Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 08:25

ለመሪዎችና ለዝነኞች ጌጣጌጦች በመስራት የተሳካላቸውአባትና ልጅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አቶ ግርማ ማናዬና ልጃቸው ያሬድ ግርማ በአሁኑ ወቅት ተክሉ ደስታ ወርቅ ቤት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አባት የ35 ዓመት፣ ልጅ ደግሞ የ13 ዓመት ልምድ አላቸው፡፡ በርካታ ጌጣጌጦችን ለታዋቂ ሰዎች፣ ለመንግሥት ባለስልጣናት፣  ለአገር መሪዎችና ለአትሌቶች ሠርተዋል፡፡ ሙያን ከቤተሰብ መውረስ ብቻ ስኬታማ አያደርግም፡፡ ለማንኛውም ሙያ ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ ያስፈልጋል፡፡ ተፈጥሯዊ ተሰጥኦን ከትምህርት ቤት በሚገኝ እውቀት ማዳበርም ይቻላል፡፡ አቶ ግርማ ማናዬና ልጃቸው ያሬድ፤ የጌጣጌጥ ስራን ትምህርት ቤት ገብተው አልተማሩም፡፡

ነገር ግን የተፈጥሮ ተሰጥኦዋቸውን በረጅም ጊዜ የስራ ልምድ አዳብረው የላቀ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡  አቶ ግርማ ማናዬ ከ45 ዓመት በፊት አርመኖች ጋ በመቀጠር ነበር የጌጣጌጥ ሥራ የጀመሩት፡፡ ታዋቂ ጌጣጌጥ ሰሪ ለመሆን ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ያኔ አሰሪያቸው የነበረው አርመናዊ ሙሴ ኤፍሬም፤ በፍጥነት ሙያውን መላመዳቸውን ያደንቅ ነበር፡፡ የደርግ አገዛዝ መምጣትን ተከትሎ በርካታ አርመናዊያን ጌጣጌጥ ሰሪዎች ከአገር ጠቅልለው ወጡ፡፡ አቶ ግርማ ከአርመኑ ባለሙያ የቀሰሙትን እውቀትና ልምድ ይዘው “ክብርዬ ደጀኔ ጌጣጌጥ ሰሪ ቤት” ተቀጠሩ፡፡ በወቅቱ በአገራችን በጌጣጌጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን ማግኘት አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን በሙያው ፈር ቀዳጅ ሊባሉ የሚችሉ ኢትዮጵያውያንም ክብርዬ ደጀኔ፣ አስፋው  ገብረህይወትና ተክሉ ደስታ ናቸው፡፡

 

አቶ ግርማ፤ በክብርዬ ደጀኔ ቤት ሲሰሩ በተለይ ለቤተመንግሥት በትዕዛዝ በርካታ ጌጣጌጥ ሠርተዋል፡፡ ያኔ ለጌጣጌጥ፤ ለስጦታና ለመዘነጫ የሚሆኑ ቁሶች ዋና መሥርያቸው ወርቅ ሲሆን በከበሩ ድንጋዮች ጌጦችን መስራት አይታወቅም ነበር፡፡ አቶ ግርማ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በወርቅ ጌጣጌጥ ሙያ መላ ቤተሰባቸውን በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከአርመኖች የቀሰሙትን ሙያ ይበልጥ ያዳበሩት ደግሞ ክብርዬ ደጀኔ ወርቅ ቤት እንደተቀጠሩ ሲሆን ጀርመን ሄደው ሙያውን ከተማሩ የቤተሰቡ ሁለት ወንድማማቾች ጋር በመስራታቸው ተጨማሪ ዕውቀት መቅሰማቸውን ያስታውሳሉ፡፡

አቶ ግርማ ከነበሩበት ለቀው “ተክሉ ደስታ ወርቅ ቤት” የተቀጠሩት ከ35 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ አዲሱ ቤት  መስራት ከጀመሩ በኋላ አንዳንድ ጊዜ ጌጦችን ቤት እየወሰዱ ይሰሩ ነበር፡፡ ያኔ ልጃቸው ያሬድ እቃ እያቀበለና እየተላላከ ከሙያው ጋር መተዋወቅ ጀመረ፡፡ 10ኛ ክፍል ሲደርስ አባቱ አንዳንድ ስራዎችን በትዕዛዝ ያሰሩት ጀመር፡፡ ያሬድ መጀመርያ የሰራው የሞአንበሳ አርማ ያለበት ቀለበት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ “የአባቴ ረዳት ሆኜ ቀላል ጌጦችን እየሠራሁ በመለማመድ እውቀቴን ማዳበር ቀጠልኩ፡፡ 12ኛ ክፍል ስጨርስ አባቴ ይሰራ በነበረበት ተክሉ ደስታ ወርቅ ቤት በሙከራ ጊዜ ተቀጠርኩ፡፡ አባቴ እንደ እሱው አንጥረኛ ለመሆን ያሳየሁትን ፍላጎት ተቃውሞኝ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ዛሬም ድረስ የምሰራውን ነገር ጥሩ ነው ብሎ አያውቅም፡፡ አያደንቀኝም፡፡ የተሻለ ለመስራት ሞክር የሚለኝ ግን የበለጠ እንድተጋ ፈልጐ እንደሆነ ይሰማኛል” ብሏል፡፡

