Monday, 13 March 2017 00:00

ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ይንደረደራሉ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(41 votes)

  መቼም እንኳንስ ለእንደኛ አገሩ ህዝብ ቀርቶ በዕድገት ለገሰገሱትም ሆነ በሃብት ለመጠቁት የዓለማችን ህዝቦችም ቢሆን አንዳንድ የማይፈቱ ችግሮችና እንቆቅልሾች አንዳንዴ አይጠፉም።  የእኛን ትንሽ አሳሳቢ የሚያደርገው ኑሮአችን ሁሉ በችግሮችና በእንቆቅልሾች የተበተበ መሆኑ ነው - አንዳንዴ ሳይሆን ሁልጊዜ፡፡ እናም ሁሌም ጥያቄዎች አሉን - መልስ የሚሹ፡፡ ሁሌም ችግሮች እንደተጋረጡብን  ነው - መፍትሔ የሚፈልጉ። ሁሌም እንቆቅልሽ ምናውቅልሽ” እንደተባባልን ነው። በጥቅሉ ኢትዮጵያችን ---- የእንቆቅልሽ አገር ናት፡፡
እንቆቅልሹን የሚፈታልን ብቸኛው አካል ደግሞ የጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ይመስለናል፡፡ እናም ሁልጊዜ ችግሮች፣ ጥያቄዎች፣ እንቆቅልሾች ወዘተ ሲያጨናንቁን፣ አስበን መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ መሮጥ ይቀናናል። በአካል ባንችል እንኳን በሃሳባችን መባዘናችን አይቀርም፡፡ እኔን አብዝቶ የሚያስገርመኝ ደግሞ ምን መሰላችሁ? የእኛ ለትንሹም ለትልቁም ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ መንደርደር ብቻ አይደለም። የእሳቸው (የጠ/ሚኒስትሩ) አለመታከትም ጭምር ነው፡፡ እኔ እሳቸውን ብሆን ግን (መቼም የምሆን አይመስለኝም!) አንድ ጠንከር ያለች ህግ አወጣ ነበር (አፋኝ ህግ ግን አይደለም!) የሥራ ጫና የምትቀንስ ቀጠን ያለች መመሪያ ቢጤ ማለቴ ነው፡፡ ሆኖም ጠ/ሚኒስትሩን አይደለሁምና------ ከዚህ ሀሉ ጣጣ ፈንጣጣ ተገላግያለሁ፡፡
አንድ ነገር ግን እጠረጥራለሁ፡፡ ጠ/ሚኒስትራችን (የአሁኑም የቀድሞውም ማለቴ ነው!) የተለያዩ ችግሮችና እሮሮዎችን የመስማትና በተግባርም ባይሆን በአፋቸው ጊዜያዊ መፍትሄ (Pain killer በሉት) የማዘዝ ወይም የመጠቆም ፍላጎት ቢኖራቸውስ? (እንደ ሆቢ ማለቴ ነው!) የዚህ ክፋቱ ግን ምን መሰላችሁ? እሳቸው ለረባውም ላልረባውም ጥቃቅን ችግሮች መፍትሄ ሲያፈላልጉ ትላልቆቹ ይዘነጋሉ፡፡ እኔ የምለው ግን ጠ/ሚኒስትሩ የማይመለከታቸው ችግር ወይም እሮሮ የለም እንዴ? ቆይ ግን የሥራ ድርሻቸው ወይም ሃላፊነታቸው ምንድን ነው? (ናላቸው እንዳይዞር ፈርቼ እኮ ነው!)  ምን እንደናፈቀኝ ታውቃላችሁ? ጠ/ሚኒስትሩ የማይፈቱት ችግር!!
