Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Wednesday, 04 April 2012 09:48

ዝነኛው ኢትዮጵያዊ ገጣሚ - በእንግሊዝ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያዊው ገጣሚ፣ ደራሲና ፀሃፌተውኔት ለምን ሲሳይ በመላው እንግሊዝ ከሚገኙ ዕውቅና ምርጥ ገጣሚዎች በቀዳሚነት ስሙ ይጠቀሳል፡፡ በዓለም አቀፍ ፀሃፊነቱ የሚታወቀው ለምን ሲሳይ፤ አምስት የግጥም መድበሎችን በእንግሊዝኛ ፅፎ አሳትሟል፡፡ የጥቁር እንግሊዛውያን ዘመነኛ ገጣሚዎችን ሥራዎች ያካተተውን “The Fire people” የግጥም መድበል የአርትኦት ስራም እንደሰራ ይናገራል፡፡ ለታዋቂው “Poetry Review” በመደበኛነት ፅሁፎችን የሚያቀርበው ገጣሚ ለምን፤ The Avron Poetry prize የተሰኘውን ውድድር ጨምሮ በሌሎች ትላልቅ የሥነ ፅሁፍ ውድድሮች ላይ በዳኝነት ሰርቷል፡፡ ቢቢሲን ጨምሮ ለተለያዩ አካላት ኮሚሽን እየተደረገ በርካታ ግጥሞችን የፃፈው ገጣሚው፤ በማንችስተርና ሌሎች ከተሞች ህንፃዎችና ጐዳናዎች ላይ ግጥሞቹ እንደ መፈክርና ማስታወቂያ የተፃፉለት ገጣሚ ነው፡፡

ግጥሞቹ ተወዳጅ ከመሆናቸው የተነሳ መፅሃፍቱ በደንብ መሸጣቸውን የሚናገረው ለምን ሲሳይ፤ የግጥም አልበሙ በሚሊዮን ቅጂዎች እንደተቸበቸቡለት ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ገጣሚው ሦስት የመድረክ ቲያትሮችንም ፅፏል - Chaos By Design (1994) Storm (2003) እና something Dark (2006) የሚሏቸውን፡፡

በእንግሊዝ ላንክሻየር ግዛት የተወለደው ለምን፤ ከእናትና አባቱ ጋር ለማደግ አልታደለም፡፡ እ.ኤ.አ በ1967 ወደ እንግሊዝ የመጡት እናቱ፤ በገጠማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ በሰሜን እንግሊዝ ነዋሪ ለነበሩ ነጭ አሳዳጊዎች “ለአጭር ጊዜ” በሚል በአደራ ለመስጠት መገደዳቸውን ያስታውሳል፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት ለቢቢሲ ስለልጅነቱ የተናገረው ለምን ሲሳይ፤ ከእናቱ ጋር የተገናኘው ከረዥም ዓመት በኋላ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ከሦስት ዓመት ፍለጋ በኋላ በ21 ዓመቴ ወላጅ እናቴን አገኘኋት ብሏል - ለምን፡፡ ከአሳዳጊዎቹ ጋር ለ11 ዓመት ከኖረ በኋላም ለልጆች አሳዳጊ ተቋም እንደተሰጠ ይናገራል፡፡ ለምን ሲሳይ ከነጭ አሳዳጊዎቹ ጋር ያሳለፈውን ጊዜ በበጐ አያስታውሰውም፡፡ “ምንም እንኳን ነጮች ቢሆኑም፣ ወላጅ አባትና እናቴ እንደሆኑ አምኜ ተቀብዬ ነበር” የሚለው ለምን፤ ዕድሜዬ 17 እስኪሆን ድረስ ከራሴ ሌላ ጥቁር አላውቅም ነበር ብሏል፡፡ የልጅነት ህይወቴን በሃሳብ ባቡር ወደ ኋላ ተንሻትቼ ሳስታውሰው፣ በማላውቀው የባዕድ ከባቢ እንዳደግሁ ይሰማኛል ይላል፡፡ ታዋቂው የእንግሊዝ ገጣሚ የ46 ዓመቱ ለምን ተስፋዬ፤ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎት ስለ ህይወቱና ስለ ሙያው ንግግር ካደረገ በኋላ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

====================

የግጥም አልበሙ በሚሊዮን ቅጂዎች ተቸብችበውለታል

ለለንደን ኦሎምፒክ በፃፈው ግጥም አሸናፊ ሆኗል

ግጥሞቹ በእንግሊዝ ከተሞች ህንፃዎች ላይ ተሰቅለዋል …

====================

እስቲ ወላጅ እናትህን ስትፈልግ ስለነበረበት ወቅት ንገረኝ … በምንድነው ስታፈላልግ የነበርከው?

