Saturday, 17 March 2012 10:42

የጥበብ “ቸርች” ያስፈልገናል

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(0 votes)

እውነትን ለመናገር ሳይሆን ለመጠቆም ነው የዚህ መጣጥፍ አላማዬ፡፡ … በሁለት ፈጣሪዎች ነበር አሉ … ይህ ሰው የሚባል ፍጥረት መጀመሪያ የተሰራው፡፡ አንደኛው ፈጣሪ መንፈሳዊ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ቁሳዊ ነው፡፡ በኋላ ሁለቱ ፈጣሪዎች እርስ በራሳቸው ተጣሉ፡፡ ሰውን ከሰሩት በኋላ ነው የተጣሉት የሚሉ አሉ፤ ከፊሎቹ ደግሞ ከመጀመሪያውም ኮከባቸው አልገጠመም ይላሉ፡፡ እኔ ከከፊሎቹ ጋር ነው በከፊል የምስማማው፡፡  እንዲያውም እኔ፤ ሁለቱ ባላንጣዎች (“ባለ-አንጣ” ማለት ሁሌም አንጣ - አንጣ የሚል የማይጠግብ ልጅ ማለት ይሆን?) ሰውን ለመፍጠር የተስማሙበት ምክኒያት ቅራኔያቸው ራሱን ችሎ እንዲዋጋ ማድረግ የሚያስችላቸው የጦር ሜዳ ለመስራት እና “እንዲዋጣላቸው” በመስማማታቸው ነው፡፡ ሰው ከራሱ ጋር ሲጣላ እነሱ ተቀምጠው እንዲያዩ?

ስለዚህ፤ እንዲያ ከሆነ ነገሩ፤ ጦርነቱን ማንም እጁን አጣጥፎ መመልከት አይችልም፡፡ አልተፈቀደለትም፡፡ እኛ አልተሰጠንም፡፡ አዳሜ ሁሉ ጐራውን መለየት አለበት፡፡ እኔ ለይቻለሁ፡፡ ወደ መንፈሳዊነቱ ነኝ፡፡ ወደ አካሉ ሳይሆን ወደ ነብሱ ነኝ፡፡ … የቁስ ማንነቴን መግደል ባልችልም እንዳይውጠኝ እየተዋጋሁ መንፈሴ ከፍ እንዲል እሞክራለሁ፡፡ … የጦር ሜዳ አሰላለፌ ይሄ ነው፡፡ ጦር ሜዳ አሰላለፍ ያስፈልገዋል … ጦር መሳሪያ … ውጊያው ከራስ ጋር ነው፡፡ በሚጨብጠው ውስጥ ሆኖ ስለማይጨበጠው መከራከር፣ ተከራክሮ መልሶ ተጨባጩን ለማስመጥ መሞከር ነው፡፡ ግዛት ለማስለቀቅ መጣር፡፡

ጦር መሳሪያው ጥበብ ነው፡፡ የጥበብ ግዛት ምናባዊ ነው፤ ሰውን ዘላለማዊ ማድረግ አላፊን ህይወት ዘላለማዊ ስፍራ እንዲያገኝ ማመቻቸት … በቁሳዊ ፍላጐት ላይ መሰረት ያደረገውን ህብረተሰብ ወደ መንፈሳዊነት ማስጠጋት፡፡

መንፈሳዊነትን ለመግለፅ የሚሞክር እስከሆነ ድረስ ሞካሪው ሀይማኖተኛ ነው፡፡ የግል እምነት ከሌሎች ጋር ሲመሳሰል ሀይማኖት ተፈጥሯል፡፡ ጥበብም ሀይማኖት ነው፡፡ ለጥበብ ኖሮ መሞት … የጥበበኛው ፅድቅ ነው፡፡ … በቅርቡ እንደዚህ አይነቱን ጀግንነት አከናውነው የሞቱ ሁለት ሰዎች … አልፈውብናል፡፡ ፀድቀውብናል፡፡ ማዕረጋቸው ቢለያይም ሁለቱም የጥበብ ጀግኖች ናቸው፡፡ ማዕረጉ ወደ ቁስ ባልቀረቡበት መጠን … ከፍ ይላል፡፡

