Saturday, 17 March 2012 10:29

“የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ግንድና ቅርንጫፎች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

ከጥቂት ዓመታት በሀገራችን ሥነ - ጽሑፍ አይን-ገብ እየሆነ የመጣው የሕይወት ታሪክና ግለ ታሪክ አፃፃፍ ጉዳይ መነጋገሪያ እየሆነ መጥቷል፡፡ በቅርቡም ይብዛም ይነስ፣ በወጉ ይሠራ አይሠራም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እንደመነጋገሪያ ተነስቶ ነበር፡፡ በእርግጥም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ሃሳብ ሰጥተውበታል፣ ፍፁም የማይመለከታቸውና አንዳች ነጥብ እንኳ መጣል ያልቻሉ የጉዳዩ ባይተዋሮችም ብቅ ብለውበታል፡፡ የሚገርም ነው - ብለን እንለፈውና ወደ ራሳችን ዋና ጉዳይ እንሂድ!

ለመሆኑ የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ እንዴት ተጀመረ? ስንል መልስ የሚሰጡን ሰዎችን በሰልፍ እናገኛቸዋለን፡፡ የመጀመሪያው በቺካጐ አንድ ኮሌጅ ውስጥ የሃይማኖት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ኢኦን ናቸው፡፡ እኒህ ምሁር፣ ይህ የአጻጻፍ ዘውግ መነሻ ግሪክ መሆኑን ያሠምሩበታል፡፡ ይሁንና እስከ አሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን (ቅድመ ክርስቶስ) ራሱን የቻለ የሥነ ጽሑፍ ዘውግ ተደርጐ አይወስድም ነበር፡፡ ሥር ወቃሉም በግሪክ “Bios” ሲሆን በላቲን ደግሞ “Vita” የሚል ነው፡፡ ትርጓሜው ደግሞ የአንድ ሰው የሕይወት ዘመን ወደሚለው ይሄዳል፡፡ በጊዜው ሲጀመርም በአብዛኛው በታዋቂ ሰዎች ሕይወትና ገድል ላይ የተመሠረተ ሲሆን ጽሑፉም የባለታሪኩን ባህሪና ሥራውን የሚቃኝ ነበር፡፡

በኋላ ግን ከሜዲትራኒያኑ ዓለም ሥልጣኔ ጋር ብቅ ያለው ሥነ ጽሑፍ፣ ታሪካዊ እሴቶችና መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ የት መጣውንና ዘውጉን መበርበር ጀመረ፡፡ የአይሁድ ባህልና ሥነሑፍም ይህንኑ የሜዲትራኒያኑ ባህል ተጋሪ በመሆን፣  ከሄለናዊያኑ ሥነ ጽሑፍ ተዋሽ ሆኖ መልኩን ቀርፆበታል፡፡ ለምሳሌ ጆሴፈስ የተባለው አይሁዳዊ የታሪክ ሊቅ፣ ለግሪክ አንባቢያን ስለጥንቱ እሥራኤል በዘመናዊ መልኩ ለመፃፍ ሞክሯል፡፡ ዘመኑን የሚመስል ዘመናዊ ቅርጽ ሰጥቶ! በዚህም ሙከራው የንጉሥ ሳኦልንና የንጉሥ ሰለሞንን ታሪክ፣ ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡ ሌላኛው አይሁዳዊ ፈላስፋ ፌሎ፤ የሙሴን የሕይወት ታሪክ እንደ ንጉሥ፣ ሕግ ሰጪ፤ ሊቀካህናትና ነቢይ አድርጐ ለመፃፍ ሞክሯል፡፡

እንደ ሌላው ምሁር ሊዎ ፕሎታርቺያ አባባል፤ የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ቅርፅ ጀማሪ የአርስጣጣሊስ ተከታዮች ናቸው፡፡ እነዚህ የአርስጣጣሊስ ተከታዮች ይጽፉ የነበረውም በዘመናቸው ስለነበሩ የጦር ጄኔራሎች፣ ፈላስፋዎችና የመንግስት ሃላፊዎች ነበር፡፡

በኒሁ ሰው አባባል ሌሎቹ የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ግንዶች አሌክሳንድሪያዊያን ናቸው፡፡ ይሁንና እነዚህም ፀሐፍት በአርስጣጢሊሳዊያን - ዘመን ተፅዕኖ ሥር የነበሩ ናቸው፡፡ ጉልህ ልዩነታቸው ደግሞ እነዚያ የጦር ጄኔራሎችንና የፈላስፋዎችን ታሪክ ሲፅፉ እነዚህ በኪነ ጥበብ ሰዎች ላይ ተመሥርተው መፃፋቸው ነበር፡፡

ታዲያ ስለ ሕይወት ታሪክ መነሻና መዳበር ስናነሳ፤ የጅማሬውንም ቁልፎች መዘንጋት የለብንም፡፡ የሕይወት ታሪክ ጽሑፍ ስንል በፓፒረስ አልተጀመረም፡፡ የተጀመረው  በድንጋዮች ላይ የጀግኖችን ስምና ዋና ዋና ገድል ብቻ በመፃፍ እንደነበር ፕሮፌሰር ዴቪድ ኢ ኦን ይገልፃሉ፡፡