እናቴን መፈለግ የጀመርኩት በደብዳቤ መነሻነት ነው፡፡ ደብዳቤው ስለ እናቴ ብዙ መረጃ ነበረው፡፡ በማሳደጊያ ድርጅቱ የማህበራዊ ሠራተኛ ባለሙያ የተፃፈ ነበር፡፡ እናም 18 ዓመት ሲሞላኝ ከማሳደጊያው ወጥቼ እናቴን መፈለግ ጀመርኩ፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ 21 ዓመት ሲሞላኝ አገኘሁአት፡፡ አባቴን ለመፈለግ 18 ዓመት ፈጅቶብኛል፡፡ በእርግጥ በሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ እያለሁም እናቴን ሳፈላልግ ነበር፡፡ ያኔ እሷ ጋምቢያ ነበረች፤ አሁን ኒውዮርክ ናት፡፡

አሁን ትገናኛላችሁ?

ምናልባት በዓመት አንዴ፡፡ በማሳደጊያው እያለሁ ምንም ቤተሰብ አልነበረኝም፡፡ አሁን እህቴ አለች፡፡ በመላው ዓለም ዘመዶች አሉኝ፡፡

ሚስት ለማግባት፣ የራስህን ቤተሰብ ለመመስረትስ?

ቤተሰቤን እስካገኝ ቤተሰብ አልመሰርትም ብዬ ነበር፡፡ አሁን ግን …

ሰባት የግጥም መፃሕፍት አሳትመሃል፡፡ ተቀባይነታቸው እንዴት ነው … በሽያጭስ?

ብዙ ሺህ ቅጂ መፃሕፍት ሸጫለሁ፡፡ ከሙዚቃ ጋር የተቀናበሩ የግጥም አልበሞች ግን በጣም ብዙ ነው የሸጥኩት … በሚሊዮን ቅጂዎች! በመድረክም ግጥሞቼ ለብዙ ሚሊዮን ሰዎች ደርሰዋል፡፡

ስለ ግጥሞችህ ንገረኝ፡፡ በቀዳሚነት የምትጠቅሰው መድበል ወይም ግጥም ይኖራል?

አንደኛ ምርጫዬ “ሁዌን ዘ ሞርኒንግ ብሬክስ ኢን ዘ ኢሊቬተር” ነው፡፡ እንግዲህ በአርታኢነት የሰራሁበትን “ዘ ፋይር ፒፕል” መድበል ጨምሮ ሰባት መፃህፍት ናቸው፡፡ ሌሎቹ “ሊስነር” “ሂድን ጄምስ”፣ “ዘ ፋየር ፒፕል”፣ “ሬብል ዊዝ አውት አፕሎዝ” እና “ቴንደር ፊንገርስ ኢን ኤ ክሌንችድ ፊስት” … በሚሉ ርዕሶች ይታወቃሉ፡፡

ሁሉም በእንግሊዝኛ ናቸው፡፡ በአማርኛ የመተርጐም ወይም የማስተርጐም ሃሳብ አለህ?

መሆን የሚችል ነው፣ ማን ያውቃል፡፡ እስካሁን ግን አላቀድኩም፡፡ ለወደፊት ምን አልባት፤ ኢንሽ አላህ፡፡ ከየመፅሐፉ ምርጥ ግጥሞችን ሰብስቤ በአንድ መፅሐፍ ወደ አማርኛ ሊተረጐሙ ይችላሉ፡፡ እኔ በበኩሌ በጣም ትንሽ አማርኛ ነው የምችለው፡፡

የግጥም አጀማመርህ ምን ይመስላል? ተፅዕኖ አሳድሮብኛል የምትለው ገጣሚ አለ?

