Monday, 27 March 2017 00:00

የኦሮሚያ “የኢኮኖሚ አብዮት” እና ባለሃብቶችን ያሰጋው እርምጃ

Written by 
Rate this item
(21 votes)

  • በክልሉ የተጀመረው እንቅስቃሴ ባለሃብቶችን ዋስትና የሚያሳጣና ሥጋት ላይ የሚጥል ነው
                • ቢዝነስ ከኢንቨስተሮች እየቀሙ ለወጣቶች መሸለሙ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም
                • ከባለሀብቶች የማዕድን ማውጫዎችን መንጠቅ የኮሚኒስቶች አካሄድ ነው

        የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ይፋ ያደረገው “የኢኮኖሚ አብዮት” እያነጋገረ ሲሆን ሰሞኑን ኦዳ ትራንስፖርት
ኩባንያን ለመመሥረት በግማሽ ቀን በተካሄደ የአክሲዮን ሽያጭ 617 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖች መሸጣቸው ታውቋል፡፡ የኦዳ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር በሙሉ አቅሙ ሲመሰረት ከወጣቶች ጋር በጋራ የሚያስተዳድራቸው የነዳጅ ማደያዎችና የነዳጅ ዲፖዎች እንደሚኖሩትም ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት 1.2 ሚሊዮን ለሚደርሱ የኦሮሚያ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር በሚል በባለሃብቶች ይዞታ ሥር የነበሩ የማዕድን
ማውጫ ቦታዎችን እየነጠቀ ለተደራጁ ወጣቶች ማከፋፈል የጀመረ ሲሆን ባለሃብቶች በዚህ እርምጃ መከፋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከ15 ዓመት በላይ በክልሉ በጠጠር ማዕድን ማውጣት ስራ ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ እንደነበር የገለጹ አንድ ባለሀብት፤ “በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎችን አስወጥቶ ለኪሳራና ለውድቀት በመዳረግ ምንም ላልለፉ ወጣቶች ማከፋፈል በፍፁም ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የክልሉን መንግስት እርምጃ ተቃውመዋል፡፡ ሌሎች የማዕድን ማውጫ ቦታቸውን የተነጠቁ ባለሀብቶችም “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ሀብት የማፍራት መብት አለው” የሚለውን የህገ
መንግስቱን አንቀፅ 40 በመጥቀስ፣ህገ መንግስታዊ መብታቸው መጣሱን ጠቁመው አቤቱታቸውን ለመንግስት እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በጉዳዩ ዙሪያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን፣ምሁራንና ጋዜጠኞችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

                 “የሥራ ዕድል መፍጠር ያለበት መንግስት አይደለም”
                         ስዩም ተሾመ (ጦማሪና የዩኒቨርሲቲ መምህር