ወደ ዘመናዊው የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ስንመጣ፣ ዶክተር ካትሪኒ ሃንትሪ የተባሉ ምሁርን እማኝነት እናገኛለን፡፡ እኒህ እንስት ምሁር እንደሚሉት፤ የዚህ ዘውግ ዘመናዊ ገጽታ የተወለደው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ሲሆን ቀድሞ የነበረው  የሕይወት ታሪክ አፃፃፍ ማለትም ገድል ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኖ መቀጠል አልቻለም፡፡ የጦርነቱ ተዋናዮች፣ ከጦር ሜዳው መልስ ፍርሀትና ስቃዩን ሲናገሩ ጉብዝና ብቻ ሳይሆን ፍርሀትና ድንጋጤ የመኖሩ ግልጥነት ተሰማ፡፡ ይህ አንዱ ለውጥ ሆነ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የባለታሪኩን ታሪክና ገድል ብቻ ሳይሆን የበቀለበትን ቤተሰብና አካባቢ፣ ልጅነቱንም ጭምር በሚገባ በማካተት የተሻለ ቀለም ይዞ ብቅ አለ፡፡

ይህንን አፃፃፍ ዛሬም የሰለጠኑት ዓለማት ፀሐፍት ይጠቀሙበታል፡፡ በእኛም ሀገር በሚፃፉት መጽሐፎች ላይ ማስተዋል ይቻላል፡፡

በሕይወት ታሪክ አፃፃፍ ላይ የአተራረክ አንፃር ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ታሪኩን ማን ቢተርከው ይሻላል? ባለቤቱ ወይስ ሁለተኛው ሰው? ይሄን በተመለከተ ሁለት አይነት አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንዳንዶች ባለቤቱ ራሱ ቢጽፈው ይሻላል ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይደለም - የተባ ብዕር ያለው ልምደኛ ቢተርከው ይበጃል” በማለት ይሞግታሉ፡፡

ይሁንና ሁለቱም ሙላትና ጉድለት አላቸው፡፡ ግለ ታሪኩን ባለቤቱ ራሱ ቢፅፈው ይሻላል የሚሉት ወገኖች፤ ባለቤቱ ሲፅፈው የተለያዩ መረጃዎችን የማግኘት የተሻለ አቅም አለው ይላሉ፡፡ ይሄን የሚሟገቱት ደግሞ ሰውየው የራሱን ታሪክ ሲጽፍ ስሜታዊ ሊሆንና ገጠመኞቹን ሊያጋን እንዲሁም ድራማዊ ሊያደርገው ወይም ሊያሳብጠው ይችላል ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከእውነት እንዲንሸራተት ያደርገዋል ሲሉም መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡

ሁለተኛ ወገን ቢጽፈው ይሻላል የሚለው ሃሳብም ቢሆን ከትችት አላመለጠም፡፡ ሁለተኛ ወገን ሲፅፍ መረጃውን እንደ ታሪኩ ባለቤት የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው፡፡ የሰውየውን ጓደኞች አሳድዶ ለማግኘት የባለቤቱን ያህል አቅሙ አይኖረውም የሚለው በአንድ በኩል ይንፀባረቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሚጽፈውን የሕይወት ታሪክ ሲያዘጋጅ ነገሮች እንዳይጋነኑና የእውነታውን ሀዲድ እንዳይለቁ ሊያደርግ ይችላል በሚል ሁለተኛ ወገንን የሚደግፍ ሃሳብ ይሰነዝራል፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ሃላፊ ፕሮፌሰርም (የማደንቃቸው ሰው ናቸው!)፤ ግለሰቦች የራሳቸውን ነገር እንደሚያጋንኑና ራሳቸው ላይ ከማተኮራቸው የተነሳ ሌሎችን ሊወነጅሉ እንደሚሞክሩ ተናግረዋል፡፡

ስለ ሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ስናነሳ ታዲያ ተራኪው ወይም ፀሐፊው ዳር ሆኖ ከመተረክ በቀር ራሱን የታሪኩ ተጋሪ በማድረግ ጊዜ መፍጀት የለበትም፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚደረገው የሰውየው የቅርብ ሰው ከሆነ፣ እንደሌሎቹ የተተራኪው ወዳጆች ወይም ዕውቂያዎች ራሱን መግለፅ ይኖርበታል፡፡

በሦስተኛ መደብ አንፃር ሲተርክ፣ ሰውየው የተናገረውን ቃል በቃል በመገልበጥ ብቻ ሳይሆን የሌሎችን አስተያየትና ገጠመኝ፣ አልፎ አልፎም የጨበጣቸውን እምነቶች ራሱ መተረክ ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ ግን ፀሐፌ ተውኔት መሆን ይመጣል፤ ምልልስ ብቻ ከሆነ ማለት ነው፡፡

እንስቷ አሜሪካዊት ዶክተር ካትሪኒ ሃንትሪ፤ “Writing Biography” በሚለው ፅሑፍዋ እንዳለችው፤ የሰዎችን የሕይወት ታሪክ ስንፍ ፈጽሞ ሕፀጽ እንደሌለበት ሰው ፍፅምና ልናጐናጽፈው አይገባም፤ ይልቅስ እነዚያ ድክመቶች እያሉበት ለሰው ልጅ የሰራቸውን ትልልቅ ሥራዎች ማተት እንጂ!

