Wednesday, 04 April 2012 08:18

የበፀጋህ - ቆይታዬ

Written by  ሜሮን የወንደሰን
Rate this item
(5 votes)

በፀጋህ ሆስፒታል ነው፡፡ከኡራኤል ወደ አትላስ ሆቴል በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኝ፡፡

ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ውስጥ እንዲህ ያለ ሆስፒታል ስለመኖሩ ሰምቼ አላውቅም፡፡አንድ ቀን ፀጉሬን ለማሳመር በሄድኩበት የውበት ሣሎን፣ እናቷን ተከትላ የመጣች የተቃለች ሕጻን የቤቱ መነጋገሪያ ሆነች፡፡ሴቱ ሁሉ እሷን መነሻ አድርጎ የልጁን ገድል ይዘረዝር ገባ፡፡አንዷ የጨዋታውን መድረኩ ትቆጣጠርና “የእኔ ልጆች ምን አደረጉ መሰላችሁ….”፤ትተርካለች፡፡ አብዛኛው የልጆች ድርጊት ለሳቅ የሚጋብዝ በመሆኑ ጨዋታው ሁሉንም ሳቅ በሳቅ አድርጓቸዋል፡፡ሌላዋ ትቀጥላች፤ እሷ ያስገረማትን የሴት ልጇን ድርጊት ታነሳና የቤቱን ሰው በሙሉ ፈገግ ታሰኛለች፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ወሬው ከእኔ በስተቀር ፀጉር ቤቱ ውስጥ ላለው ሰው በሙሉ ተዳረሰ፡፡

በጨዋታው ተሳታፊ ከነበሩት ሴቶች አንዷ ከእኔ ጎን ተቀምጣለች፡፡ ፊቷን ወደ እኔ ስታዞር፣ የፈራሁት ወሬ እኔ ጋር እንደደረሰ ገባኝ፤ እና ሁሌም የተነሳውን አርእስት የማመልጥበትን ዘዴ ለመጠቀም ሞከርኩ፡፡ዘዴው በጣም የተራቀቀ እንዳይመስላችሁ፡፡ ቀድሞ መቆጣት እና ነገረኛ ሴት መምሰል ነው ወይም የጨዋታው ተሳታፊ ለሆኑት ሰዎች ያለኝን ንቀት በፊቴ ማሳየት፡፡ አልተሳካልኝም! ሴትየዋ ልብም ሳትለኝ በሳቅ ስትፈርስ፣ ዐይኗ ላይ የፈሰሰውን እንባ እየጠራረገች፤ “አይ የልጅ ነገር ልጆች እኮ በጣም ነው የሚያስቁት” አለችኝ፤ እንዳልሰማ ሆኜ ዝም አልኳት፡፡ “መቼስ የልጅ ነገር… የማያስቃት ባትወልድ ነው” ብላ መልሱን ለእራሷ ሰጠችው መሰለኝ፣ ፊቴ ላይ የሚነበበውን የቁጣ ስሜት ልብ ሳትል፤ “አልወለድሽም?” ጠየቀችኝ፤ የለመድኩት ጥያቄ ነው ‹‹አልወለድኩም›› ብላት ቀጥላ የምትጠይቀኝ  “‹አላገባሽም?” ብላ እንደሆነ አውቀዋለሁ፤ ለዚህ ጥያቄዋም “አላገባሁም” ብዬ ብመልስላት “ቶሎ አግቢ እንጂ” ትለኝ እና ጋብቻ ያለውን ጥቅም ትዘረዝርልኛለች፤ ከዚህ ሌላ ምን ትለኛለች፡፡ “‹አግብቻለሁ” ብላት ደግሞ ትቀጥላች፤ “ካገባሽ ስንት ጊዜ ሆነሽ? ፈልገሽ ነው፤ ኧረ ተይ ልጅ በልጅነት ነው…..››አቤት መቼስ ምክር አይከፈልበት፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥያቄ አስቤ አስቤ የደረስኩበት አጭር መልስ አለኝ ‹‹ልጅ እንቢ ብሎኝ አልወለድኩም›› ፍጥጥ ያለ - ከጎኔ ላለችው ፈጣጣ ሴት መለስኩላት፡፡ እሷ ግን  እንደከዚህ ቀደሞቹ ጠያቂዎቼ የምትገባበት አልጠፋትም፤ ጭራሽ ወደ እኔ ተስተካክላ ተቀመጠች፡፡