ይህ የፅሁፌ መነሻ ነው፡፡ አሁን ወደ ዋናው ነጥብ መግባት አለብኝ፡፡ ግጥም ለወቅታዊ ቁሳዊ አላማ ሲፀነስ ግጥሙ መፈክር ነው፡፡ ለዘላለማዊ መንፈሳዊ አላማ ሲፀነስ ፀሎት ነው፡፡ የጥበብ ፀሎቶች በየዘውጋቸው (በሙዚቃ፣ በስነ ፅሁፍ፣ በስዕል … በቅርፃቅርፅ …) የሚቀርቡበት ቤት ያስፈልጋል፡፡ መሰብሰቢያ ቤት፡፡ የጥበብ ቸርች መመስረት አለበት፡፡

የሚፈልጉበት መንገድ ቢለይም … መነኮሳት ቤተ መቅደስ አላቸው፡፡ አላማቸውን የሚያሟሉበት ከቁሳዊ መደናገር ራሳቸውን የሚጠብቁበት ቦታ አላቸው፡፡ በተቃራኒ ጠላት በተጣለ አደጋ የቆሰሉ ነብሶችን የሚያክሙባቸው … ሀጢአትን የሚያናዝዙባቸው … ተጨባጭ ስፍራ አላቸው፡፡

ለጥበብ ሀይማኖተኞችም ተመሳሳይ ስፍራ ያስፈልጋል፡፡ አልፈው አልፈው የጥበብ ስራዎችን ለሚያገላብጡት፣ ለሚያደምጡት፣ ለሚመለከቱት ሳይሆን ይህ ስፍራ የሚያስፈልገው … ሙሉ ለሙሉ ለጥበብ ብለው ለመነኑት ነው፡፡ የጥበብ ብትውትናን ለመረጡት ሳይሆን ለተመረጡት ነው፡፡ የሃይማኖቱ ውጤት በጥበብ ስራ መልክ በኋላ ለሁሉም ይደርሳል፡፡

እዚህ ሥፍራ ላይ በጥበብ ስም የቁሳዊ አለም ፖለቲካ እንዲገባ አይፈቀድም፡፡ የተቀደሰ ስፍራ ነው፡፡ ፈላስፎች የሚወያዩበት ነው፡፡ ረጅም ድርሰቶች ተዘርተው የሚያድጉበት … ረቂቅ ሙዚቃ … ማህሌት መስሎ የሚሰማበት ነው፡፡ ድምጽ አልባ ጥበቦች (ስነ ጽሑፍ እና ስዕል) በፀጥታ የሚፈነዱበት ስፍራ ነው፡፡ በግጥም ሰይጣን ተረጭቶ የሚወጣበት ነው፡፡ …ጫማ ተወልቆ የሚገባበት “ሆሊ” ቦታ ነው፡፡

ቀልድ አይደለም፡፡ የሙኒ (Muni) የሀሳብ ወሬም አይደለም፤ (Muni በሂንዱዝም በአእምሮ ጅምናስቲክ የመናወዝ ሂደት ነው) …

ስለ ጥበብ ቀልድ የለም፡፡ ነኝ … ነበርኩ … ወደፊት የሚሆኑትን መጠበቅ እፈልጋለሁ፡፡ ስንት ችግኝ ሲሰበር አይቻለሁ፡፡ ስንት ፍሬ በቁሳዊ አለም ውስጥ መንፈሱ ጠፍቶ የስሜት መጫወቻ ሲሆን አይቻለሁ፡፡ የጥበበኛው የፍለጋ ስኬት መጨረሻ ጥበቡ ነው፡፡ … በቀጥታ ተጠምቆ የሚገባበት ሀይማኖት ስላልሆነ፤ ብዙ ተከታይ እና መነኮሳት አያፈራም፡፡ ጥበብን የሚወድ ሁሉ ጥበበኛ አይሆንም፡፡ ጥበበኛ ሁሉ የተሟላ ጥበብ ላይፈጥር ይችላል፡፡ ግን እንቁላል የምትጥለዋ ዶሮ በባህሪዋ ስለምታስታውቅ ዝርያዋ ተመርምሮ … እድሜ ልክ ስታምጥ እንድትቆይ የሚፈቅድ ጠባቂ ያስፈልጋታል፡፡ መጀመሪያ የመዳብ እንቁላል ልትጥል ትችላለች፡፡ … ወርቅ ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም፡፡ ስንት ሂደት አለው፡፡ የማጥናት፣ የማወቅ፣ የመሰቃየት፣ የመላቀቅ፣ የመመሰጥ፣ የመሠጠት፣ … የመስዋእትነት፣ … ወርቅ እንቁላል ላይ ዝም ብሎ አይደረስም፡፡ እንቁላሉ ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱ ፈጣሪዎቻችን የተከናወነውን ጦርነት ህያው ምስክርነት የምናቀርበው ከግጭቱ በፈነጠቀው ጥበብ ነው፡፡ ተራ ከሰል በብዙ መታወቅ አልማዝ ይሆናል፡፡ ተራ አቶም ደግሞ የፀሐይን ሃይልና ብርሐን ይሰጣል፡፡ ጥበብ ነው፡፡ ምስክርነት በውበት ብቻ ነው የሚገለፀው፤ በውበት ሀይማኖት፡፡