እኔ እንጃ፡፡ ገጣሚ መሆኔን ከመናገሬ በፊት የተሰጠኝ ስጦታ ነው፡፡

ሕፃናት ማሳደጊያ ከመግባትህ በፊት ያሳደጉህ ወላጆች አሁንም አሉ?

አሳዳጊ አባቴ ሞቷል፡፡ እናቴ አለች፡፡ ልጠይቃቸው ብፈልግም ብዙ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ቢቢሲ በ1995 እ.ኤ.አ ስለ እኔ በሰራው ዶክመንታሪ ፊልም ላይ ተናግሬአለሁ፡፡ እነሱ ወደ ልጆች ማሳደጊያ ተቋም ሲያስገቡኝ እጃቸውን ታጥበዋል፡፡

አባትህ ፓይለት ነበሩ፡፡ ሕይወታቸው ያለፈውም በአውሮፕላን አደጋ ነው፡፡ አውሮፕላኑ የተከሰከሰበትን ሥፍራ አይተህ እንደመጣህ ሰምቻለሁ፡፡

ትክክል ነው፡፡ ሰሜን ተራሮች አካባቢ ሄጄ አደጋው የደረሰበትን ስፍራ አይቼአለሁ፡፡  አንዳንድ ፍንጮችም አግኝቼ ተመልሻለሁ፡፡ ምንም ስብርባሪ ግን ይዤ አልተመለስኩም፡፡ ስብርባሪዎቹን በቤተመዘክር ለማሰባሰብ ሃሳብ መኖሩ ግን ጥሩ ነው፡፡

ለለንደኑ የ2012 ኦሎምፒክ ግጥም መፃፍህን ሰምቻለሁ፡

ከስድስት ገጣሚያን የመጀመርያው እኔ ነኝ፡፡ ለለንደን ኦሎምፒክ 2012 ያዘጋጀሁት የግጥም ሥራዬ በከተማዋ ትልቅ ግንብ ላይ ተፅፎ ይነበባል፡፡ ግጥሙን የፃፍኩት ጥናት አድርጌ ነው፡፡ በምስራቅ ለንደን የሚገኝ የክብሪት ፋብሪካ አለ፤ እሱን ከጐበኘሁ በኋላ ነው…

ግንኙነት አለው? ከኦሎምፒክ ጋር …

ኦሎምፒክ በጥንታዊት ግሪክ ሲጀመር ግጥም ያካትት ነበር፡፡ በለንደን ኦሎምፒክም ያንን ስሜት ለመፍጠር ታስቦ ነው፡፡ በኦሎምፒክ ችቦ ይቀጣጠላል፡፡ ለዚህ ነው ክብሪት ፋብሪካውን የጎበኘሁት፤ ለግጥሙ ግብአት ለማድረግ፡፡ የክብሪት ፋብሪካ ሠራተኛ ሴቶች ታሪክ የእንግሊዝ ሠራተኞች ትግል አካል ነበር፡፡ አመፅ መጫር፣ ክብሪት መጫር … እንደዚያ የመሳሰሉ ሃሳቦችን ያጭራል፡፡ በዚያ መልኩ ነው ግጥሙን የፃፍኩት፡፡

ለለንደን ኦሎምፒክ ላዘጋጀኸው ግጥም ዳጐስ ያለ ክፍያ የተከፈለህ ይመስለኛል፡፡ ምን ያህል ተከፈለህ? ግጥምህን በኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ ታቀርበዋለህ? ወይስ …

ስለ ክፍያው መጠን እንኳ መናገር አያስፈልግም፡፡ ያው ተከፍሎኛል፡፡ በነገራችን ላይ መኖርያዬ ከኦሎምፒክ መንደር አምስት ደቂቃ ብቻ ነው የሚርቀው፡፡ ግጥሙን ማቅረብ አለማቅረቤን ግን አላውቅም፤ እስካሁን ጥሪ አልቀረበልኝም፡

ወደ ኢትዮጵያ የመጣህበት የተለየ ምክንያት አለህ? ስንተኛህ ነው ስትመጣ?