‹‹ምን ምን ሞከርሽ?›› ተበሳጨሁ ‹‹የዛሬዋ ደግሞ የሕይወት ታሪኬንም ጭምር እንድተርክላት ትፈልጋለች እንዴ?›› ተገረምኩ፤ ግርምቴንም በዝምታ መለስኩላት፡፡ እሷ መች ተበገረች!  የእሷን፣ የጓደኛዋን፣ የምታውቃቸውን ሰዎች ተሞክሮ ሁሉ ትዘረዝር ገባች፡፡ ይህንንም ለምጄዋለሁ፡፡የሆስፒታል፣የሐበሻ መድኃኒት፣ የጠንቋይ ኧረ የስንቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተሞክሮ አይደል ስሰማ የኖርኩት! ብቻ የዚችኛዋን የሚለየው፣ እሷ የምትለው ዶክተር 85 በመቶ የተሳካለት ነው፡፡ የሆስፒታሉን ስም ሰምቼው ስለማላውቅ፣በሆዴም ‹‹ለየት ያለ ጥቆማ ለያሰ ፊት ይሰጠዋል››ስል ለዚችኛዋ ተናጋሪ ፊት ተለሳለስኩላት፡፡አወራኋት አድራሻውንም ወሰድኩ፡፡ ቀናት ሳላባክን በሆስፒታሉ ተገኘሁ፡፡

ስለ ሆስፒታሉ መግቢያዬ ላይ ነበር አይደል ማውራት የጀመርኩት … እናላችሁ በዚህ መንገድ ተመርቼ ነበር በበፀጋህ ሆስፒታል የተገኘሁት፡፡ ስገባ ግን ጭራሽ ያላሰብኩት ነገር ገጠመኝ፡፡ እኔ በዚህ ሆስፒታል የጠበኩት፣ የእኔ ቢጤ የልጅ ችግርተኞችን ነበር፡፡ ሆስፒታሉ ግን አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ እርጉዞች ስብሰባ የተጠሩበት ይመስላል፡፡ ጊቢው እና የኮሪደሩ መተላለፊያዎች በነፍሰጡሮች ተሞልቷል፡፡ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡ ሌላ የማልፈልገው ትእይንት ከፊቴ ድቅን አለ፡፡ በአባቶቻቸው ክንድ የታቀፉ፣ በማዘያ የታዘሉ እና በዘንቢል የተንጠለጠሉ ሕፃናት ልጆቻቸውንም የሚያጠቡ አይቻለሁ መሰለኝ፡፡ እኔ እንኳን እንዲህ አንድ ላይ ተሰባስበው ለማየት ይቅር እና ተነጣጥለው የሚተኙትን ማየት አልወድም፡፡ማንም ቢሆን አራስ መጠየቅ እና ልደት ቤት መሄድ አያስደስተኝም፡፡ በፊት በፊት ያልጠየኳቸው ወዳጆቼ ያቄሙብኛል እያልኩ እየደበረኝም ቢሆን እሄድ ነበር፤ አሁን ግን ‹‹ለምን የፈለጉትን አይሉኝም›› ብዬ ወላድ ለመጠየቅ በር አላንኳኳም፡፡ ለምን ይደብረኝ? የምኖረው ለራሴ አይደል!

