Monday, 27 March 2017 00:00

‹‹የህብረተሰቡን ጤና ለአደጋ የሚያጋልጡ ምርቶች እየቀረቡ ነው›› ዶ/ር መብራኸቱ መለሰ (የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ)

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

 • በምግብ ምርቶች ላይ ያሉትን ደረጃዎች አስገዳጅ ማድረጉ ትልቅ ጠቀሜታ አለው
                       • ገበያ ላይ ከሚቀርበው የጨው ምርት በአዮዲን የበለጸገው 26 በመቶው ብቻ ነው
                       •  ለቆዳ ማልፊያ የሚሰራው ጨው ሳይቀር ለምግብነት ለሽያጭ ይውላል

           የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉና በህገ ወጥ መንገድ የሚመረቱ ምርቶች ለገበያ እየቀረቡ መሆኑን የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራኸቱ መለሰ፤ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ
እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ህብረተሰቡ በስፋት በሚጠቀምባቸው እንደ ጨው፣ ዘይትና የስንዴ ዱቄት ያሉ ምርቶች
ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት ለምግብነት ከሚውለው
የጨው ምርት ውስጥ በአዮዲን የበለጸገው 26 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከዶ/ር መብራኸቱ መለሰ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡

       የምግብ ማበልፀግ ምክክር መድረኩ ዋነኛ ዓላማው ምንድነው? ምን አይነት ምግቦችን ለማበልፀግ ነው ዕቅድ የተያዘው?
የምክክር መድረኩ ዋነኛ ዓላማ፣ በአገራችን ከፍተኛ ችግር የሆነውን የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግር ለመከላከልና በአገር አቀፍ ደረጃ የሥነ-ምግብ ሥርዓት ለመዘርጋት ነው፡፡ በአእምሮና በአካል ያልበለፀገ ዜጋ በበሽታ በቀላሉ ይጠቃል፡፡ አምራች ዜጋ ሊሆን አይችልም፡፡ ችግሩ እስከ 55 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ እንደሚያደርስም በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ይህ ደግሞ በአጠቃላይ የአገሪቱ ልማት ላይ የሚያስከትለው ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ በዚህ የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም ተደራሽ የሚሆኑት አብዛኛው ህብረተሰብ በየዕለቱ የሚጠቀምባቸው የምግብ አይነቶች ናቸው፡፡ ሥራው የሚሰራው ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡ በተለይም ከግሉ ሴክተር ጋር፡፡ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነቱ የተሰጠው ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡
ሥራውን አሁን ለመጀመር የተፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?
የህብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ አንፃር እስከ አሁን እየተሰራ ያለውና የተገኘው ውጤት በቂ አይደለም፡፡ ጥራታቸውን ያልጠበቁና በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች ለምግብነት እንዲውሉ ገበያ ላይ በስፋት እየቀረቡ ነው፡፡ እነዚህን መቆጣጠርና ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የምግብ ምርቶችን ለህብረተሰቡ እንዲዳረስ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ጤንነቱ የተጠበቀ፣ ለህብረተሰቡ ጤና አስፈላጊ የሆኑ የምግብ አይነቶች እንዲመረቱና በምግብ ማበልፀግ ሂደት የተሟላ ሆነው እንዲቀርቡ ማድረጉ አስፈላጊ ነው፡፡
እርስዎ በምክክር መድረኩ፣በጨው ምርት ላይ የተደረጉ ጥናቶችን ጠቅሰው እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ ከሚውለው ጨው 26 በመቶው ብቻ ነው በአዮዲን የበለፀገው፡፡ ይሄ የሆነው ለምንድን ነው?
በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የተደረገውና በመንግስትም ተቀባይነት ያገኘው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት ለምግብነት እንዲውል ገበያ ላይ ከሚቀርበው የጨው ምርት የአዮዲን ማዕድንን በውስጡ የያዘው 26 በመቶው ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ችግሮች አሉ። አንደኛው ከጥሬ ዕቃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ሌላው ጨውን አዮዳይዝድ አድርጎ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም አልነበረም፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ቀደም ሲል አንድ የመንግስት የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተገንብቶ እየሰራ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አንድ የውጭ ባለሃብት ገብቶ ፋብሪካ አቋቁሟል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካዎቹ በተገቢ መጠን እየሰሩ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች አሉ። የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግሩ ዋነኛው ነው፡፡
በጨው አምራች ድርጅቶችና በፋብሪካው መካከል አለመግባባቶች እንዳሉ በስፋት ሲገለፅ ነበር፡፡ ያለመግባባቱ መንስኤ ምንድን ነው? ለጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት ነገሮችስ ምንድን ናቸው?
በጨው አምራች አካላትና በፋብሪካው መካከል አለመግባባቶች አሉ፡፡ ለዚህም እንደ መነሻ ምክንያት ሆኖ የተገለፀው ጨው አምራቾቹ ምርቱን ለፋብሪካው ከማቅረብ ይልቅ እንደ ቀድሞው በራሳቸው ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ይፈልጋሉ። ሥራውን ቀደም ሲል ጀምሮ ሲሰሩት እንደቆዩ በመግለፅ፣ ወደፊትም ፋብሪካ ገንብተው ተገቢው የአዮዲን ይዘት ያለውን ጨው ለህብረተሰቡ እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡ እነሱ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካ ሳይኖራቸው፣ ገና ፋብሪካ ገንብተው ወደ ሥራ እስከሚገቡ ድረስ ህብረተሰቡ ጥራቱን ያልጠበቀና ተገቢው የአዮዲን ይዘት የሌለው ጨው እንዲጠቀም ማድረጉ አግባብ አይደለም፡፡
አምራቾቹ ለፋብሪካው የጨው ምርት ባለማቅረባቸው የተነሳ ፋብሪካው ማምረት አልቻለም፡፡ በርካታ ኢንቨስትመንት ፈሶበት በውጪ ባለሃብቶች የተቋቋመው ይኼ ፋብሪካ በአግባቡና በሙሉ አቅሙ ለመሥራት እንዳይችል ሆኗል፡፡ ስለዚህም ሁለቱም ወገኖች ተስማምተው ወደ ሥራ መግባት አለባቸው፡፡ አምራች ድርጅቶቹም አቅማቸውን ማጎልበትና የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካውን ማቋቋም ይኖርባቸዋል። ፋብሪካው ደግሞ ጥሬ ዕቃ በበቂ መጠን አግኝቶ ወደ ሥራው መግባት ይኖርበታል፡፡ ኩባንያው ከአምራቾቹ ጋር ያለውን ልዩነት ፈትቶ በሙሉ አቅሙ መስራት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት የአፋር ክልል መንግስት ነው፡፡ ከዛ ባለፈ ደግሞ የፌደራል መንግስቱ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መ/ቤቶች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በሚፈለገው መጠን አዮዲን ያለው የጨው ምርት ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሱቆችና የገበያ ሥፍራዎች ለሽያጭ የሚቀርቡትና ህብረተሰቡ እየገዛ የሚጠቀምባቸውን የጨው ምርቶች በተመለከተ ቁጥጥር የሚያደርገው አካል ማነው?
ህገወጥ ነጋዴዎች አዮዲን የሌለበትንና ያልታጠበ ጨው በስፋት ገበያ ውስጥ ይዘው በመግባት ለህብረተሰቡ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ለቆዳ ፋብሪካዎች ለቆዳ ማልፊያ የሚሰራው ጨው ሳይቀር ለምግብነት ለሽያጭ ሲውል እየታየ ነው። የዚህ አይነቱ የጨው አይነት የአዮዲን አለመኖር ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ለጤና እጅግ አደገኛ የሆኑ ባእድ ነገሮችንም የያዘ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ለኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ኃላፊነት ተሰጥቶ፣ ጨው በቀጥታ ከአምራች ወደ ኢንዱስትሪዎች እንዲወስዱና እንዲያከፋፍሉ፤ ለቆዳ ማልፊያ የሚውለው ጨው ወደ ሌላ ቦታ እንዳይሄድ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡
በአገር ውስጥ የሚመረቱት ብቻ ሳይሆን ከውጪ የሚመጡትም ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መ/ቤቶች ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ መጣር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ በምግብ ምርቶች ላይ ያሉትን ደረጃዎች አስገዳጅ ማድረጉም ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ አስገዳጅ ደረጃው ሲወጣ መኖር ያለበትና የሌለበትን ለይቶ ስለሚያስቀምጥ ቋንቋው አንድ ይሆናል። አምራቹም ሻጩም ደረጃውን የማክበር ግዴታ ይጣልበታል ማለት ነው፡፡ ይህ እስኪሆን ግን ህብረተሰቡ ለምግብነት በሚያውላቸው ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል፡፡

Read 5776 times