Saturday, 17 March 2012 10:51

ቡናና ጊዮርጊስ ዝግጅታቸው አላረካም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከሳምንት በኋላ በሜዳቸው ትልልቆቹን የሰሜን አፍሪካ ክለቦች የሚያስተናግዱት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅ/ጊዮርጊስ ዝግጅታቸው የሚረያረካ አልሆነም፡፡ በሊግ ጨዋታዎች ተስተካይ ፕሮግራም መደራረብና የአቋም መፈተሻ  የወዳጅነት ጨዋታዎች አለማድረጋቸው ይጎዳቸዋል፡፡በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ አዲስ አበባ የሚጫወቱት አልአሃሊና ክለብ አፍሪካን ለግጥሚያው በሰጡት ትኩረት የተሻለ ተዘጋጅተዋል፡፡ ቀዮቹ ሰይጣኖች የሚባለው የግብፁ አልሃሊ ክለብ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ለ14 ቀናት ተዘጋጅቶ 3 የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ወደ ግብፅ ከተመለሰ በኋላ የሊግ ውድድሩ መሰረዝ ቢያሳስብም ክለቡ ከቡና ጋር ከመጫወቱ በፊት ሁለት ተጨማሪ የወዳጅነት ጨዋታዎች  ያደርጋል፡፡ የመጀመርያውን ከትናንት በሰቲያ ተጫውቷል፡፡ የመጨረሻ የአቋም መፈተሻ ግጥሚያውን ደግሞ ሰኞ ያደርጋል፡፡

በኮንፌደሬሽን ካፕ የሚሳተፈውና የቱኒዚያውን ክለብ አፍሪካን የሚያስተናግደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የግብፁን አልአሃሊ የሚገጥመው ኢትዮጵያ ቡና ይሆናል፡፡ በ27 ነጥብ ፕሪሚዬር ሊጉን መምራት የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆን ቡና ደግሞ በሊጉ በ19 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ሁለቱም ክለቦች በሜዳቸው ለሚያደርጉት ወሳኝ ኢንተርናሽናል ግጥሚያ  በፕሪሚዬር ሊግ  ወቅታዊ አቋም ዝግጅታቸው ተወስኗል፡፡ ቡና ከሱዳኑ ክለብ አልሜሪክ ጋር  የወዳጅነት ጨዋታ ፈልጎ ነበር፡፡  የፕሪሚዬር ሊግ ሁለተኛ ዙር መጀመሩ፤ የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት ላለማስተጓጐልና የጥሎ ማለፍ ውድድር ለመጀመር በተያዙ እቅዶች ሳቢያ በአዲስ አበባ ስታድዬም  ጨዋታውን የማስተናገድ እድል በፌዴሬሽኑ  ተከልክሏል፡፡ በሌላ በኩል በሊጉ ከአየር ኃይል ጋር የሚያደርገው ተስተካካይ ጨዋታ ጊዮርጊስን አስጨንቆታል፡፡ በገለልተኛ ሜዳ ይደረጋል የተባለው ጨዋታው በድሬዳዋ እንዲካሄድ በፌደሬሽን መወሰኑ ደስተኛ አይደለም፡፡ ይሄው ተስተካካይ ጨዋታ ሃዋሳ ቢደረግ እያለ ነው፡፡ በተስተካካይ ጨዋታ የሚደረግ ረጅም ጉዞ መከናወኑ ተጨዋቾቹ ለኢንተርናሽናል ግጥሚያ የሚኖራቸው ብቃት ያዳክማል በሚል አማርሯል፡፡

 

 

Read 2123 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 10:56