ይኸውላችሁ አሁንም የጀመርኩትን ረሳሁት እናም ይህን ሁሉ አልፌ እንግዳ ተቀባዮቹ ጋር ደረስኩ፡፡እንግዳ መቀበያውም ተጨናንቋል፡፡ እንደምንም አንድም እርጉዝ ላለመግፋት ተጠንቅቄ፣ የዶክተሩን ስም ጠቅሼ እገባ ዘንድ ጠየኩ፡፡ እንግዳ የምትቀበለውም ሴት እርጉዝ ነች፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ ፍላጎቴ ይበልጥ ጨመረ፤85 በመቶ ተሳክቶለታል የተባለው እውነት ሳይሆን አይቀርም አልኩ፡፡ብቻ ሴትየዋ ትልቅ መዝገብ አውጥታ ገለጠች፡፡ መግባት የሚቻለው በቀጠሮ መሆኑን ነግራኝ፣ ቀጠሮ ለመመዝገብ ብዕሯን አሾለች፤ ቦታ ያለው መቼ እንደሆነም ነገረችኝ፡፡ ቦታ ያለው ለመቼ መሰላችሁ? ከአንድ ዓመት በኋላ! ካላመናችሁኝ ሄዳችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፡፡እኔ ይህን የተባልኩት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር፡፡ አሁን ምናልባት ቀጠሮው ከሁለት ዓመት በኋላ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ወሬ አላርዝምባችሁ፤ አማራጭ እንደሌለኝ ሳውቅ ቀጠሮ ያዝኩ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላም ተራ ደርሶኝ፣ ባለፈው ሳምንት ሄድኩ፡፡

የመጨረሻዋ መጨረሻ

የአንድ ዓመት ቀጠሮ አስታውሶ መሄድ ከባድ ሊመስል ይችላል፡፡ ለእኔ ግን አልከበደኝም፤ አንድ ሳላዛንፍ በቀኔ ደረስኩ፡፡ ምን ያደርጋል? ሰዓት ግን አሳልፌ ነበር፤ በቀጠሮው መሠረት ዶክተሩ ጋር ለመግባት፣ ለካ የዕለቱ ባለ ቀጠሮዎች እንደገና ሌላ ተራ መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መች አውቄ! የመጨረሻዋ ባለተራ ሆኜ ተመዘገብኩ፡፡ ተራዬን ጥበቃም በአንዱ አግዳሚ ላይ  ቁጭ አልኩ፡፡ ቀስ እያለ ቦታው በእኔ ቢጤዎቹ ተያዘ፡፡ የእኔ ቢጤዎቹ ማለቴ መቼስ ገብቷችኋል! ቅርጻቸውን የሚጠብቁ ሸንቃጦቹ ማለቴ ነው፡፡

ቀስ እያለ ወሬው ደራ፡፡ አንዳንዱ ሁለት ወልዶ ሦስተኛ ፍለጋ የመጣ ነው፡፡ሁለተኛ እና አራተኛ ፍለጋ የመጣ አለ፡፡እንደኔ አንድ የሌላቸው ጥቂቶች ናቸው፡፡ የሚገርመው አንድ የሌላቸውን ወዲያው ለየኋቸው፡፡ ምክንያቱም የጨዋታው ተሳታፊዎች አልነበሩም፡፡ ጨዋታው ሌላ ቦታ ያሰለቸኝ ‹‹የእኔ ልጆች እንዲህ አድርገው፣እንዲህ ብለው›› ዓይነት ነው፡፡እነሱ ምን ቸገራቸው!አንድ አላጡ….. ጭማሪ ፈለጉ እንጂ፡፡

ቀስ እያልኩ እኔም ከቢጤዎቼ ጋር ጨዋታዬን ጀመርኩ፡፡ ከአንዷ ጋር የጀመርኩትን ሳልጨርስ ተጠርታ ስትሄድ፤ ከሌላዋ ጋር እቀጥላለሁ፡፡ እሷም ትጠራ እና ትገባለች፡፡ ምን እንደተባሉ እንኳን ሳይነግሩኝ በዛው ሲሄዱ እኔ ከሌላኛዋ  ጋር እቀጥላለሁ፣አንዷ አንጀት የሚያርስ የደህና ሁኚ ሰላምታ ሰጥታኝ ስትሄድ፤ ደሞ ከቀረችው ጋር ስጫወት እሷም ጥላኝ ስትሄድ፣ በመጨረሻ የመጨረሻዋ መጨረሻ ሆንኩና ብቻዬን ቁጭ ብዬ ተራዬን እጠብቅ ጀመር፡፡ እግረመንገዴንም ከእኔ ቢጤዎቹ ጋር የተጨዋወትኩትን አሰላስል ገባሁ፡፡