ያሬድ የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ በቋሚነት ሲቀጠር፣ የመጀመርያ ስራዎቹ ሂልተን ሆቴል ለሰራተኞቹ ሊሸልም ያዘዛቸው ሜዳልያዎች ነበሩ፡፡

አቶ ግርማ፤ ክብርዬ ቤት ሲሰሩ ለንጉሡ ልጆች የተለያዩ ጌጦችን በመስራት ይታወቁ እንደነበር ልጃቸው ያስታውሳል፡፡ የፖስታ መቅደጃዎች፤ የሲጋራ ሣጥን፤ በወርቅ የተለበጠ ጋሻ፤ ከንፁህ ወርቅ የተሰሩ ቦርሳዎች ለንጉሳውያን ቤተሰቡ ሰርተዋል፡፡ ግርማዊነታቸው በውስጧ ምስጢራዊ ነገሮችን የምታስቀምጥ ቀለበት ነበረቻቸው፡፡ ያቺ ቀለበት ጣሊያን የተሰራች ስትሆን በነጭ ወርቅና አልማዝ የተንቆጠቆጠች ነበር፡፡ ቀለበቷ ግርማዊነታቸው ሲያረጁ ሰፋቻቸው፡፡ አቶ ግርማ ስፋቷን አጥብበው፤ የምስጢር መቆለፊያዋ ሳይበላሽ በልካቸው እንዲሰሩ ትዕዛዝ ደረሳቸው፡፡ በጥንቃቄ በመስራት ቀለበቷን አጠበቡላቸው፡፡ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሣቤት ለጉብኝት ኢትዮጵያ መጥተው በነበረበት ወቅትም በቀጫጭን የብር ገመዶች (ኤርባን) ለፍራፍሬ ማቅረቢያ የሚሆን  መጠኑ ከትሪ አነስ ያለ ሰሀን ሰርተዋል፡፡

አባትና ልጅ በተክሉ ደስታ ወርቅ ቤት ብዙ ደንበኞችን አፍርተዋል፡፡  ለኦፕራ ዊንፍሬይ የተበረከተውን ከብር የተሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ቁልፍ አባትና ልጅ ናቸው በጋራ የሠሩት፡፡ ቁልፉ 20 ሳ.ሜ ርዝመት ሲኖረው፣ 80 ግራም በሚመዝን ብር ተለብጦ የተሰራ ነው፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ሌሎች ባለስልጣናት ወደ ውጭ አገር ሲሄዱ ለሚጎበኟቸው አገር ሰዎች ለመታሰቢያ የሚሰጧቸውን ገፀ በረከቶችም ሰርተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትዕዛዞች ብዙውን ጊዜ የሚሰጣቸው ከጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ ወይም ከውጪ ጉዳይ ሚ/ር  ነው፡፡

ታዋቂ ሰዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ዝነኞች፣ ቱሪስቶች፣ ለስብሰባ የሚመጡ የአገር መሪዎች ሁሉ  ደንበኞቻቸው እንደሆኑ ያሬድ ይናገራል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የማላዊ ፕሬዝዳንት፤ ተክሉ ደስታ ወርቅ ቤት ተገኝተው ያሬድ ግርማ የሠራውን ጌጥ ገዝተዋል፡፡ አብረውትም የማስታወሻ ፎቶግራፍ ተነስተዋል፡፡ የላይቤርያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆን ሰርሌፍ፤ የሞአንበሳ አርማ ያለበት ቀለበት እንዲሠራላቸው አዝዘው ተሠርቶላቸዋል፡፡ የአሜሪካ ዝነኛ የሙዚቃ ባንድ አባላት እነ “ቻካ ዲሞስ ኤንድ ዘ ፕላየርስ” እና ድምፃዊው ሻጊ ከተክሉ ደስታ ወርቅ ቤት ልዩ ልዩ ጌጦችን ገዝተዋል፡፡ የቦብ ማርሌይ ሚስት ሪታ ማርሌይና ሎረን ሂል የገዙት ጉትቻና ፔንዳንት የአባትና ልጅ የሥራ ውጤት ነው፡፡ የቦብ ማርሌይ ልጆችና መላው ቤተሰብ ደግሞ የኃይለሥላሴ ፎቶ እና የሞአንበሳ አርማ ያለባቸውን በከፊል ከከበረ ድንጋይ፣ ወርቅና ብር የተሰሩ ጌጦችን ገዝተዋል፡፡ አንዳንዶቹ በአቶ ግርማ አብዛኛዎቹ ደግሞ በልጃቸው በያሬድ የተሠሩ ናቸው፡፡

