Wednesday, 04 April 2012 07:04

በመምህራን የደመወዝ ጭማሪ ሰበብ የተነሳው ተቃውሞ ቀጥሏል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(4 votes)

ጥያቄያችን መሠረታዊ በመሆኑ ምላሽ ሳናገኝ ሥራ አንጀምርም - መምህራኑ

መምህራን ማህበሩ ስለማይወክለን በስማችን መግለጫ ማውጣት አይቻልም - መምህራኑ

ጭማሪው የተገኘው በመምህራን ማህበሩ ትግል ሆኖ እያለ አይወክለንም ማለት አይችሉም - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር

የመምህሩና የትምህርት ቢሮው መገናኛ ጋዘጣ አይደለም - የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ

መንግስት በቅርቡ ለመምህራን ያደረገውን የደመወዝ ጭማሪና የስኬል ማስተካከያ ተከትሎ መምህራኑ ያነሱት ተቃውሞ ቀጥሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ ት/ቤቶች መካከል፣ አንዳንዶቹ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

እስከ ትላንት ድረስ እየተዘዋወርን በተመለከትናቸው ኮልፌ አጠቃላይ፣ ከፍተኛ 12፣ ሚኒሊክ፣ አዲስ ብርሃን፣ ደራርቱ ቱሉና ኮከበጽብአ ትምህርት ቤቶች መምህራኑ በሥራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው ትምህርት ተቋርጧል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር እንደሚናገሩት፤ የመምህሩ ጥያቄ መሠረታዊና የህይወት ጥያቄ በመሆኑ፣ መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የመምህሩ ጥያቄ ውይይትና ማግባቢያ የሚፈልግ አይደለም፤  ጥያቄያችን አንድና አንድ ነው፤ የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ በድጋሚ እንዲታይና መንግስት የሰጠውን መግለጫ በአስቸኳይ እንዲያስተባብል ነው፤ ይህ ሳይፈፀም ወደ ሥራችን መመለስ አንችልም ብለዋል፡፡

ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ወደ ሥራ ገበታቸው እንደማይመለሱ በመግለጽ ፊርማቸውን አሰባስበው ወደ ዝግጅት ክፍላችን የመጡ መምህራን በሰጡት አስተያየት፤ “መንግስት ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ ታስቦበትና በጥናት የተደረገ ነው የሚል እምነት የለንም፤ ጭማሪው መንግስት ለመምህሩ ያለውን ግምት የሚያሳይ በመሆኑ እጅግ አዝነናል፡፡ ከዚህም በላይ የአብዛኛውን መምህር ሞራልና ሕሊና የነካው፣ በመምህሩ ስም የተቋቋመው የመምህራን ማህበር የሰጠው መግለጫ ነው” ብለዋል፡፡ ማህበሩ መላውን የኢትዮጵያ መምህር ሊወክል ስለማይችል በስማችን መግለጫ ከመስጠትም ሆነ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንዲቆጠብ እንፈልጋለን ሲሉም መምህራኑ አሳስበዋል፡፡ መምህራኑ ለማህበሩ የሚያደርጉትን የአራት ብር ወርሃዊ መዋጮም ከቀጣዩ ወር ጀምሮ እናቋርጣለን ብለዋል፡፡

መንግስት በጭማሪው ላይም ሆነ በሰጠው መግለጫ ላይ ማስተካከያ እስካልሰጠ ድረስ ወደ ሥራችን አንመለስም ሲሉ መምህራኑ ተናግረዋል፡፡