አንዷ የባሏ ቤተሰቦች ውትወታ ሰላም አሳጥቷታል፡፡ሌላዋን ደግሞ የሰፈሯ ሰዎች መጠቋቆሚያ አድርገዋታል፡፡ የቀይዳማ ቢጤዋን ጎንደር ያሉ ጎረቤቶቿ ጥያቄ አላስቀምጥ ሲላት፣መፍትሄ ብላ አዲስ አበባ ብትገባም አልቀረላትም፡፡እንደውም የባሰ ሆነባት፡፡ አዲስ የተዋወቃት ሁሉ ይጠይቃታል፡፡ “ጠይሟ ናት መሰለኝ፤ አዎ ጠይሟ፤ የእሷ ደግሞ ያለእርሷ አንድ የሌላቸው እናቷ በወቅቱ ባለመውለዳቸው የፈጠረባቸውን ቁጭት በእሷ ለመወጣት ጠዋት ማታ ይነዘንዟታል፡፡ የመሥሪያ ቤቷ ሴቶች በወሊድ ስም ዕረፍታቸውን ሲጠቀሙ፣ እሷ ግን ከዓመት ዓመት ያለ ዕረፍት መሥራቷ እንደሚያንገበግባት ያጫዋተችኝም ነበረች፡፡የአንዷ ጨዋታ አንጀቴን በላኝ አንድ መሥሪያ ቤት ጉዳይ ለመፈጸም ስትሄድ ኃላፊው ‹‹አግብተሻል?››ሲል ይጠይቃታል እንዳገባች ትነግረዋለች፤ይቀጥልና ‹‹ወልደሻል?›› እንዳልወለደች ትነግረዋለች ትዳሯን በከፍተኛ ስሜት አናንንቆ ‹‹ታዲያ ምን አግብቻለሁ ትያለሽ››ሲላት ልትፈጽመው የሄደችውን ጉዳይ ትታ በእንባ መሥሪያ ቤቱን እንደለቀቀች አጫወተችኝ፡፡ደግሜ ደጋግሜ ጨዋታውን አሰብኩት፡፡ የሴቶቹ ጭንቀት ግን የእራሳቸው አይደለም፡፡ አንዳቸውም፤ ‹‹ልጅ ወልጄ ልጄ ቤቱን ሲቦርቅበት ማየት ናፈቀኝ›› ወይም ደግሞ ‹‹ልጅ ወልጄ አስተምሬ ለቁምነገር ማብቃት ናፈቀኝ›› ሲሉ አልተሰሙም፡፡ እንዲህ ያለ ፍላጎት ሳይኖራቸው ቀርቶ ግን አልመሰለኝም ይህን ያላነሱት፡፡ ከራሳቸው በላይ የጠያቂው ጭንቀት አስጨንቋቸዋል፡፡ የልጅ መውለድ ጉጉታቸውን ማሳካት የፈለጉት፣ ከግል ፍላጎታቸው በላይ በዙሪያቸው ሆኖ በጥያቄ ያሰለቻቸውን ማኅበረሰብ ለማስታገስ ነው፡፡ የእነሱን በዚህ ደመደምኩ፡፡እኔስ? ስል እራሴን ጠየኩ እናም አሰብኩበት፡፡ የእኔም ያው ነው፡፡ እንደማንኛውም ሰው ልጅ ለመውለድ እፈልጋለሁ፤ ግን ደግሞ አልጠፈጥፈው፡፡ ፈጣሪ ካልሰጠኝ ከየት አመጣዋለሁ? እንዲህ ብዬ እራሴን ማሳመን አያቅተኝም ነበር፤ግን በወጣሁ በገባሁ ቁጥር በጥያቄ ናላዬን የሚያዞሩኝን ምን ላድርጋቸው? እንዲህ እየተሟገትኩ የመጨረሻ መጨረሻ ሆንኩና ዶክተሩ ጋር ገባሁ፡፡