ታዋቂ ሰዎች አሰርተው የወሰዷቸውን ጌጦች መዝግቦ ለታሪክ የማስቀመጥ አሰራር በአገራችን  የተለመደ አይደለም፡፡ ያሬድ ግን በግሉ ፎቶ በማንሳትና ከደንበኞቹ ጋር የማስታወሻ ፎቶግራፍ በመነሳት እንዲሁም ፊርማቸውን በወረቀት እያስፈረመ ለታሪክ እንዲቀመጥ ጥረት እያደረገ መሆኑን ይናገራል፡፡

ከሲድኒ ኦሎምፒክ መልስ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ያሰራው ልዩ ሜዳልያ፣ ያሬድ ከሰራቸው ትልልቅ ስራዎች ግንባር ቀደሞቹ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ በሜዳልያው ላይ የሲድኒ ኦሎምፒክ ሎጎ የተቀረፀበት ሲሆን “ሲድኒ 2000” የሚሉ ፊደሎችን ከጋዜጣ ላይ ቆርጦ በማውጣት ቀርፆ እንዳስገባበት ያሬድ ተናግሯል፡፡ ለአትሌቶቹ የተሰራው የወርቅ ሜዳልያ መጠን ባስመዘገቡት ደረጃ ልክ ሲሆን የወርቅ ሜዳልያ ላስመዘገቡ አትሌቶች እስከ 20 ግራም የሚመዝን ወርቅ ተሰጥቶ ነበር፡፡ የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ለወሰደው ገዛኸኝ አበራም፣ በግሉ አንዲት በውስጧ ትንንሽ ምስጢራዊ ነገሮች ማስቀመጥ የምትችል ቀለበት እንደሰራ ያሬድ ገልጿል፡፡

አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአባባ ተስፋዬ የሰጧቸውን፣ 20 ግራም ወርቅ የሆነውን ሜዳሊያም የሰራው ያሬድ ነው፡፡

ለፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስም የሰራው ሜዳልያ አለ፡፡ ሜዳልያው የወላይታ ካርታ ሆኖ መሃሉ ላይ የብሔሩ ባህላዊ ቤት እንዲሁም ጠርዙ በወርቅ በተጠለፈ የወላይታ የጥበብ ጥለት የተሰራ ሲሆን 100 ግራም ወርቅ እንደፈጀ  ይናገራል፡፡ ለሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲም ተመሳሳይ ሜዳልያ መሥራቱን ገልጿል፡፡

ያሬድ በከበሩ ድንጋዮች ጌጣጌጥ መስራት የጀመረው በአጋጣሚ ነበር - አባቱ ከስራ ቀርተው የወለቀች ነገር መልሶ በመግጠም፡፡ በከበሩ ድንጋዮች በቋሚነት መስራት ከጀመረ ከሦስት ዓመት በላይ እንደሆነው የሚገልፀው ያሬድ፤ ስራዎቹ አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭም ገበያ እያገኙ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ “ብዙውን ጊዜ የውጭ ምርቶች በብዙ መሳሪያዎች ይሰራሉ፡፡ ዋናው ግን ጭንቅላት ነው” የሚለው ያሬድ፤ መሳሪያዎች ስራን ቢያቀላጥፉም በእኛ አገር ሙሉ በሙሉ በእጅ የሚሰሩ ጌጦችን አደንቃለሁ ይላል፡፡ “ለፈጠራ ስራዬ የሚያነሳሳኝ ገንዘብ አይደለም፤ ደንበኞች ሲደሰቱ ማየት ትልቁ ክፍያዬ ነው” ሲልም ለሙያው ያለውን ፍቅር ገልጿል፡፡