ጠ/ሚኒስትሩ የአገሪቱ ከፍተኛው መሪ ቢሆኑም የሥራ ክፍፍል ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያለዚያማ እነዚያን ሁሉ ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ኮሚሽነሮች---- ወዘተ መሾም ለምን አስፈለገ?  ትዝ ይላችኋል አይደል-----የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አርቲስቶችን ማወያየታቸው! ቆይ  ዓመታዊ የጥበብ ቀን እንዲታወጅ ለመጠየቅ ወይም ለማስፈቀድ ጠ/ሚኒስትሩ ያስፈልጉ ነበር? እውነት ለመናገር ----- አንድም ጠ/ሚኒስትሩ የማይመለከታቸው ጉዳይ እኮ የለም። የኮፒራይት ጉዳይ---- ለጠ/ ሚኒስትሩ፤ በሴቶች ላይ የሚደርስ የሃይል ጥቃት-----ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን የመኖርያ ቤትና የመኪና ጥያቄ---- ለጠ/ሚኒስትሩ (የትምህርት ጥራት እንኳን ቢሆን የአባት ነው!) የፊልም ኢንዱስትሪው የተጋረጡበት ፈተናዎች------ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የትዳር ፍቺ መጨመር ጉዳይ----- ለጠ/ሚኒስትሩ-፣ የሃይማኖት መሪዎች ውዝግብ ------- ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የትራንስፖርት ችግር (አሁንም) ------ ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የፎርጂድ መንጃ ፈቃድ ጉዳይ-------ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የመብራት መቋረጥና የውሃ መጥፋት--------ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የስልክ ኔትዎርክ መጨናነቅ-------ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የኢንተርኔት መንቀራፈፍ-------ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የአትሌቶች ድል ማጣት-------ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የንባብ ባህል አለመዳበር ችግር--------- ለጠ/ሚኒስትሩ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጥ ውዝግብ-------ለጠ/ሚኒስትሩ ወዘተ ... ወዘተ... ወዘተ... 
እኔ ጠ/ሚኒስትሩን ብሆን “ሥልጣን ይቅርብኝ” ብዬ አገር ጥዬ የምጠፋ ይመስለኛል - በምሬት፡፡ በነገራችን ላይ የጠ/ሚኒስትሩ ሹመኞች ይሉኝታ-ቢስ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ሥልጣንና ደሞዙን ብቻ የራሳቸው አድርገው  ሥራውንና ሃላፊነቱን ወደ እሳቸው መግፋት ምን ይባላል? (የመልካም አስተዳደር ችግር እኮ ነው!)
በእርግጥ ጠ/ሚኒስትሩም ለዚህ ችግር በከፊልም ቢሆን ተጠያቂ ይመስሉኛል፡፡ እንዴት ብትሉ... ሁሉን ነገር በየዋህነት መቀበላቸው እኮ ነው ለዚህ ሁሉ ዕዳ የዳረጋቸው፡፡ አንዳንዴ እንኳ “No! እያንዳንድሽ ሰርተሽ ብይ!” ማለት ነበረባቸው፡፡ (ሹመኞቻቸውን ማለቴ ነው!) ጠ/ሚኒስትሩ የዩኒቨርስቲ መምህራንን ባነጋገሩበት ወቅት ከቀረቡላቸው አያሌ ጥያቄዎች መካከል አንዱ፤ “እኛ እኮ የምንፈልገው መጠለያና አንዲት ባለ አራት ጐማ ቆርቆሮ ብቻ ነው፤ እነዚህን ካገኘን ተረጋግተን እናስተምራለን” የሚል ነበር። መልስ የማያጡት ጠ/ሚኒስትሩም እንዲህ ብለው መለሱ አሉ፤ “ባለ አራት ጐማ ባንችል እንኳን ባለ ሦስት ጐማ ቆርቆሮ እንፈልጋለን” ይህችን የሰማ ሁሉ ገና ትንሽ ችግር ሲገጥመው፣ በራሱ መንገድ መፍትሔ ከመሻት ወይም የሚመለከተውን  አካል ደጅ ከመጥናት ይልቅ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ መሮጥን ፋሽን አድርጎት ቁጭ አለ፡፡  
እስካሁን ጠ/ሚኒስትሩ ቅሬታ ባያሰሙም እንኳን ጉዳዩ በዚህ መቀጠል ያለበት ግን አይመስለኝም። ነገርዬው እንደ ምንም ወግና ሥርዓት መያዝ አለበት። እናም ለአገሩ እንደሚቆረቆር አንድ ዜጋ፣ አንዲት ቀጠን ያለች ፕሮፖዛል አርቅቄአለሁ። ለትንሹም ለትልቁም ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ መሮጥን  የሚያስቀረው አዲሱ ፕሮፖዛሌ፤ ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ሳይሆን ወደየሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ማምራት እንዳለባቸው ይጠቁማል፡፡ (ሹመኛም ሰርቶ ይብላ እንጂ!)