እኔ እና ዶ/ር መኮንን

ዶ/ር መኮንን ቅልል ያለ ሰው ነው፤ ሰላምታው እራሱ ደስ ይላል፡፡ ያን ሁሉ ሴት ሲያስገባ ሲያስወጣ ስለዋለ ተዳክሞ ይጠብቀኛል ብዬ ነበር፤ እሱ ግን ምንም የድካም መንፈስ ሳይነበብበት በፈገግታ ተቀበለኝ፡፡ ጥያቄዎቹ የለመድኳቸው ቢሆኑም ለእርሱ መመለስ ግን አላበሳጨኝም - ዶክተር ነዋ! ቢያንስ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል አገልግሎት ይለግሰኛል፡፡  እነዛኞቹ እኮ ከንፈር ከመምጠጥ የዘለለ ምንም ላይፈይዱልኝ…. ሐሳቤን ሰብስቤ ለዶክተሩ ጥያቄ ተገቢውንና ትክክለኛ ምላሽ ሰጠሁት፡፡ ዶክተሩም በሚገባ ካዳመጠኝ በኋላ፣ በተራው በሚገባ እና በማይሰለች ሁኔታ የሚከተለውን ትንታኔ ሰጠኝ፡፡

የዶ/ር መኮንን ትንታኔ

ስለ መካንነት ምክንያቶችና መፍትሔዎች ከመነጋገራችን በፊት እርግዝና እንዴት ይከሰታል የሚለውን ማወቅ እንደሚያስፈልገኝ ነገረኝ፡፡ ስዕል እያሳየም ይተነትንልኝ ገባ፡፡ ሐሳቤን ወደ እርሱ ሰብስቤ ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ እርግዝና እንዲከሠት የሚያደርጉት ቅድመ ሁኔታዎች ዘረዘረልኝ፡፡

እርግዝና እንዲከሰት በቂ እና ጤናማ የወንድ ዘር ሕዋስ (Sperm Cell) መፈጠርና ዝግጁ ሆነው መገኘት አለባቸው፣የግብረ ሥጋ ግንኙነት እነኚህን የዘር ሕዋሶች እሴቷ ብልት ውስጥ እንዲገቡ ይረዳል፡፡ የሴቷ ማኅፀን የወንዱን የዘር ሕዋስ በመቀበል፣ ከሴቷ የዘር ፍሬ ዕንቁላል ጋር እንዲገናኝ ይረዳል፡፡ ለዚህም የሴቷ ፍሬ ማኅፀን (Womb) እና ማስተላለፊያ ቱቦ (Fallopian Tube) ክፍት መሆን አለበት፡፡

የሴቷ የዕንቁላል ማመንጫ ከረጢት (Ovary) ዕንቁላል አዘጋጅቶ መፈልፈል ይገባዋል፡፡ የሴቷ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ (Fallopian Tube) ከዕንቁላል ማመንጫ (Ovary) የተዘጋጀውን ዕንቁላል ተቀብሎ፣ የወንድ ዘር እና ዕንቁላል ውሕደት (Fertilization) እንዲፈጽሙ ማመቻቸት አለበት፡፡

እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉ የወንድ ወይም የሴት ወይም የሁለቱንም መካንነት ሊያስከትል እንደሚችል አስረዳኝ፡፡ እኔም አምላኬን እማጸን ገባሁ፤ ለእራሴ ሳይሆን በጥያቄ አላስቀምጥ ላሉኝ ለእነዛ ሰዎች…..መቼም እነማን እንደሆኑ እራሳቸው ያውቁታል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ዶክተሩ ስለ አንድ የ37 ዓመት ሴት ታሪክ ነገረኝ፡፡ ሴቲቱ በትዳር ውስጥ ከባለቤትዋ ጋር  ለዓምስት ዓመታት ቆይታለች፡፡ አርግዛም ልጅ ወልዳ አታውቅም፡፡ ምንም ዓይነት የእርግዝና መከላከያ ወስዳም አታውቅም፡፡ የዕድሜዋም መጨመር ያሳስባታል፡፡ ወር አበባዋም በየወሩ መጠኑ እየጨመረ መሄዱ ስላሳሰባት እና ልጅ ባለማግኘቷ ወደ ሕክምና ቦታ ለመሄድ ትወስናለች፡፡ ሕክምናም ካደረገች በኋላ፣ ያላረገዘችበት ምክንያት በማኅፀኗ ላይ እጢ በመውጣቱ ነው፡፡ ይህም እጢ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦውን በመዝጋቱ እንደሆነ ይገለጽላታል፡፡ እንድታረግዝ፣ ልጅም እንዲኖራትና የወር አበባ መጠኑ መብዛት እንዲስተካከልላት፣ የግድ የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጎ እጢው መውጣት እንዳለበት ይነገራታል፡፡ እሷም ባለቤቷም ምክንያቱ በመታወቁ ይደሰታሉ፡፡ ለሕክምና ወጭም ይዘጋጃሉ፡፡ ቀዶ ሕክምናውም በተሳካ ሁኔታ ይከናወናል፡፡ ከሦስት ወር በኋላም በተደረገው ምርመራ፣ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦው ክፍት እንደሆነና ማርገዝ እንደምትችል ይነገራታል፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ጽንስ መያዝ ቻለች፡፡ ዶክተሩ የእኔን ሞራል ከፍ ለማድረግ እና ጉጉቴንም ለመጨመር ታሪኩን እንዳጫወተኝ ገባኝ፡፡ እኔም አዳምጬ ስጨርስ ‹‹ከሰው ወሬ ተገላገለች›› አልኩ - ግን በልቤ ነው፡፡ ዶክተሩ ቀጠለ፤ እኔም ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡

የሴት መካንነት ሊያመጡ የሚችሉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ሲል ጠየቀኝ፤ ቀደም ሲል የጎበኘኋቸው ዶክተሮች ብዙ ሰብከውኝ የነበረ ቢሆንም የእሱን ደግሞ ለመስማት ጆሮዬን ሰጠሁ፡፡

አንደኛ፡-የሴቷ የዕንቁላል ማመንጫ (Ovary)  እንቁላል ማመንጨት ሳይችል ሲቀር መካንነት ሊከሰት ይችላል፡፡ ለዚህም ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች

ከሰውነታችን ከተለያዩ ክፍሎች የሚለቀቁ ሆርሞኖች መዛባት

እንቁላል እንዳይፈለፈል የሚያደርጉ መድኃኒቶችን መውሰድ

በድንገት ክብደት መጨመር ወይም መቀነስ

ሰውነትን የሚጎዱ ከባድ የሜዲካል በሽታዎች

ሁለተኛ፡-የወንድ የዘር ሕዋስ የሚተላለፍበት የሴት ማኅጸን ክፍል የመደፈን ወይም የመዘጋት እክል ቢያጋጥመው፣ የወንድ የዘር ሕዋስ በማኅፀን አልፎ ከሄደ በኋላ፣ ዕንቁላሉን የሚያገኝበት ቦታ (Fallopian Tube) ላይደርስ ይችላል፡፡ ይህም እርግዝና እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡ የማስተላለፊያ ቱቦን ሊዘጉ የሚችሉ ነገሮች ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ተጠቅሰዋል፡፡

የተለያዩ የማኅጸን ኢንፌክሽኖች የሚፈጥሩት ጠባሳ የማኅፀኑን የውስጠኛውን ክፍል እና የዘር ማስተላለፊያ ቱቦውን ሊዘጉት ይችላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የወንድ የዘር ሕዋስ እና የሴት ዕንቁላል ሊገናኙ አይችሉም፡፡

ከማኅጸን ላይ የሚነሱ የተለያዩ እጢዎች የማኅፀኑን የውስጥ ክፍል እና የዘር ማስተላለፊያ ቱቦውን ሊዘጋ ስለሚችል የዘር ውሕደት እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እርግዝናም አይከሰትም፡፡

ሦስተኛ፡-የማኅፀን በር አፍ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለወንድ የዘር ሕዋስ (Sperm Cell) አደገኛ የሆኑ ወይም የማይመቹ ኬሚካሎች ወይም ንጥረ ነገር ሊያመነጭ ይችላል፡፡ ይህ ንጥረ ነገር የወንድ የዘር ሕዋስን ስለሚጎዳ፣ የዘር ሕዋሱ ወደ ማኅፀን ውስጠኛ ክፍል እና የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ዕንቁላል ወደ ሚገኝበት ቦታ ለመሄድ ያዳግተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም እርግዝና አይከሠትም አለኝ፡፡ ጉዳዩን በቀጥታ ከእኔ ጋር አገናኝቶ መፍትሔ እንዲሰጠኝ ብጓጓም ነገሮችን እንዲህ በዝርዝር በማወቄ እየተደሰትኩ ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡

ዶክተሩ፤ የሴት መካንነት ችግር መፍትሄ አለው ወይ? ሲል ጠየቀ እና ማብራሪያውንም በዛው ቀጠለበት፡፡መፍትሄዎቹም ልክ እንደ ችግሮቹ ዓይነት ይለያያል፡፡የዕንቁላል የመፍልፈሉ ችግር የተከሰተ ከሆነ፣ ዕንቁላል ያልተፈለፈለበትን ምክንያት ለማወቅ የተለያዩ ምርመራዎችን ማድረግ እና ዕንቁላል ያልተፈለፈለበትን ምክንያት አጣርቶ ማስቀመጡ ትክክለኛውንና ውጤታማ የሆነውን መፍትሄ ለማግኘት ይረዳል፡፡ ለምሳሌ የሆርሞን የመዛባት ችግር፣ በደም በሚደረግ ምርመራ ማወቅ የሚቻል ሲሆን መፍትሄውም የሆርሞኑን መዛባት ሊያስተካክሉ የሚችሉ መድኃኒቶችን፣ እንክብልም ሆኑ መርፌዎች መስጠት ይቻላል፡፡ ሌላው እንቁላል እንዲፈለፈል የሚያግዙ መድኃኒቶች ይሰጣሉ፡፡

የወንድ የዘር ፍሬ እንዳይተላለፍ የሚያደርጉ የማኅጸን ክፍሎች ችግሮች እንደ መንስኤዎቹ ዓይነት መፍትሄዎቹም ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ የማኅፀን በርን ወይም አፍን የሚዘጋ ዕጢ (Tumor) ዕጢውን በቀዶ ሕክምና ማስወገድ፣ ይህም የተዘጋውን ክፍል በመክፈት፣ ያለውን ችግር ማስወገድ ነው፡፡ የሴት የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ  (Fallopian Tube) የመዘጋት ችግር፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በቀዶ ሕክምና ማስተካከል ይቻላል፡፡ የዚህም ውጤታማነት ማለትም ተመልሶ የመከፈት ዕድልና የማርገዝ ዕድል አናሳ ነው፡፡ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ዕድገት! እንደዚህ ዐይነት ችግር ያጋጠማት ሴት፤ በ Invitro Fertilization - embryo transfer  ማርገዝና ልጅ ማግኘት ትችላለች፡፡

በመጨረሻም

ሕክምናውን ለመስጠት ችግሮቹ ምንድናቸው የሚለውን መለየት ስለሚያስፈልግ፣ ምርመራ እንዳደርግ ነግሮኝ በርካታ የምርመራ ማዘዣ ጻፈልኝ ፡፡‹‹አንድ እንጨት አይነድ›› በማለትም ሌላ የምርመራ ወረቀት ጨመረልኝ፡፡ ውጤቱን ይዤ እንድመጣም ነገረኝ ‹‹ከአንድ ዓመት በኋላ?›› ስል ጠየኩት፡፡

ረጅም ቀጠሮ የሚሰጡት ሕክምናውን በአግባቡ ለመስጠት በማሰብ፣ በአንድ ቀን የሚያክሙትን ሰው ቁጥር በመመጠናቸው መሆኑን ነግሮኝ፣ ውጤት ከያዝኩ ግን በዕለቱ ባለተራዎች ጣልቃ ገብቼ መስተናገድ እንደምችል ገልፆልኝ ሸኘኝ፡፡

እኔም የምርመራ ውጤቴን ይዤ ጉጉቴ ይበልጥ እየጨመረ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡ ማን ያውቃል አንድ ዓመት የጠበቅሁት ተራ በዓመቱ ፍሬ ይሰጠኝ ይሆናል፡፡

 

 

Read 6789 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 08:24