“በጌጣጌጥ ስራ እንደ ባለሙያ ለመከበር የፈጠራ ችሎታ ሊኖርህ ይገባል፡፡ በትዕግስት፤ በጥንቃቄ ከከበረ ድንጋይ የሚገኘውን  ውበት የሚያጐላ ዲዛይን መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ እጅንና ጭንቅላትን በሚያስደንቅ ቅንብር መጠቀም ይኖርብሃል” ያለው ባለሙያው፤ ምንም ዓይነት ካታሎግ ሳይጠቀምና የሌላ ሰው ዲዛይን ሳይኮርጅ እንደሚሰራም ይናገራል፡፡ በተቀመጥኩበትና በምሄድበት ሁሉ ስለ ዲዛይን አስባለሁ፤ አንዴ የሆነ ሃረግ አይቼ ቅጠሎቹ ያምራሉ፤ ግንዱ ደግሞ ልዩ ነው፤ ዙርያውን ጉጦች አሉት፡፡ በዚያ ዲዛይን ከአልማዝ እና ከከበሩ ድንጋዮች ጌጥ ሠራሁ፡፡ ብዙውን ጊዜ ዲዛይን ከውስጤ ፈንቅሎ ይወጣል፡፡ አንዳንዴ እየሰራሁ በዚያው ቅፅበት ሌሎች የሰራኋቸውን ተመልክቼ አዲስ ሐሳብ አገኛለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እየሰራሁ መሃል ላይ ሐሳብ ይጠፋብኛል፡፡ የምሰራውን ትቼ ሌላ ስራ እቀጥላለሁ፡፡ ከጊዜ በኋላ ያንን ያለላቀ ስራ ሐሳብ ሳገኝ እጨርሳለሁ፡፡ የምሰራው ጌጥ እኔን ካስደሰተ ሌላም ሰው ይደሰትበታል ብዬ ነው የማስበው፡፡” በማለት ስለ ሥራው አብራርቷል፡፡ በሚሰራው ጌጥ ለማንኛውም ሰው ያለው አክብሮት እኩል እንደሆነ የሚናገረው ያሬድ፤ በዝና እና በእውቅና ለየት ያለ ስራ እንደማይሰራ ገልፆ፤ በትዕዛዝ የሚሰራቸውንም በጊዜ ገደብ ጨርሶ እንደሚያስረክብ አውስቷል፡፡ አንድን ስራ ረጅም ወይም አጭር ጊዜ እንዲወስድ የሚያደርገው የዲዛይኑ ውስብስብነት ወይም መቅለል እንደሆነ ሲያስረዳም፣ የጋብቻ ቀለበቶች በ30 ደቂቃ፣ እንደሜዳልያ ያሉ፣ በላያቸው ላይ ቅርፅ እና ፅሁፍ የሚሰፍርባቸው ደግሞ ከሳምንት በላይ ወይም ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ - ብሏል፡፡

ከምንም በላይ የሚያስደንቀውንም ሲናገር፤ ከከበሩ ድንጋዮች እጅግ ውድ ከሆነው ጥቁር አልማዝ  ጌጥ መስራቱ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ያሬድ፤ ነጩና ብርጭቆ በሚመስለው አልማዝ ብዙ ጌጦችን ሰርቷል፡፡ “አልማዝ የተለየ ባህርይው ጥንካሬው ነው፡፡ ብረት ማቅለጫ ውስጥ ብትጨምረው አልማዝ ተውቦ ይወጣል እንጂ በሙቀት ምንም ጉዳት አይደርስበትም፡፡ነገር ግን በቀለማት ህብሩ የሚታወቀው ኦፓል፣ እሳት ወይም ሙቀት አይወድም፤ በተለያዩ ቀለማት ሲያንፀባርቅ ደስ ይላል እንጂ ኦፓል ብዙ ጥንካሬ የለውም፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ስራዎች በኦፓል የሚሰሩ ናቸው፤ ምናልባት በአገር ውስጥ ኦፓል በብዛት ከመውጣቱ ጋር የተያያዘ ይሆናል፡፡