      ከባለሀብቶች የማዕድን ማውጫዎችን መንጠቅ የኮሚኒስቶች አካሄድ ነው፡፡ በስነ ምጣኔ አመክንዮ ስንመለከተው፤ መንግስት በተለያዩ ቢዝነሶች መግባቱም የሚደገፍ አይደለም፡፡ ከግለሰቦች የኢንቨስትመንት ቦታ መውረስም ሆነ መንግስት ነጋዴ መሆኑ በየትኛውም መንገድ አይደገፍም፡፡ ይሄ የኮሚኒስት ስርአት ባህሪ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ይሄን በማድረጉ ግለሰብ ባለሀብቶችን እየቀጣ ነው ማለት ነው፡፡
የስራ ዕድል መፍጠር ያለበት እኮ መንግስት አይደለም፡፡ የስራ ዕድል በገንዘብ አይገዛም። መፍጠር የሚችለው ማህበረሰቡ ራሱ ነው፡፡ መንግስት ኃላፊነቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ የፋይናንስ ስርአቱን፣ ቢሮክራሲውን ማስተካከል፣ የቢዝነስ ስልቶችን ማስተማር የመሳሰሉት ናቸው የመንግስት ኃላፊነቶች፡፡ ከባለሀብቶች ላይ ሀብት ቀምቶ ለስራ አጥ ወጣቶች ማከፋፈል ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ይሄ ማለት እናለማለን ያሉትን ኢንቨስተሮች እንደ መቅጣት ነው፡፡ እነዚህ ተነጥቆ የሚሰጣቸው ወጣቶችም ቢሆኑ በሙሉ ፍላጎታቸው ሳይሆን በመንግስት ግፊትና ድጎማ ወደ ስራው ስለሚገቡ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በግላቸው ተሯሩጠው አዲስ የስራ መስክ የፈጠሩትን ሰዎች እየቀጡ፣ የቢዝነስ ክህሎት ለሌላቸው ስራ አጦች መሸለም በየትኛውም አካሄድ አይደገፍም፡፡ ቢዝነስ ከግለሰቦች እየቀሙ ለስራ አጥ መሸለሙ ወጣቶችን ምርታማ አያደርግም። ምክንያቱም እነሱ ስለ ቢዝነሱ በቂ እውቀት አይኖራቸውም፡፡ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የሚቻለው በዚህ መርህና አካሄድ አይደለም፡፡ ተወዳዳሪና ብቁ የቢዝነስ ሰዎችንም በዚህ አካሄድ መፍጠር አይቻልም፡፡ የአለም ተሞክሮም ይሄን አያሳይም፡፡ ሰዎች በሚሰሩት ስራ በቂ እውቀት፣ ፍላጎትና ክህሎት ሲኖራቸው ነው ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት፡፡
በሌላ በኩል መንግስት ከባለሀብቱ ልጣመርና ቢዝነስ ላቋቁም የሚለውም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም ታይቶ ውጤት ያላመጣ አካሄድ ነው። በነዚህ አካሄዶች ቀደም ሲል ህዝቡ ሲጠይቃቸው ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡ ተወዳዳሪ የቢዝነስ ሰዎችን ለመፍጠር በመጀመሪያ የሚደራጁት ሰዎች ብቃትና ፍላጎት ወሳኝነት አለው፡፡ ዝም ብሎ አደራጅቶ ሀብት ውረሱ ማለት እንዴት ውጤት ያመጣል? እነዚህ ሰዎች በምንም መመዘኛ ተወዳዳሪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እየጨመረ ለሚሄደው የስራ ዕድል ፍላጎትም ተጨማሪ የስራ ዕድል አይፈጥርም፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ በነበረው ተቃውሞ ወደ አደባባይ የወጡት ወጣቶች ጥያቄ በእርግጥስ የስራ ማጣት ጥያቄ ብቻ ነው? የሚለውንም መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደ‘ኔ የነበረው ጥያቄ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ከአንዱ ነጥቆ ለሌላው በመስጠት ማስታገስ አይቻልም፡፡ በአመፁ ወቅት በዋናነት የተነሳው ጥያቄ፤ ከፊንፊኔ ዙሪያ የሚፈናቀሉ ሰዎች መብትና ጥቅማቸው አልተከበረላቸውም የሚል ነው፡፡ ይሄን ደግሞ በዚህ መንገድ ለመፍታት መንቀሳቀስ ከስነ ምጣኔ መርህ አንፃር አያስኬድም፡፡ የመብት ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ሁኔታ ይሄን ቁንፅል እርምጃ ለመውሰድ መሞከር ትክክል አይደለም፤ ውጤትም አያመጣም፡፡   

-------------------

                          “ባለሃብቶች የሚወረሱ ከሆነ ምን ዋስትና ይኖራቸዋል?”
                         አቶ ጥሩነህ ገሞታ (የኦፌኮ አመራር)

        የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ የሚደገፍ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ማንም አይቃወምም፡፡ ዋናው ሪፎርሙ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ይችላል ወይ የሚለው ነው፡፡ አሁንም አድሮ ቃሪያ አይነት ከሆነ ግን ምንም ውጤት ስለሌለው አይደገፍም። በኦሮሚያ ክልል በመንግስት በሚገለፀው ደረጃ የሪፎርም ስራ ሲሰራ አላየንም፡፡ የሚታይ ነገር ካለ ግን የምንቀበለው ይሆናል፡፡
ለወጣቶች በሚል ከባለሀብቶች የሚነጠቁ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ አንድ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ በ1967 ደርግ የገጠር መሬትና የከተማ ቤትና ቦታ እንዲሁም ፋብሪካዎችንና ኢንዱስትሪዎችን ወረስኩ ሲል የነበረውን ያስታውሳል፡፡ ደርግ በወቅቱ የግለሰቦችን ወፍጮ ቤቶች ሳይቀር ወርሷል፡፡ የተቧደኑ ግለሰቦች ማህበር በሚል እየተቋቋሙ ወፍጮ ቤትና የተለያዩ የሰው ንብረቶችን የወሰዱበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሄም አካሄድ ያንን የሚያስታውስ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ስርአቱ የግል ባለሃብቶች ኢንቨስት አድርገው ሀብት ማፍራት ይችላሉ የሚል ፖሊሲ በማስቀመጡ ነው ግለሰቦች ዋስትና አለን ብለው ተማምነው ኢንቨስት የሚያደርጉት፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በህግ አግባብ ግዴታቸውን እየተወጡ ያሉ ከሆነና ይህን ችላ ብሎ ልማታቸውን የሚነጥቅ ከሆነ የሚደገፍ አይደለም፡፡ ቀድሞውኑ በህገ ወጥ ሁኔታ የያዙት ከተወረሱ ግን እንደተወረሱ አይቆጠርም፡፡ ህጋዊዎች በዚህ መንገድ ዋስትና አጥተው የሚወረሱ ከሆነ ግን ለወደፊት ኢንቨስተሮች ምን ዋስትና ይኖራቸዋል? የሀገራችንን የሰው ኃይል ቀጥረው ሊያሰሩና ስራውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ኢንቨስተሮች ከየት ሊመጡ ይችላሉ? የሚል አስደንጋጭ ጥያቄም ያስነሳል፡፡ ስለዚህ ባለሀብቶች በዚህ መልኩ ሀብታቸውን እየተነጠቁ ከሆነ በግልም ሆነ በፓርቲያችን ደረጃ አንቀበለውም፡፡
ወጣቶችን ወደ ስራ ማስገባት ከተፈለገ‘ኮ ካፒታል መድቦ አዳዲስ የቢዝነስ እቅዶችን አውጥቶ ማሰማራት ይቻላል፡፡ ይሄ ከተደረገ ብቻ ነው የምንደግፈው፡፡ የሰው ሀብት ነጥቆ ለሌላ መስጠት ግን የማይደገፍ ነው፡፡ ወጣቶችን በፓርቲ ደረጃ ጠርንፎ ከመያዝ ወጣቱን ለቀቅ አድርጎ፣ በፈለገበት የስራ መስክ እንዲሰማራ ማድረግ ነው የሚያስፈልገው፡፡ የወጣቶችን አቅም አጎልብቶ ወደ ስራ እንዲገቡ ከማድረግ ይልቅ የሌሎችን ሀብት ወርሶ መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ አላስፈላጊ ከሆኑ በጀቶች እየቀነሱ የተለያዩ ዘርፎች ላይ ማሰማራት ይቻል ነበር፡፡ ይሄ የሚደረገው ለህዝባዊ እንቅስቃሴው ምላሽ ለመስጠት ከሆነ፣ ህዝቡ ያነሳው የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የመብት ጥያቄም ነው፡፡ በዚህ ብቻ ለማስተንፈስ ከተፈለገ ዘላቂ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡

----------------------

                       “ከአንዱ ነጥቆ ለአንዱ መስጠት አይበረታታም”
                          አቶ ቶሎሣ ተስፋዬ (የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር)

       እኛ በህዝቡ የሚሰሩትን የልማት ስራዎችና ህዝቡ የሚቀበላቸውን ነገሮች ሁሉ እንደግፋለን። ወጣቱ የስራ እድል ጥያቄ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ለዚህ የወጣቶች ጥያቄ እንደ ሀገርም እንደ ኦሮሚያ ክልልም እየተቀመጡ ያሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በበጎ እንቀበላቸዋለን፡፡ በተለይ የኦሮሚያ “የኢኮኖሚ አብዮት” ብዙ ወጣቶችን ያሳትፋል የሚል እምነት አለን፡፡ መንግስት ቆም ብሎ አስቧል፤ ችግሩን አይቷል፤ የህብረተሰቡን ክፍል በየደረጃው አወያይቷል፡፡ በዚህም ችግሩን ለይቶ አውቋል የሚል ግምት አለን፡፡ ችግሩን ለይቶ ካወቀ በኋላ እየወሰደ ያለው የመፍትሄ እርምጃ የሚበረታታ ነው፡፡ ህዝብም ድጋፍ እየቸረው ነው፡፡ ሰሞኑን በተደረገው የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ መገኘቱ፣ ህዝቡ ለዚህ ድጋፍ እንዳለው ያመላክታል፡፡
ከዚህ ቀደም እንደ ፓርቲ ስንለው የቆየነውን ነው አሁን መንግስት እየሰራ ያለው፡፡ በተደጋጋሚ ወጣቱ ስራ አጥ ሆኗል፤ ጥቂቶች ሀብት ያለአግባብ እያካበቱ ነው ስንል ነበር፡፡ በተለይ ከአመራሩ ጋር ቅርበት ያላቸው ጥቂት ሰዎች፣ በኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ ሀብት እያካበቱ የሀብት ክፍፍሉ ከፍተኛ ልዩነት እያሳየ ነው፡፡ አብዛኛው የሚበላው እያጣ ነው፡፡ በተለይ ወጣቱና የተማረው ክፍል ተረስቷል እያልን ስንጮህ ቆይተናል፡፡ ለዚህ ጩኸት ምላሽ እየተሰጠ ይመስላል፤ የተጀመረው ነገር ጥሩ ነው፣ ውጤት ያመጣል የሚል እምነትም አለን፡፡
ይህን ስንል ግን ከአንዱ ነጥቆ ለአንዱ መስጠትን አናበረታታም፡፡ መጀመሪያውኑ ከባለሀብቶች ጋር በኦሮሚያ ውስጥ ሲሰራ የቆየው ፍትሃዊነት የሌለው ነበር፡፡ አንድ ባለሀብት የህዝብ መሬት ይዞ አጥሮ፣ አስርና ከዚያ በላይ ዓመት ያለምንም ጥቅም ማቆየትና መሬቱን አትርፎ ለመሸጥ ገበያ የመጠባበቅ አዝማሚያ ነበር፡፡ በእነዚህ ዓይነቶቹ ላይ እርምጃ መወሰዱ የሚበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን በህጋዊ መንገድ ከሚሰራው ላይ የሚነጠቅ ከሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ ብዙ የተማሩና ልምዱ ያላቸው ወጣቶች አሉ፤ እነዚህ ወጣቶች መነሻ ካፒታል ማግኘታቸው ስራቸውን ውጤታማ ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡
በህጋዊ መንገድ እየሰራ፣ ሀገርን እየጠቀመ ያለን ኢንቨስተር መሬትና ሀብት እየነጠቁ ለወጣቱ እንሰጣለን የሚባለውን እኛ አንቀበለውም፡፡ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትና በቀጣይ ጥያቄ የማይነሳበት አሰራር ነው መፈጠር ያለበት። ባለሀብቶችን ከስራ ውጪ አድርጎ ለሌላ ወገን መስጠት በየትኛውም መመዘኛ የሚበረታታ አይደለም፡፡ ሁሉም ዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡

------------------

                          “የኢኮኖሚ አብዮት እንደቃሉ ቀላል አይሆንም”
                             በፍቃዱ ኃይሉ (ጦማሪና ጋዜጠኛ)

          ኢህአዴግ የሚከተለው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በየወቅቱ የሚቀያየር በመሆኑ በግልፅ አይገባኝም፡፡ በአሁን ወቅት በዓለም ላይ ያለውን ሰፊ ሁኔታ ስንመለከት፣ ወደ ነፃ ኢኮኖሚ ያዘመመ በመሆኑ፣ ይህን ብንከተል የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ባለሀብቶች በህጋዊ መንገድ ያገኙትን የኢንቨስትመንት እድል ለወጣቶች ስራ ፈጠራ በሚል መንጠቅ ወንጀልም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ኢንቨስተሮችን ዋስትና አሳጥቶ ኢንቨስት ከማድረግ እንዲቆጠቡ ያደርጋል። ይሄ አካሄድ ወጣቶች ኢንቨስትመንቶችን አቃጠሉ ከተባለውም የባሰ ነው፡፡ ኢንቨስተሮች ይሄንን እያዩ ከዚህ በኋላ እንዴት ኢንቨስት ሊያደርጉ ይችላሉ? ከዚህ አንፃር አካሄዱ ፈፅሞ ትክክል አይደለም፡፡ በጣም አስደንጋጭና አሳዛኝ ነው የሚሆነው፡፡
በእርግጥ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠር አለበት፤ ነገር ግን አዳዲስ እድል መፍጠር እንጂ የሌላውን መሻማት አግባብ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ የማዕድን ማውጫዎችን በተመለከተ ወጣቶቹ ከባለሀብቶቹ ጋር በሰንሰለታማ የንግድ ስርአት ተቀናጅተው እንዴት መስራት እንደሚችሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ እንጂ ንብረት እየነጠቁ መስጠት አያዋጣም፡፡ ነገ ከነገ ወዲያም ሌላ መዘዝ ይዞ ነው የሚመጣው፡፡
በተለይ ስለ ማክሮ ኢኮኖሚ ዘላቂነት ስናስብ፣በዚህ አካሄድ ኢንቨስተሮችን እያቀጨጩ እንዴት መጓዝ ይቻላል? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ያመጣው “የኢኮኖሚ አብዮት” ቃሉ በጣም ማራኪ ነው፡፡ የኢኮኖሚ አብዮት በእርግጥም ያስፈልገናል፡፡ ግን እንደ ቃሉ ቀላል አይሆንም፡፡ እርግጥ ነው ማህበረሰቡ ከአካባቢው ከሚገኘው ሀብት ተጠቃሚ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ኢንቨስተሮች በሚሰሩት ልማት ወጣቶች ተቀጥረው በመስራት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ጥቅሞች ለየአካባቢው ወጣቶች ማስጠበቅ ነው የሚሻለው፡፡  

Read 8871 times