ውበት፣ እውነት ነው፡፡ እውነት ደግሞ ፍቅር፡፡ እግዜር እንዴት ፍቅር እንደሆነ የሚያሳዩ ሀይማኖቶች ማሳየት ከሚችሉት ባላነሰ፣ ፍቅር እንዴት ጥበብ እንደሆነ ቁልጭ ባለ የጥበብ እይታ ማቅረብ የሚችሉ ፈላስፎች አሉን፡፡ ግን ፈላስፎቻችን ግኝታቸውን የሚንከባከብ … እንዲያገኙ ሂደቱን ቀላል የሚያደርግ አካል የለም፡፡ እስካሁን ጥበበኞች እንደ እብድ ሲታዩ ኖረዋል፡፡ መኖር (በህልውና) እንዲቀጥሉ ከተፈለገ እይታው መቀየር አለበት፡፡

ማንንም ሊቀይርልን አይችልም፡፡ ከራሳቸው ከጥበበኞቹ በስተቀር፡፡ ልቀይርላችሁ ብለው የሚመጡትም በስተመጨረሻ ሲቀይሩ የታየው ራሳቸውን ነው፡፡ የቁሳዊ ግዛት የጠላት ወረዳን ይዞታ ሲያጐለብቱ፡፡ አርት፡- በArty types ብቻ ነው መያዝ ያለባት፡፡ በአርቲ-ቡርቲ አይነቶቹ ከተያዘች መሞቷን ትቀጥላለች፡፡ … ሞታለች እያሉ ከመሞቱ በፊት ቀብረው የመንፈስ ንብረትን ለመውረስ የሚሻኮቱትን እጅ ጭነን ግጥም እንገምጥባቸዋለን፡፡ በጥበብ ስም!

ጥበብ ቀልድ አይደለም፡፡ ጥበበኞችም አጫዋች አይደሉም፡፡ ሌሎችን ከድብርት ለማላቀቅ ብቻ የቆመ አርት መንፈሳዊ ሳይሆን ማህበራዊ ነው፡፡ ርቀት ያስፈልጋል፡፡

መለየት ያስፈልጋል፡፡ ከየትኛው ጐን ነህ? ከሚወጣ ወይንስ ወደ ማህበረሰቡ ኑሮን መስሎ ከሚወርደው?

ተሀድሶ ያስፈልጋል፡፡ የጥበብ ተሀድሶ … የጥበብ ሰባኪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ መንቃት ያለባቸውን ብቻ የሚያነቁ፡፡ … የጥበብ መብታቸው መጠበቅ ያለባቸውን የሚያስጠብቁ፡፡ በኢግናይተስ ሎዮላ እንደተመሰረተው የካቶሊክ ተሀድሶ… የጥበብ ተሀድሶ አብዮት ያሻዋል፡፡ ፈራርሶ የሚሰራበት ሳይሆን፤ የተሰራው የማይፈርስበት … ወደፊት የሚሰሩት የሚጠበቁበት፡፡ የጥበብ “ጀዝዊቶች” ያስፈልጋሉ፡፡ ለሀይማኖታቸው ወታደር እና ቄስ የሚሆኑ፡፡

ይህንን መጥሪያ ለሚመለከታቸው ልኬያለሁ፡፡ በጥበብ ስም ብዙ የሚደረግበት ጊዜ ላይ ነን፤ እውነተኛ ጥበብ በአርቴፊሻል ብልጭልጭነት እውነተኝነቱን ለቁሳዊ ዋጋው ሲባል ያጣበት ጊዜ ላይ፤ የተሸፈነበት፡፡