በአምበርና መኻሉ ላይ በከፊል የከበረ ማዕድን የሚሠራ ጌጥ አለ፡፡ ተፈጥሮአዊው አምበር እስከ 4 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ካለው ዛፍ እንደሙጫ የሚፈልቅ ነው፡፡ ፈረንጆች ይህ አምበር ከሚፈልቅበት ስፍራ ላይ ሸረሪት ወይም ጉንዳን ይለጥፉበትና ይሸፍኑታል፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ ሙጫው ደርቆ ሲጠጥር፣ ፖሊሽ ተደርጐ በጣም ልዩ የተፈጥሮ ድንጋይ ሆኖ በውስጡ የነፍሳት ምስል ያለው ይሆናል፡፡ ዋጋው ታዲያ አይቀመስም - በጣም ውድ ነው፡፡ በጥንቃቄ ሰርቼ ነው የማስረክበው፡፡ ጥንቃቄው ለከበሩ ድንጋዮች አቀማመጥ የምትሰጠው ትኩረት ላይ ነው፡፡ ሙቀት ወይንም አንዳንድ ኬሚካሎች የማይስማማቸው የከበሩ ድንጋዮች ስላሉ እንደየባህርያቸው በጥንቃቄ ታስቀምጣቸዋለህ፡፡ ከስንት ጊዜ አንዴ “በከፊል የከበረ” በሚባሉ ድንጋዮች ላይ ስትሰራ ወድቆ የመሰበር ወይም መሸረፍ ያጋጥማል፡፡ የተበላሸ የከበረ ድንጋይ ዋጋ አያወጣም፡፡ ከከበሩ ድንጋዮች መውደቅ የሌለበት በተለይ ኦፓል ነው፡፡ አፓል ብዙ ጊዜ  ለቀለበት አይመረጥም፤ ምክንያቱም  ተጋጭቶ ሊሰበር ስለሚችል ነው፡፡ ለአንገት ሃብልና ለጉትቻ ግን ጥሩ  ነው፡፡

ብዙ ሰዎች የከበሩ ድንጋዮች ልዩ ኃይልና ምስጢራዊ መልዕክቶች እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ከልደት ቀን ጋር ተያይዘው የተሰየሙ የከበሩ ድንጋዮች አሉ፡፡ ድንጋዮቹ የልደት ምልክት ሆነው ውክልና ይሰጣቸዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በዚህ ታሪክ መነሻነት በልደታቸው የከበረ ድንጋይ ቀለበት ያሰራሉ፡፡ የጣት ቀለበታቸው ሲሰራ የከበረ ድንጋዩ ቆዳቸውን እንዲነካ የሚያዙም አሉ፤ ኃይል ይሰጠናል ብለው ስለሚያስቡ፡፡ 12ቱን የዞዲያክ ወራቶች ስያሜ የሚወክሉ የከበሩ ድንጋዮች አሉ፡፡ ድንጋዮቹ የከበሩ ወይም በከፊል የከበሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለአንዳንዱ የእድሉ ድንጋይ አልማዝ ሊሆን ይችላል፤ ለሌላው ደግሞ ፐርል ይሆናል፡፡ እኔ አሁን ለምሳሌ ኮከቤ ካንሰር በመሆኑ የእድል ድንጋዬ ሩቢ ነው ያለው ያሬድ፤ አንተ ፒሰስ ስለሆንክ አኳዋማሪን የእድል ድንጋይህ ነው ብሎኛል፡፡ በልደት ድንጋይ የሚሰሩ ጌጦች ዋጋቸው እንደ አይነታቸው ይለያያል፡፡የሚረዳኝ ሰው ካገኘሁ በውጭ አገር ዘመናዊ የጌጣጌጥ ትምህርት ለመቅሰም ጥረት አደርጋለሁ የሚለው ያሬድ፤ ስለወደፊቱ ምን እንደሚያስብ ሲያብራራ፤ “በሙያዬ የምሰራቸው ነገሮች የራሳቸው የንግድ ምልክት እና የመታወቂያ ብራንድ እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ፡፡ መለያቸው ጥራታቸው እንዲሆን ሐሳብ አለኝ፡፡ በዓለም ታዋቂ መሆንም እቅዴ ነው፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት ሙያውን ያስተማርኳቸው ስዊድናውያን የሠራኋቸውን ጌጦች ተመልክተውና በቪሲዲ ቀርፀው ስዊድን ለሚገኘው የዓለም ባህል ማዕከል በማሳየት፣ ለአንድ ታላቅ ዓለም አቀፍ ትርዒት ተጋብዣለሁ፡፡ ወደፊት በእንደዚህ ዓይነት ዓለምአቀፍ አውደ ርዕይ ላይ ለመሳተፍ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ እኔ የምሰራቸው ስራዎች ከሚሸጡ በሞዴልነት ቢቀመጡ መርጣለሁ፡፡ ወደፊት የራሴ ፈጠራ ላለባቸው ጌጦች ካታሎግ ማዘጋጀት ይኖርብኛል ብዬ አስባለሁ፡፡” ብሏል፡፡

 

 

Read 7042 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:24