ችግሮችና እሮሮዎች ሁሉ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳያመሩ ሲደረግ ከሁሉ በፊት ጠ/ሚኒስትሩ በሥራ ጫና ከሚመጣ ውጥረት (Stress) ይገላገላሉ - ይላል ፕሮፖዛሌ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ያልተገቡ ጥያቄዎችን (ችግሮች) ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ከማምዘግዘግ ስንታቀብ፣ እሳቸው ለአንገብጋቢ ችግሮች አንገብጋቢ ምላሽ ለመሻት ፋታ ያገኛሉ።
በጥሞና  ለማሰብና የፈጠራ ችሎታቸውን ሙሉ አቅም ለመጠቀም በቂ ጊዜ ይኖራቸዋል። ስለ ኢኮኖሚ ፖሊሲው፣ ስለ ዲሞክራሲ ሥርዓቱ፣ ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ፣ በኢህአዴጋውያን ብቻ ስለተሞላው የህዝብ ፓርላማ፣ ነጋዴውን ስለሚያማርረው የግብር ሥርዓት፣ ስለ ሸቀጦች ዋጋ መናር፣ ስለ ሥራ አጥነት፣ በቀን አንዴም እህል ቀምሶ ማደር ስለተሳነው ዜጋ፣ ስለ ኑሮ ውድነቱ፣ በየቦታው ስለሚቀሰቀሰው የህዝብ ተቃውሞና ግጭት ---- ወዘተ ለማሰብ በቂ  ጊዜ ያገኛሉ፡፡ እኛ ፋታ ስንሰጣቸው፣ እሳቸውም (እንደ መንግስት) የኑሮ ፋታና እርካታ የምናገኝበትን መንገድ መላ መላውን ይዘይዱልናል!! ለዚህ ሁሉ ግን ፕሮፖዛሌን ወደ ተግባር የሚለውጥ አካል ያስፈልጋል፡፡ ያኔ ብቻ ነው ጥያቄዎችና ችግሮች ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ከመንደርደር የሚገቱት፡፡
በአንዲት ፈገግ የምታሰኝ ቀልድ ብንሰነባበት ምን ይለናል?! እነሆ፡-
ድህነት ባደቀቃት አንዲት የሶሻሊስት አገር ውስጥ ነው አሉ፡፡ ሁለት ጓደኛሞች ሌሊት ከቤታቸው ወጥተው የሚላስ የሚቀመስ ለመሸመት ሱፐርማርኬት በር ላይ ወረፋ ይዘዋል። አንደኛው የየቀኑ ሰልፍ ትክት ብሎታል። እናም፤ “አሁንስ መረረኝ፤ ነጋ ጠባ ወረፋ!” ሲል ምሬቱን ለጓደኛው ይገልጽለታል፡፡
“መቻል ነው እንግዲህ፤ እሱ ያመጣውን እሱ እስኪገላግለን” ይለዋል ጓደኝየው፡፡
“እኔ ግን በቃኝ፤ ፅዋዬ ሞልቷል፤ ለዚህ ሁሉ መከራ የዳረገንን ሰውዬ ግንባሩን ብዬ እገላግለዋለሁ” አለና ከተሰለፈበት ወረፋ እመር ብሎ ወጣ (የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ማለቱ ነው).
ጓደኝየው ተከትሎት ቢሄድ ይወድ ነበር። ሆኖም የሆዱ ነገር አሳስቦት ቀረ፡፡
ከአንድ ሰዓት በኋላ ወረፋው ብዙም ሳይነቃነቅ፣ ጓደኛዬው ደካክሞ ተመልሶ መጣ፡፡
“እንዴት ነው ያሰብከውን አድርገህ  መጣህ?” ወረፋ የሚጠብቀው በጉጉት ጠየቀው፡፡
“በፍጹም! ጨርሶ የሚሞከር አይደለም!” መለሰ፤ ተስፋ በቆረጠ ቃና፡፡
“እንዴት---?”
“ሰውየውን  ለመግደል ያለው ወረፋ፣ ከዚህኛው ይበልጣል!”
(ከላይ የቀረበው ጽሁፍ ከዚህ ቀደም ወጥቶ የነበረ ቢሆንም ብዙ መሻሻሎችና ለውጦች ታክሎበት እንደገና እንዲነበብ ሆኗል፡፡ እውነታው እንደሆነ ባሰበት እንጂ አልተሻሻለም።)

Read 7984 times