ከተፃፈ ከረምረም ያለና ኦን ሆፍማን የተባሉ ፀሐፊ የፃፉት መፅሐፍ፤ ስለ ሕይወት ታሪክ አፃፃፍ ብዙ ይመክራል፡፡ እኒህ ሰው እንደሚሉት ከሆነ፣ የአንድ ሰው የሕይወት ታሪክ ጽሑፍ በጋዜጣና በመጽሔት ከተፃፉት ፕሮፋይሎች ሊያድግ ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ የሕይወት ታሪክ የሚፃፍላቸው ሰዎች በሕይወት እያሉ ወይም ከሞቱ ብዙም ሳይርቅ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዱ ፀሐፊ በአንድ ጉዳይ ላይ አድልቶ ሲጽፍ ሌላኛው በሌላ ጉዳይ ላይ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ስቴፈን ሎረንት፤ የአብርሃም ሊንከንን ሕይወት ሲጽፉ ላይ ላዩንና ከሜሪ ቶድ ጋር የነበረው ፍቅር ላይ ሲያተኩሩ፤  ዴል ካርኒሮ ደግሞ ሜሪ ቶድ የሲዖል ያህል ከባድ፣ የሞት ያህል መራራ እንደሆነች፤   ምስጢራቱን ሌላው ቀርቶ ለሁለተኛ ምርጫ ሲወዳደር ሚስቱ ከሰዎች የተበደረቻቸውን ድብቅ ፈዳዎች ሳይቀር አነፎንፎ ጽፏል፡፡ ሌላው ስማቸውን የማላስታውሳቸው ፀሐፊ ደግሞ ሊንከንን እንደ ፀሐፊ አቅርበውታል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፤ በሕይወት ታሪክ አጻጻፍ እጅግ ውብ ቃላትን የሚጠቀሙ፣  የትረካ ቅደም ተከተሉን አሳምረው የሚያንፁ የፅሁፍ መሀንዲሶች ያሉትን ያህል የሚጣፍጠውን ታሪክ እጅ እጅ እንዲል የሚያደርጉ ጐልዳፎችም ሞልተዋል፡፡ የቢ. ጆንሰንን ታሪክ የፃፉ አንድ ብዕረ-ጐልዳፋ ፀሐፊ ለዚህ ማስረጃ ይሆኑኛል፡፡ ቶማስ አልቫ ኤዲሰንን አጣፍጦ በገጣሚ ቋንቋ፣ በውበት ደመና የከበበውና የድራማ ያህል ያሳየኝን ፀሐፊ ከቶም አልረሳውም፡፡

የሕይወት ታሪክ አፃፃፍ ጉዳይን ስናስብ ግብዐቶችን እንድንተልም ሆፍማን ይነግሩናል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ የሕይወት ታሪክ ፀሐፊ ለመፃፍ ሲነሳ ሊፈትሻቸው የሚችሉ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የሚተረክለት ሰው ራሱ ሲሆን ሌሎችም በርካታ ነገሮች ታሪኩን ቁልጭ ለማድረግና አሳማኝነቱን ከፍ ለማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በተለይ በኛ ሀገር ደረጃ ሊጠቅሙን የሚችሉትን እንመልከታቸው፡፡

የሕትመት ውጤቶች፣ ዜና እረፍት መረጃዎች፣ የሕትመትና የድምጽ እንዲሁም የምስል መረጃዎች፣ ቴፖች፣ ሲዲዎች … የታሪኩ ባለቤት በሕይወት ዘመኑ እያለ የተፃፈለት ወይም እርሱ ለሌሎች የፃፈው ደብዳቤ፤ ዳያሪና ማስታወሻ የያዘባቸው ወረቀቶች፣ በአደባባይ ያደረጋቸው ንግግሮች (በቢሮ፣ በስፖርት ሥፍራ፣ በእድር፣ በዕቁብም ሊሆን ይችላል) የጉዞ ማስታወሻ ወዘተ ያስፈልጋሉ፡፡

የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ መልኮች በጥቂቱ ይህንን ይመስላሉ፡፡ ለቅርጽና ለውበት ጥንቃቄ ቢደረግ፤ ማራኪ፣ ያልተዝረከረኩና ያልመነቸኩ የህይወት ድርሳኖችን ማንበብ ይቻላል፡፡ ጀግኖቻችንም የጀግና ወግ ያገኛሉ!

 

 

Read 3670 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 10:34