ለጥበብ የተፈጠሩ ወጣቶች መንፈሳቸውን ለማሳረፍ በእሁድ ቀን ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ ካየሁ በኋላ ከተጠነሰሰ ሀሳብ ይህ ማመልከቻ ተፅፏል፡፡ መንፈስን ከፍ ለማድረግ ሀይማኖቶች ሁሉ ሊያገለግሉ ቢችልም በትክክለኛ የጥሪ ቋንቋው ሁሉም ፀሎቱን ማቅረብ ይችላል፡፡ አለበትም፡፡  ማህበሮች እንዳሉ አልጠፋኝም፡፡ ግን ማህራት አንዳንድ ጊዜ እንደ መንግስታት ይሆናሉ በተግባራቸው፡፡ ብዙ ማህበርተኞችን ያቅፋሉ ግን የታቀፉትን ሁሉ እንደ ፈጣሪ ጆሮ እኩል ለማድመጥ አይችሉም፡፡ ሺ ማህበርተኛን ትተው አንድ የጠፋ ጠቦትን ለመፈለግ አይሄዱም፡፡ … የመንጋው ተንከባካቢ የመሲህ ባህሪ መላበስ ግዴታ አለበት፡፡ በሁሉም ሀይሉ፣ በሁሉም ፍላጐቱ፣ በሁሉም ተግባሩ …ለበጐቹ የሚቆረቆር መሆን አለበት፡፡ በጐቹ ለዚህ አጀንዳ ጥበበኞች ናቸው፡፡ ወይንም የጥበቤ አይነቶች በአጠቃላይ፡፡ … መንጋው በጐች ከሆኑ ተኩላ እረኛ ሊሆን አይችልም፡፡ መንጋውን መሪው መምሰል ይኖርበታል፡፡

በተለያዩ ሀይማኖቶች ውስጥ ያሉ ተከታዮች ወደ ሀይማኖቱ የሚገቡት ወይንም ለአምልኮ በሀይማኖቱ ማዕከሎች የሚመጡት ተከፍሏቸው አይደለም፡፡ ከፍለውም አይደለም፡፡ በነፃ ለመስጠት እና ለመቀበል የተቀመጠ ነገር መንፈሳዊ ባህሪ አለው፡፡ እውነተኛ ጥበብም በዚህ ውስጥ የሚቀመጥ ነው፤ ለኔ፡፡ ከጥበብ መንፈሳዊ ከፍታ እንጂ ቁሳዊ ትርፍ አይገኝም፤ ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ ነጥብ ላይ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚቆሙት…  … ጥበብን መንፈሳዊ አድርገው የማይመለከቱት ናቸው፡፡ ወይንም መሆኑን ለመቀየር የሚሞክሩ፡፡… እነሱ በሌላኛው ፈጣሪ ስበት የሚጐተቱ ናቸው፡፡

ንግድ እና ኢኮኖሚ … ማህበረሰብ እና የማህበረሰብ ተቀባይነት የሚመለከታቸው ናቸው፡፡ ለእነሱ ተጨባጩ የቁሳዊ አለም ቤተ መቅደሳቸው ሊሆን ስለሚችል የተለየ ስፍራ አያስፈልጋቸውም፡፡ ማህበረሰቡ በጉያው አስገብቶ ያሞቃቸዋል፡፡ ፊልም መድረስ ይችላሉ፣ ሀውስ ሙዚቃ ማቀናበር ይችላሉ … በብዙ መቶ ሺ ብር የሚሸጥ ስዕል መሳል ይችላሉ፡፡

የእነሱ ሀይማኖት ከእኛ ይለያል፡፡ እኛ እና እነሱነት በእያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮ ውስጥ ቢኖርም፤ ሁለቱንም ወደ አንድ ለማምጣት መጣር ግን ጦርነቱን በድል ማሸነፍ ነው፡፡ …ሰይጣን እና መልአክን ወደ አንድ ማምጣት የሚቻለው ከሁለቱ አንዱን በድል ሌላውን በሽንፈት በመሸኘት ነው፡፡ ቁሳዊ የጥበብ ሃይማኖት ባይኖር መንፈሳዊውን ማቋቋም ባላስፈለገ ነበር፡፡

 

 

Read 3692 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 11:56