጋሚና አታካች ናቸው፡፡ ጣቢያው የጋዜጠኞች የእውቀትና የክህሎት ችግር አለበት፡፡ ይሄን ነው ጥናቴ ያመላከተኝ፡፡ ለዚህ ነው ከምሁራን ጋር እንዳይሰራ የሆነውም፡፡ በጣቢያው ላይ ያለበቂ ጥናትና ምርምር የሚቀርቡ ፕሮግራሞችም በርካታ መሆናቸው በጥናቴ ተመላክቷል፡፡ ይሄ ነው በህዝብ ዘንድ ለትችት የሚዳርገው፡፡
በጋዜጠኝነት ውስጥ ቀላሉ መርህ “እውነትን መናገር” የሚለው ነው፡፡ ይሄ በኛ ሀገር ገና አልመጣም። የባለስልጣናት ጉዳይ እንጂ ህዝብ ጋ ያለ እውነትን ለማግኘት ጥረት አይደረግም፤ የህዝብ እውነታም ሲቀርብ አይስተዋልም። ሌላው የፕሮፓጋንዳ ተጠቂ መሆን ወይም ለፕሮፓጋንዳ ማስተላለፊያነት የተመቻቸ መሆኑ ነው፡፡ ገለልተኝነት ማጣት ሌላው ትልቁ ችግር ነው፡፡ ጋዜጠኞች ከባለስልጣናት ራሳቸውን አለማግለላቸው ይባስ ብሎ ከነሱ ጋር እጅና ጓንት መሆን ይታያል፡፡ ኃይልና ስልጣን ላላቸው ሰዎች ተገዢ የመሆን ነገር ይታያል፡፡ ለህሊና ተገዥ ያለመሆን ችግር በስፋት እንደሚታይ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ አንዳንዴ ባልተፃፉ የጋዜጠኝነት መርህና ህግ ሁሉ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
ጣቢያው ልማታዊ ጋዜጠኝነት እከተላለሁ ካለ፣ በሚገባ መርሁን መተግባር አለበት፡፡ ለምሳሌ የህዳሴው ግድብ ያለበትን ደረጃ ለመግለፅ የሚሰራ ዘገባ፤ ከጊዜው የዘገየ ከሆነ ለምን ዘገየ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
ጣቢያው በአጠቃላይ መሻሻል ከፈለገ፣ ጋዜጠኞች ሙሉ ነፃነት ማግኘት አለባቸው። ተቋሙም ነፃ ሆኖ መንቀሳቀስ መቻል አለበት፡፡

--------------

                     ‹‹ኢቢሲ አለቃው ህዝብ ነው››
                      ተሻገር ሽፈራው (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር)

     የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የሚመሩት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተወጣጡ የቦርድ አባላት ነው፡፡ የቦርድ አባላቱ ከሚዲያዎቹ ህዝቡ ፍትሃዊ የሆነ ዘገባ እንዲቀርብለት፣ በመንግስትና በህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል፣ የዲሞክራሲ ባህልን እንዲያሣድግ የመሣሰሉ ጉዳዮችን የመከታተል ሃላፊነት አለባቸው፡፡
ይሄ በማቋቋሚያ ደንቦችም ተደንግጓል፡፡ ሚዲያዎቹ የህዝብና ሃብት መሆናቸው፣ እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ህዝብን አሳታፊ እንዲሆን በድንጋጌዎቹ ተቀምጠዋል፡፡ አሁን ዋናው ችግር እየታየ ያለው ይሄን ወደ ተግባር መለወጡ ላይ ነው፡፡
በተግባርና በሙያ መርሀ መካከል ያለውን ክፍትት መሙላት ከተቻለና መርሆዎቹ መሬት ከወረዱ እነዚህ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ትልቁ ችግር ይሄ እየተፈፀመ አለመሆኑ ነው፡፡ለምሳሌ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደተጨባጭ ሁኔታ ትክክለኛና ፍትሃዊ የዜና ሽፋን ማግኘት መብቱ ቢሆንም በተግባር እየታየ ያለው ከተማ ተኮር ወይም ባለስልጣናት ላይ የሚያተኩር ዘገባ ነው የሚቀርበው፡፡ ህዝብ ስለእያንዳንዱ ነገር ማወቅ አለበት፤ ይሄ እየሆነ አይደለም፡፡
በመንግስትና በህዝብ መካከል ድልድይ መሆን አለበት ስንል የውይይት መድረክ ያዘጋጃል፡፡ በዚህም ሃሣብ ከላይ ወደታች ብቻ ሳይሆን ከታችም ወደ ላይ ይወጣል ማለት ነው፡፡ ይሄ እስካሁን አልተሠራም። አሁን ግልፅ ልዩነት ያለው በአዋጆቹና በተግባር መካከል ነው፡፡ ያንን ማቀራረብ ከተቻለ ነው የሚፈለገው ለውጥ የሚመጣው፡፡
ኢቢሲ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተጠሪ ሲሆን አለቃው ህዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በተግባር ስናየው የመንግስት ቢሮዎች ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት ከፍተኛ ተፅዕኖ ይታይባቸዋል። ከነዚያ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ መረጃዎች ናቸው እንጂ በሚዲያው በኩል ከፍተኛ ግምት ሊሠጣቸው የሚገባው፡፡ እነሱን የሚገዳደር ነገር መምጣት የለበትም፡፡ ኢቢሲ ከመንግስት አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ተፅዕኖ ወጪ መሆን አለበት፡፡ አለቃው ህዝብ ነው፤ ስለዚህ ህዝብ ነው የሚቆጣጠረው እንጂ አስፈፃሚ አካሉ አይደለም፡፡
ዋናው ኢቢሲ እንዲሻሻል ከተፈለገ፤ ሙያዊ ነፃነቱን፣ የጣቢያውን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ማክበር ነው፡፡ ኤዲተሮች/አዘጋጆች ራሳቸውን ከተፅዕኖ ነፃ አውጥተው፣ የተሠጣቸውን የሙያ ነፃነት መርህ በድፍረት ከተገበሩ ነው ሚዲያው የህዝብ መሆን የሚችለው፡፡

Read 4580 times