በስልክ ያገኘናቸው የአንዳንድ ት/ቤቶች ርዕሳነ መምህራን፤ በመምህራኑ የሥራ አድማ የተነሳ ትምህርት መቋረጡን ገልፀው፤ ሁኔታውን ለማስተካከልና በመጪው ሰኞ መምህራኑ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከመምህራኑ ጋር ለመወያየት እየሞከሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የኮከበ ጽባህ 2ኛ ደረጃ መሰናዶ ት/ቤት፤ መምህራኑ እስከ ሰኞ መጋቢት 17/2004 ዓ.ም ድረስ በሥራ ገበታቸው ላይ ካልተገኙ፣ በፈቃዳቸው ሥራቸውን እንደለቀቁ የሚቆጠር መሆኑን በመግለጽ፣ ለ105 መምህራን የጻፈውን ማስጠንቀቂያ መምህራኑ አንቀበልም በማለታቸው፣ በት/ቤቱ የማስታወቂያ ቦርድ ላይ እንደተለጠፈ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቴሮ፤ በኮከበ ጽባህ ት/ቤት ተገኝተው መምህራኑን ለማወያየት ቢሞክሩም፣ መምህራኑ “የምናነጋግረው ጥያቄያችንን የሚመልስ አካል ነው፤ የሚያስተባብልልን አካል አንፈልግም” በማለት ስብሰባው ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ መምህራኑ በግላቸው ተሰባስበው ከተወያዩ በኋላ ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጡ ሲሆን በዚህ መግለጫቸውም፤ መንግስት በመምህራን ደሞዝ ጭማሪ ላይ የተናገረው ከእውነት የራቀ በመሆኑ በአስቸኳይ ማስተባበያ እንዲሰጥበት፣ በዚህ ምክንያትም ሞራላችን በመነካቱ የሞራል ካሣ እንዲከፍለን፤ በጭማሪ የተናገረውን የደሞዝ መጠን እንዲጨምርልን፤ ከሌላ ፕላኔት የመጡ እስኪመስለን ድረስ ከኛ የተለየ አቋም የሚያራምዱት የመምህራን ማህበሩ አመራር አካላት በእኛ ስም መነገዳቸውን እንዲያቆሙ የሚሉ ነጥቦች የሰፈሩ ሲሆን፤ ይህ እስካልተፈፀመ ድረስ ወደ ሥራ ገበታቸው እንደማይመለሱና የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እስካለመፈተን የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱ አስገንዝበዋል፡፡

የአዲስ ብርሃን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ካሣሁን ተሰማ፤ ስለት/ቤቱ መረጃ እንዲሰጡን ስልክ ደውለንላቸው፤ “ጋዜጣው የግል ነው የመንግስት?” የሚል ጥያቄ ካቀረቡልን በኋላ፣ የግል መሆናችንን ስንገልጽላቸው “የግል ከሆናችሁ የምሠጣችሁ መረጃ የለኝም” ብለውናል፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ በንቲ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፤ ማህበሩ የመምህሩን ጥያቄ ወደ መንግስት ለማድረስ ከፍተኛ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፤ የተገኘው የደመወዝ ጭማሪም የማህበሩ የትግል ውጤት ነው ብለዋል፡፡ መንግስት ከመምህራኑ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት፣ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያውን አድርጓል ያሉት አቶ ዮሐንስ፤ “መምህራኑ ቀጣይ ጥያቄ ካላቸው ደግሞ በሒደት የሚታይ ይሆናል፡፡ እኛም ትግላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡ መንግስት ያደረገውን በጐ ነገር ማመስገን እንደሚገባም ተናግረዋል - የማህበሩ ሊ/መንበር፡፡ ማህበሩ አይወክለንም በሚለው ጉዳይ ላይ ሊቀመንበሩ ሲናገሩ፤ ይህ ጤናማ አመለካከት ካለው የማህበሩ አባል የሚነሣ ነገር ነው ብለው እንደማያምኑ ገልፀው፤ ማህበሩ 356ሺ አባላት ያሉት ሲሆን እንዲህ አይነት ነገር የሚያነሱት ምናልባትም ጥቂቶቹ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ከመምህሩ በየወሩ ከሚዋጣው 4 ብር ወደ ማህበሩ የሚደርሰው 40 ሳንቲም ብቻ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ፤ ይህቺ ገንዘብ ተጠራቅማ ነው ጭማሪው እንዲደረግ ያስቻለው ጥናት የተካሄደው ብለዋል፡፡ ከመምህራኑ ጋር ስለጉዳዩ ለመነጋገር ሞክራችሁ ነበር ወይ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄም “እኛ ወደ ታች ወርደን በየትምህርት ቤቱ እየዞርን መምህራኑን አናወያይም፤  ይህ የመዋቅር ጉዳይ ነው፤ በየደረጃው ካሉ የማህበሩ ኃላፊዎች ጋር ሊነጋገሩ ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይለስላሴ ፍሰሃ ቢሮ ደውለን ስለ  ጉዳያችን ካስረዳናቸው በኋላ፣ መምህራኑ መብታቸውን በአግባቡ መጠየቅ እንደሚችሉ ገልፀው፤ በመምህራንና በትምህርት ቢሮው መካከል የሚኖረው መገናኛ ጋዜጣ አይደለም ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከመምህራኑ ጋር በስፋት እየተወያዩበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይለስላሴ መንግስት ለመምህራኑ ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ ሳይሆን የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ነው፡፡ ለሁሉም ግን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መምህራን ጋር ውይይት በማድረግ አንድ እልባት ላይ እንደርሳለን ብለዋል፡፡

መምህራኑ ባወጡት የአቋም መግለጫ ላይ፤ ማንኛውም አካል በመምህራኑ ላይ በተናጠል እርምጃ ለመውሰድ ቢሞክር፤ አቋማቸውን አጠናክረው ተቃውሞአቸውን እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡

 

 

 

Read 15168 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:04