ሦስተኛዬ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1995 የቢቢሲ ዶክመንታሪ ሲሰራ መጥቼ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ ትንሽ ቆይቼ ለወንድሜ ሰርግ መጣሁ፡፡ ከዚያ ደግሞ ይሄው አሁን መጣሁ፡፡ ያሁኑ አመጣጤ በብሪቲሽ ካውንስል ግብዣ ነው፡፡ የእንግሊዛዊው ደራሲ ቻርለስ ዲከንስ ሁለት መቶኛ ዓመት ልደት ሲከበር እንግዳ ሆኜ ነው የመጣሁት፡፡

ህይወትህ በቻርለስ ዲከንስ “ግሬት ኤክስፔክቴሽን” ልቦለድ ውስጥ ካለው ዋና ገፀ - ባህርይ ጋር  ይመሳሰላል፤ የሚል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ አብራራልኝ …

ጥሩ፡፡ እንደውም የእኔ ህይወት ከገፀ - ባህርይው ይልቅ ከደራሲው ሕይወት ጋር በብዙ ነገር ይመሳሰላል፡፡ በምን ያህል መጠን የሚለውን ግን መመለስ አልችልም፡፡  ዲከንስ ወደ ማደጐ ቤት ሄዷል - እንደእኔ፡፡ ምንም ውጤታማ ቢሆን ሁሌም በልጅነቱ ያሳለፈውን ያስታውስ ነበር፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ሃሳባቸውንና ስሜታቸውን መናገር፣ መግለጽ የማይችሉ ሰዎችን በስራዎቹ ይገልፅ ነበር፡፡ እኔም ተመሳሳዩን እየሰራሁ እንደሆነ አስባለሁ፤ በግጥሞቼ፡፡

እስቲ ስለህፃናት ማሳደጊያ ንገረኝ?

ሕፃናት እንደ ምርት ናቸው፡፡ ሕፃናትን የሚንከባከቡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ገበሬዎች ማለት ናቸው፡፡ ለማሳደግ የሚሄዱት ሸማቾች ሲሆኑ መሬት ደግሞ እናታቸው ናት፡፡

ልጆቹ በሸማች እንደተወሰደ እህል ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች እዚህ መጥተው፣ ሕፃናቱን በጉዲፈቻ እንዲወስዱ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ እዚህ እንዲመጡ ያደረጋቸው የልጅ ፍላጐት ነው፡፡ በቬትናም፣ በሮማንያ … በሁሉም ሀገራት ያለ ነው፡፡ በጣም የሚከፋው በልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ የደረሰው አይነቱ ነው፡፡ ራሳቸውን የሚገድሉ፣ አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ይሄ ነው መጥፎው ነገር፡፡

ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባደረግኸው ንግግር፣ በተፈጥሮአችን ፈጣሪ (Creative) ነን፤ ግን ያንን እንዳንፈጥር እንማራለን ብለሃል፡፡ ምን ለማለት ነው?

ፈጠራ የማንነታችን ማዕከል ነው፡፡ እያደግን ስንሄድ የፈጠራ ብቃታችን እያነሰ ይሄዳል፡፡ ዶክተር ወይም የሕግ ባለሙያ በመሆን እና በፈጠራ መካከል መደጋገፍ እንጂ መቃረን መኖር የለበትም፤ ፈጠራ በጣም አስፈላጊያችን ነው፡፡ ሳይታወቀን እንኳ እንፈጥራለን፡፡ አለባበሳችንን፣ አባባላችንን፣ አሠራራችንን ተመልከት፡፡

ለሕፃናት መፃፍ አስቸጋሪ መሆኑንም የተናገርክ ይመስለኛል፡፡ “ግን ያረካል” ብለሃል… እንዴት?

ለሕፃናት መፃፍ በጣም ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በዓለማችን ትልልቆቹ ሃያስያን ሕፃናት ናቸው፡፡ ለምሳሌ የእኔ “ዘ ኤምፐረርስ ዋች ሜከር” ለሕፃናት የተፃፈ ነው፡፡

በመጨረሻ የምትለው ካለህ …

ልምዴን ለአንባቢዎቻችሁ በማጋራቴ ክብር ይሰማኛል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቴ በእውነቱ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

 

 

Read 2753 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:41

Latest from